Saturday, 14 October 2017 15:36

በዓለማችን በየቀኑ 20 ሺህ ልጃገረዶች ያለዕድሜያቸው ይዳራሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 11 ወጣት ሴቶችን የገደለው ሜክሲኳዊ በ430 አመታት እስር ተቀጣ

      በዓለማችን በየቀኑ 20 ሺህ ልጃገረዶች የየአገራቱ የጋብቻ ህጎች ከሚፈቅዱት ውጭ ያለ ዕድሜያቸው በህገወጥ መንገድ ወደ ትዳር እንዲገቡ  እንደሚደረግ የአለም ባንክ እና ሴቭ ዘ ችልድረን ባወጡት አዲስ የጥናት ውጤት አስታወቁ፡፡ ተቋማቱ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረጉት በዚህ አለማቀፍ የጥናት ውጤት መሰረት፤ በመላው ዓለም በየዓመቱ 7.5 ሚሊዮን ያህል ልጃገረዶች  በተመሳሳይ መልኩ በህገወጥ መንገድ ወደ ትዳር እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡አገራት ልጃገረዶች ወደ ትዳር መግባት የሚችሉበትን የዕድሜ ገደብ ቢያስቀምጡም፣ በአንጻሩ በበርካታ አገራት ህጉ ተግባራዊ ሳይደረግ ልጃገረዶቹ በለጋ እድሜያቸው ወደ ትዳር እንዲገቡ እንደሚገደዱ በ112 የአለማችን አገራት ላይ የተሰራው ይሄው ጥናት አመልክቷል፡፡
ልጃገረዶች ያለዕድሜያቸው ወደ ትዳር እንዲገቡ ከሚደረጉባቸው አካባቢዎች መካከል ቀዳሚነቱን የሚይዙት የምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ናቸው ያለው ዘገባው፤ በማደግ ላይ ከሚገኙ አገራት ሶስት ልጃገረዶች አንዷ ከ18 አመት በታች ወደ ትዳር እንድትገባ ትደረጋለች ብሏል። በተለያዩ የአለማችን አገራት 100 ሚሊዮን ያህል ልጃገረዶች ያለእድሜያቸው እንዳይዳሩ የሚከለክል ህግ እንዳልተቀመጠላቸው በጥናቱ መረጋገጡንም ዘገባው አመልክቷል፡፡በተያያዘ ዜናም፣ ከአምስት አመታት በፊት ሲዩዳድ ጁአሬዝ በተባለው የሜክሲኮ ገጠራማ አካባቢ 11 ወጣት ሴቶችን በአደንዛዥ እጽ በማደንዘዝ
ወደ ወሲብ ንግድ ካስገባ በኋላ በጭካኔ ገድሏል የተባለው ሜክሲኳዊ፣ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት ቀርቦ፣ በ430 አመታት እስር መቀጣቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ የሴቶቹን አስከሬን በሸለቆ ውስጥ ጥሎት መገኘቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ጥቃቱን ያደረሰባቸው ሴቶች እስከ 15
አመት እድሜ ያላቸው እንደነበሩም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3999 times