Print this page
Saturday, 07 October 2017 14:52

የልማት ተነሺዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙ ተገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የልማት ተነሺዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙ ተገለፀ
አለማየሁ አንበሴ
በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የልማት ተነሺዎች ላይ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጥናት ያረጋገጠ ሲሆን ጥናቱ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ከካሣ ክፍያና ከምትክ ቦታ አሰጣጥ ጋር የተገናኙ መሆናቸው በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡  
 ጥናቱ በዋናነት የተደረገው በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ ሲሆን የልማት ተነሺዎች በቂ ካሳና ምትክ ቦታ እንደማይሰጣቸው፣ የልማት ተነሺዎች መሰረተ ልማት በተሟላለት አካባቢ ምትክ ቦታ ያገኛሉ ቢባልም፣ ይህ ህግ ተግባራዊ አለመደረጉ ተጠቁሟል፡፡
ከካሳ ክፍያ አፈፃፀምና ከምትክ ቦታ አሰጣጥ ጋር በተገናኘም እንግልትና የመብት ጥሰቶች እንደሚስተዋሉ ለውይይት መነሻነት በቀረበው ጥናት የተገለፀ ሲሆን የሚሰጣቸው የምትክ ቦታ ማነስም ሌላው ችግር መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ የልማት ተነሺዎች ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ በተደጋጋሚ እንዲነሱ እየተደረጉ መሆኑን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ ይህም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ብሏል፡፡ ኮሚሽኑ ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን መለየቱንና በጥናት ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በጥናት ውጤቱ ላይ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ውይይት የተደረገበት መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለጹት የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ፤ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት የሰጧቸው አስተያየቶችና ሃሳቦች የጥናቱ አካል ሆነው፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚቀርብና የጥናቱ ዝርዝርም ጉዳይም ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡  
በአዳማው የውይይት መድረክ ላይ ከፌደራልና ከክልሎች ከተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች የቀረቡ አስተያየቶችን ያካተተ የመጨረሻ የጥናት ውጤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚቀርብም አቶ ደምሰው ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

Read 2051 times