Saturday, 14 October 2017 15:17

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር አልተለቀቀም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

  “የእስር ጊዜውን ጨርሶ አለመፈታቱ ተስፋ አስቆርጦናል” - ቤተሰቦቹ-

      በ”ፍትህ” ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ሦስት የተለያዩ ጽሁፎች ክስ ቀርቦበት፣ የሦስት ዓመት እስራት የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ የእስራት ጊዜውን አጠናቆ በትላንትናው ዕለት ከዝዋይ ማረሚያ ቤት እንደሚለቀቅ ቢጠበቅም ባልታወቀ ምክንያት ሳይፈታ መቅረቱን ቤተሰቦቹ በሃዘን ገልፀዋል፡፡
 ሦስት ዓመት የእስራት ጊዜውን ማጠናቀቁን የሚናገሩት የጋዜጠኛው ቤተሰቦች፤ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፣ ከእስር እንደሚለቀቅ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ማረጋገጫ አግኝተው እንደ ነበር፤ ሆኖም ትላንት እንደሚፈታ ሲጠብቁ ውለው መጨረሻ ላይ እንደማይፈታ ተነገረን ይላሉ፡፡ ምክንያቱን ስንጠይቅ፤ በደፈናው፤ “ማጣራት ያለብን ጉዳይ አለን” የሚል መልስ ከሃላፊዎቹ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል መፈታቱን በጉጉት ስንጠብቅ ጨርሶ ባልጠረጠርነው ሁኔታ ከእስር እንደማይለቀቅ መስማታችን ተስፋ አስቆርጦናል ይላሉ-የተመስገን ደሳለኝ ቤተሰቦች። መቼ እንደሚፈታ ስንጠይቅም፤ “ሲፈታ ታውቁታላችሁ” ተብለናል ያሉት ቤተሰቦቹ፤ እኛ ግን እየተመላለስን በመሄድ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
አቃቤ ህግ በጋዜጠኛው ላይ ከመሰረታቸው ሦስት ክሶች አንደኛው፤ ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም በ”ፍትህ” ጋዜጣ ላይ “ሞትን የሚደፍሩ ወጣቶች” በሚል ርዕስ በፃፈው ፅሁፍ፣ ወጣቶችን ለአብዮትና ለለውጥ እንዲነሳሱ አደፋፍሯል፣ ለማሳያነትም የአፄ ኃይለስላሴን ስርአት፣ ወጣቶች እንዴት እንዳፈረሱትና በአረቡ ዓለም ወጣቶች የነበራቸውን ሚና ጠቅሷል የሚል ነበር፡፡
በጋዜጠኛው ላይ የቀረበው ሁለተኛው ክስ ደግሞ ሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም “የሁለተኛ ዜግነት ህይወት በኢትዮጵያ እስከመቼ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ፅሁፍ፣ መንግስት በተለያዩ ክልሎች የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅሟል በማለት የአገሪቱን መንግስት ስም አጥፍቷል የሚል ነው፡፡ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበው ሦስተኛ ክስ፤መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም “ሲኖዶሱና መጅሊሱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያ” በሚል ርዕስ በጋዜጣው ባወጣው ፅሁፍ፣ የህዝቡን አስተሳሰብ ለመለወጥ ሀሰተኛ ወሬዎችን በማሰራጨት፣ ህዝብን ማነሳሳት የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡  
ጋዜጠኛው ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ በሦስቱም ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ የታሰረ ሲሆን ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ፍ/ቤቱ፣ የሦስት ዓመት እስራት ውሳኔ አሳልፎበታል፡፡ ጋዜጠኛው የአመክሮ ጊዜ ተከልክሎ፣ የሦስት አመቱን የእስራት ጊዜ በዝዋይ ማረሚያ ቤት  ያጠናቀቀ መሆኑ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የጋዜጠኛው “ጊዜ ለኩሉ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ለገበያ መቅረቡ ተገለጸ፡፡ መፅሐፉ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በዝዋይ ማረሚያ ቤት ሳለ፣ በተለያየ ጊዜ የፃፋቸውን ግጥሞችና መጣጥፎች ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

Read 3967 times