Print this page
Saturday, 07 October 2017 14:42

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  -ተመስገን -
Rate this item
(0 votes)

“ሐይማኖቴ መልካምነት ነው፤ በሰላምና በነፃነት የምኖርበት ቦታ ሁሉ አገሬ ነው”

ወዳጄ፤ አንድ ነገር እንዲህ ነው፤ እንዲህ መሰለኝ፤ ገመትኩ፤ ተሰማኝ፣ በል፣ በል አለኝ፤ ውቃቢዬ ነገረኝ፤ ታውቆኝ ነበር፤ ወይ በተቃራኒ፡- አላሰብኩም ነበር፤ ውል አላለኝም፤ ያልጠበኩት ነገር ነው፤ ጉድ እኮ ነው፤ አልመሰለኝም … የምንላቸው ነገሮች በቀጥታ ወይ በተዘዋዋሪ ከስሜታችን ጋር፤ ስሜታችን ደግሞ ከዕምነታችን፣ ዕምነታችን ከዕውቀታችን፣ እውቀታችን ከዕውነታችን ጋር የተሳሰሩ ይመስላሉ፡፡
እምነት በሚታይና በተጨበጠ ነገር (empirical) ላይ እንደሚደረግ ሁሉ በማይታይና በማይጨበጥ እንደ ሃሳብ፤ ህሊናና ዕውቀት ከመሳሰሉትም (rational) ጋር ይዛመዳል፡፡ አለበለዚያ የቤተሰብ፤ የጓደኛን ወይም “ብዙ” የምንላቸው ሰዎች ስሜት የሚከተል፣ ሌሎች ስላደረጉት ልክ የሚመስለውን ጉዳይ ይሆናል፡፡… ፋሽን መከተል እንደሚሉት፡፡
በተለያዩ ስሞች በሚጠራው ግን አንድ ነው ብለን በምናስበው ሰብዓዊ ባህርይ ባለው አምላክ (anthromorphic deity) ማመን (ሰብዓዊ ባህርይ ስንል፣ ‹ቀናተኛ አምላክ ነኝ› ብሏል እንደምንለው ማለት ነው)፣ መንፈስ እንጂ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ባህርይም ሆነ የተለያየ ስም የሌለው፤ አንድና አንድ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት (monotheists) እንዳሉ ሆነው፣ አንዱ ብዙ ነው፤ ብዙው ደግሞ አንድ ነው የሚሉ ወይም ለተለያዩ አማልክት ጎንበስ የሚሉ እንደ ሂንዱኢዝም ዓይነት ዕምነቶች አሉ፡፡ (ሂንዱኢዝም ብራህማ (creater god)፣ ቪሽኑ (the god who maintains the universes)፣ ሺቫ (the god of destruction) በተሰኙ አማልክት ቢገለጥም፤ የረጋና የማይቀር ከሚመስለው ግን በፈጠነና በረቀቀ ለውጥ ውስጥ (Cosmos flight) የሚገኘው ብራህማን የተለያዩ ገፆች ናቸው ይላል፡፡) በነገራችን ላይ ሂንዱ ማለት ከእምነት ጋር ተያያዥነት የሌለው የዐረብኛ ቃል ሲሆን የኢንዶስ ወንዝን ምስራቃዊ ክፍል (ቦታ) የሚያመላክት አንደማለት ነው፡፡ ሂንዱኢዝም በብዙ መልኩ Pantheism ከሚባለው የአስተሳሰብ ግንድ ጋር ይዛመዳል ወይም በሱ ይጠቃለላል፡፡
ፓንቴኢዝም፤ እግዜር ማለት ሁሉም ነገር ነው፡፡ (Everything is good) ወይም እግዜር ማለት የተፈጥሮ ህግና ስርዓት (the law and order of feature) ማለት ነው የሚል ዕምነት ነው፡፡ ባሩክ ስፒኖዛን ጨምሮ ብዙ ፈላስፋዎች በዚህ ይስማማሉ፡፡ ሲያዩት ይህን የሚመስል ሲያስቡት ግን የራሱ መልክ ያለው፤ ከቡዲሂዝም ጎን የተሰለፈ የፓንቴኢዝም አካል አለ፡፡…Ja'nism:: ጄኒዝም ልክ እንደ ቡድሂዝም የሂንዱ ካስት ስርዓትን ይቃወማል፡፡ ቡድሃ (ሲድሃርታ ጉተማ) በነበረበት ጊዜ በኖረው ማህቪራ የተጀመረው ይህ እምነት የታነፀው ማንኛውንም ተፈጥሮ አለመጉዳት ወይም ፀረ አመፀኝነት (None harm, none violence) በሚል መሰረት ላይ ነው፡፡
ጄኒዝም፤ አሚኒዝም (aminism) ከሚባል ሌላኛው እምነት ጋር የሚጓዝበት መንገድ አለ፡፡ ሁለቱም የተፈጥሮ ዑደት ክብ ነው (Vicious circle ) ይላሉ፡፡…አንዱ ለመኖር ሲል ሌላውን ለምግብነት ቢጠቀም ወይም ቢገድለው፣ እሱም በተራው ሲሞት ለሌላው ምግብ ይሆናል፡፡… ለምሳሌ፡- ሰው በሬ አርዶ ወይ አጋዘን አድኖ ሊበላ ይችላል፡፡ በሬው ወይ አጋዘኑ ደግሞ ዕፅዋትን ይመገባል፣ ዕፅዋት ደግሞ ሰው ሲሞትና አፈር ሲሆን እየተመገቡት ያድጋሉ፡፡ ዘመናዊው ሰው ግን ይህን ዙርያ ገብ ድግግሞሽ አይረዳም፤ ራሱን በራሱ ሳጥን (Square) ውስጥ ቆልፎታል፡፡ አልጋው አራት ማዕዘን፣ ቤቱ አራት ማዕዘን፣ ቴሌቪዥኑ፣ ፍሪጁ፣ ምድጃው ሁሉ አራት ማዕዘን፤ መኪናዎቹ አራት ማዕዘን መሆናቸው የ4 ነፀብራቅ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ የዚህ እምነት ተከታዮች ዕፀዋትን ለምግብነት ሲጠቀሙ ከልባቸው ይቅርታ ይጠይቋቸዋል፡፡ ተገድጄ እንጂ መብቴ እንዳልሆነ እንደማውቅ ዕወቁልኝ … ይላሉ፡፡ ሰውና ተፈጥሮ ተደጋጋፊ ናቸው፡፡ እናት ተፈጥሮ፤ ለሰው ልጅ እሸቷን እንዲቅም፣ ፀጋዋን እንዲያፍስ፣ ውበቷን እንዲታደም ቸርነቷን ለግሳዋለች፡፡
እሷም በተራዋ ፍቅርና እንክብካቤን ትሻለች፡፡ የሰው ልጆች ይህን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፤ ግድ ነው ይለናል - አንትሮፖሎጂስቱ ካርሎስ ካስቴናዳ “Journey to Ixalan” በሚለው መፅሃፉ፡፡
የአሚኒዝም ዕምነትና አስተሳሰብ በመጀመሪያ ደረጃ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ የተጠቀሰውን የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ እንዲኖረው የተባረከለትን የበላይነት ህግ አይቀበልም፡፡ ሁለተኛው የአሚኒዝም ጥብቅ ጉዳይ ደግሞ “ሰው የተፈጥሮ ህላዌ ነፍስ በኩር ነውና፣ የአያት ቅድመ አያቶቹን መንፈስ ይወርሳል፡፡" የሚል ነው፡፡
የአያት፣ ቅድመ አያቶች መንፈስ በባጀች ወይም በሌላ ቅርብ ዘመድ ላይ እየተመላለሰ ሊኖር ወይም በቋሚነት ሊሰፍር ይችላል፡፡ ብዙ የተለመደ ባይሆንም አንዳንዴ ይህ ውርስ ወይም ‹መተካካት› ሟች በህይወት እያለ መንፈሱ ከሱ ነቅሎ ወደ ተተኪው የሚሰርፅበት ሁኔታም ይከሰታል፡፡
ቀደም ሲል በሰሜን አሜሪካና አፍሪካ በተለይም በናይጄሪያና ኡጋንዳ አካባቢ በሚኖሩ የዩሩባና የሉግባራ ጎሳ ነዋሪዎች፤ከአሚኒዝም እምነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ነበሩ፡፡ ወደ እኛ ነገር ስንመጣ ይህ ዕምነት በተለያዩ ቦታዎች፣ በተለያየ ስምና ስርዓት (ceremonies) እንደሚከናወን እናውቃለን፡፡ ዛር፣ ውቃቢ፣ ከራማ፣ ቆሌ … እየተባለ፡፡
ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር መወዳጀታቸው ጠቅሟቸዋል፡፡ ከወዳጅነትም በላይ የአካሏ ክፋይ ናቸው፡፡ መንፈሷ ተዋህዷቸዋል፡፡ … በተለይ ደግሞ አፍሪካውያኖች!! ይላሉ፡፡ እንደውም ከቅኝ ገዠዎች ወረራና የአዲስ ባህል መስፋፋት ቀደም ብሎ የአፍሪካዊ ፍልስፍና መገለጫ የነበሩት አፍሪካውያን፣ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው የአንድ መሆን ስሜትና ጎሰኝነት እንደነበሩ ይገልፃሉ፡፡ እንግዲህ ወዳጄ፤ የአፍሪካዊ አስተሳሰብና ባህል ዋናው መሰረት፣ ተፈጥሮን ከመንከባከብና ከማምለክ ጋር የተያያዘ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ኢትየጵያዊ ደግሞ የራሳችን የሆኑ ባህላዊና ትውፊታዊ ወግና ልማድ ቢኖረንም ዞሮ ዞሮ የአፍሪካዊ እምነትና ባህል (African traditional and cultrural belief) አካል መሆናችን መዘንጋት የለበትም፡፡
እና ወዳጄ፤ አንዳንድ ጊዜ እኛ፣ ‹የኛ› እያልን የምናከብራቸው፣ ዩኔስኮ ካልመዘገበልን ሞተን እንገኛለን ኡ! ኡ! የምንልላቸው አንዳንድ በአላት የአከባበር ስርዓት ልዩነት (performance of ceremonies) ካልሆነ በስተቀር ነገረ ስራቸው የዚሁ አፍሪካዊ ባህልና ልማዳዊ እምነት አካል ይመስሉኛል፡፡
… ነገርን ነገር ያነሳዋልና አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡፡ “እምነት” ስል፣ የክርስትና ወይም እስልምና እምነት (christian faith, Islamic faith) እንደምንለው ሳይሆን “belief” የሚለውን ቃል ለመጠቀም በማሰብ ነው፡፡
ወዳጄ፤ ልቤ መቼም ጨዋታ ነውና “ሐይማኖት” ብዙ ሊቃውንት በተለይ ደግሞ ዊሊያም ጀምስ እንደፃፈልን እጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ህብር ያለው ትርጉም ስላለው፣ በድፍኑ ‹መልካምነት› በሚለው ቢገለፅ ያስኬዳል፡፡ በኛ አገር መልካም የሆነን ሰው፤ “እንዴት ዓይነት ሐይማኖተኛ መሰለህ” እንደምንለው፣ በአውሮፓና አሜሪካ (He is very religious, she is angelic, He is Godly, when I am good; am God, to do good means to be God etc--)  ማለት ከተለመደ ዘመናት አልፈዋል፡፡
“… የማንኛውም ዕምነት ተከታይ የሆኑ ሰዎች “መልካም” እስከሆኑ ድረስ ሃይማኖተኞች ይባላሉ፡፡ “መልካም” ካልሆኑ ግን የሚከተሉት፣ የሚሰበሰቡበት፣ የሚያዘወትሩት ቤተ እምነት ወይም ተቋም አባላት እንጂ ሃይማኖተኛ አያሰኛቸውም፡፡ … ማንም በምንም ሆነ ምንም የሚያምን ወይም ወደማንኛውም ቤተ እምነት የማይሄድ ሰውም “መልካም” እስከሆነ ድረስ ሃይማኖተኛ ነው” ይሉናል ዐዋቂዎች!!
አንዳንዶች ደግሞ እንደ ጉስታብ ሌቦን ዓይነቶቹ፤ “አለማመን” የሚባል ነገር የለም፡፡ “አለማመን” በራሱ እምነት ነው (none beliving by itself is a belief) ብለው ይከራከራሉ፡፡ ቶማስ ካርላይል ደግሞ እንዲህ ይለናል፡-
“ሐይማኖቴ መልካምነት ነው፣ የሰው ልጆች ሁሉ ወንድሞቼና እህቶቼ ናቸው፣ በሰላምና በነፃነት የምኖርበት ቦታ ሁሉ ሃገሬ ነው፡፡" (To be good is my religion, all human beings are my brothers and sisters, wherever I can live free and in peace is my country.)   
አንተስ ወዳጄ ምን ትላለህ?
ሠላም!!

Read 1924 times