Saturday, 07 October 2017 14:40

(እውነተኛ ታሪክ) የመስቀል ዋዜማ የሩጫ ምሽት!

Written by  ኃይለይ ገብረእግዚአብሔር
Rate this item
(7 votes)

   ሰሞኑን የያዝኩትን ስራ መጨረስ አሊያም ማገባደድ ስለነበረብኝ ዛሬም አመሽቼ ነበር ከቢሮ የወጣሁት፡፡ እንደ ትናንትናው በጣም ባላመሽም ከመስሪያ ቤት  ስወጣ ግቢው ፀጥ እረጭ ብሎ ነበር፡፡ ያው የመስቀል በአል ዋዜማ አይደል፡፡ ብዙ ሰው ወደ መስቀል አደባባይ ሄዶ ነው የሚል ሀሳብ ጭንቅላቴ ውስጥ ሽው ሲል፣ የታክሲ ነገር ትዝ ብሎኝ፣ ቤት በቶሎ ደርሶ የማረፍ ተስፋዬ ዳሸቀ። አብዛኛውን ጊዜ ከሜክሲኮ ወደ ቤት ለመሄድ የአራት ኪሎ ታክሲ ብመርጥም ዛሬ ግን የአራት ኪሎ ታክሲ በቀላሉ ማግኘት ብርቅዬ እንስሳ እንደ ማሰስ ያህል እንደሚያዳግት እየገመትኩ፣ እያቅማማሁም ቢሆን የፒያሳን ታክሲ ለመያዝ ከራሴ ጋር ከስምምነት ደረስኩ፡፡ የተደገሰልኝን እሳት መቼ አውቄ!!!
ታዲያ የፒያሳን ታክሲስ ቢሆን እንዲሁ ያገኘሁ እንዳይመስላችሁ! ከወደ መስቀል አደባባይ አቅጣጫ ወደየሰፈሩ የሚጎርፍ ህዝበ ምእመናን ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ እንዲያውም መቶ ሚሊዮን መሙላታችንን ለሚጠራጠሩ ፈረንጆች፤ ይሄን ማሳየት ነበር አልኩኝ፣ ከአመት በፊት ከአንድ ኮንጎአዊ (ግር አይበላችሁ “የኮንጎ ዜግነት ያለው” እንዳልል ከአንድ በጣም ታዋቂ ያልሆነ ሬድዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ አነጋገር ጋር እንዳይመሳሰልብኝ ብዬ ነው፡፡ ድንቄም ማካበድ!!) ጋር ያደረግሁት ክርክር ትውስ ብሎኝ፡፡ ለዚያውም የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን ሳይጨምር ነው፡፡
እንደዚህ እንደ አቅሚቲ እየተፈላሰፍኩኝ የፒያሳ ሰልፈኞችን ተቀላቀልኩ፡፡ ሰልፉም ያው እንደምታውቁት ነው፡፡ የአንድ ቀበሌ አባወራዎች የሚያክሉ ሰዎች ተኮልኩለዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት የትራንስፖርት እንግልትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ (?) ከጫንቃችን ለማሽቀንጠር ተደራሹ መፍትሄ፤ ተደራጀቶ ታክሲ መግዛት ነው አልኩ በምናቤ፡፡ ሄሄሄሄ …ሃሃ… ‘የማይመስል ነገር ለምንህ አትንገር’ ነበር የሚባለው፡፡ ብቻ እንደው ጭንቅ ሲለኝ ነው፡፡ ከዚያ  ራሴን በሀሳብ ሳንገላታ፣ ልብ ሳልለው ከፊቴ የነበረው ህዝብ ታክሲ ውስጥ ገብቶ ኖሮ ከኋላዬ የነበሩት ተሰላፊዎችና ተራ አስከባሪው ሲጮሁብኝ፣ ደንገጥ ብዬ ተንደርድሬ ገባሁ፡፡ በመጨረሻው ወንበር ጥግ ላይ በቀኝ መስኮት በኩል ተቀመጥኩ። ለምን እንደሆነ እንጃ ብቻዬን፣ ስሆን ጥግ የቀኝ መስኮቱ ባለበት ቦታ መቀመጥ ለምዶብኛል፡፡ ሌላ ሰው ቀድሞኝ ሲቀመጥ ራሱ ቅር ይለኛል፡፡ እናም እንደ ልማዴ እዛችው ቦታ ላይ ዘጭ አልኩ፡፡ ሶስት ሴቶች ተከታትለው ገቡ፡፡ ወያላው (ውይ ይቅርታ ረዳቱ ለማለት ነው!) እናም ወያ…..ኧረ  ማለቴ ረዳቱ፤ “ሶስት ሶስት ነው ጠጋ ጠጋ በሉ”  ሲል ሰማሁት፡፡ ሌላ ጊዜ የይቅርታን ልባስ እያለበሱ ነበር የሚያዙን፡፡ ዛሬ ግን ይቅርታዋ ቀርታለች፡፡ ይሁን ግድ የለም ዛሬ፣ የበአል ዋዜማ ስለሆነና ታክሲም ስለሌለ ጌቶችን እንታዘዛቸው አልኩኝ፣ በማያገባኝ፡፡ (ያው ጥግ ላይ አይደል የተቀመጥኩት)
ታክሲው ትርፍም ኪሳራም ጭኖ መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ ከጎኔ የተቀመጡት ሁለት ሴቶች (ፊታቸው የጩጬዎች ቢመስልም ጩጬዎች እንዳልላቸው የእድገት ጣርያቸውን ለመንካት እየተቃረቡ ያሉ ስለመሰሉኝ)፤ ወይም በቃ ልጆች ልበላቸው….. እናም ልጆቹ መንጫጫት ጀመሩ፡፡ እነሱ እያወሩ ነበር፡፡ ግን እኔ መንጫጫት ብለው ይሻለኛል። አንዴ ስለ ሳሚ ያወራሉ፡፡ ስለ ሳሚ ሳይጨርሱ ሸዋዬ ወይም ሸዋ… ብቻ እንደዛ ነገር የሚባል ሰውን ያማሉ፡፡ (ተገድጄ ነበር ስሰማ የነበረው) ቆይተው ደግሞ ይዘባበታሉ፡፡ አንዷ ሌላኛዋ ላይ ትዝታለች። ቆይተው ስለ ሀበሻ ቀሚስ ያነሳሉ፡፡ ያነሱትን ሀበሻ ቀሚስ ወደ ነበረበት ሳይመልሱ ስለ ምግብ ያወራሉ፡፡ የባጥ የቆጡን እንዳልል፣ የባጥ የቆጡን ብቻ አይገልፀውም። በዛ ላይ ጮክ ብለው ነው የሚያወሩት፡፡ አንዷ ደግሞ በትርፍ ከፊት ለፊቴ በነበረው ጣውላ ላይ ነበር የተቀመጠችው። ድምፅዋ ከአፏ ወጥቶ ከጎኔ ወደ ነበሩት ጓደኞቿ ጆሮ ለመድረስ መጀመሪያ የግራ ጉንጬን ታክኮ፣ በግራ ጆሮዬ በኩል ማለፍ ነበረበት። ደግሞ ያለችኝ ጆሮ እሷ ናት፡፡ የቀኜ እስከዚህም ናት፡፡ እንግዲህ በቦታው ባትገኙ እንኳን ሁኔታውን ሳሉት፡፡ ፊቴ በፂም ባይሸፈን ኖሮ እንደ የብራዚሎች ባርበኪዩ ወይም ጋዝ ላይት ጥብስ…..
እነዚህ ሁሉ ተባዝተው-ድካምም ተጨምሮበት አቅሌን አሳጡኝ፡፡ መድረሻዬም ናፈቀኝ፡፡ ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ ሳይሆን ከአዋሳ ወደ ዛላምበሳ እየሄድኩ ያለሁ መሰለኝ (አጋነንከው ማለት መብታችሁ ነው)፡፡ በትእግስት ማጣት መንፈስ፣ አይኖቼን እያቅበዘበዝኩ፣ ወደ አስፋልቱ ወረወርኩ፡፡ ህዝቡ የቸርችል ጎዳናን አቀበት ተዘርቶበታል፡፡ ብዙ ሴቶች የሀበሻ ቀሚስ ለብሰዋል፡፡ አንዳንዶቹ አምሮባቸዋል። አንዳንዶቹ ግን እኛስ ከማን እናንሳለን በማለት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት የለበሱት ነው የሚመስለው፡፡ “ቆይ ግን የሀበሻ ቀሚስ መልበስ ፋሽን ሆነ እንዴ?” የሚል ድምፅ የጆሮ ግንዴን ለብልቦኝ አለፈ፡፡ ስቅጥጥ አለኝ፡፡  
ስልክ እንደያዝኩ አሁን ገና ትዝ ያለኝ ይመስል፣ በድንገት እጄን ወደ ኪሴ ከትቼ ስልኬን አወጣሁ፡፡ አላማ የለሽ በሆነ ሁናቴ መጎርጎር ጀመርኩ፡፡ አንዴ contact የሚለውን ወደ ታች አንሸራትታለሁ፡፡ ለአፍታ እንኳን ሳልቆይ የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላትን ከፈትኩ፡፡ ለጥቄ ደግሞ የስፔንኛ ቋንቋ አፕልኬሽን፣ እንደገና candy crush፣ ቀጥሎ ቫይበር….ጣቶቼ ሰከን ማለት አቃታቸው፡፡ ጭንቅላቴ ባተለ፡፡
ታክሲው ኤልያና ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኝ የትራፊክ መብራት ጋ ሲደርስ ፍጥነቱን ቀነሰ፡፡ በዚህ ቅፅበት ከየት እንደመጣ ያላየሁት እጅ፣ የታክሲውን መስተዋት ከፍቶ፣ በእጄ የያዝኩትን ስልክ መንትፎኝ ውልብ አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ያደረግኳቸው ድርጊቶች ሀሉም ደመነፍሳዊ ነበሩ፡፡ በመስኮቱ ልዘል ስል መኪናው ስለተንቀሳቀሰ ነው መሰለኝ፣ ሚዛኔን አስቶኝ አስፋልቱ ላይ ተፈጠፈጥኩ፡፡ ከፊቴ ተቀምጣ የነበረችው ልጅ ሁለቴ ስትጮህ የሰማኋት ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው፣ ከየት መጣ ያላልኩት እጅ ሞባይሌን ሲመነትፈኝ ሲሆን ሁለተኛው ድግሞ አስፋልቱ ላይ ስፈጠፈጥ ነው። ከወደቅኩበት ከመቅፅበት ተነስቼ፣ ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ ቁልቁል መሮጥ ጀመርኩ፡፡ ከፊት ለፊቴ የሚሮጥ ልጅ ይታየኛል፡፡ የነበረኝን ጉልበት አሰባስቤ፤ “ሌባ ሌባ ያዙት” እያልኩኝ ልጁን ተከታተልኩት፡፡ ስሮጥ ከጀርባዬ የሰዎች ጩኸት በግማሽ ልቦናዬ ይሰማኛል፡፡ “ሌባ ሌባ” መሰለኝ ሲሉ የነበረው፡፡ ከፊት ለፊቴ የነበሩት ቆመው የሚያዩኝ ይመስለኛል፡፡ በኋላ እንደጠረጠርኩት “ሌባ ሌባ” ብዬ ብጮኽም ሌባው እኔ ሆኜ  እየሸሸሁ ያለሁ መስያቸው ይሆናል፡፡ ወይም በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡  ከፊት ለፊቴ በሩቁ የሚሮጠውን ልጅ አላዩት ይሆናል፡፡  ብቻ እኔ ግን “ሌባ ሌባ… ያዙት ያዙት” እያልኩ መሮጤን አላቆምኩም፡፡ ጠዋት ጠዋት መሮጥ ካቆምኩ ወደ አንድ አመት ገደማ ቢሆነኝም ቅሉ የኔ መሆኑን ባጠራጠረኝ ፍጥነት ተፈተለኩ፡፡
ከመንታፊው ጋር የነበረው ርቀት እየጠበበ ሄደ፡፡ ከፊቴ ፍንትው ብሎ ይታየኝ ጀመር፡፡ ይህም ብርታቴን ጨምሮልኝ እያለከለኩም ቢሆን መሮጤን ቀጠልኩ፡፡ አሁንም ከኋላዬም ከጎኔም ሰዎች እየሮጡ ያሉ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን ከፊት ለፊቴ፣ ፊቱን መለስ እያደረገ ከሚሸሸው ልጅ ዐይኖቼን አልነቀልኩም፡፡ እየተጠጋሁት መምጣቴን የተረዳው መንታፊ፤ ሞባይሉን አስፋልቱ ላይ አስቀምጦ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ ዐይኖቼ አስፋልቱ ላይ የተቀመጠውን ሞባይልና የሚሸሸውን ልጅ እያፈራረቁ ይመለከታሉ፡፡ “ሌባ ሌባ ያዙት” ብዬ እጮኻለሁ፡፡ ሰዎቹ ግን ከሩቅ ፈዘው ያያሉ፡፡ ስልኬ ከተቀመጠበት ቦታ እንደደረስኩ ስልኩን አንስቼ መሮጤን ቀጠልኩ፡፡
ከፒያሳ ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ በሚወስደው ቁልቁለት፣ በቀኝ በኩል የቁጥቋጦና የትናንሽ ተክሎች ክምችት ይገኛል፡፡ መንታፊው ያንን ክምችት ተገን በማድረግ ከዐይኔ ተሰወረ፡፡ በንዴት እየጦፍኩ፣ ቁጥቋጦው ያለበት ቦታ ለመድረስ የነበረኝን አቅም አሟጥጬ ሮጥኩ፡፡ ተክሎቹን አልፌ ስመለከት፣ የነተበ ግራጫ ዓይነት ሹራብ ለብሶ፣ ከፊት ለፊቴ ሲፈረጥጥ የነበረውን ልጅ አጣሁት፡፡ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ዐይኖቼን ሳንከራትት፣ የተወሰኑ ልጆች በቅርብ ሆነው ያዩኛል፡፡ “ፖሊስ ይይዘዋል….  ምናምን ” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
ገልመጥ ብዬ ሳይ አንድ ልጅ ፈንጠር ብሎ እያለከለከ አየሁት፡፡ እኔም ቁና ቁና እየተነፈስኩ ወደ እሱ ተጠጋሁና፤ “አንተ ነ…ህ…..” ብዬ ልረግጠው ስል “አኔ አደሉም… ሌባውን  ስከተል ኖው ኢንዲህ…” ብሎ መማፀን ጀመረ በተሰባበረ አማርኛ። በዙርያው የነበሩት የእሱ እኩዮችም፤ “ ኧረ እሱ አይደለም…ምናምን” አሉ፡፡
በምሽት የመንገድ መብራት የመንታፊውን ፊት ባላየውም ልጁ ግን ራሱ መሆኑን እርግጠኛ ነበርኩ። ሌላ መንታፊን ለማሳደድ አቅም ያልነበረው ገና ልጅ ነበር፡፡ ልጆቹም የእሱ ጓደኞች ነበሩ፡፡ ብልጭ ብሎብኝ ልዘነጣጥለው ስል አንድ ነገር ትውስ አለኝ። የ3600 ብር ስልክ ለማዳን፣ የ20 ሺ ብር ላፕቶፔን ታክሲው ውስጥ ጥዬ ነበር የተከተልኩት። ለዚያውም የመንግስት ንብረት! ከታክሲው ስዘል፣ ይሄን ሁሉ ማስታወስና ማመዛዘን የማይታሰብና የቅንጦት ያህል ነበር፡፡ አሁን ትዝ ሲለኝ ግን ክው አልኩ፡፡ ትቼያቸው ወደ ላይ አቅጣጫ መሮጡን ተያያዝኩት፡፡ የሩጫ ምሽት!
ከሩቅ ስመለከት ታክሲው በነበረበት ቦታ የለም። “ወይኔ!” አልኩኝ፡፡ ላፕቶፑን ሊሰጡኝ ቢፈልጉ ራሱ፣ በምን አድራሻ አግኝተውኝ ይሰጡኛል? አተርፍ ባይ አጉዳይ ልሆን? ሁለት አመት ያገለገለ ሞባይልን ለማዳን ብዬ፣ አዲስ ላፕቶፔን ላጣ ነው? አእምሮዬ በጭንቀት ተወጥሮ፣ ፍጥነቴን ጨምሬ ዳገቱን ተያያዝኩት፡፡ ራቅ ብሎ የትራፊክ መብራቱ ሥር አንድ ነጭ ታክሲ ቆሞ አየሁ፡፡ የነበረችኝ ቅንጣት ታህል ተስፋ ስታንሰራራ ታወቀኝ፡፡ ፈጠን ፈጠን ብዬ ተራመድኩ፡፡ እንደ ቅድሙ ለመሮጥ አቅም አልነበረኝም፡፡
ታክሲው በር ላይ ሰዎች ተሰብስበው እኔ ላይ ይጠቋቆማሉ፡፡ ቀረብ አልኩ፡፡ ታክሲው ራሱ ነው። ኦ! ተመስገን ጌታዬ! በሩ ጋ የነበሩት ሰዎች፤ “አገኘኸው?” አሉኝ፡፡
“አዎ” አልኳቸው እያለከለኩ፡፡ ስልኩን በእጄ ይዤው ነበር፡፡
“ጀግና! ጀግና! ” እያሉ አጨበጨቡ፤ ታክሲው ውስጥ የነበሩ ሰዎች፡፡ አንዱ ጀርባዬን ቸብ አደረገኝ። ፊቴ ላይ የፈገግታ ብልጭታ ታየ፡፡
 “ጀግና” እና “ብራቮ” በሚሉ ቃላት ታጅቤ፣ ወደ ታክሲው ገባሁ፡፡ ቦርሳዬን፣ ትከሻን ከሚፈታተን ላፕቶፑ ጋር ተቀምጬበት ከነበረው ወንበር ላይ አገኘሁት፡፡ እውነትም ጀግና ነኝ ብዬ፣ ራሴን ካብኩ።
“ውይ የሚገርም ነው” አለች አንዷ፡፡
“እንዴ ምን ሆነህ ነው ግን እንደዛ የተፈጠፈጥከው?” አለች ሌላኛዋ፡፡
“መስኮቱን ከፍቶ ሲወስድበት ታድያ ምን ያድርግ? ድንጋጤ ነዋ!” መለሰች፤ ከጎኔ የነበረችው፡፡
“አይዞህ ተረጋጋ” አለ፤ ከወደ መሃል የመጣ የወንድ ድምፅ፡፡
“ድፍረታቸው!” አለች፤ ሌላ ሴት፡፡
ከዚህ በፊት እንደ አብዛኛው ሰው፣ ካ’ንዴም ሁለቴ ስልኬን ተሰርቄ አውቃለሁ፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ከተናደድኩና ከተከዝኩ በኋላ ግን ረሳኋቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ዐይን-አውጣ ድፍረት ግን በወሬም ሰምቼ አላውቅም፡፡ እኔ ራሴ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ በአንድ ህጣን ልጅ ተወስዶ ሳላስመልሰው ብቀር ኖሮ በጣም…እጅጉን በጣም ነበር የምጨሰው፡፡ አለ አይደል የሚያንገበግብ ነገር ነበር የሚሆንብኝ፡፡ ከፈለጉ ታክሲ ውስጥ ለመግባት ስጋፋ፣ ሳልሰማና ሳልባንን ቢወስዱት አንድ ነገር ነው፡፡ እንጂ በእንደዚህ?? አይሆንም!! ሰው፣ የራሱ የሆነውን ንብረት ቀርቶ፣ አውቆ የጣለውን እንኳን ሲያነሱበት  አይወድም፡፡
ታክሲው ውስጥ ገብቼ ትንሽ እንደተረጋጋሁ፣ የቀኝ እጄ ሦስት የመሀል ጣቶቼ አንጓቸው ላይ መላላጡንና መድማቱን አየሁ፡፡ የግራ እጄ ክርን ላይም እንዲሁ የሕመም ስሜት ተሰማኝ፡፡ የእጅ ሰዓቴን ስፈልግ እጄ ላይ አጣሁት፡፡ እጄን ወደ ኪሴ ስሰድ አገኘሁት፡፡ መቼ እንደከተትኩት አላስታውስም፡፡ እቤት ስገባ ደግሞ የግራ እግር ጉልበቴ ክፉኛ መላላጡን አየሁ፡፡ “የጀግንነት ምልክቶች” አልኩኝ፤ ለራሴ ፈገግ እያልኩኝ፡፡
“ ሂድ ወደዛ ጉረኛ! ጦርነት የዘመትክ መሰለህ እንዴ” አለ፤ ሌላኛው ውስጤ ደግሞ፡፡
መስከረም 16 ቀን 2010 ዓ.ም
ራሳችሁንም ንብረታችሁንም ጠብቁ!!

Read 2363 times