Print this page
Saturday, 07 October 2017 14:45

እግዚአብሔር የሚሰራው በሎጂክ ነው!!

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(13 votes)

“ተፈጥሮ የእግዚአብሔርን እውነትና ሞራሊቲ ተሸካሚ ነው!” ዘርዓያዕቆብ

   እስቲ ዛሬ ደግሞ ድርቅ ወዳለው ፍልስፍና ልውሰዳችሁ፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች ሎጂክና እምነትን ተቃራኒዎች ናቸው ብለው ያስባሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሎጂክ ይሄንን ግዑዛዊ ዓለም የምንረዳበት መሳሪያ ሲሆን፣ እምነት ደግሞ ከዚህ ዓለም ውጭ ያለውን ረቂቁንና መንፈሳዊውን ዓለም የምንረዳበት ነው የሚል ነው፡፡ በዚህ መስመር የሚከራከሩት ሃይማኖታዊ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ፈላስፎችም ጭምር ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፈላስፎች ውስጥ አንዱ ጀርመናዊው ኢማኑኤል ካንት ነው፡፡
ካንት በ1781 ዓ.ም ባሳተመው Critique of Pure Reason በተባለው ድርሳኑ ውስጥ የዚህን ዓለም ታዋቂነት በተመለከተ ሁለት ነገሮች እንዳሉ ፅፏል - አእምሯዊ ዓለም (Phenomena) እና ጭራሽ ምንነቱ የማይታወቀው ዓለም (Neumena)። ዓለምን የምናየው በአእምሯችን አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ ዓለም እንዴት ዓይነት ናት? ቢሉ አእምሯችን እንደተረጎማት ዓይነት ናት። ዓለምን ከአእምሯችን ወጥተን ማየት ስለማንችል፣ ይህ ዓለም በእርግጠኝነት እንደዚህ ዓይነት ነው ብለን መደምደም አንችልም፡፡ አንድ የምናቀው ነገር ቢኖር ግን ምንነቱ የማይታወቅ ከእኛ ውጭ የሚኖር ዓለም መኖሩን ብቻ ነው፤ “የማይታወቅ ግን የሚኖር ዓለም”፡፡ ምክንያቱም ይህ ምንነቱ የማይታወቀው ዓለም በስሜት ህዋሶቻችን አማካኝነት በሚልከው ህወስታዎች (Sensation) አማካኝነት ነው በውስጣችን አእምሯዊውን ዓለም የሚፈጥረው፡፡
እንደ ካንት አመለካከት በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለው ይህ አእምሯዊ ዓለም ሐሳቦችን የሚያዋቅረው በሎጂክ አማካኝነት ነው፡፡ አእምሯችን መንስዔና ውጤት (cause and effect)፣ አንድና ብዙ (one and many)፣ ዓይነትና ብዛት (quality and quantity) እያለ ሐሳቦችን የሚያዋቅረው በዚህ ሎጂክ አማካኝነት ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ ይህ ሎጂክ የሚሰራው በአእምሯችን ውስጥ ለተፈጠሩ ህወስታዎች እንጂ ምንነቱ ለማይታወቀው ውጫዊው ዓለም አይደለም፡፡ የካንት ፍልስፍና እዚህ ድረስ ችግር የለውም፡፡ ካንት ብዙ ፈላስፋዎችንና ሃይማኖታዊ ምሁራንን ያስቆጣ ነገር ያመጣው ምንነቱ ስለማይታወቀው ውጫዊው ዓለም የፃፈው ነገር ነው፡፡ ካንት እግዚአብሔርንና የሰውን ልጅ ነፍስ እዚህ ምንነቱ የማይታወቀው ውጫዊው ዓለም ውስጥ ይመድባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ “አእምሯችን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለነፍስ ህወስታ (Sensation) የለውም” የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ህወስታ ለሌለን ነገር ከእምነት ውጭ በሎጂክ የምናቅበት ነገር የለም፡፡
ይሄ የካንት ድምዳሜ አጥባቂ ሃይማኖተኛ ለነበረው የ18ኛው ክ/ዘ የጀርመን ማህበረሰብ እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ የካንት ፍልስፍና ታች ላለው ህዝብ አሉታዊ አንድምታ አለው - “የምታመልኩት አምላክ ምንነቱ አይታወቅም” የሚል ትርጓሜ ይሰጣልና። ጀርመኖቹ “የምናመልከው አምላክ የማይታወቅ ሳይሆን በደንብ የሚታወቅ ነው” በማለት ለካንት መልስ ለመስጠት የግድ Neumena የሚለውን የካንት ሐሳብ ማፍረስ ነበረባቸው፡፡ ይሄንን ሳያፈርሱ ካንትን መቃወም አይችሉም፡፡ ይሄም ከካንት በኋላ የመጡት ፈላስፎች (ፊክተ፣ ሼሊንግና ሄግል) የቤት ሥራ ሆነ፡፡
እነዚህ ፈላስፎች ይሄንን የቤት ሥራቸውን ለመስራት በሚታገሉበት ወቅት Neumena የሚለው የካንት ሐሳብ ላይ አንድ ስስ ብልት አገኙ። Neumena የሚለው ሐሳብ ቃል በቃል ሲተረጎም “የማይታወቅ ሆኖም ግን የሚኖር ዓለም” ማለት ነው፡፡ እንዴት አንድ ነገር መኖሩን እያወቅን ሆኖም ግን ምንነቱ አይታወቅም እንላለን? ይሄ እርስ በርሱ የሚቃረን ነገር ነው፤ ቢያንስ ህልውናውን እናውቃለንና፡፡
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከአእምሯችን ውጭ ያለው ዓለም የሚታወቀው ህልውናው ብቻ ሳይሆን፣ ምንነቱም የሚታወቅበት አንድ ነገር አለ፤ ይሄውም ውጫዊው ዓለም (ተፈጥሮ) የሚሰራው በአእምሯችን ውስጥ ካለው ሎጂክ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ተፈጥሮ የሚሰራበት ህግ (ሎጂክ) እና አእምሯችን ህወስታዎችን የሚያዋቅርበት ሎጂክ አንድ ዓይነት ነው፡፡
ኒውተን ሦስቱን የእንቅስቃሴ ህግጋት ቀምሮ (The Three Laws of Motion) ወረቀት ላይ ፅፎ ሰጠን፡፡ ኒውተን ወደ ጠፈር መሄድ ሳያስፈልገው በአእምሮው ውስጥ ብቻ ያውጠነጠነውን ሎጂክ ወረቀት ላይ አሳየን፡፡ እኛም የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ ስንመለከት፣ እውነትም ፕላኔቶቹ ኒውተን ወረቀቱ ላይ በፃፈው ቀመር መሰረት ሲንቀሳቀሱ ተመለከትን። እኛም ራሳችንን ጠየቅን፣ እንዴት የተፈጥሮ ህግ በአእምሯችን ውስጥ ካለው ሎጂክ ጋር አንድ ዓይነት ሊሆን ቻለ? እንግዲህ እንደዚህ ከሆነ፣ አእምሯዊው ሎጂክ እና የተፈጥሮ ህግ አንድ ዓይነት ናቸው ማለት ነው፡፡ The inner nature of our mind is in harmony with the laws of nature.
የተፈጥሮን ህግ በሂሳባዊ ቀመር ማስቀመጥ የቻልነው ለዚህ ነው፡፡ ሂሳባዊ ቀመር የአእምሮ ሎጂክ ነው፤ የተፈጥሮ ህግ ደግሞ ከእኛ አእምሮ ውጭ ያለ ሌላ የተፈጥሮ ሎጂክ ነው፡፡ እናም እነዚህ ውስጣዊና ውጫዊ ሎጂኮች አንድ ዓይነት መሆናቸው የሚያመላክተን ነገር ቢኖር፣ የውጫዊው ዓለም ምንነት እና አእምሯችን ስለ ውጫዊው ዓለም ምንነት የሚያቀርብልን ምስል ፍፁም አንድ ዓይነት መሆኑን ነው፡፡ ሄግል ይሄንን ሐሳብ ሲገልፅ እንዲህ ይላል - The rational is real, and the real is rational. ስለዚህ “የማይታወቅ ሆኖም ግን የሚኖር ዓለም” የሚባል ነገር የለም፡፡ በመሆኑም፣ ስለ ውጫዊው ዓለም ለማወቅ ከአእምሯችን መውጣት ሳያስፈልገን፣ አእምሯዊው ዓለም የውጫዊው ዓለም ትክክለኛ ነፀብራቅ ነው ማለት እንችላለን፡፡
ይህ በሎጂክ የሚሰራው ተፈጥሮ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው ስንል ደግሞ ይሄ ፍልስፍና ሌላ ከፍታ ያገኛል፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ ይሄንን ሎጂክ ከየት አገኘው ወደሚል ሌላ ጥያቄ ይወስደናልና፡፡ ተፈጥሮ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ከሆነ፣ ተፈጥሮ ይሄንን ሎጂክ ያገኘው ከፈጣሪው ነው ማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት እግዚአብሔር ተፈጥሮ ውስጥ የሚሰራው በሎጂክ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ ሎጂክ ከእግዚአብሔር ባህሪዎች ውስጥ አንደኛው ነው ማለት ነው፤ ነገሮችን የሚከውንበት ባህሪው፡፡ ይሄም፣ አመክንዮ ከእግዚአብሔር ሊነጠል የማይችል፣ ይልቅስ የእግዚአብሔር ውስጣዊ ህይወቱና ባህሪው መሆኑን ያስረዳናል፡፡ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር “ፍፁማዊ የሆነ ንቃተ ህሊና ነው” ብቻ ሳይሆን፣ ንቃተ ህሊናውም በአመክንዮ (በሎጂክ) የሚሰራ ነው፡፡ እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን” ሲል፣ ከመቅፅበት ብርሃን የሚሆንበት ምክንያት በተአምር ሳይሆን ራሱን የቻለ መለኮታዊ ሎጂክ አለው ማለት ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚያሳዩን አንድ ነገር ቢኖር - እግዚአብሔር፣ ሰውና ተፈጥሮ አንድ በጋራ የሚያስተፃምራቸው ነገር መኖሩን ነው - እሱም ሎጂክ ነው፡፡ ስለዚህ ሎጂክ ዓለማዊ የመሆኑን ያህል መለኮታዊም ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ሎጂክ ይሄንን ዓለም የምንረዳበት መሳሪያ ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሳዊውንም ዓለም የምናውቅበት ጭምር ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ “መንፈሳዊውን ዓለም በሎጂክ ማወቅ አንችልም” የሚለው አባባል አይሰራም፡፡
“ተፈጥሮ የሚሰራው እግዚአብሔር በሰጠው ሎጂክ ነው” የሚለው አባባል ግን በእግዚአብሔርና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ወደሌላ ከፍ ወዳለ ፍልስፍና ይወስደናል፡፡ እዚህ ላይ ዘርዓያዕቆብን ማንሳት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። ዘርዓያዕቆብ ይሄንን በፈጣሪና በተፈጣሪ መካከል ያለውን የግንኙነት ዓይነት በተመለከተ ሁለት ምልከታዎችን በሐተታው ውስጥ ፅፏል፡፡
የመጀመሪያው፣ “ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል” የሚለው ሲሆን፤
 ሁለተኛው ደግሞ “የእግዚአብሔርን ባህሪና ፍላጎት የምናውቀው የተፈጥሮን ህግና ሥርዓት በማየት ነው፤” የሚል ነው፡፡
እነዚህ ሁለቱ ሐሳቦች በፈጣሪና በተፈጣሪ መካከል ያለውን የግንኙነት ዓይነት በተለያየ ደረጃና ጥልቀት የሚያስቀምጡ ሐሳቦች ናቸው፡፡ እስቲ በየተራ እንመልከታቸው፡፡
“ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል፤” የሚለው ሐሳብ “ፍጡሩ ስለ ፈጣሪው ይናገራል” ማለት ነው። ጥያቄው ግን፣ ፍጡሩ ስለ ፈጣሪው ምንድነው የሚነግረን? የሚለው ነው፡፡ ፍጡር ስለ ፈጣሪው የሚነግረን ሁለት ነገር ብቻ ነው — ህልውናውንና ችሎታውን፡፡ በመሆኑም “ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል፤” የሚለው ሐሳብ ስለ እግዚአብሔር የሚነግረን በጣም ውስን ነገሮችን ብቻ ነው፡፡ ልክ ወንበር ካለ አናፂ አለ እንደምንለው መሆኑ ነው፡፡
ወንበር ሁለት ነገሮችን አጣምሮ ይይዛል — ህልውናንና ዲዛይንን፡፡ በመሆኑም የወንበሩ መኖር ስለ አናፂው ማንነት የሚነግረን ሁለት መረጃዎችን ብቻ ነው — ይሄውም የአናፂውን ህልውናና ችሎታ ብቻ፡፡ የወንበሩ ህልውና ስለ አናፂው መኖር (ህልውና) የሚነግረን ሲሆን፣ የወንበሩ ዲዛይን ደግሞ ስለ አናፂው ችሎታ (ዕውቀት) ይነግረናል፡፡
በመሆኑም “ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል፤” የሚለው ሐሳብ የሚነግረን በፍጡርና በፈጣሪ መካከል ያለውን ስነ ዕውቀታዊ ግንኙነት (Epistemological Relationship) ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ አናፂው የሚገለፀው በእነዚህ ሁለቱ ባህሪዎች — በህልውናና በዕውቀት — ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ ስለ ሞራላዊ ባህሪውና እሴቱ አይነግረንም፡፡
“ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል፤” የሚለው አባባል ሌላም ውስንነት አለበት፤ ይሄውም ፍጡር ፈጣሪውን መሸከም (ተሸክሞ ማኖር) አለመቻሉ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ “ወንበር ካለ አናፂ አለ” የሚለው አባባል ወንበሩና አናፂው በአካል የተለያየ ቦታ ላይ መኖራቸውን (ፍጡርና ፈጣሪ በአካል መገነጣጠላቸውን) ያመላክታል፡፡ በመሆኑም፣ “ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል፤” የሚለው አባባል ፈጣሪ በፍጡሩ ላይ ህልውናውንና ችሎታውን ገለፀበት እንጂ ህይወቱን፣ እስትንፋሱን፣ እሴቱን ለፍጡሩ አለማጋራቱን ያመላክታል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ፈጣሪ በፍጡሩ ውስጥ አይኖርም፤ ፈጥሮ ትቶታል ወደሚለው የአርስቶትል ሐሳብ ይወስደናል፡፡ ዘርዓያዕቆብም “ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ ይኖራል፤” የሚለው ይሄንን ግንኙነት ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ ዘርዓያዕቆብ “የእግዚአብሔርን ሞራላዊ ባህሪና ፍላጎት የምናውቀው የተፈጥሮን ህግና ሥርዓት በማየት ነው፤” ሲል በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ግንኙነት ጥልቀት ይሰጠዋል — ግንኙነቱን ከስነ ዕውቀት ባሻገር ሞራላዊ ገፅታን ያክልበታል፡፡ ፍጡር የፈጣሪውን ሞራላዊ ባህሪ የሚያንፀባርቀው ፈጣሪ በፍጡሩ ውስጥ በቋሚነት ሲኖር ብቻ ነው። የፈጣሪን ባህሪና ፍላጎት በተፈጥሮ ህግና ሥርዓት ውስጥ የምናገኘው ከሆነ ፈጣሪ ለፍጡሩ ህይወቱን፣ እስትንፋሱን፣ እሴቱን ማንነቱን አጋርቶታል ማለት ነው፤ ፍጡር ፈጣሪውን ተሸክሞታል ማለት ነው፤ ፈጣሪ ከፍጡሩ ጋር አብሮ ይንቀሳቀሳል ማለት ነው። በምሳሌ ላስረዳ፡፡
ማንኛውም ልጅ የወላጆቹን ባህሪ (DNA) ተሸክሞ ነው የሚወለደው፡፡ ይሄ ማለት በልጁ ውስጥ ወላጆቹ አሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን ወላጆቹ ከልጁ የተገነጠለ አካል የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ወላጆች ከልጃቸው የተገነጠለ አካል ስላላቸውም በልጃቸው ውስጥ የሉም ማለትም አይደለም፡፡ ሁኔታው ፕሌቶ እንዳለው ነው - “እናት ለልጇ የምትንሰፈሰፈው እናትየዋ በልጇ ውስጥ ዳግም ተወልዳ ስለምታድግ ነው፡፡” የወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ መከሰት ግንኙነታቸውን ከስነ እውቀታዊ ወደ ሞራላዊ ግንኙነት ከፍ ያደርገዋል - በሁለቱ መካከል ሞራላዊና ስሜታዊ ትስስር ይፈጥራል፡፡
በልጅና በወላጅ መካከል ሞራላዊና ስሜታዊ ትስስሩ የሚመጣው ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ ስለሚከሰቱ ነው፡፡ በሃይማኖታዊው አስተሳሰብ ከሄድን የሰው ነፍስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ናት፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በሰው ውስጥ (ፈጣሪ በፍጡሩ ውስጥ) ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ይሄ አንዱ በሌላው (ፈጣሪ በፍጡሩ) ውስጥ የመከሰቱ ነገር ነው፣ በሁለቱ መካከል ሞራላዊና ስሜታዊ ትስስር የሚፈጥረው፡፡
በሌላ አነጋገር፣ ፍጡር የፈጣሪውን የሞራል ኩነት (ሞራሊቲ) የሚያንፀባርቅ ከሆነ፣ ፈጣሪ በፍጡሩ ውስጥ ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብም የሚለው፣ ተፈጥሮ የእግዚአብሔርን ሞራሊቲ ተሸክሟል፣ ምክንያቱም ተፈጥሮንና ሥርዓቷን ተመልክተን፣ እግዚአብሔር ጥሩና መጥፎ ያለውን ነገር (የእግዚአብሔርን ሞራሊቲ) ማወቅ እንችላለን። ተፈጥሮ የእግዚአብሔርን ሞራሊቲ የሚያንፀባርቅ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ውስጥ ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ ትቶታል የሚለው የአርስቶትል ሐሳብ አይሰራም። ይሄም የአርስቶትል ዓይነት ከተፈጥሮ የተገነጠለ እግዚአብሔር እና የስፒኖዛ ዓይነት “ምዑት ተፈጥሮ” ሊኖር እንደማይችል፣ እንዲሁም የኒውተን ዓይነት ሜካኒካል የሆነ ዩኒቨርስ ሊኖር እንደማይችል ያመላክተናል፡፡
ሼሊንግና ሄግል በዚህ መልኩ የአርስቶትልን፣ የስፒኖዛንና የኒውተንን ሐሳብ ውድቅ ካደረጉ በኋላ እንዴት እግዚአብሔር በሰው ልጅ ውስጥ ሆኖ በማህበረሰብ እድገትና ሥልጣኔ ውስጥ በታሪክ ይበልጥ እየተገለጠ እንደሚሄድ በሰፊው ፅፈዋል፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሐፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 8602 times