Saturday, 07 October 2017 14:52

ወይ እንታደስ አሊያም እንፍረስ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

በቅርቡ ለንባብ የበቃው የአሌክስ አብርሃም የግጥም መጽሐፍ ርዕስ በእጅጉ ቀልብ ሣቢ ነው፡፡ መዐዛውም ሠሞናዊና ትኩረት ማራኩ ይመሥላል፡፡ ይሁንና ሽፋኑ ላይ ያሉት ሃይማኖታዊ ቆቦችና ከላይ ከፍ ብሎ ያለው ወታደራዊ መለዮ ሁለት ዐይነት ሃሣብ ይጭራሉ፡፡ ጉዳዩ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ይሆን? የሚል መንፈስ ይፈጥራሉ፡፡.. “አንፈርስም አንታደስም” ነው ርዕሱ፡፡ ማነው የማይፈርሰውና የማይታደሰው? እነማን ናቸው?
የመጽሐፉ ገፅ ሲገለጥ የፍቅር፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ስብስብ ናቸው - ግጥሞቹ። ይሁንና በውበትና በቅርፅ፣ በምናባዊ ምጥቀትና በቋንቋ ልዕቀት፣ ዋናውን ርዕስ ከያዘው ይልቅ የሚያሥከነዱ ሌሎች ግጥሞች ቢኖሩም “አንፈርስም አንታደስም” የሚለው ርዕስ ሃሣቤን አሥሮ አክርሞታል፡፡ ለምን አንፈርስም? ለምን አንታደስም?
“እንፍረስ” የሚለው ነገር መቼም የሚያሳምምና አሥደንጋጭ ነው፡፡ ጆሮዋችንም ይህንን ሲሠማ ወዲያው ወደ ሀገራችን ጉዳይ ሄዶ ቂብ ይላል፡፡ ይሸክከናል፡፡ ያመናል፡፡ የአሌክስ አብርሃም ግጥም ግን የሚለው ሌላ ነው፡፡ እስቲ ወደግጥሙ ሀሳብ እንግባ፡-
ይች አገር… ይች ኢትዮጵያ በቋፍ ነው ያለው ሰላሟ
አንድነቷ አፋፍ ላይ ነው- ሊፈጠፈጥ ትልቅ ህልሟ!
የኔን ደም ጉበን ቀብተህ… የሞት መላ‘ክ ካልዘለለህ፣
እመነኝ እኔ ከሌለሁ ወገኔ አደጋ ላይ ነህ!
ዝጋ!!
የመግቢያው አንጉዋ- ንቡር ጠቃሽ ዘይቤ ተጠቅሞ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘፀዐት- ጋር ያናፅራል። እሥራኤል በባርነት የገዛው የግብፅ መንግስት ፈርዖን፣ የህዝቡን ነፃ መውጣት አልቀበል ብሎ- አሻፈረኝ ባለ ጊዜ፣ እግዚአብሔር /እሥራኤል አምላክ/ የግብፃውያንን የበኩር ልጆች በሞት- ሲመታ እሥራኤላዊያን የሞት መልዐክ እንዳያገኛቸው፣ ጉበኖቻቸው ላይ የበግ ደም- እንዲቀቡ ተነግሯቸው ነበር፡፡… ያንን የበግ ደም ያየው የሞት መልዐክ፣ ያልፋቸው ነበር፡፡… የበጉ ደም በጉበኑ ላይ የሌለ ሁሉ አደጋ ላይ ነው!
ገጣሚው አሁንም አገርህ ቋፍ ላይ ናት፤ አንድነቷ አፋፍ ላይ ነው፤ ስለዚህ የኔን ደም በርህ ላይ ካልቀባህ አለቀልህ! እያለ የሚያሥፈራራን አለ!... እያለ ነው፡፡ እኔ ከሌለሁ የለህም አይነት!
በርግጥም ይህ የመፍረስ ነገር፣ ይህ የሠላም ጣጣ ድምፅ ከምንጊዜውም የበለጠ የልባችንን በር እያንኳኳ እንደሆነ ብዙዎች ይሥማሙበታል፡፡ ገጣሚው ዮናስ ኪዳኔም- ስለ አንድነት የሚገርሙ ስንኞች ተርትሯል፡፡ እንዲህ ብሎ፡-
አንቺም ስሚኝ ፍቅሬ!
“እምዬ ሃገሬ
መመኪያዬ ክብሬ” አትበይኝ አስሬ!
ክልል፣ ጎሳ፣ ብሔር ስም ሆኖ መለያ
ለዘር ግጥም ዜማ ከተሰራ ወዲያ
ወዴት ነች አንድ ሃገር፤ የታለች ኢትዮጵያ!
ገጣሚ ዮናስ ኪዳኔ፣ ጭራሽ አልቆላታል፤ ቆሎ ሆናለች እያለ ነው፡፡ ስሟ አየር ላይ ተንጠለጠለ እንጂ፣ ተበታትናለች ነው፤ ሃሳቡ፡፡ ሁሉም ስለ ሰፈሩ፤ ስለ መንደሩ እንጂ ስለ ሀገሩ ማሠብ ትቷል፡፡
ኤሌክስ አብርሃም በ“አንፈርስም አንታደስም” ግጥሙ፤ “የኔን ደም ቀቡ፤ እኔ ከሌለሁ አትኖሩም” የሚለውን ወገን እንዲህ ይለዋል፡-
ፉግር ነገር ሸራቢ አቃቢ ዘመነ ብታኔ፤
ግንዱን ራሱ ፈልጦ…ልጥ ነኝ ይሉት የባብ ቅኔ!!
በላ አገር አጣቅስ …ማነው ታስሮ አንድ የሆነ፤
የቱ ልጥ ነው የቱ ገመድ - ከፍቅር በልጦ ያዋገነ!
እዚህ ጋ ደሜን ካልቀባችሁ ያለው እንደገና ልጥ ሆኖ፤ “በኔ ካልታሠራችሁ፣ አንድነት የለም!” ይላል። ገፀሰቡ ግን ማነው በመታሰር አንድ የሆነ? ይልቅስ የፍቅርን ያህል ለአንድነት የሚሆን ምን አለ? ሲል ያጠይቃል፡፡
የግጥሙ ጠቅላላ ሀሳብ፤ “ትፈርሣላችሁ!” ይሉናል፣ ግን አንፈርስም፣ መፍረሥ ብቻም አይደል አንታደሥም ነው፡፡” ርዕሱ ሲታይ “አንፈልግም!።” የሚል ይመሥላል፤ ግን አይደለም፡፡ ገፀ ባህሪው የያዘው ሽሙጥ ነው፡፡ ለመታደሥ ዝግጁ አይደለንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለመፍረሥም ቀላል አይደለንም፡፡ የለዘዘ እንጨት ዐይነት ነን፡፡ በራድ ወይም ሙቅ ያለመሆን ዐይነት! ለዚህም እንደ ማጠናከሪያ እንዲህ የሚሉ ስንኞች አሉልን፡-
“ምን ነበር” ብለን አንዞር “ምን መጣ?” ብለን አንሰጋ…
ዛሬያችንን እየበላን ከዕለት እንጀራችን ጋ፣
መጠበቅ ነው ጉልበታችን ጨለማችን አስኪነጋ…
ነግቷል ሊለን ዶሮ ቢጮህ… መድፍ በደጅ ቢያጓራ
ዘመን ያገነነው ኢምንት ቢገዝፍ እንደተራራ
ደማሚት ነው ትዕግስታችን ያለት ብልት የሚመትር፤
የተካበውን የሚንድ… የተናደን የሚከምር
መጨቆን እጅጅ ቢለን - ከብሶት ብንፀነስም፤
ዙፋን ላይ እኛም ብሶት ነን- አንፈርስም አንታደስም!!
የዙፋን ላይ ብሶት የምንሆነው፣ እኛው ተጨቆንን ባዮቹ ነን - ነው አዝማሚያው፡፡ አንዱ - ያለ መታደሳችን ምክንያት ይህ ነው፡፡ …
ገጣሚዋ ምስራቅ ተረፈ፤ ሀገርና መሪን እንዲህ እያለች - ታዛምዳቸዋለች፡፡ ጥቂት ስንኞች ልምዘዝ፡
በሕዝብ ጫማ ቆመህ አንጋጠህ ወደ ላይ፣
ውረድ የምትለው ከአናቴ ጫንቃ ላይ፤
ይህ ያንተ ተቃውሞ መሪ ሆኖ ሲታይ.
ይህ ያንተ ተቃውሞ በስልጣን ሲሰማ፣
እንዲህ ማለት ነው “ሚስትህን ልቀማ”
ታዲያ ይሄ ወንጀል አያስከስስህም?
ያለ ፍርድ ውሳኔ አያሳስርህም?
ለዚህ መተላለፍ ሞትስ አያንስህም?
በተዛባ ትርጉም አትበለው ውረድ፣
ቦታው ላይ ሳትሆን መሪ ላይ አትፍረድ፡፡
እንኳን የገዛ ሚስት አትዋስም ገረድ፤
ያለመታደሳችን - ምክንያት ሥልጣንን የሚስትን ያህል መውደዳችን ነው፡፡ አንድ ነፍስና አካል መሆናችን! የሙጢኝ ማለትታችን … እኔ ከሌለሁ ይህቺ ሀገር ትፈርሳለች፣ ትጠፋለች ዓይነት! ዲስኩራችን፡፡
…ደርግም፤ - አብዮቱ እንዳይቀለበስ፣ ፀረ ህዝቦች ቦታውን ይዘው፣ ሰፊውን ህዝብ እንዳያሰቃዩ ነበር የሚለው፡፡ አሁንም ኢህአዴግ፤ - ከብተና ያወጣሁዋት ሀገር፣ (ስላቅ መሰል አባባል) የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረላት ሀገር፤ በፀረ ሰላም ኃይሎች፣ ባለፈው ሥርዐት ናፋቂዎች እጅ እንዳትወድቅ፣ መጋደል ነው፡፡ ዛሬም - ገና ትግል ነው!!
በዚህ አባዜያችን፣ የአሌክስ አብረሃም መጽሃፍ እንዲህ ይላል፡-
ያለን የነበርን የምንኖር … እንደ ፅልመት ሳንጨልም፣ እንደፀሐይ ሳንፈካ፣
ሽክርክሪት ታሪካችን አቦል … ቶና … በረካ!
ከጅማሬያችን ሳንርቅ ከፍጻሜያችን ሳንጠጋ፣
ከተነሳው ማዕበል ጋር ሆነን ስንላጋ
አንዱ ስልጣኔ ባጅቶ … አፍንጫችን ሥር ቢከስም፣
ታሪክ እማኛችን ነው - አንፈርስም አንታደስም!
እንዲህ ነው - ታሪካችን! … አዙሪታችን ይህ ነው፡፡ ሁሉም፤ ለሀገር እንደኔ ያለ የለም ብሎ ይፈጠማል፡፡ … ንጉሱም እንደዚያ ነበሩ፣ ደርጉም፤ በዚያው መንገድ ሄደ፡፡፣ አሁን ያለውም እራሱ በጎሳ በሸነሸናት ሀገር ላይ ተቀምጦ፣ “እኔ ከሌለሁ ልትፈርስ - ነው!” ይላል፡፡ አሁንስ ምን ቀራት ይሆን? …
አሌክስ አብርሃም በመንግስት ብቻ ሳይሆን በእኛም በሀገሪቱ ህዝብ ላይ ይሳለቃል፡፡ የኃይለ ሥላሴ ወጥ ቤት ኃላፊ የነበረው የደች ተወላጅ በፃፈው መጽሐፍ ያንፀባረቀውን ስሜት አሌክስም ደግሞታል ልባችን ወላዋይ ነው፤ በሚል ዐይነት ስሜት፡፡
የግዜር ደጃፍ ተሳልመን የጠንቋይ እግር ብንስም
ያበሾች አምላክ እማኝ ነው- አንፈርስም አንታደስም!
ንጉሥ እግዜር ቀባኝ ቢል…. አፈሙዝ ቢያዞር ወታደር፤
ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ቢፀነስ- ርዕዮት ለጉድ ቢሰደር፤
እንዲህ እንዲያ እያለ- የምፅዐት ቀን ቢደርስም
ስርዓት ይከሽፋል እንጂ- አንፈርስም አንታደስም!
ጧት በተስኪያን፣ ረፋድ ላይ ጠንቋይ-ቤት መሄዳችንም የአቋማችንን ልልነት ያሣያል ይላሉ አሌክስና የንጉሡ ወጥቤት ሃላፊ፡፡ ስለዚህም አንድ ልብና ውሳኔ ስለሌለን፣ እንደ ኩሬ ውሃ እዚያው ነን፤ አንደርቅም፣ አንፀድቅም!
ታዲያ እስከ መቼ ነው የማንለወጠው? እስከ መቼ ነው ያለፈ ታሪካችንን እየደሰኮርን የዓለምን ጆሮ የምናደነቁረው? ምናልባት ችግሩ … ገጣሚ ዮናስ ኪዳኔ ያለው ይሆን?
በስልጣን እርከን ላይ ትልቅ እውነት አለ
ቅንነት ወራጅ ነው ሹመት ከፍ ካለ?

Read 1007 times