Saturday, 14 October 2017 15:33

“ለውጥ” እና “ነውጥ” የሚያላጋት ሀገር!!

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(4 votes)

     ሀገራችን በለውጥና በነውጥ ማዕበል ሳትንገላታና ሳትላጋ የኖረችባቸውን የተረጋጉ ዘመናትንና ዓመታትን እንዲጠቁሙን የታሪክ መዛግብትንና የዕድሜ ባለጠጎችን ብናማክር፣ ወደ የትኛው የታሪካችንና የዘመናችን አቅጣጫ እንደሚጠቁሙን ለመገመት በእጅጉ ያዳግት ይመስለኛል፡፡ ብዙ የአውሮፓ ሀገራት ወርቀ ዘቦ አልብሰው እንደሚኳሹት ዓይነት፣ “ሰላማዊና ወርቃማ ዘመን” በየትኛው ወቅት ተጎናፅፈን እንደነበር ለመመስከርም በግሌ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ዘመነ አክሱምም ይሁን ዘመነ ላሊበላ ወይንም ምስራቁ፣ ምዕራቡ፣ ደቡቡና ማዕከላዊው የሀገራችን ክፍሎች ወደ አስመዘገቧቸው ቀደምት ታሪኮች በምልሰት ወደ ኋላ ብናፈገፍግ፣ ቁርጥ ያለና ሁሉንም ጎራ የሚያስማማ ሀገራዊ “የወርቃማ ዘመን” ምሳሌ ለመጠቆም የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አዘውትረን ከምንዘምርላቸው የሥልጣኔዎቻችን ቀለመ ደማቅ ገፆች መካከልም ቢሆን የገዘፉና ጥቋቁር ነቁጦችን መንቀሳችን አይቀርምና፡፡
የግል የንባብ ፍቅሬና በዘመነ ፍሬሽማን የወሰድኩት የታሪክ ኮርስ ዕውቀቴ፣ ከዚህ መንደርደሪያ በላይ “እንዳልተርክ” በራሱ ተማምኖ በክርክር ሊረታልኝ ስለማይችል፣ አቅመ ደካማውን ብዕሬን እየኮለኮልኩ፣ ዘመን ወለድ ወደሆነው ስሜታዊና ያልተፈለገ የፍልሚያ ጎራ ላሰልፈው ስለማልፈቅድ ወደ መነሻ ዓላማዬ ማቅናቱ የተሻለ ይመስለኛል፡፡
የትኛውም ሀገር ቢሆን ያለ ነውጥ ለውጥ አላመጣም ወይም ነውጥና ለውጥ መንትዮች ናቸው የሚል ተሟጋች ብቅ ካለም ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ ነውጥና ለውጥ እንደ ነፍስና ሥጋ የተዋሃዱ መሆናቸው እውነት ቢሆንም የእኛው ሀገሩ ነውጠኛ ሱናሚ ግን በየዘመናቱ ሥርዓት ወለድ በሆኑ አውዳሚ ወጀቦችና ማዕበሎች በመታገዝ ከዓመት ዓመት ሲያተራምሰን ለምን እንደሚኖር እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፡፡ ለእንቆቅልሼ ጥያቄ “ምን አውቅልህ” ባይ መላሽ አገኝ እንደሆን ብዬም፣ እነሆ ውሉ ጠፍቶብን እየተወሳሰበ ግራ ባጋባን በሀገሬ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመቆዘም ይህንን ርዕስ መርጫለሁ፡፡ “አይጣልን ያቀሏል” እንዲሉ፡፡
ካቻምና ትምህርት አልሰጥ ብሎን፣ የአምናውን ልምድም ማስታወስ ተስኖን፣ የዘንድሮንም ክስተቶች እንደ ዘበት እያለፍናቸው፣ ሀገሬ ነጋ ጠባ የመልህቋ ገመድ እንደተበጠሰባት ጀልባ፣ በሁሉም የሕይወታችን ዐውዶች በአውሎ ነፋሶች ስትንገላታ ማየት በእጅጉ ቅስምንም ልብንም ይሰብራል፡፡ “ዐይታው የማታውቀው የልማት ለውጥ ባለቤት ሆናለች” እየተባለች የሚደሰኮርላት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ዝንጉርጉር መልክ ባለው የበረታ ወጀብ፣ ዕለት በዕለት ስትናወጥ ማየቱም የዘወትር ምሳ እራታችን ከሆነም ሰነባብቷል። የሰላማዊ ምህዳር አየር ሽታ እየናፈቀንም በየቤታችን እንደየ እምነታችን ቀኖና፣ በክራሊያሶ አራራይ ዜማ ወደ ፈጣሪ በመቃተት ላይ ነን፡፡ የሚያሳዝነውና ለሰሚው ግራ የሆነው የጓዳችን ብሔራዊ ገበናም ከእኛ “ትልልቅ” ተብዬዎች አልፎ ተርፎ፣ ነፍስ ወዳላወቁት እንቦቀቅላ ሕፃናቶቻችን ሳይቀር መዛመቱም እንቆቅልሻችንን ይበልጥ እያመሳጠረው፣ “ወየው ለነገ ትውልዳችን” እያሰኘን ነው፡፡
መቼም ይህን መሰሉ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሳ፣ በቀጥታ በፖለቲካው ነገረ ሥራ ላይ ለማተኮር ታስቦ ይመስላል፡፡ እውነት ነው፣ የብዙ ሀገራት የቀውስ መንስዔ፣ የፖለቲካው ጤና እጦት መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ቢሆንም የእኛው ሀገራዊ የበሽታ ደዌ ግን ከፖለቲካዊም ህመም ትንሽ ዘለል ብሎ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ላይ መዛመቱ አልቀረም። ቀድሞውንስ ቢሆን እጀ ረጅሙ የሀገራችን ፖለቲካ የማይገባበትና የማይነካካው ምን ጉዳይ ይኖራልና ካላልን በስተቀር፡፡ ለምሳሌ፤ ሃይማኖትን ለአብነት እንጥቀስ፡፡ “የሰላም ዘብና ተሟጋቾች ነን” በሚሉት በበርካታ የሀገራችን ቤተ እምነቶች ውስጥ የተፋፋመው ወቅታዊ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚጠቀሰውን አርማጌዶን ያስታውሳል፡፡
ምዕመናንን “የምድር ጨው እና የዓለም ብርሃን ናችሁ” እያሉ እንዲያስተምሩ መለኮታዊ ትዕዛዝ ተቀብለናል በሚሉት ቤተ እምነቶችና ቤተ ፀሎቶች፣ “አገልጋዮች” መካከል የተፋፋመው ውጊያ፣ እግዚኦ ከማሰኘትም የዘለለ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ባመቻቸው ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጫኑትን የመረጃ ምንጮች የከፈተ ሰው፣ የሚዥጎደጎዱለት መረጃዎች ጉድ እያሰኙ ነው፡፡ እከሌ ተከሌ ብሎ ለመፈረጅ እስከሚያዳግት ድረስ እርስ በእርስ መወጋገዙ፣ መዘላለፉ፣ መሰዳደቡ፣ መነቋቆሩ እውነትም የመሲሁ መምጣት ከደጅ ደርሶ ይሆንን ያሰኛል፡፡ ልብ በሉ፤ ለማስታረቅና ሰላምን ለማወጅ መለኮታዊ ሥልጣን ተሰጥቶናል በሚሉት “ምርጥ አገልጋዮች ነን” ባዮች መካከል፣ ይህን መሰሉ ራስን ማዕከል ያደረገ ሃይማኖታዊ ነውጥ፣ ወደ ምን እንደሚያደርሰን ለመተንበይ ይቸግራል፡፡ “ለነፍሳችን አድረን ነፍሳትን ወደ ዘላለማዊ የጽድቅ ሕይወት እንመራለን” እያሉ በሚሰብኩት ቤተ አምልኮዎች ውስጥ የሰፈነው ጉዳጉድ፣ “ከተከድኖ ይብሰል” ደረጃ አልፎ በይፋ ሻምላ ወደማማዘዝ ደረጃ አድርሷል፡፡ ነውጥ! ነውጥ! ነውጥ!
“ባለ ሁለት አሃዝ አስመዝጋቢው” የኤኮኖሚያችን ነውጥና ለውጥ ግን እየባሰበት መሄድ ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑን ወገናችንን የዕለት ጉርሱን አሸንፎ ለማደር ወደማያስችልበት ደረጃ ላይ እያደረሰው እንዳለ ምስክርነት የምንጠራው የዕለት ጉሮሮአችንን ማንቋረር ነው፡፡ የነጋዴው ኡኡታ አየሩን ሞልቶታል፡፡ የሸማቹ እሪታ ወደ ፀባዖት እየተቃረበ ነው፡፡ የመንግሥት ምላሽም ማድበስበስ ሆኗል፡፡ እድገት ነዋ፡፡ ቲማቲም አርባ ብር ቢደርስ፣ ስኳር ለመድሃኒት ቢጠፋ፣ ጤፍ ወደ ቅንጡ ምግብነት ቢለወጥ፣ በቆሎ ለአይን ብርቅ ቢሆን፣ የመሸመቻው የበረንዳ ገበያችን ቢነጥፍ፣ ዕድገቱ ያመጣው “ዕድገት” ስለሆነ ቻሉ ተብለናልና እንችለዋለን፡፡ መከራውን በጫንቃችን ተሸክመን በስውሩ ጓዳችን እንደየ እምነታችን  እንደፈለግነው፣ የፈለግነውን ሥርዓትም ሆነ ሹም እያሳቀልንም ሆነ እየረገምን መፀለዩ ላይ ግን እስካሁን በአዋጅ አልተከለከልንም፡፡
“እንኳንስ ዘንቦብሽ” እንዲል የሀገሬ ሰው፣ እንኳንስ ሰበብ ተገኝቶ ይቅርና ገና ለገና ሳይሆን አይቀርም እየተባለ ሸማቹ ሕዝብ አለበቂ ምክንያት በዋጋ ውድነት በሚቀጣበት ሀገር፣ ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ግንዛቤ፣ የዶላር ምንዛሪ መመንደግ የሚያስከትለው “የቡሃ ላይ ቆረቆር” ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አይከብድም፡፡ ነገ ተነገወዲያ ምን መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ፣ ነብይ መሆን የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡ መች ይሆን አንድን መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ፣ ለዜና ማሰራጫ ከመላኩ አስቀድሞ የምሁራን ጉባዔ መክሮበት፣ የዘርፉ ጠበብት ተከራክረውበት ተግባራዊ የሚሆነው።  መቼስ ይሆን፣ “ሥልጣንን በምርጫ ካርዳችን ያጎናፀፍናቸው ክቡራትና ክቡራን” ወንበረተኞች፣ በሀገራቸው ጉዳይ በነፃነት ተከራክረውና በሃሳብ ተሞሻልቀው፣ የመንግሥትን ፖሊሲ በመሞገት ቀልብ የሚያስገዙት፡፡ አልሆን ካላቸውም፣ ወንበራችሁን ተረከቡን ብለው የሚጨክኑት፡፡ ነውጥ! ነውጥ! ነውጥ!
የፖለቲካ ቡድኖችና ቡድንተኞች፣ ለውጥና ነውጥ ግን የዘመናችን ልዩ ክስተት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የማይስማሙ ፖለቲከኞቻችን “ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ” እየተባባሉ፣ የሕፃናት ልጆቻችንን ጨዋታ ከነጠቋቸውም ሰነባብቷል። በእያንዳንዱ የፖለቲካ ጓዳ ውስጥ ትልቋን ኢትዮጵያና የተከበሩት ብሔረሰቦቻችንን፣ በልዩነታቸው ኅብር አቀራርቦ ከማስዋብ ይልቅ ልዩነታቸውን በማጉላት ብቻ በጎጠኝነት ሰበካ ላይ እየባዘኑ እንዳሉ እያስተዋልን ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን ለውጣቸው በነውጥ፣ ኅብረታቸው በእልኝነትና በእኔ አውቃለሁ ባይነት ብቻ ሲፈረካከስም እያስተዋልን ነው፡፡ የራስን ዝናና ጥቅም ካማከለ አስተሳሰብ መቼ እንደምንላቀቅ አላውቅም፡፡ ነውጥ! ነውጥ! ነውጥ!
የሰሞኑ አሳራችን ግን በአጭሩ ካልተቀጨ በስተቀር ከትውልድ ትውልድ ተቀጣጥሎ እየፈነዳ የሚሸጋገር ድማሚት እንዳይፀንስብን ስጋታችን ከፍ ያለ ነው፡፡ ከቀናት በፊት አብሮ አደግ ጓደኛማቾች በሚገናኙበት ወርሃዊ የፍቅር ማዕድ ላይ ይወራ የነበረው ስጋት በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነ ገምቻለሁ፡፡ በወቅቱ ያሸተትኩትንም የውይይት ጭስ አልወደድኩትም፡፡ አብሮ አደግ ማኅበርተኞቹ የአንድ ዘመን ትውልዶች ሲሆኑ የወለዷቸውም ልጆች በዕድሜም ሆነ በትምህርት ተቀራራቢ ናቸው፡፡ እነዚህ ጓደኛማቾች ልጆቻቸው ወደሚማሩበት የተለያዩ ክልሎች፣ የትምህርት ተቋማት ከመመለሳቸው አስቀድሞ ተሰባስበውና ትንሽ ዘና ብለው እንዲጫወቱ በማሰብ፣ ሁሉም የየራሱን ልጅ ወደ ምሳው ግብዣ ይዞ መጥቶ ነበር፡፡
በግብዣው ላይ ዋና አጀንዳ የነበረውም ልጆቻቸውን ወደሚማሩበትና ወደተመደቡበት የየክልሉ የትምህርት ተቋማት እንላካቸው ወይንስ አንላካቸው የሚል ክርክር ነበር፡፡ በዚህ የወላጆች ውይይት ላይ ወጣቶቹም እንዲሳተፉና የየግላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ እድል ተሰጥቷቸው ስለነበር ይወረወሩ የነበሩት ስጋቶችና ፍርሃቶች፣ በእውነቱ ሀገሬ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሳለች የሚያሰኝ ነበር። እንዴት የአንድ እናት ወገን ይፈራል? እንደምንስ ልጄን እዚያ ዩኒቨርሲቲ ከምልከው ባይማር ይቅር፣ “ጎመን በጤና” አሰኝቶ ያስተርታል? በራሳቸው ሀገር፣ ሕዝቤ በሚሉት ሕዝብ መሃከል? ፍርሃት፣ መሳቀቅ፣ አለመተማመን! “የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” የሆነብን ይመስለኛል፡፡
ልጆቻቸውን በየተመደቡበት የትምህርት ተቋማት ለመሸኘት የተስማሙት ቤተሰቦችም ቢሆኑ በጋራ የደረሱበት ውሳኔ የብሔረሰባቸው ማንነት በይፋ የታተመበትን የቀበሌ መታወቂያ፣ ልጆቻቸው ሳይዙ እንዲሄዱ መምከር ነበር፡፡ “የእኔ ልጅ እንኳን ከፋም ለማም የክልሉን ቋንቋ ስለሚችል አደጋው ሊቀንስለት ይችላል” ብለው የተፅናኑም ነበሩ፡፡ ወይ ሀገሬ! እዚህ ደረጃ ላይ እንድረስ፡፡ ምናለ ከሩዋንዳ ተምረን በመታወቂያችን ላይ “ብሔር” የሚለውን መገለጫ አውጥተን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን ብናጎላ፡፡ ምንስ አለበት እንደ ፓስፖርቱ ሁሉ ዜጎች የሚይዙት አንድ ተመሳሳይ ብሔራዊ መታወቂያ ቢዘጋጅልን፡፡ ነውጥ! ነውጥ! ነውጥ!
መንግሥትና መሪው ፓርቲ የነካካው የአንድ ሰሞን የጥልቅ ተሃድሶና የሙስና ጉዳይ ምን ያህል አቧራ እንዳጨሰ አይዘነጋም፡፡ “ጥልቅ ተሃድሶው አጥልቆ ከመዳበስ ይልቅ በጣቱ የነካካው፣ የላይ ላዩን አቧራ ብቻ ነው” ከሚለው ሃሜታ ጀምሮ ያልተባለ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ደካማ ተብሎ የተፈረጀው ሹም፣ በአምባሳደርነትና በተሻለ ዝውውር ሲሸጋሸግ ተመልክተን፣ እውነትም “ተጠልቆ ታድሷል” ብለን በዜግነታችን ስልጣን፣ “ወንበር የሰጠነውን መንግሥትና ፓርቲ” በግላጭም በለሆሳስም በሃሜት ጨርግደነዋል፡፡
የሙስናውም ጉዳይ እንደዚያው ነው፡፡ ለካንስ የዚያን ያህል በሚሊዮኖች እየተዘረፈ፣ ህሊናን በጥቁር ሻሽ ጠፍሮ፣ በየሚዲያው ላይ ስለ ትራንስፎርሜሽን ስኬትና ውጤት፣ ልብን ሞልቶ መናገር ቀላል ነበር ብለንም አምተናል። ኤኮኖሚስቶቹ ጓደኞቻችንም ተዘረፈ የተባለው ገንዘብ፣ ለሕዝብ ጥቅም ቢውል ኖሮ ምን ያህል የጤና ተቋማት፣ ግድቦችና ትምህርት ቤቶች ሊሠራ ይችል እንደነበር ሲያስጎመጁን፣ ሚስቶቻችን የሚያማርሩት የሀገራችን ዘይት አንጀታችንን ያቃጠለው አንሶ፣ የእነርሱ ሙያዊ ገለፃ ይብሱን ቆሽታችንን አድብኖታል፡፡ የሙስናው ዘመቻ ሰንሰለት ከየት ተነስቶ የት ይደርስ ይሆን፣ እግዚኦ እያልንም በመገረም ጠብቀን ነበር፡፡ እግር ጥሎን በአንዳንድ ሃሜታው በሚዘንብባቸው ሕንፃዎችና የሙስና ሰፈሮች ስናልፍ ስናገድምም ቆይ፣ “እንደ ሊቀ መልዓኩ” የተመዘዘው የሙስና ሰይፍ በቅርቡ ሳይቀመጥላችሁ አይቀርም እያልንም ገላምጠናቸው አልፈናል፡፡ የተሳለ የመሰለን የሙስና ሰይፍ፣ በረጅሙ መመዘዙ አይቀርም እያልን በጉጉት ስንቋምጥም ዘመቻው፣ “ለአጥንት የሰነዘርኩት ሰይፍ በጉበት ታጠፈ” አሰኝቶ አስተርቶናል፡፡ ነውጥ! ነውጥ! ያለ ለውጥ፡፡
መቼም ደጋግመን እንደወተወትነው ብሔራዊ መግባባትም ይባል ብሔራዊ ዕርቅ ማስፈን እስካልቻልን ድረስ የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ነውጥ ይገታል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ የሃይማኖት ቤተሰቦችም፣ ፖለቲከኞች አለያም የሀገሪቱ አዛውንቶችና ምሁራን፣ ዐውዳቸው በሚፈቅደው ልክ በሃገራዊ መግባባት ላይ በጋራ መስራት ካልቻሉ በስተቀር የውጥር የያዝን ሀገራዊ ችግር ፋታ ሊሰጠን መቻሉ ያጠራጥራል፡፡ “ችግር ያለባቸው ሊታረቁ ይችላሉ፡፡ እኛ ከማንም ጋር ችግር የለብንም” የሚለው የየትኛውም ክፍል ፉከራ የትም የሚያደርስ አይደለም፡፡
የፌዴራሊዝም ሥርዓታችን መዋቅር ቢፈተሽ፣ የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ፍልስፍናችን ቢገመገም፣ የክልል ሽንሻኖ ልምዳችን ለውይይት ቢቀርብ ምፅዓትን የሚያቃርብ አይመስለኝም። የተሻለ መስሎ ከታየን፣ በአሸናፊነት እልል ብለን እናስቀጥለዋለን፡፡ ህፀፅ ካለበትም ይታረማል። ያለበለዚያ ግን የሚቀጥለውን ከማስቀጠል፣ የሚለወጠውን ከመለወጥ፣ የሚታረመውን ከማረም፣ የሚሻሻለውን ከማሻሻል ይልቅ አንዳች ሃሳብ በሆነ አካል በተሰነዘረ ቁጥር፣ ለሕዝቦች ልዕልና ሕይወታቸውን የገበሩ ፅኑዓን ሰማዕታትን ካረፉበት ዘላለማዊ እረፍት እየቀሰቀሱ፣ በአጽማቸው ማስፈራራት በግሌ አግባብ አይመስለኝም፡፡ እነዚያ ለሕዝባቸው ክብር ሲሉ የወደቁ ኃያላንም ቢሆኑ በመንፈስ ይታዘቡ ይመስለኛል፡፡  
በችግሮች ሥርና መሠረት ላይ በሚገባ ተወያይቶና የበቀልን መንፈስ አርቆ መነጋገር ጀግንነት እንጂ የተሸናፊነት ምልክት አይደለም። ስልጣኑን መተግበር ተስኖት ለተበላሸ ሃገራዊ ጉዳይ ኃላፊነቱን ወስዶ፣ “ይህ ችግር በእኔ ምክንያት የተፈፀመ ስለሆነ ወንበሬን ለቅቄያለሁ” የሚል ጀግና የመንግሥት የስራ ኃላፊ መቼና እንዴት ማግኘት እንደምንችል ባላውቅም መፈጠሩ ግን እንደማይቀር ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ከብዙዎቹ የሩቅ ወዳጆቼ ጋር በሀገሬ ጉዳይ ስንወያይ፣ በበርካታ ጉዳዮች ስሜታቸው እንደሚዳምን ይነግሩኛል፡፡ እውነት ነው ስለ ኤኮኖሚ ዕድገታችን፣ እኛም የምንለው እነርሱም የሚሉት ነገር አለ፡፡ የትኛው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ነበር “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ያለው? የኤኮኖሚያችን የሁለት አሀዝ ዕድገት የሚተረክልንን ያህል የሰላማችን እድገትም ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊተረክልንና ሊተገበርልን ይገባል። እድገት ብቻውን ያለ ሰላም ትርጉሙ ይሳሳል፡፡ ያለ ምንም ፍረጃ፣ ለሕዝብ አስተያያት እህ ብለው የሚያደምጡ ሹማምንትም ይናፍቁናል፡፡ ማድመጥ ብቻ ሳይሆን የተግባርና የመልካም ሰብዕና ጠረን ያላቸው መሪዎችን ብናገኝም ደስታውን አንችለውም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሀገራችን በተለያዩ የነውጥ ማዕበሎች ከመመታቷ አስቀድሞ ወጀቡን ፀጥ ማሰኘት የሚችሉ መሪዎችን ማግኘት እንደምን መታደል ነው፡፡ እነሆ የጯሂው ድምፅ ሰልችቶት እስኪሰልል ድረስ ይህን መሰል አጀንዳ እያነሳን፣ “ጆሮ ያለው እንዲሰማን” እንጮሃለን፡፡ ቸር እንሰንብት!!

Read 2210 times