Saturday, 14 October 2017 15:18

በሰሞኑ የኦሮሚያ ከተሞች ተቃውሞ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል

Written by 
Rate this item
(27 votes)

 “የክልሉን ህዝቦች አንድነት ለማበላሸት የተወጠነ ሴራ ነው”

      ሰሞኑን በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ  የ8 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የገለጸው የክልሉ መንግስት፤የተቃውሞ እንቅስቃሴው እየተጠናከረ የመጣውን የክልሉን ህዝቦች አንድነት ለማበላሸት የተወጠነ ሴራ ነው ብሏል፡፡   
ባለፈው ረቡዕ  በአምቦ፣ ወሊሶ፣ ሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ ሃረር - ጨለንቆና በኬ ከተሞች ተቃውሞ የተደረገ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ ህዝብ ተሳትፎበታል ሲሉ የአይን እማኞች በገለፁት የሻሸመኔው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡  
በተጨማሪም በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ቦኬ ወረዳ በተካሄደ ሰልፍ ላይም የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን የገለጸው  የክልሉ መንግስት፤ አጥፊዎችን ተከታትዬ ለህግ አቀርባለሁ ብሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ደግሞ በወሊሶና በአምቦ ከተሞች ተቃውሞ አይሎ መስተዋሉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በተቃውሞ  ሰልፎቹ ላይ በስፋት ከተደመጡ መፈክሮች መካከልም፤ “አቶ ለማ መገርሳ ፕሬዚዳንታችን ነው፤ ከጎኑ እንቆማለን!”፣ “የታሰሩ የኦፌኮ አመራሮች ዶ/ር መረራ እና በቀለ ገርባ ይፈቱ”፣ “የወገኖቻችን መፈናቀል ይቁም!” የሚሉና የመንግስት ለውጥን የሚጠይቁ ይገኙበታል ብለዋል፤ ምንጮች፡፡
በአምቦ የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሳታፊ ብዛት የላቁ ናቸው የሚሉት ምንጮች፤ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ነው የሚመስለው ብለዋል፡፡
በሰሞኑ የኦሮሚያ ከተሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የክልሉ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት እየሰራ ያለው ስራ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ እንዲሁም አንድነትን እያጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፣ “አፍራሽ ኃይሎች” ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የቆሙ በማስመሰል፣ ወጣቱን በስሜት አነሳስተው፣ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት የተጀመሩ ስራዎችን ለማክሸፍ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል፡፡ ህዝቡ የእነዚህን አካላት ጥሪ እንዳይቀበልም ዶ/ር አብይ ጠይቀዋል፡፡
የተቃውሞ እንቅስቃሴዊቹ በተደረጉበት ወቅት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ያለጦር መሳሪያ ህዝቡን ወደየቤቱ እንዲመለስ ሲመክሩና ሲያግባቡ መታየታቸውን ጉዳዩን አስመልክቶ ለቪኦኤ መረጃ የሰጡ የአይን እማኞች አስረድተዋል፡፡
በሻሸመኔ እና በበኬ ከደረሰው የሞት አደጋ በስተቀር በሌሎቹ ከተሞች የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸውን የየአካባው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

Read 5906 times