Saturday, 07 October 2017 14:41

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የተቃጠለው የወረቀት ጭስ መልዕክት

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(1 Vote)

   የዛሬው ዐውድ በማይደፍረው ቀደምት አባባል ልንደርደር፡፡ እናቴ ደጋግማ ከምትናገረው አባባል። “ጨዋ ባል. . .” ትላለች ወ/ሮ ወሰኔ፤ “ጨዋ ባል ሚስቱን የሚገስፀው መጀመሪያ ባርኔጣውን አውልቆ አክብሮቱን ከገለፀ በኋላ ነው፡፡” ይህንን የእምዬ አባባል የምወደው ከአንጀቴ ነበር፡፡ “ጨዋ ሚስትስ ባሏን ስትገስፅ?”  ብዬ በተገዳደርኳት አንድ ዕለት እናቴ የሰጠችኝ መልስም አብሮ ቢታከልበት ክፋት የለውም፡፡ “አይ የእናንተ ትምህርት! ክንብንቧን ዝቅ አድርጋ ነው እንድልህ ነው?” በጨዋነት ወዝ የታሸ ግሩም የጥበብ ንግግር ይሏል እንዲህ ነው፡፡
እኔም በአየር መንገዳችን ላይ ቅር ያሰኘኝን ትዝብቴን ከመግለጼ አስቀድሞ ለውጤታማው የአየር ላይ ጥያራችን አክብሮቴንና አድናቆቴን በአንዳንድ ትዝታዎቼ እያዋዛሁ የምገልፀው በቅድሚያ ባርኔጣዬን አውልቄ “ብራቮ አየር መንገዳችን! ብሩክ ሁንልኝ!” እያልኩ በየጊዜው ስለሚያስመዘግበው ውጤት በመመረቅ ነው፡፡
ይህን አክብሮቴን የምገልፀው ለማለት ያህል ብቻ እንዳይደለ ማረጋገጫውን መስጠት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ አየር መንገዳችን የሀገራችን አምባሳደር ነው መባሉ አውነት ነው፡፡ የሀገር ኩራት ተብሎ ቢንቆላጰስም አያንስበትም፡፡ የአፍሪካ አውራ መሰኘቱም አግባብ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሽልማቶች መንበሽበሹም ስለሚገባው ነው፡፡ አየር መንገዳችን ለኢኮኖሚያችን ድጋፍ፣ ለፖለቲካው የፊት ጥላሸት እንደማበሻ ቅባት፣ ለማኅበራዊ ትስስራችን እንደ መልካም አብነት፣ ለቱሪዝም ዘርፉም እንደ ዋና አጋዥ ወዘተ. ማገልገሉን አሌ የምንለው አይደለም፡፡ በአየሩም ላይ በዝናውም ላይ መልካም በረራ እመኛለሁ፡፡
አየር መንገዳችን የአገራችን አምባሳደር የመሆኑን ያህል እኛ ተጠቃሚዎቹም የአየር መንገዳችን አምባሳደሮች መሆናችን እንደማይካድ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለሆነም ነው እሶሶ ማለት ብቻ ሳይሆን መውደዳችንን የምንገልፅለትን ያህል ህፀፅ የመሰለንንም ነገር የማመልከት ግዴታ ያለብን፡፡ በአንድ ወቅት በውጭ ሀገር ትምህርት ላይ በነበርኩበት ወቅት ሀገሬን ካልጎበኘህ እያልኩ ፋታ የነሳሁት  የትምህርት ቤት ጓደኛዬን ምስክርነት በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ አግባብ ይመስለኛል። ይህ ጓደኛዬ ለውትወታዬ ምላሽ ሰጥቶ ሀገሬን ለመጎብኘት የመወሰኑን የምስራች ሲነግረኝ አክዬ ያዘዝኩት ተጨማሪው ትዕዛዝ፤ “የምትጓጓዘው በኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን እንዳትዘነጋ” የሚል ነበር፡፡
ከአለም አቀፍ ሚዲያዎች ከሚሰማቸው አንዳንድ የሀገሬ የወቅቱ ሁኔታዎች ትንሽ ቅሬታ ብጤ ሽው ብሎበት የነበረው ጓደኛዬ፤ ከጉብኝቱ እንደተመለሰ አስቀድሞ በተፍለቀለቀ ስሜት የገለፀልኝ የአየር መንገዳችንን ብቃት፣ ቅልጥፍናና አኩሪ መስተንግዶ ነበር፡፡ እሰይ፡፡ ቀጥሎ የመሰከረልኝ ደግሞ በኢትዮጵያዊ ትህትናና አክብሮት፣ ባለቤቴ በቤታችን የጋበዘችውን የባህላዊ ቡና መስተንግዶ ነበር፡፡ ግሩም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ፊቱ እየዳመነ በቅሬታ የገለፀልኝ ግን በጉብኝቱ ወቅት ባስተዋላቸው መልካም ሀገራዊ እሴቶች ከመደሰቱ የተነሳ የሀገሬ ወጣቶች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ የስኮላርሺፕ ፕሮግራም ለማመቻቸት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ለመግለፅ፣ ከራሱ ሀገር የኤምባሲ ሰዎች ጋር ወደ በርካታ መንግሥታዊ መ/ቤቶች  በሄደበት ወቅት ያጋጠመው የቢሮክራሲያችን አሸማቃቂ ፈተና ነበር፡፡ አይጣል፡፡ “በራሷ አረም እባብ ይዛ ታስፈራራለች” ይሏል በእንዲህ አይነቱ ጊዜ ነው፡፡
ይህንን ጓደኛዬን ለስሙ የትምህርት ቤቴ ጓደኛ አልኩት እንጂ በሀገሩ እጅግ የተሳካለት የቢዝነስ ሰው ነበር፡፡ ከዚህ ሰው ጋር አብረን የተማርነው የእውቀት ጥማት ስለነበረው እንጂ በሚያገኘው የትምህርት ማስረጃ እንጀራ እንደሚወጣለት አስቦ እንዳልነበር መግለፁ አግባብነት አለው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄው ጓደኛዬ የሀገሬ ቢሮክራቶች ጥርቅም አድርገው በሩን እንደዘጉበት ሲረዳ፣ ቃሉን ለመጠበቅ ሲል ብቻ የወሰደው እርምጃ፣ በኬኒያ ለሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ዕድሉን ማመቻቸት ነበር፡፡ ተሳክቶለትም ብዙ ልጆቻችንን ለማስተማር ችሏል፡፡ ወዳጄ ቲም ሃለኩዬስት፤ ውለታህንና በሀገሬ ጉዳይ የተሰማህን ድብልቅልቅ ስሜት፣ አንድ ቀን በቋንቋችን በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ መግለፄ አይቀርም ያልኩህን ቃሌን አክብሬ እነሆ ዛሬ ተግባራዊ አድርጌዋለሁ፡፡ ለአየር መንገዳችሁ ምስጋናዬን አድርስልኝ በማለት የጣልክብኝን የአደራ ቃልም  እነሆ ቢዘገይም አጋጣሚውን አግኝቼ በማድረሴ ከአደራ በልነት ተርፌያለሁ፡፡
ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ገና አልገባሁም፡፡ የወረቀቱን ጭስ ጉዳይ አስመልክቶ የምገልጸው ወደ ኋላ ግድም ነው፡፡ ከሆነ አይቀር ስለ አየር መንገዳችን ያለኝን አንድ ቆምጠጥ ያለ ትዝታ ልቀስቅስ፡፡ በኮሞሮስ ደሴት ላይ የተከሰከሰው የአውሮፕላናችን ክፉ ትራዤዲ፣ ከብዙ ዜጎች አእምሮ በቶሎ የሚጠፋ አይደለም፡፡ እኔን ጨምሮ፡፡ ያ የኮሞሮስ እልቂት በተፈፀመበት እለት በአጋጣሚ በአሜሪካኗ የሃዋይ ክፍለ ግዛት በምትገኘው የማዊ ደሴት ላይ ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ስልጠና ላይ ነበርኩ፡፡ እናም በዚያ ክፉ ዕለት፣ ክፉ ዕጣ የገጠመው አውሮፕላናችን ከሰማይ እየተምዘገዘገ ወርዶ በባህር ላይ መከስከሱን ያስተዋሉት የስልጠናው ተካፋዮች፣ አውሮፕላኑ የሀገሬ ንብረት መሆኑን ሲረዱ፣ በእግር በፈረስ አስፈልገው ዜናውን እንድከታተል መርዶውን አረዱኝ፡፡ እናም ያንን ትራዤዲ በእንባ እየታጠብኩ ተመለከትኩት፡፡ እንባዬን እያዘራሁ ምግብ በአፌ እንደተንቀዋለለ እስከ ሰልስቱ ድረስ እየቆዘምኩ ሰነበትኩ፡፡ “አወይ ወገኖቼ! ይህ ክፉ እጣ የደረሳቸው እነማን ይሆኑ?” እያልኩ በመሳቀቅ፡፡
ሁኔታውን እስካጣራ ድረስም እረፍት አጣሁ። በሀገር ቤት ያሉት ቤተሰቦቼና የስራ ባልደረቦቼ የስልክ ልውውጥ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ያለቁትን ወገኖቼን ማንነት በመሸሸግ፣ “ስትመጣ ይደርሳል” እያሉ የመርዶውን ጉዳይ አመሳጠሩብኝ። ስልጠናዬን አጠናቅቄ የሀገሬን ምድር ለመርገጥ የበቃሁትም እንባዬን እያዘራሁ ነበር፡፡ የፈራሁት አልቀረም ያ ክፉ እጣ ካጋጠማቸው የሀገራችንና የውጭ ሀገራት ወገኖቻችን መካከል አንደኛው የቅርብ የስራ ባልደረባዬና ወደ አሜሪካ ከመብረሬ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በፀሎት የሸኘኝ፣ በጋብቻ ከኢትዮጵያዊቷ መልካም ሴት ጋር የተጋባው ርህሩሁና ለሀገሬ ድሃ ወገኖች ራሱን በመስጠት ሲያገለግል የነበረው እንግሊዛዊው አንዲ ሚከንስ ነበር፡፡
ሁለተኛው የዚያ ክፉ ቀን ሰለባ የሆነው የረጂም ዘመን ወዳጄ ፍልቅልቁ በየነ ጉተማ ነበር፡፡ ሦስተኛው ሰው ነፍሳቸው በተአምራት እንድትተርፍ ከሰማይ ምህረት ከታወጀላቸው መካከል አንዱ የረጂም ዓመታት ወዳጄና ቡና አጣጬ፣ የቅርብ ጎረቤቴ ዶ/ር ይስሃቅ ነበር፡፡ ሕይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን ህልፈት በመሪር ሃዘን ብንቀጣም እንደ ዶ/ር ይስሃቅ በሕይወት ትረፉ ያላቸውን ወገኖች ማየት ደግሞ በእጅጉ የሚደንቅ ነበር፡፡
አሁን ወደ አየር መንገዳችንና ወደ ጭሱ መልዕክት ጉዳይ እናኮብኩብ፡፡ በቅርቡ አየር መንገዳችን የደረሰበትን የዕድገት ጫፍ ለማመልከትና የዘመነ ቴክኖሎጂው ትሩፋት ተቀዳሚ ተጠቃሚ መሆኑን ለማብሰር ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ጨምሮ በርካታ ጎምቱ እንግዶች በታደሙበት ፕሮግራም ላይ አንድ ተምሳሌታዊ ድርጊት መፈፀሙን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እያጨበጨቡና እየተቀባበሉ ዘግበውታል፡፡ የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ፣ አየር መንገዳችን በወረቀት የሚሰጠውን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ አቁሞ “ከወረቀት ንክኪ ነፃ ወደ ሆነ የቴክኖሎጂ አገልግሎት መሸጋገሩን” ለማብሰር ነበር፡፡ የምሥራቹ ማብሰሪያ ዘዴ ደግሞ በይፋና በግላጭ አይንህን ላፈር ብሎ ከእርግማን ባልተናነሰ ፉከራ ዘመነ ጽሕፈት እንዳረጀና እንዳፈጀ ለመግለፅ የወረቀት ክምር በማቃጠል አዋጅ ማስነገር ነበር፡፡ አዬ ጉድ! አዬ ጉድ!!!
ከወረቀት አገልግሎት ወደ ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መሸጋገርን ለማብሰር ወረቀትን በማቃጠል ደስታን መግለፅ ለምን አስፈለገ? ለመሆኑ አየር መንገዳችን ይህንን መሰል ግዙፍ ታሪካዊ ስህተት ለመፈፀም ሲዘጋጅ፣ እስቲ ቆይ ደጋግመን እናስብበት፣ ብሎ የሚያማክር የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ እንዴት ይጠፋል? ሹማምንቱስ የወረቀት ማቀጣጠያ ክብሪት ከቆነጃጂቱ እጅ ሲቀበሉ፣ ህሊናቸው ምንም እውነታ ሹክ አላላቸውም? ያ እንደ መስቀል ደመራ ከእዮሃ ዝማሬ ባልተናነሰ ስሜት የተቃጠለው የወረቀት ጭስ፣ ገና በንባብ ባህል ላልዳበረውና “ፊርማና ወረቀት ጠፊ ነው ተቀዳጅ መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ” እያለ ለሚያንጎራጉረውና ለንባብ ባህል ሙሉ ለሙሉ አይኑ ላልተከፈተውና በሚሊዮን ለሚቆጠረው “ወረቀት ብርቁ” ወገናችንስ ምን ትርጉም ይሰጣል? ታዳጊዎቹ ልጆቻችን ከወረቀት ፍቅር (ንባብ) እንዳይፋቱ ርብርብ ያሻዋል እየተባለ በሀገራችን ምሁራንና የድርሰት ቤተሰቦች ጥረት በሚደረግበት ወቅት አየር መንገዳችን “የምን ወረቀት” በማለት በቃጠሎው ጭስ፣ ለሕዝባችን አዋጅ ማስነገሩ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው?  
ደግሞስ በሌላው ገጽታ የቴክኖሎጂውን ጥበብ እጅጉን በተካኑና በተራቀቁ ዓለም አቀፍ ወንበዴዎች (Cyber Attackers) ምድራችን በምጥ ጣር ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት ጥቃቱን ወይንም ሰበራውን ለመከላከል ሀገራዊ አቅማችን ምን ያህል የዳበረ ቢሆን ነው፣ አየር መንገዳችን ወረቀት እያቃጠለ ቻዎ! ቻዎ! ወረቀት በማለት “ዘራፍ” ሲል የተደመጠው፡፡ ግዴለም ሀገራዊ አቅማችን አስተማማኝ ነው ብለን እንመን፣  ለቴክኖሎጂ ሰባሪ ወንበዴዎችም አለመበገራችን እውነት ነው እንበልና እንቀበል፡፡ ለመሆኑ ወረቀትን ማቃጠሉ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ለአየር መንገዱ ገጽታ መዳበርስ ምን የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አለው? ከአቻ አየር መንገዶች ጋር ለሚኖረው ውድድርስ አስተዋፅኦው ምን ያህል ነው?
እንኳንስ በቴክኖሎጂ ሀሁ ላይ የምንገኝ እኛን መሰል ታዳጊ ሀገራት ቀርቶ በቴክኖሎጂ አቅማቸው የዳበሩና በዘርፉ የተጠበቡት ሀገራትም ቢሆኑ የወረቀት አገልግሎት ማብቃቱን ለማረጋገጥ በሰነዳቸው ላይ እሳት እየለኮሱ ከወረቀት ለመቆራረጥ የወሰኑ አይመስለኝም፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት ታላቋ አሜሪካ የወረቀት አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ አስቀራለሁ ብላ ቀረርቶዋን ስታሰማ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአጥቢያዋ ተገኝቶ ይታዘብ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ባይሳካላትም፡፡
ይህቺው ሁሉ በእጄ፣ ሁሉ በደጄ ባይ አሜሪካ አልፎም ተርፎ በየጊዜው የሳይበር ጥቃቱ እያየለ በመምጣቱ ሀገሪቱ መያዢያ መጨበጫ አጥታ፣ በፖለቲካ የስልጣን ውድድሩም ሆነ በኤኮኖሚው ዘርፍ የጥፋት ፍልፈሎቹን መቋቋም ተስኗት ግራ እንደተጋባች አለች፡፡ Equifax የተባለ ትልቁ የአሜሪካ የዱቤ ሪፖርቶች አቀናባሪ ኮርፖሬሽን፣ በቅርቡ በገጠመው የሳይበር ወረራ ምክንያት በአንድ ወር ብቻ ከ145 ሚሊዮን በላይ የደንበኞቹ አካውንት ላይ ጥቃት ስለደረሰበት አንገቱን በሀዘን እንደደፋ ሲሆን የኮርፖሬሽኑ ሹማምንትም በመርማሪው አካል እየተተራመሱ ይገኛሉ፡፡
በቴክኖሎጂ ቀማኞች ምክንያት በአብዛኛዎቹ ተቋማቷ ላይ በገጠማት ሀገራዊ ቀውስ የተነሳ ዩክሬን እስካሁን ድረስ ማገገም አቅቷት እየተንገዳገደች ትገኛለች፡፡ በቅርብ ወራት ውስጥ ብቻ እንኳ የአሜሪካኖቹ ዴልታ፣ ዩናይትድ ኤርላየንስና ብሪትሽ ኤርዌስን የመሳሰሉት የአየር መንገዳችን ጓደኞች፤ በኢኮኖሚክ ትራንዛክሺን፣ በኃይል መቆራረጥ፣ በትራፊክ አየር ቁጥጥር በመሳሰሉት ዘርፎች የሳይበር አጥቂዎቹ ያደረሱባቸውን ጉዳት በተመለከተ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ከጆሮዎቻችን ያደረሷቸውን መረጃዎች እናስታውሳለን፡፡
አንዳንድ ሀገሮችም የሆስፒታሎቻቸው፣ የንግድና የትምህርት ተቋሞቻቸው ሳይቀሩ ዳታዎቻቸው በእነዚያ የሰይጣን መልዕክተኛ የሳይበር አጥቂዎች እየተሰበሩ፣ ለከፍተኛ አደጋዎች እየተጋለጡ በከፊልም ቢሆን ወደ ወረቀት አገልግሎት ለመመለስ እየወሰኑ ይገኛሉ፡፡ ለእኛው አየር መንገድና እኒህን መሰል አጥቂዎችን በዋና ተከላካይነት እንዲታደግ ሀገራዊ ኃላፊነት ለተሰጠው ኢንሳ፣ ይህ ጉዳይ ይጠፋቸዋል የሚል አቋም የለኝም። ከማንም በተሻለ ሁኔታም እውቀቱና የመከላከሉን ዘዴ እንደተካኑበት አይጠፋኝም፡፡ ቢሆንም ግን ገና ለገና በስሜት ሙቀት በሙሉም ሆነ በከፊል ከወረቀት ጋር መፋታትን ለማወጅ በቃጠሎ ጭስ እወቁልኝ ማለት አግባብ አይመስለኝም። ጊዜውም አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ የወረቀትን አገልግሎት እኮ በምንም ተአምር ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል የሚል ግምት የለኝም (የጸሐፊውን የጥበባት ጉባኤ መጽሐፍ ማመሳከር ይቻላል፡፡)
የደርግ መንግሥት ጠላቴ ብሎ የፈረጀውን የፊውዳል ሥርዓት ያወደመ መስሎት፣ የቻይናን የባህል አብዮት እየጠቀሰ ሊተኩ የማይችሉ ጠቃሚ የሀገር ሰነዶችንና መጻሕፍትን በአደባባይ አቃጥሎ መፍጀቱን ዕድሜውን ያደለን ዜጎች በሀዘን የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚህኛው ስርዓትም ቢሆን ከምናከብራቸው አብያተ መጻሕፍት እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ሰነዶችና መጻሕፍት በኪሎ መቸብቸባቸው እንደተሰማ ለአደጋ ከመጋለጣቸው አስቀድሞ በተቆርቋሪ ዜጎች ኡኡታ ወደ መደርደሪያቸው እንዲመለሱ የተደረገበት አጋጣሚ እንደነበርም አንዘነጋም፡፡ ያለፈው ሲገርመን በአየር መንገዳችን የተወሰነው “ቅን መሰል” የወረቀት “ግባ እሳት” ድርጊትም በእጅጉ የሚያስገርም ችኮላ የተስተዋለበት ርምጃ ነበር ከማለት በስተቀር ምን ማለት ይቻላል፡፡
በአንድ ፈገግ የሚያሰኝ የቀድሞ ቀልድ ነገሬን ልቋጭ። ሰውዬው የሎተሪ ዕድል ፊቱን አዙሮለት እጣ ወጣለት ይባላል፡፡ የዕጣውን እውነታ እንዳረጋገጠም ሲገሰግስ ወደ ቤቱ በመሄድ ደስታውን ለሚስቱ ካበሰረ በኋላ ድህነት ተጠራርጎ ከቤታቸው መውጣቱን ለማብሰር፣ የለበሰው የሥራ ቱታ ሳይቀር የመገልገያ ዕቃዎቻቸውን በሙሉ በመሰብሰብ፣በዕልልታ አጅበው አቃጠሏቸው። ዕድላቸው ያዘነበላቸውን የሎተሪ ሲሳይ ለመሰብሰብም ወደ ሎተሪው መስሪያ ቤት ደርሰው፣ የዕጣውን ሎተሪ ሲጠየቁ፣ የወረቀቱ ሎተሪ ከየት ይገኝ። ለካንስ ከአሮጌው የሥራ ልብስ ኪስ ውስጥ ሳይወጣ አጋይተውት ኖሯል፡፡ “ልብ ያለው ልብ ያድርግ፤ የቦርከና ወንዝ ማለት ይሄ ነው” አለ ይባላል፤ የክፉ ቀን ማምለጫ መንገድን ለሚስቱ የጠቆመ ባል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

Read 1394 times