Print this page
Saturday, 07 October 2017 14:46

ሞኝ ነጋዴ፤ በራሱ መቀማት ሳያዝን የጓደኛው ማምለጥ ይቆጨዋል

Written by 
Rate this item
(12 votes)

የሚከተለው ተረት “ከብላቴን ጌታ ማሕተመ ሥላሴ ወ/መስቀል ስብስብ ሥራዎች” ያገኘነው ነው፡፡
“ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ቤት ሊሠራ ፈቀደ፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው ተመልካችና ጠንቃቃ አልነበረምና ይህች አዲስ ቤት የምትሠራበትን ጠንካራውን መሬት መምረጡን ትቶ፤ ሥራው የሚፋጠንበትን አኳኋን ብቻ ተመልክቶ፣ ዐቀበት ከሌለው ከረባዳ መሬት፣ እንጨቱንም፣ ደንጊያውንም ያለ ብዙ ድካም ለማግኘት እንዲችል፣ የሚፈቅድለትን ቦታ መረጠ፡፡
ደግሞ የገንዘብ ቁጠባ ያደረገ መሰለውና የቤቱን መሠረት አጎድጉዶ፣ ዝቅ ብሎ ከጥብቅ መሬት ወይም ከደንጊያ ላይ እንደ መሥራት መሠረቱን ሳይቆፍር፣ እንዲያው ካሸዋው ላይ ሰራ ጀመረ፡፡
አንደኛው ሰው ግን በጣም ተመልካችና ጠንቃቃ ነበርና ቤቱን ለመሥራት ባሰበ ጊዜ አወቀድሞ በመልካም አድርጎ፣ አዳጋ ከሆነ ሥፍራ ላይ በጣም ጥንካሬና ጭንጫነት ያለውን መሬት መረጠ፡፡
ይህ ሰው የቤቱን መጠነ ነገር እንጂ ከዚህ ካቀበት ቤት ለመሥራት በድንጋይ፣ በኖራ፣ ባሸዋ በእንጨት ማቅረብ ያለውን ሁሉ ድካምና የገንዘብ ወጪ አልተሰቀቀም፡፡
የመሠረቱም ድንጋይ በሚጣልበት ጊዜ አስቀድሞ የሚበቃ ያህል መጎድጎዱን፤ ከሥርም መሰረቱ የሚያርፍበት ጠንካራ ጭንጫ መሬት መውጣቱን መረመረ፡፡
የብልሁም፣ የሞኙም ሰው ቤቶች ተሠርተው ባለቁ ጊዜ፤ ወዲያው ኃይለኛ ነፋስ ተነሣ፡፡ ግራ ቀኝም ነፈሰ፡፡ ብርቱ ዝናብም ዘነመ፡፡
ፈረፈሮችም፤ ፈፋዎችም፣ ወንዞችም ሁሉ ሞሉ፡፡ ኃይለኛውም ጎርፍ ወደ ዘባጣው ቦታ ካሸዋ ላይ ወደተመሠረተው ቤት በብዛት ይወርድ ጀመር፡፡ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ይህ ኃይለኛ ርኅራኄ የለሽ ጎርፍ የቤቱ መሰረት ያረፈበትን አሸዋውን ጠርጎ፤ ወሰደው፡፡ ቤቱም መሰረት ስላጣ እየተነሰነጠቀና እየተገመሰ በየማዕዘኑ ወደቀ፡፡ የቤቱንም ድንጋዮች፣ ወጋግራዎቹንና ካንቾቹን ሁሉ እያንከባለለ እያዳፋ አወረዳቸው፡፡
ከድንይ ላይ የተመሠረተው የሌላው ሰው ቤት ግን እንደዚህ አልሆነም፡፡ ኃይለኛ ነፋስ ነፈሰ። ብርቱ ዝናምም ዘነመ፡፡ ወንዞችም፤ ፈረፈሮችም፤ ፊፋዎችም፣ ሁሉ ሞሉ፡፡ ድንጋዮን የሚፈነቅሉ የሚያንከባልሉ፣ ዛፎችንም ከሥራቸው የሚነቅሉ እጅግ ብርቱ የሆነ ጎርፎች ጎረፉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ከቶ ይህ ቤት አልተናወፀም፡፡ ቁጣውንም ሁሉ ምንም ነገር ሳይገኘው አሳልፎታል፡፡
* * *
የሀገራችን ፓርቲዎች በአብዛኛው በአሸዋ ላይ የተሠራው ቤት ዓይነት ናቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ወይ ኃይለኛው ነፋስ ነው፣ ወይም ደግሞ አለት ላይ የተሠራው ቤት ነው፡፡ ጠንካራው ቤት ላይ ግትርነት ተጨምሮ ሲታሰብ፣ ክፉውን ጊዜ መቋቋም ብቻ ሳይሆን ክፉ መሆንም ይመጣል፡፡
ማን አለብኝ ይመጣል፡፡ ይሄ ቢሮክራሲን ሲንተራስ ደግሞ ይብስ የቤት- ጣጣ ይኖረዋል! ከዚህ ያውጣን! የፖለቲካ ፀሀፍት የኋላ-ቀር አገራት ፓርቲዎች ጣጣ የሚጀምረው ከ bureaucratization of the party ነው ይላሉ፡፡ ይህም፤ ጥንትም ሆነ አሁን፤ በሀገራችን አንዱ የገዢ ፓርቲ ዋና ችግር ሲሆን በቢሮክራሲው ውስጥ ጉዳይ ፈፃሚና አስፈፃሚ አባላትን መሰግሰግ ነው፡፡ ቢሮክራሲያዊ ፓርቲ መፍጠር ነው!
ገዥው ፓርቲ ራሱ ፖሊሲ ይቀርፃል፡፡ ራሱ ይተገብራል፡፡ ይህን የሚፈፀመው መንግሥት ውስጥ ባሉ አባላቱ አማካኝነት ነው፡፡ ስለሆነም ቢሮአዊ ፓርቲ ይሆናል ማለት ነው! የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ፤
መንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አባላቱ የፓርቲውን ዓላማ የሚፃረር አቋም ያላቸውን ሰዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይገድባል፡፡ በተግባር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይፈጠር ማድረጉ ነው! ወይ በከፊል ለመንግሥት የገበረ ፓርቲ አሊያም ፀባይ ያለው ተቃዋሚ/ ተንበርካኪ ፓርቲ እንዲፈጠር ያደርጋሉ- Mute opposition እንዲሉ፡፡ የፓርቲ አባላት እጅግ ኃይለኛ/ ጠንካራ የሚባሉትን የመንግስት ቢሮዎች እንዲይዙ ይደረጋል/ተደርጓል፡፡
ከዚያም ሁኔታዎችን ይቆጣጠራሉ፤ አባላት ይመለምላሉ፡፡ የማይመቿቸውን ሰዎች ከቢሮ ያርራሉ፣ የሚሆኑዋቸውን ሰዎች በወገናዊ መንገድ ያስቀጥራሉ! መተካካት ይሉታል ሲፈልጉ፡፡ የራሳቸውንም ሰው የሚያባርሩበት ጊዜ አለ፡፡ አንደሌኒን “The Party purges itself” ይላሉ፡፡ ፓርቲ ራሱን አጠራ፤ እንደማለት ነው! ቢሮክራሲና ፓርቲ ከተጋቡ ቆይተዋል፡፡
ቢሮክራሲና ፓርቲ ካልተለያዩ ሁሌ መዘዝ አለ-ወገናዊነት፣ ዘመዳዊነት፣ ብቃት-አናሳነት፣ አድር-ባይነት፣ ግትርነት፣ ኢፍትሐዊነት ወዘተ ዝርያዎቹ ናቸው፡፡ ስልቹነትና ምን-ግዴነት ዋና ጠባይ ይሆናል። የመንግሥት መመሪያን ከፓርቲ መምሪያ መለየት አደጋች ይሆናል፡፡
የሥራ ትጋትና ፍጥነት አይኖርም!
አንድ ጊዜ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ግብፅን ሲጎበኙ፤ “ታላቁን ፒራሚድ ለመገንባት ሃያ አመት ነው የፈጀው” ተባሉ፡፡ ይሄኔ ካርተር፤
“የመንግሥት ድርጅት እንዲህ በፈጣን ጊዜ መገንባቱ አስደንቆኛል” አሉ፡፡ አግቦኛ ንግግር ነው፡፡ ቢሮክራሲ ሥራ አፋጥኖ አያውቅማ! የቢሮክረሲ ቀይ-ጥብጣብ (bureaucratic red-tape) ሁሌም የሥራ፣ ብሎም የዕድገት አንቅፋት ነው፡፡ በተለይ ፓርቲው ድልን የተቀዳጀው የቀድሞን ሥርዓት በኃይል አሰገድዶ ገርስሶ ሲሆን፤ እንደ ብዙ የአፍሪካ መንግሥታት ሁሉ፤ ዘርፈ-ብዙ የአገዛዝ ውጥንቅጥ ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ሁሉን ነገር በገዢ ፓርቲ ኮሚቴ እንምራ የሚል ዘይቤ ይጫነዋል፡፡
እኔ ሁልጊዜ የማስበው “ግመል፤ በኮሚቴ ፈረስ ናት ተብላ የተሰራች፣ እንስሳ ናት!” ብዬ ነው - ብሏል ፍሬዲ ሌከር የተባለ የፖለቲካ ተንታኝ፡፡
በየመስሪያ ቤቱ ስብሰባዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ግምገማዎች፣የቅጥርና የማባረር ሥርዓቶች፣ የቀረጥ አያያዦች፣ የሙስና አፈራረጆች ላይ ሁሉ የስብሰባ ሂደቶች፣ የኮሚቴና የቡድናዊነት (groupism) ስሜትን የተላበሱ መሆናቸው፣ አንዱ የፓርቲ ቢሮክራሲያዊነት ባህሪ ነው፡፡
አንድ ያልታወቀ ፀሀፊ፤
“አንድን ሀሳብ መግደል ከፈለክ ወደ ስብሰባ ውሰደው” ይላል፡፡ በእርግጥም በስብሰባ ሀሳብን ማሳደግም፣ መግደልም ይቻላል፡፡ ዋናው ጉዳይ የፓርቲ መዋቅር በቢሮክራሲ ውስጥ፤ ሥር- እንዲሰድ የማድረግ ነገር ነው፡፡ ያለፈው መንግሥት፤ ፍጥጥ ያለና ዓላማው ፖለቲካዊ ተልዕኮን ያነገበ “የለውጥ ሃዋሪያ” የሚባል ወኪል ነበረው!!
የመንግሥት ሶሻሊዝም፣ አንድ ነጠላ፣ የተማከለ፣ ፈላጭ-ቆራጭ አምባገነን ፈጥሮ፣ ፍፁም የሆነ ሥልጣንን ይይዛል፡፡ ይሄንን የሚፈፅመውም ባሉት ቢሮክራሲያዊ ወኪሎች ነው፤ ካፒታሊዝም ደግሞ ብዙ ትናንሽ አምባገነኖችን መፈልፈል ነው ሥራው፡፡ እያንዳንዱ አምባገነን የየራሱን የንግድ ግዛት ይመራል! (አልደስ ህክስ ሌይ ነው ያለው) በፖለቲካዊ መልኩ ፈላጭ-ቆራጭ፣ በኢኮኖሚ መልኩ ደግሞ በዝባዥ /ሙሰኛ) ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡ ችግሩ አፍጦ የሚመጣው እንደ ዛሬው ፖለቲከኛውን ከሙሰኛው ነጥሎ ማየት ሲያቅት ነው! ይሄ ሀገራችንን በጣም በረዥሙና በሰፊ መረብ የሚፈታተን፣ ከተልባ ውስጥ አፈር የማበጠር ያህል አስቸጋሪ አባዜ ነው!!
ይሄን አባዜ በቀላሉ መገላገል አይቻልም፡፡ ምነው ቢሉ በአብዛኛው፤ በቅጡ ስንመረምረው ከፊውዳሊዝም የወረስነው ምቀኝነት፣ ተንኮልና ደባ በውስጡ የተንሰራፋ ስለሆነ ነው! የእኔ ፓርቲ ቅዱስ፣ የአንተ ፓርቲ እርኩስ ማለት ሳያንስ፤ ያንተ ፓርቲ ካልወደቀ የኔ ፓርቲ አይለመልምም ወደሚል እሳቤ መጓዝ ይመጣል፡፡ ስለዚህ “ያንተ ፓርቲ ይውደም!” ይሆናል መፈክሩ፡፡ ዛሬ በይፋ የምናየው “ሞኝ ነጋዴ በራሱ መቀማት ሳያዝን የጓደኛው ማምለጥ ይቆጨዋል” የሚለው ተረት በንግድም፣ በፖለቲካውም በፓርቲ ውስጠ-ነገር፣ በመከላከያም፣ በልማት ፕሮጄክትም፣ በትምህርትም ውስጥ ይሰራል፡፡ ቆም ብለን አካሄዳችንን እንመርምር!!

Read 7311 times
Administrator

Latest from Administrator