Saturday, 07 October 2017 15:07

ዋልያዎቹ በወዳጅነት ጨዋታዎች ተወጥረዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ኢትዮጵያ ማስተናገድ ትፈልጋለች - ካፍ፤ ጥያቄ አላቀረብንም - ፌደሬሽን
• EFFCONNECT ሰኞ ስራ ይጀምራል


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታዎች የተወጠረ ሲሆን ፌደሬሽኑ ለቡድኑ የአቋም መፈተሻ የለም በሚል ከየአቅጣጫው የሚቀርበውን ትችት ምላሽ እየሰጠሁ ነው ብሏል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ2018 የቻን ውድድር እንዲሁም ከ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ውጭ በሆነበት ሰዓት ተደራራቢ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረጉ ብዙዎችን የሚያነጋር ሆኗል።
አንዳንድ የስፖርት ቤተሰቦች የወዳጅነት ጨዋታዎቹን ከሽርሽር የላቀ አስተዋፅኦ እንደማይኖራቸው እየተቹ ቢሆንም የወዳጅነት ጨዋታዎቹ  በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ያለን የደረጃ እርከን ለማሻሻል ሊጠቅም ይችላል።  የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ለብሄራዊ ቡድኑ የአቋም መፈተሻ አያዘጋጅም በሚል መተቸቱን ያረምኩበት ጥረት ነው በሚለው አቋም ፀንቷል፡፡ ከሞሮኮ በፊትም ዋልያዎቹ ከዩጋንዳ ፣ ዛምቢያ እና ቦትስዋና ጋር ባለፈው 1ዓመት ውስጥ መጫወታቸው ይታወቃል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ለቦትስዋና  51ኛ ዓመት የነፃነት በዓል መታሰቢያ በጋቦሮኒ ከተማ ተጫውቶ 2ለ0 የተሸነፈው ብሄራዊ ቡድኑ በውድድር ዘመኑ በሌሎች የወዳጅነት ጨዋታዎች ከኡጋንዳ ጋር በሜዳው 0ለ0  እንዲሁም ከሜዳ ውጭ ከዛምቢያ ጋር 0ለ0 መለያየቱ ይታወሳል፡፡
ዋልያዎቹ የፊታችን ማክሰኞ ደግሞ በራባት ከተማ ከሞሮኮ የቻን ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚጫወቱ ሲሆን ሁለቱ አገራት ከወዳጅነት ጨዋታዎቹ በፊት ሁለቱ አገራት በ3 የዓለም ዋንጫ እና በ2 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች 5 ጊዜ ተገናኝተው ሁሉንም ያሸነፈችው ሞሮኮ ነበረች፡፡
ዋልያዎቹ በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ያለፈውን ሰሞን በዝግጅት ላይ የቆዩ ሲሆን፤ ዋና አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለና ሌሎች የቡድኑ አባላት የወዳጅነት ጨዋታው በተለያዩ ምክንያቶች አያስፈልገንም በማለት የተከራከሩት በቂ እና የተሟላ ዝግጅት አላደረግንም እና የልምምድ ቲሸርት  እንዲሁም ሌሎች የትጥቅ አቅርቦቶች አልተሟሉንም በሚሉ ቅሬታዎች እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ ዋልያዎቹ ወደ ራባት ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ ሙሉ የአየር ትራንስፖርት ወጪ በሞሮኮ እግር ኳስ ፌደሬሽን እንደሚሸፈን የተገለፀ ሲሆን፤ በ2018 በሚደረገው የቻን ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የማትካፈል ቢሆንም ተሳትፏዋን ያረጋገጠችው ሞሮኮ  የወዳጅነት ጨዋታውን አቋሟን የምትፈትሽበት ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን  ለ2018 የቻን ውድድር ምትክ አዘጋጅ እያፈላለገ ሲሆን  አስቀድሞ በአዘጋጅነት መርጧት የነበረችውን ኬንያ የመስተንግዶውን መስፈርቶች ባለማሟላቷ እድሉን ነጥቋታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የቻን ውድድሩን በምትክነት የሚያስተናግደውን አገር ከሳምንት በኋላ እንደሚያስታውቅ የገለፀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ፤ ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ  ጥያቄ ማቅረባቸውን በኦፊሴላዊ ድረገፁ ከሁለት ሳምንት በፊት አስታቋል።
በጉዳዩ ላይ  የኢ.እ.ፌ ፕሬዝዳንት ጁነይዲ ባሻ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የማዘጋጀት ጥያቄ አለመቅረቡን የገለፁ ሲሆን የመረጃው ምንጮች አንዳንድ የኬንያ ስፖርት ጋዜጠኞች እና ሚዲያዎች ናቸው እየተባለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውድድሩን የማስተናገድ ፍላጎት በ2020 እኤአ ሲሆን ካፍም ለዚህ ፈቃድ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ኢኳቶርያል ጊኒ ስለመስተንግዶ ጥያቄዋ ምላሽ ያልሰጠች ቢሆንም የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮ ግን መስተንግዶውን ለመውሰድ እንደምትፈልግ ብየፋ መግለጫ በመስጠት አረጋግጣለች፡፡ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ ለቻን መስተንግዶው 4 ስታድዬሞች ዝግጁ መሆናቸውን ያመለከተ ሲሆን እነሱም ኦጋዲር አድሚር፤ ታንዛዩፊስ ኢብን፤ በካዛብላንካ የሚገኘው መሃመድ አምስተኛ እና የማራኬሹ ግራንድ ስታድዬሞች ናቸው፡፡
በሌላ ዜና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በፊፋ ኮኔክት የምዝገባ መዋቅር መስራት በመጀመር ከአፍሪካ 7ኛ አገር እንደሚሆን ታውቋል፡፡ ባለፈው ሰሞን የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር 5 የአይቲ ኢንስትራክተሮች እና ባለሙያዎች ስለፊፋኮኔክት አሰራር ከ25 አገራት ለተውጣጡ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ስልጠና መስጠታቸውን ለስፖርት አድማስ ያስታወቀው በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የአይቲ፤ የሲኤምኤስ እና የፊፋ የተጨዋቾች ምዝገባ ወይንም ቲኤምኤስ ማናጀር አቶ ሚካኤል እምሩ ነው፡፡
ፊፋ ኮኔክት የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሽኖች እና ባለድርሻ አካላት በአንድ ላይ የሚጋሩትን የመረጃ መረብ ለመዘርጋት እና መረጃዎችን ለማከማቸት ተፈጥሯል ያለው አቶ ሚካኤል፤ በምዝገባ መዋቅሩ ከፊታችን ሰኞ አንስቶ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች እና በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ሌሎች ተቋማት የሚገኙ የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት መመዝገብ እንደሚችሉ፤ በሁሉም አገራት እንደሚደረገው የኢትዮጵያ የምዝገባ ቋት EFFCONNECT በሚል ስያሜ ስራ እንደሚጀምር አመልክቷል፡፡
የፊፋ ኮኔክት የምዝገባ መዋቅር ከ10 ዓመት በላይ ለሚሆናቸው የእግር ኳስ ተጨዋቾች እንደ እግር ኳስ ፓፖርት እና መታወቂያ የሚወሰድ ሲሆን፤ ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ዳኞች፤ አሰልጣኞች፤ የጨዋታ ኮሚሽነሮች፤ የክለብ አመራሮች፤ የቡድን መሪዎች፤ የፌደሬሽን አመራሮች በመረጃ ቋቱ የሚመዘገቡ ይሆናል፡፡







Read 1455 times