Print this page
Saturday, 07 October 2017 15:05

በግል ት/ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ወላጆች ተማረናል አሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“ት/ቤቶቹ በራሳቸው ስልጣን የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይችሉም”

በዘንድሮው ዓመት በአንዳንድ የግል ት/ቤቶች የተደረገው የክፍያ ጭማሪ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ የገለፁ ወላጆች፤ ጭማሪው ልጆቻቸውን በግል ት/ቤቶች ለማስተማር እንዳይችሉ የሚያደርግ መሆኑን ተናገሩ፡፡ ት/ቤቶቹ በራሳቸው ፍቃድና ፍላጎት በየጊዜው በክፍያ ላይ የሚያደርጉት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አቅማቸውን የሚፈታተንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን ወላጆች ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ በበኩሉ፤ት/ቤቶቹ በራሳቸው ስልጣንና ፍላጎት ብቻ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እንደማይችሉና ጭማሪ ለማድረግ ሲፈልጉ፣ ጭማሪውን ለማድረግ ያስገደዳቸውን በቂ ምክንያት በመዘርዘር፣ ለኤጀንሲው አቅርበው፣ ኤጀንሲው በጉዳዩ ላይ ከት/ቤቶቹ ባለቤቶችና ከወላጅ ኮሚቴዎች ጋር በሚደረግ ውይይት የሚወሰን መሆኑን ገልጿል፡፡
ሁለት ህፃናት ልጆቻቸውን በአንድ የግል ት/ቤት ውስጥ ላለፉት አራት አመታት ማስተማራቸውን የሚናገሩ አቶ ሰለሞን ታየ የተባሉ ወላጅ፤ “በዘንድሮው ዓመት የተደረገው 80 ፐርሰንት ጭማሪ ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ልጆቼን ከት/ቤቱ ለማስወጣትና በመንግስት ትምህርት ቤት ለማስገባት ተገድጃለሁ፤” ብለዋል፡፡
 የክፍያ ጭማሪውን በተመለከተ አስቀድሞ የተነገራቸው ነገር አለመኖሩን የሚገልፁት እኚሁ ወላጅ፤ ት/ቤቶቹ ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ሲቃረብና በሌሎች ት/ቤቶች ምዝገባ ሲጠናቀቅ የክፍያ ጭማሪ ማድረጋቸውን የሚያሳውቁት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚወስዱበት ሌላ ቦታ ስለማይኖር የዋጋ ጭማሪውን በግዳቸው ይቀበላሉ ከሚል መነሻ ነው ይላሉ፡፡ ቤተ ክህነት በምታስተዳድረው ት/ቤት ልጆቻቸውን  እንደሚያስተምሩ የገለፁልን  ሌላ ወላጅ ደግሞ፣ ት/ቤቱ በየጊዜው በዘፈቀደ የሚያደርገው የዋጋ ጭማሪ በእጅጉ እንዳማረራቸውና ለሚያቀርቡት አቤቱታ ምላሽ የሚሰጣቸው አካል በማጣታቸው ተስፋ መቁረጣቸውን ገልፀዋል፡፡
ት/ቤቶቹ በየጊዜው ከሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ በላይ እጅግ ያማረራቸው “የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች”  እየተባሉ ለት/ቤቱ ገቢ እንዲያደርጉ የሚጠየቋቸው እንደ ሶፍት፣ ሳሙና፣ ደስታ ወረቀት፣ ደርዘን እስኪርብቶና እርሳስ የመሳሰሉት መሆናቸውን ወላጆች ይጠቅሳሉ። “ጉዳዩ ተመልካችና ሃይ ባይ በማጣቱ፣ ት/ቤቶቹ እንደፈለጋቸው ይጫወቱብናል፤” ሲሉም ያማርራሉ። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አንዳንድ የግል ት/ቤት የሥራ ኃላፊዎች፤ ማነጋገር ያለብን የት/ቤት ባለቤቶቹን እንደሆነ ገልፀውልናል - እነሱ ተቀጥረው የሚሰሩ በመሆናቸው ምላሽ ለመስጠት እንደማይችሉ በመጠቆም፡፡ ሆኖም የት/ቤቶቹን ባለቤቶች ለማግኘት ያደረግነው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ፍስሃ በበኩላቸው፤ ት/ቤቶቹ በራሳቸው ፍቃድና ፍላጎት በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉና ጭማሪውን ለማድረግ የተገደዱበትን ምክንያት በዝርዝር ለኤጀንሲው የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ኤጀንሲው ከት/ቤቶቹ ባለቤቶች ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ ት/ቤቶቹ ከወላጅ ኮሚቴ ጋር ተወያይተውና በጭማሪው መጠን ላይ ስምምነት ላይ ደርሰው፣ ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የሚያደርጉትን የክፍያ ጭማሪም የትምህርት ዘመኑ ከመጠናቀቁ 3 ወር በፊት፣ በቀጣዩ ዓመት ጭማሪ የሚያደርጉ መሆኑን ከነጭማሪው መጠን ገልፀው የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ኃላፊው ተናግረዋል። ከዚህ አሠራር ውጪ የሚደረገው ጭማሪ ግን ህገ ወጥ እንደሆነና ቅሬታ ያላቸው ወላጆች፣ በየደረጃው ለሚገኙ የት/ቢሮዎች በማሳወቅ፣ በህገወጦች ላይ እርምጃ ማስወሰድ እንደሚችሉ አቶ ኃይለሥላሴ ፍስሃ ገልፀዋል፡፡


Read 1970 times
Administrator

Latest from Administrator