Saturday, 14 October 2017 15:10

በቅማንት ህዝበ ውሣኔ፣ አንድ ቀበሌ ብቻ የቅማንት ራስ ገዝ አስተዳደርን መርጧል

Written by 
Rate this item
(14 votes)

 የቅማንት ህዝበ ውሣኔ ከተደረገባቸው 8 ቀበሌያት መካከል በ7ቱ፣በነባሩ አስተዳደር እንቀጥላለን የሚለው አብላጫውን ድምጽ ሲይዝ፣በአንድ ቀበሌ ደግሞ በቅማንት አስተዳደር ስር የሚለው አብላጫ ድምፅ ማግኘቱን የምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
ህዝበ ውሣኔውን አስመልክቶ ሪፖርታቸውን ለፌደሬሽን ም/ቤት ያቀረቡት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፀሃፊና የፅ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ነጋ ዲፊሣ፤ በጭልጋ ወረዳ ስር የምትገኘው “የኳበር ሎምዬ” ቀበሌ ላይ የተደረገው ህዝብ ውሣኔ፣ በቅማንት አስተዳደር ስር እንካለል የሚለው አብላጫ ድምፅ በማግኘቱ፣ ቀበሌው በቅማንት አስተዳደር ስር እንደምትካለል ያረጋገጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ሠባት ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳደር ስር ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ህዝበ ውሣኔ ገና ያልተካሄደባቸው ቀሪ አራት ቀበሌዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የአማራ ክልል አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ከቀበሌዎቹ ህዝብ ጋር ውይይት አካሂዶ ሲያጠናቅቅና ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ የክልሉ አስተዳደር ለፌዴሬሽን ም/ቤት ጥያቄ ሲያቀርብ የሚፈፀም መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በስምንቱ (8) ቀበሌያት በተካሄደው ህዝበ ውሣኔ ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገበው 23 ሺህ 283 መራጭ መካከል 89 በመቶው ወይም 20 ሺህ 824 ነዋሪዎች ድምፅ መስጠታቸውን በአቶ ነጋ ሪፖርት ላይ ተጠቁሟል፡፡ ከምርጫ ቦርድ በዚህ መልኩ የቀረበለትን ሪፖርት የገመገመው የፌዴሬሽን ም/ቤትም ውጤቱን አፅድቆታል፡፡

Read 2510 times