Saturday, 07 October 2017 14:33

ሙሰኞች የማይጠግቡት ለምንድን ነው?

Written by  ተመስገን ጌታሁን ከበደ (temesgengt@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

“እነሆኝ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፡፡ የማንን በሬ ወስድሁ?”
“የማንንም አልወሰድክ”
“የማንንስ አህያ ወሰድሁ?”
“የማንኛችንንም አልወሰድክ”
“ማንንስ ሸነገልሁ?”
“ማንንም አልሸነገልክም”
“በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ?”
“በማንኛችንም ላይ ግፍም አላደረክብንም”
“ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን እጅ ጉቦ ተቀበልሁ?”
“ከሰው እጅ ምንም አልወሰድህም”
ይህ በእግዚአብሔር፤ በእስራኤል ሕዝብና ለንግሥና በተቀባው በመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ በሳኦል ፊት፣ በነቢዩ ሳሙኤልና በሕዝቡ መካከል የተደረገ የምስክርነት ቃል ነው (1ኛሳሙ 12፤3-5)፡፡
በሌላ አነጋገር፤ እስራኤሎች ከነቢይ አስተዳደር ስርአት ወደ ንጉሥ አስተዳደር ስርአት ሲሸጋገሩ የተፈጸመ፣ በሕዝቡና ያስተዳድራቸው በነበረው በነቢዩ ሳሙኤል መካከል የተደረገ የምስክርነት ቃል ነው፡፡
“ቸር ተመኝ ቸር ታገኝ ዘንድ” ይባል የለ? አምነናቸው ወይም በግድ አሊያም በሌላ መንገድ  የሾምናቸው ነገሥታት፤በአንድ የምርጫ ዘመን ተሸንፈው፣ ወር ተራው የሌላ ሆኖ፣ የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስት ያስረክባሉ ብለን ተስፋ እናድርግና እንዲህ እንቀጥል፡፡  
ግዴለም በሌላ መንገድ እንየው፡፡ ያው ላለፉት 26 ዓመታት የለመድነው አውራ ፓርቲ፣ በሕዝብ ምርጫ ያሸንፍ፡፡ እንደተባለው የኢህዴግ ቁንጮ የሆነው መሪ፣ የስልጣን ዘመኑ ሁለት የምርጫ ዘመን ነው እንበል፡፡ የፓርቲ ለውጥ ሳይኖር “የንጉሥ” ለውጥ ሲደረግ ወይም የዙፋን ሽግግር ሲደረግ፣ ሥልጣን ላይ የነበረው “ንጉሠ ነገሥት” ሥልጣኑን ሲያስረክብ፣ (አንድ ቀን ይህ መሆኑ አይቀርም) ልክ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል፣ እጁ በሙስና ያልተጨማለቀ መሆኑን መናገሩ አይቀርም፡፡ እንዲህ ብሎ፡-
“ይኸው መስክሩብኝ፤ በቸርችል ጎዳና ፎቅ ሰርቼአለሁ?”
ሕዝቡም፤ “ኧረ ምን ቆርጦህ”
“በካሳንቺስ፤ በቦሌ፤ በመገናኛ፤ በባምቢስ ---- የመንግሥት ካዝና ዘርፌ፣ እንደ ሰናኦር ግንብ፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ሠርቼአለሁ?”
ሕዝቡም፤ “አልሠራህም”
“ከነጋዴ ጀርባ ሆኜ ንግዱን አሳልጬ፣ በሕገወጥ መንገድ ያካበትኩት ሀብት አለኝ?”
“ንጉሥ ሆይ፤ በሕገወጥ መንገድ ያካበትከው የለህም”
“የኢትዮጵያን ብር ንቄ፣ በብር ዶላሩን መንዝሬ፣ ወደ ፈረንጅ ባንክ ዶላር አሻግሬአለሁ?”
እኛ መንጋው ሕዝብም፤ “ምናምኒት አልነካህም” ብለን ስንመሰክርለት ማየትን ተመኘሁ፡፡ ከዚያም ተሰናባቹን ንጉሣችንን በትከሻችን ላይ አድርገን፣ ፍቅራችንንና ውዴታችንን እየገለጽንለት፣ ከቤተ መንግሥት ወደ ተዘጋጀለት ወደ ግል ቤቱ እስኪገባ ድረስ ቄጠማ ጎዝጉዘን፣ፈንዲሻ በትነን፣ በሆታና በእልልታ ስንሸኘው ማየት ተመኘሁ፡፡
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት፤ጉቦ መቀበል ዓይንን የሚያሳውር፣ ልብን የሚያደነድን መሆኑን ነቢዩ መስክሮልናል፡፡ የዓይን መታወር ትርጉሙ የአካላዊ ዓይን መታወር አይደለም፡፡ የሚያመዛዝን ህሊና ማጣትን፤ በንዋይ ፍቅር ዓይነ ህሊናን ማሳወርን ነው የሚያመላክተው፡፡ ዓይነ ሕሊናው የታወረና ልቡ የደነደነ ሰው፣ የሚያመዛዝን አእምሮ፣ ከሳሽ ህሊና የለውም፡፡
አንድ ሰው አንድ ጊዜ ሙስና ውስጥ ከተዘፈቀ የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ከሙስና የጸዱ ዓይነ ሕሊናቸው አጥርቶ የሚያይ፤ልባቸው ያልደነደነ በጣም ብዙ ሰዎች፣ በየዋህነት ስለ ሙሰኞች የሚናገሩት ነገር አለ፡፡ ሙሰኞች ዘረፉ የተባለውን የገንዘብ ቁጥር የትየለሌነት ሲሰሙ፤ “ይህ ሁሉ ገንዘብ ምን ያደርግላቸዋል? ቤት ከሰሩ፤ መኪና ከገዙ፤ በባንክ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ካላቸው ዘረፋውን ትተው፣ ፊታቸውን ወደ ልማቱ ቢመልሱ ምን አለበት?” እያሉ እርስ በእርስ ሲነጋገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡
ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ የሙስና መሰረታዊ ችግሩ በቂ ሀብት የማግኘት ጉዳይ አይይለም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ሙሰኞች ሀብት ካከማቹ በኋላ ሙስናን እርም ብለው ይተዉ ነበር፡፡ ሙስና መሰረታዊ ችግሩ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ዘርፎ መበልጸግ ብቻ አይደለም፡፡ ሙስና ከመቶ ፐርሰንት በላይ ሁሉንም ነገር ለራስ አግበስብሶ መውሰድ ነው፡፡ ለሙሰኞች መቶ ፐርሰንት ምናቸውም አይደለም። ከመቶ ፐርሰንት በላይ ያለ ነገር ነው የሚፈልጉት። አንድ ሺህ ፐርሰንትም አይበቃቸውም፡፡ ሁሉንም አይደለም የሚፈልጉት፡፡ የሚገታቸው ነገር ካልኖረ በቀር ሁሉም ያንሳቸዋል፡፡
ሙስና ከዚህም በላይ አስፈሪ ነው፡፡ የታላቁን አሳቢ ስብሀት ለአብን ነፍስ ይማርልንና፣ ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ  አራት ኪሎ ቤተ መንግስት በገባ ሰሞን፣ “እፎይታ” የሚባል መጽሔት ላይ “ፈርዖን ሢሦ ዝና” በሚል ርዕስ (ይመስለኛል) የጻፈውን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲህ የሚል ነው፡-
“--ያ ዓይነ ሕሊናው የታወረ፣ልቡ የደነደነ ፈርዖን፤ በሩቅም በቅርብም ያለውን ሁሉንም ጠራርጎ ቆረጣጥሞ በላ፡፡ ዙሪያውን ቢቃኝ ምንም የሚላስ የሚቀመስ ነገር አጣ፡፡ ከዚያ የገዛ እግሩን፤ የገዛ እጁን እየበላ የራሱን የሰውነት ብልቶች-- ሆዱን፤ ባቱን፤ ራሱን፤ ምላሱን ምኑንም ሳያስቀር በልቶ ጨረሰ፡፡ የቀረው ነገር ቢኖር ጥርሱ ብቻ ነበር፡፡ ጥርሱን በጥርሱ ባለመብላቱ ግን በጣም ይቆጨዋል፡፡”
 በቃ ሙሰኛ ማለት ይሄ ነው፡፡


Read 1381 times