Saturday, 07 October 2017 14:56

በ”ዳንኤል ታዬ” ምን ታየ?

Written by  ሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(2 votes)

   የዚህ ጽሑፍ መነሻ መስከረም 18 ተከፍቶ እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም በጣሊያን የባህል ማዕከል በመታየት ላይ ያለው፣ የሠዓሊውን ስም የያዘ፣ “ዳንኤል ታዬ” የተሰኘው “የሥዕል አውደ ርዕይ” ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሥዕል ትርዒት መግለጫነት የማይወክለውን  ቃል ማለትም “አውደ ርዕይ”ን በቸልታ መጠቀም ተለምዷል። አንድ ትርዒት “አውደ ርዕይ” ለመባል በየዓመቱ መደረግ አለበት፡፡ አውድ ዓመት እንደሚባል ሁሉ። የሆነው ሆኖ ይህን ትርዒት በታደምኩበት ምሽት የተፈራረቁብኝ ስሜቶች፣ የትርዒቱን አስፈላጊነትና ምንነት እንዲሁም ሠዓሊው ያቀረባቸው ስራዎች በትርዒቱ የተካተቱበትን አመክንዮ ከመመርመር የተመዘዘ ጠያቂነት (Curiosity) ነበር ለመጻፍ ያነሳሳኝ፡፡
የአንድ የሥነ- ጥበብ ወይም የሥዕል ትርዒት ብርታት ተመልካቹ ላይ በሚፈጥረው ተፅዕኖ ሊመዘን ይችላል፡፡ እንደ ግለሠብ ተመልካች፣ “ዳንኤል ታዬ” የተሰኘው ትርዒትን ከተመለከትኩ በኋላ ደጋግሜ ሳስብ የነበረው፣ ትርዒቱ ያቀበለኝ እውነተኛ እሴት ይኖር ይሆን በሚል ነበር፡፡ በትርዒቱ የቀረቡ ሥራዎች ያመቋቸው የሃሳብ ቀረጢቶች፣ ንቃተ ህሊናዬንም ሆነ ስሜቴን የመግዛት አቅም የሌላቸው፣ ልል ወይም የላሉ ሆነው ነበር ያገኘኋቸው፡፡ ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ሳቢያ ይመስለኛል፡፡
አንደኛው በትርዒቱ ከቀረቡ 23 ሥራዎች መካከል ከ4 ሥራዎቹ በስተቀር፣ 19ኙን በሚገባ የማውቃቸው ናቸው፡፡ አራቱ አዳዲስ (ከሆኑ) ስራዎች፣ ከ19ኙ ጋር መቅረባቸው ለትርዒቱ ምሉዕ ወይም ወጥ የሆነ የትርዒት ባህሪ አይቸሩም።  በትርዒቱ የተካተቱት ሥራዎች ቢያንስ ከ1988 ዓ.ም እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የተሰሩ ሲሆኑ የቅርብ ጊዜ የሆኑትን ሥራዎች ለመለየት የሚያስችል መረጃ በሥዕሎቹም ሆነ ለተመልካች ተጨማሪ መረጃ በሚሰጡ ጽሑፎች አልተካተተም። በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተፃፈ የሥዕሎቹን ርዕስና ዋጋ ከሚገልፅ ሰንጠረዥ ውጪ የሠዓሊውን መደንግግም (statement) ሆነ ግለ-ታሪክ የሚናገር፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ትርዒት ማሟላት የሚገባቸው ደጋፊ መረጃዎች ከመጓደላቸውም በላይ ቢያንስ ከሠዓሊው የዳበረ ልምድ አንፃር፣ በሥነ-ጥበብ አጋፋሪ ታጅቦ፣ አጋፋሪውም የትርዒቱን ምክንያታዊነት በትንታኔ ማስደገፍ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ይህ ሁሉ አለመከሰቱ ትርዒቱ አትኩሮቴን ሊገዛ ላልቻለበት ምክንያት ምርቃቶች ናቸው፡፡
በእርግጥ እኔ እንደ ግለሰብ ተመልካች፣ ትርዒቱና ሥራዎቹ ስሜቴን መግዛት አለመቻላቸው፣ የተሰላቸና የተዳከመ ምናልባትም ውስጣዊ ተነሳሽነት የተነጠቀ የሚመስለውን የሠዓሊውን ግላዊም ሆነ ሙያዊ ብርታት የራቀው የሥራ መንፈስ፣ በትርዒቱና ባቀረባቸው ሥራዎች ውስጥ ማየቴ፣ትርዒቱ ከውጥኑ ሊያስተላልፍ የሚሻውን እውነተኛ እሴት በመሳቴ ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ አንድን ትርዒት በመረዳት ሂደት ውስጥ ያላዳበርኩት አተያይ በመኖሩ ሊሆን ስለሚችል፣ ይህን የማላውቀውን ጉዳይ ለማስተንተን ይከብደኛል፡፡
በሌላ በኩልም ሠዓሊ ዳንኤል ታዬ በተለይም በ1980ዎቹ አጋማሽ፣ ዘመነኛ የሀገራችን ሥነ-ጥበብን በአፍላ የወጣትነት እድሜው ከተቀላቀለበት የስኬት ጊዜያቱ ጀምሮ የተራመዳቸውን ሥነ-ጥበባዊ እመርታዎችና ያበረከታቸውን አስተዋፅኦዎችን መለስ ብለን ብንቃኛቸው፣ ትርዒቱን እንደ ትውስታም ሆነ እንደ እመርታ፣ ሌላው ቢቀር እንኳን ሠዓሊው አሁን የት ጋ እንደደረሰ በእርግጠኛነት ሊያመላክት የሚችል ትርዒት ስለመሆኑ ሚዛን የሚደፋ እውነተኛ እሴት በማጣቴ ነው ትርዒቱን ለመዳሰስ የወሰንኩት፡፡
ትርዒቱ ከግላዊ ስሜት ብቻ ሳይሆን የሃገራችንን የዘመንኛ ሥነ-ጥበብ ስንዳስስ፣ ሊቃኙ ከሚገቡ ሙያዊ እይታዎች አንፃር ስመለከተውም፣ በቸልታ ለማለፍ የማያስችለኝን ሀሳብ የሚያጠናክርልኝ ደግሞ ትርዒቱ ድፍረት የሚታይበት በመሆኑ ነው። አንድ ሠዓሊ ስራዎቹን ለትርዒት የማቅረብ ወኔና ጥረት ኖሮት ማሳካት ከቻለ፣ ሥራው ምንም ሆነ ምን በልበ ሙሉነት ከሰዎች ፊት የመቆም አቅምና ፍላጎት አለው ማለት ነው፡፡ በትርዒቱ ከቀረቡት 23 ስራዎች 4ቱ ከተሰሩ በኋላ ምንም ጭማሪ ሳይደረግባቸው እንዳሉ የቀረቡ ሲሆኑ፣ ሌሎች 19ኙ በድጋሚ የተነካኩና መነካታቸውም የማበላሸት ስሜታዊና ውጥናዊ ውሳኔዎችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡ ይህ የሠዓሊው ፍላጎት እንደሆነ እሙን ቢሆንም ምክንያቶቹም በግልጽ ቢታወቁ፣ ስራዎቹን ይበልጥ ለመረዳት ከማስቻሉም በላይ በሠዓሊው ሥነ-ጥበባዊ ጉዞ፣ ማስታወሻ ጥለው ሊያልፉ ይችሉ ነበር፡፡
በኔ አረዳድ የተዳከመም ሆነ የተሰላቸ መንፈስ ተጭኖትም ቢሆን በጭላንጭልም ሆነ በተዳፈነ ብርሃን የሚታየውን (ማን ያውቃል ለሱ በፀዳልም ሊሆን ይችላል የሚታየው) እንካችሁ ለማለት አደባባይ መውጣት የቻለን፣ ያውም እንደ ዳንኤል ታዬ ያለ የቀደመ ብርታት ያለው ሠዓሊ፤በዚህ አይነቱ ትርዒት ምን ለማለት እየፈለገ እንደሆነ ለመመርመር የምሻው፣ በትርዒቱ ከቀረቡ ሥራዎች መካከል በአውታረ መጠን ትልቅ የሆኑትንና “Untitled” ወይም “ያልተሠየመ” እንዲሁም “አብቹ” የተሰኙ ሥራዎቹን በመመርኮዝ ነው፡፡ በዚህም የትርዒቱን አቅጣጫ ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡
እነዚህ ሁለት ስራዎች በአሰራር በዘይቤም ሆነ በይዘት የተለያዩ ከመሆናቸው የተነሳ ሁለት ጽንፍ የያዙ ሠዓሊዎች ስራዎች ነው የሚመስሉት። “Untitled” የተሰኘው ስራ ለሚያነሳቸው ሃሳቦች መያዣ መጨበጫ ማበጀት ያልቻለ፣ እይታዊ ልጓሙ ዝርው የሆነና በጥናትና ምርምር ከተፈረጁ ሥነ-ጥበባዊ ምድቦች ያፈነገጠና የፈረጠጠ ነው፡፡ ይህ ሥራ የተለያዩ ሽርፍራፊ ሃሣቦችን መወርወርን እንጂ በአንድ ዕይታዊ መዋቅር ማደራጀትን ያልተጨነቀ፤ ይልቁንስ ሠዓሊው ሥራውን ሲወጥነውም ሆነ ሲሰራው ያስተናገዳቸውን ሃሳቦችና ስሜቶች የዘራበት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ስራዎች በበርካታ ሠዓልያን የሚሰሩ ቢሆንም ይህን አይነት ስራዎችን እንዲሰሩ የሚገፏፏቸውን ግለሰባዊ ወይም ሰብዕናዊ፣ ማሕበረሰባዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ባጠቃላይም የሕይወት ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ በማሰብና በመስራት ሂደት ያበጇቸውን ዘመንኛ ገዢ ሃሳቦች ለማተት የሚጠቀሙበት ነው። ሥራው የሠዓሊውን ሥነ-ጥበባዊ አቅጣጫ ከማመላከት አንፃር ወደ ኋላ መለስ ብለን ልንቃኘው የሚቻለን ዋቢ ማጣቀሻ ብንፈልግለት፣ ሠዓሊው ሠርቶ ካበላሻቸው ስራዎች በቀር አምሳያ ወይም ዘመድ የምናገኝለት አይሆንም፡፡ በዚህም ምናልባት ሠዓሊው በሌሎቹ ባበላሻቸው (በእርግጥ ያበላሻቸው ሳይሆን በማበላሸት የቋጫቸው ብንላቸው የተሻለ ይመስለኛል) ስራዎቹ ሙከራ አድርጎ፣ በዚህ “Untitled” በተሰኘው ስራ ባሳየው አይነት አቀራረብ ሊወጣው የሚፈልገውን ዳገት በይፋ የጀመረበት አመላካች ሆኖ ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም ስራው የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ለትርዒት የመብቃት ብስለት እንዳለው፣ ሠዓሊው ለትርዒት እንዲቀርብ በወሰነው ውሳኔ እንጂ የሠዓሊውን ሥነ-ጥበባዊ አቅጣጫ አመላካች መሆን አለመሆኑ፣ በጊዜ ሂደት የምንመለከተው ይሆናል፡፡ ዋጋው ሃምሳ ሺ ብር ሲሆን ትርዒቱ በተከፈበት ምሽት የታደሙ የሥዕል ሰብሳቢን ቀልብ በመግዛት ለመሸጥ ችሏል፡፡ ለስራው የተጠየቀውን ገንዘብ የከፈሉትም አድናቂ፤ በዚህም ሆነ በማንኛውም ምክንያት ስራውን ንብረታቸው ማድረግ መቻላቸው የሚያስደስት ነው፡፡ ዘመን ያፈራው የሥነ-ጥበብ ሥራ፤ በዘመኑ ዋጋ ሲሰጠው እንደማየት ምን የሚያስደስት ነገር አለ?
ሌላኛው ሥራ “አብቹ” የተሠኘው ሲሆን ሠዓሊው ቀድሞ በሚታወቅበት የእውነታዊነት (Realism) የአሳሳል ዘይቤ የተሠራ ነው፡፡ በስራው በጣሊያን ወረራ ወቅት አይነተኛ ተጋድሎ ያደረገውንና በሰፊው የተዘመረለትን የፍቼ ሰላሌውን ጀግና ለማውሳትና ለመዘከር አስቦበት፣ ሠዓሊው በሥነ-ጥበብ ት/ቤት ቆይታው አዳብሮ፣ ኋላም በሠዓሊነት ያጎለበተው የእውነታዊ አሳሳል ዘይቤን መርሆዎች በመመርኮዝ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ ለሚያስባቸውም ሆነ ያላቸውን ለማስታወስ የተሰራ ስራ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ስራ ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ ሠዓሊው የገራና ፈር ያስያዘውን ሥነ-ጥበባዊ አቅጣጫ መመልከት ይቻላል። በአንጻሩም ከላይ በተጠቀሰው “Untitled” በተሰኘው ስራ ሊያጉተመትም የሚፈልገውን ዳር ዳርታ ተመልክተናል፡፡ በነዚህ ሁለት ጽንፎች መሃከል ሠዓሊውን የወጠሩት ገመዶች ምን እንደሆኑ ለመመራመር ጊዜና የሠዓሊው ፍቃደኝነት ያሻሉ። ይህ መሆን ካልቻለ ግን ያው እንደተለመደው፣ ”ትርዒቱ ተከፈተና ተዘጋ” ይሆናል፤ ያውም ግድ የሚሰጠው ካለ፡፡ ዘመንኛ የሚባለው ሥነ-ጥበባችንም እንዲሁ የዕውር ድንብሩን እያነሳ ሳይሆን እየጣለ ይኳትናል፡፡
ዳሰሳዬን ለመቋጨት ያህል ሁለት ነጥቦችን አነሳለሁ፡፡ አንድ ትርዒት ያነገበውን እውነተኛ እሴት ለማስጨበጥ አንኳር ነጥቦችን ያነገቡ ስራዎችን ማቅረብ ብቻ በቂ ነው፡ ሌሎች ለአጀብ የሚመጡትን ስራዎች ዋጋ ያሳጣልና፡፡ ይህን የምለው ከትርዒት መሰረታዊ አስፈላጊነትና ምንነት አንጻር እንጂ ስራዎቹ ካላቸው አቅምና ሃሳብ አልያም ከተሰጣቸው ዋጋ አንጻር እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ሌላኛው ደግሞ አንድ ሠዓሊ ትርዒት ሲወጥን፣ ሙያዊ ደረጃውን በጠበቀና ባሟላ መልኩ ሲሆን ከታሪክም አንጻር ያለውንና ሊሰጠው የሚገባውን ቦታ ታሳቢ አድርጎ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ባለቤቱ ላልተጨነቀለት አጥር፣ ጎረቤት ግድ የማይሰጠው ሃገር ላይ እየዋለለ መሆኑን መዘንጋቱን ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!!!


Read 620 times