Saturday, 14 October 2017 15:21

ተቃዋሚዎች፤ የፕሬዚዳንቱን የፓርላማ መክፈቻ ንግግር ተቹ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(40 votes)

“አገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ ያገናዘበ አይደለም”


     ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ሰሞኑን ለፓርላማው ያቀረቡት የዓመቱ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎችን አመላካች ሪፖርት፣ ሀገሪቱ ያለችበትን “ፖለቲካዊ ቀውስ” ያገናዘበ አይደለም ሲሉ የተቹት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ለችግሮች እልባት የሚያስገኝ አይደለም ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱን ዋነኛ የፖለቲካ ችግሮች ቸል ብለው፣ የኢኮኖሚ ዕድገት አሃዞች ላይ ማተኮራቸውን በመጠቆም፣ ሪፖርታቸው ሀገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ችግር አቅልሎ ያቀረበና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
በሀገሪቱ ግጭት፣ ተቃውሞና አለመረጋጋቶች አሁንም ድረስ መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ጫኔ፤ ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ጉዳዮች እንዴትና በምን ሁኔታ ይፈታሉ የሚለውን ጉዳይ አለማንሳታቸው ግራ አጋቢ ነው  ብለዋል፡፡
“መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ ብሎ የደረሰበትን ደረጃ እንኳ የሚያመላክት ነገር በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ አልተመለከትንም” የሚሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ሁሉም ነገር እንዲህ ተደባብሶ የሚያልፍ ከሆነ በሀገሪቱ በጥቂቱ እየታየ ያለውን የኢኮኖሚ እድገት ተስፋ መልሶ እንዳያዳፍነው ያሰጋል ብለዋል፡፡
 “ከፕሬዚዳንቱ የፓርላማ ንግግር፣ መንግስት፤ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ዕቅድ እንደሌለው ነው የተገነዘብነው፤ ይሄ ደግሞ ለሀገር አንድነትና የወደፊት ተስፋ አደገኛ ነው” ብለዋል - ዶ/ር ጫኔ፡፡
“የፌደራልና የክልል መንግስት ግንኙነት በላላበትና የኦሮሚያ - ሶማሌ ክልል ግጭት ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችን ባፈናቀለበት ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ፣ የፌደራል ስርአቱ እያበበ ነው ማለታቸው አስገራሚ ነው” የሚሉት ደግሞ የመኢአድ ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ናቸው፡፡ የኑሮ ውድነት በናረበትና የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተባባሰ ባለበት ሁኔታ፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው መባሉን የሚቃወሙት አቶ አዳነ፤ ይህ ሁኔታ የበለጠ መንግስትና ህዝብን ሆድና ጀርባ የሚያደርግ ነው ብዬ እሰጋለሁ ብለዋል፡፡  
“ፕሬዚዳንቱ የመንግስታቸውን የ2010 የትኩረት አቅጣጫዎች ባስቀመጡበት ንግግራቸው ላይ በዋናነት በሀገሪቱ እንዴት ሰላምና መረጋጋት ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ጉዳይ ማካተት ነበረባቸው” የሚሉት አቶ አዳነ ጥላሁን፤” መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ የሆነባቸውን ጉዳዮች ከእነ ምክንያቱና መፍትሄው የሚዘረዝር ጥናትም እንዲቀርብ መጠቆም ነበረባቸው” ብለዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፤ መንግስት በሀገሪቱ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶችን በብሄራዊ መግባባትና እርቅ የመፍታት እቅድ እንደሌለው ከፕሬዚዳንቱ ንግግር ተረድቻለሁ ይላሉ፡፡ “ህዝብ ካልተግባባና ካልተፋቀረ፣ ሀገሩን የኔ ነው ብሎ ካልወደደ ስለ ልማት ብቻ ማውራት ምን ዋጋ አለው?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ አበበ፤ዲሞክራሲ እንዴት ይስፋፋ የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ሳይቀር በፕሬዚዳንቱ የመንግስት አቅጣጫ ማመላከቻ ንግግር ላይ ትኩረት አለማግኘቱ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ንግግር በሃገሪቱ ያሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ከመጠቃቀስ በዘለለ በግልፅ ያስቀመጠው ነገር የለም የሚሉት የመድረክ ም/ሊቀ መንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፤” ባለፈው ዓመትም የፖለቲካ ምህዳሩን እናሰፋለን፤ ለወጣቶችም የሥራ እድል እንፈጥራለን ብለው በቃላቸው አልተገኙም” ሲሉ ነቅፈዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደውም የበለጠ እየጠበበ መጥቷል ያሉት ም/ሊቀመንበሩ፤ ዶ/ር መረራ ጉዲናን የመሳሰሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች መታሠራቸውን በምሳሌነት  ይጠቅሳሉ፡፡  
አሁንም ድረስ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተቃውሞዎችና ግጭቶች መኖራቸውን የሚያነሱት አቶ ጎይቶም፤የፕሬዚዳንቱ ንግግር እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ፈትቶ፣ሃገሪቱን እንዴት ከወድቀት ማዳን ይቻላል የሚለውን ወሳኝ ጉዳይ በቸልታ ያለፈ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡  

Read 5405 times