Saturday, 14 October 2017 15:42

“ቱሪዝምን ለማስፋፋት ትልቅ የሀብት ማፈላለግ ስራ መሰራት አለበት”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

• በቀበሌና በወረዳ ያሉ መስህቦችን ጎብኝቼ እጨርሳለሁ ማለት ዘበት ነው
                        • ቱሪዝምን ከባህል ነጥሎ ማየት በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይሆናል
                        • በክልሉ ገና ብዙ ያልተጎበኙ ዋሻዎች፣ ፏፏቴዎችና ሀይቆች አሉ
                                 ዶ/ር ሂሩት ካሳው (የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ)

    በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ - ፅሁፍ ተመርቀዋል፡፡ በዚህ ሳይገደቡ ትምህርታቸውን የገፉት የዛሬዋ እንግዳችን፤ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (MA) የአማርኛ ቋንቋን የማስተማር ዘዴ በሚል ዘርፍ ከአገኙ በኋላ በ1998 ዓ.ም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን በመቀላቀል፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሁፍ አማርኛ ትምህርት ክፍል መስራት ጀመሩ፡፡ ከዚህ በፊት ግን በኦሮሚያ ክልል የአማርኛ መምህር ሆነው ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች አስተምረዋል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን (PhD) ለመስራት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት እንግዳችን፤ “ተግባራዊ ስነ- ልሳን በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማስተማር” (Applied Lingusitcs) ተመርቀው ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመመለስ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም መስርተው ለሁለት ዓመታት ሰርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እሳቸው “የአገር ጥሪ ነው” ወደሚሉት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት በሹመት የመጡት -
ዶ/ር ሂሩት ካሣው፡፡ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ደግሞ እርሳቸው በተሾሙበት ወቅት ለክልሉ ብቻም ሳይሆን ለመላ አገሪቱ በተለይም እሳቸው ለተሾሙበት ዘርፍ ፈታኝ የሆነው አለመረጋጋት የተከሰተበት ወቅት ነው፡፡ በዚያ ላይ ለስራው አዲስ ነበሩ፡፡ ያንን ፈታኝ ወቅት እንዴት አለፉት? በዘርፉ ላይ የተጋረጠውን ፈተና እንዲሁም የአካባቢውን ገፅታ ለመመለስ ምን እንቅስቃሴዎች ተደረጉ? የዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀን እንዴት ተከበረ? የክልሉን የቱሪስት መስህቦች ይበልጥ ለማስተዋወቅ ምን ታስቧል? እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊን ዶ/ር ሂሩት ካሣውን በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡

      ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንዴት ወደ ክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት  መጡ?
እኔ ይህንን የአገር ጥሪ ነው ብዬ ነው የተቀበልኩት። አንድን ሰው አገሩ ይሆነኛል፣ ያገለግለኛል ብላ ስትጠራው፣ በሙያው አቅሙ በቻለ መጠን ማገልገል አለበት፡፡ እኔም ይህን ስለማምን ጥሪውን ተቀበልኩት እንጂ ቀደም ብሎ፣ በዚህ ቦታ ላይ ተሹሜ እሰራለሁ የሚል እቅድ አልነበረኝም፡፡ በህልሜም በእውኔም አስቤውም አላውቅም፡፡ እንዳልኩሽ የአገር ጥሪ ነው፤ ጥሪውን ተቀብዬ ማገልገል ጀመርኩ፡፡ ወደ ቢሮው ኃላፊነት የመጣሁት፣ በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም ነው፤ አሁን ዘጠኝ ወሬ ነው ማለት ነው፡፡   
ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የተማሩት ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሁፍ ጋር በጣም የተዛመደ ነው፡፡ የተማሩበት ዘርፍና የተሰጥዎ  ሃላፊነት ይጣጣማሉ?
እንዳልሺው ሁሉም የትምህርት ዝግጅቴ በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ - ፅሁፍ ጋር ይገናኛል፡፡ ነገር ግን ሦስተኛ ዲግሪዬ (አፕላይድ ሊንጉስቲክስ) በጣም ሰፋ ያለ ነው፡፡ በቋንቋ ላይ የሚመጣ ተፅዕኖና ቋንቋ በማህበረሰቡ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ላይ የሚያተኩር ስለሆነ፣ ቋንቋን ማህበረሰብን ስታጠኚ በዚያውም የማህበረሰቡን ባህልና ማንነት አብረሽ ታጠኚያለሽ። እንደውም ከቋንቋና ከባህልም ያልፋል፡፡ ሦስተኛ ዲግሪዬ የሚዳስሰው የባህል መገለጫ ስንል፣ አልባሳትንና ከላይ የሚታዩ ጌጣጌጦችን ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ የአስተሳሰብን ውጤት ሳይቀር ይመረምራል፡፡ የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ውጤቶች በቋንቋ ላይ ተፅዕኖ ሲያደርጉ ወይም ቋንቋ በተቃራኒው ያለውን ተፅዕኖ የሚዳስስ ስለሆነ እስከ ማስተማር ይደርሳል፡፡ ትምህርቱ በዚህ መልኩ እገዛ አለው፡፡ ነገር ግን ባህልና ቱሪዝም ከመምጣቴ በፊት ትኩረት የማልሰጣቸው ነገሮች ግን ትኩረት ማድረግ የሚገቡኝን ነገሮች እንዳስተውል አድርጎኛል። ቱሪዝም የሚለውን ነገር በአግባቡ ለማወቅና ለመረዳት ወሳኙ ነገር ባህልን ማወቅ ነው። ቱሪዝምን ከባህል ነጥሎ ማየት በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይሆናል፡፡ ስለ ባህል ትልቅ ግንዛቤ የሌለው ሰው፤ የቱሪዝም ሀብቶችን ማወቅና መለየት አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ሦስተኛ ዲግሪዬ፣ አሁን ለተሾምኩበት ስራ ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል፡፡
እርስዎ የሚመሩት ቢሮ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ የቱሪስት መስህቦቹ ብዛትና ስፋት ግዙፍ ነው፡፡ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ቅርሶች አብዛኞቹ ያሉትም በዚህ ክልል ይመስለኛል፡፡ ይህንን ግዙፍ የክልል ቢሮ መምራት አይከብድም?
በክልሉ ያለውን እያንዳንዱን የቱሪዝም ሀብት ማወቅ በጣም ከባድ ነው፡፡ እኔ በፊት የሚመስለኝ ኃላፊው ቢሮ ተቀምጦ፣ በስሩ ያሉት ኃላፊዎች ሄደው፣ መረጃውን አምጥተውለት፣የሚነግሩትን የሚያስተባብር ዓይነት ነበር፡፡ በፍፁም እንደዚያ አይደለም!! ለማስተባበርም መጀመሪያ የክልሉን ሀብት ዞረሽ ማየት፣ መገንዘብ፣ ሁኔታዎችን ማጤን ያስፈልግሻል፤ ይሄ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ቢሮ ቁጭ ብለሽ ልትሰሪው የምታስቢውና ሄደሽ በአካል የምትመለከቺው ነገር እጅግ በጣም ይለያያል፡፡ ሲነገርሽ ትንሽ የሚመስል፣ በአካል ስታገኚው ትልቅ ሀብት መሆኑን ታስተውያለሽ፡፡
ከዚህ አንፃር እርስዎ ምን ያህሉን የክልሉን የቱሪዝም መስህቦች ተዘዋውረው ተመልክተዋል?
ሁሉንም አይቻለሁ ማለት ይከብዳል፡፡ እንደ ብዙሃኑ አስተሳሰብ፤ ሰው የቱሪስት መስህብ ሲባል ፋሲል ግንብ፣ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ሶፉመርና ሌሎች በዩኔስኮ ተመዝግበው እውቅና ያገኙ መስህቦች ይመስላቸዋል፤ ግን አይደለም፡፡ በተለይ በአማራ ክልል በየመንደሩ በየወረዳው እጅግ አስደናቂ የሆኑ፣ በርካታና ለቁጥር የሚያታክቱ መስህቦች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ቀበሌና ወረዳ፣ በየመንደሩ ያሉ መስህቦችን ጎብኝቼ እጨርሳለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡
አሁን ለምሳሌ በአዊ ብሄረሰብ ዞን ብቻ የሚገኙትን እንደ ፏንግ ፏፏቴ፣ የደንና አስካስታ ዋሻዎች፣ ደንዶር ፏፏቴ፣ ጥርባ ሃይቅ---የሚባሉትን ማየት ቀርቶ ስማቸውንም ሰምተን አናውቅም። አንቺም የነዚህን ፏፏቴዎች፣ ሀይቆችና ዋሻዎች ታሪክ ስትሰሚና በአካል ተገኝተሸ ስትመለከቺ፣ ኢትዮጵያን እንደማታውቂያት ይገባሻል፡፡ ስለዚህ እየተዘዋወርኩ እጎበኛለሁ ግን ሁሉንም ለማዳረስ ጊዜም አይበቃም፤ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሁሉንም ጎብኝቻለሁ ማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም በየዞኑ አይደለም፣ በየመንደሩ ያለውን ሀብት እየሄዱ መጎብኘት ከባድ ነው፡፡ ለዚህ እንደ መፍትሄ የተቀመጠው፣ እስከ ወረዳ ድረስ የተዘረጋው መዋቅር ነው፡፡ እነዚህ በየወረዳው ያሉ የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ በየመንደሩና በየጥጋጥጉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶቻቸውን ባህላዊ፣ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊውን በሶፍት ኮፒ እንዲያቀርቡ እናደርጋለን፡፡ በዚህ አማካኝነት ነው ለማወቅ የምንሞክረው፡፡ በአንድ ወረዳ አዊ እንኳን ከ12 በላይ ፏፏቴዎችና ዋሻዎችን ነው የተመለከትነው። ከየወረዳዎች የሚመጡልንን መስህቦች እናይና፣ የትኛው ቅድሚያ ተሰጥቶት ይተዋወቅ፣ የትኛው ይከተል የሚለውን ለመወሰን ቦታው ድረስ እንሄዳለን፡፡  
ዘንድሮ በክልሉ ለ25ኛ ጊዜ፣ “ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት” በሚል ከመስከረም 23 እስከ 29 በተከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን፣ በዓሉን ለማክበሪያና ለጉብኝት ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ አዊ ብሔረሰብ ዞንና ሰሜን ጎንደር ዞን  የተመረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
የዘንድሮውን የዓለም የቱሪዝም ቀን በዋናነት ያልታዩና ያልተጎበኙ የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን በማስተዋወቅ ማክበር ላይ ነው ትኩረት ያደረግነው። ሁለተኛው ዓላማ፣ በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ጋዜጠኞች በአካል ቦታው ላይ ተገኝተው እንዲያረጋግጡ ማድረግ ነው፡፡ በመጎብኘት ረገድ ምዕራብ ጎጃም ዞንና አዊ ማህበረሰብ ዞን ተመርጠው፣ ያላቸው የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ ሆነዋል፡፡ ያው አንቺም እንዳየሽው፣ አስደናቂ ፏፏቴዎች፣ ትልልቅ ርዝመት ያላቸው ዋሻዎች፣ የሰባት ቤት አገው የፈረስ ትርኢት ተጎብኝተዋል፡፡
 የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋሽራ የባህል ቡድን፣ የተለያዩ ዋሻዎችን የደጃች ሀይለየሱስ ፍላቴ (አባ ሻወል) ሀውልት ታይተዋል፡፡ እነዚህ ላይ በደንብ መስራትና ሀብት ማግኘት ስለሚያስፈልግ ማለት ነው፡፡ ሌላው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ ሊማሊሞና “የንግስት ማረፊያ” የተባለው ታሪካዊ ቦታና በወገራ ወረዳ ኮሶዬ የተባለ አካባቢ ያለው የቱሪስት መስህብ ተጎብኝተዋል። ይህ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ከሰላም አለመኖር ጋር በተያያዘ አሁንም ብዙ ይወራል፤ ግን አካባቢው መቶ በመቶ ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ ነው፡፡ ይህንን እናንተ እንድታዩና እንድትታዘቡ ለማድረግ ነው አላማው፡፡
ግን እኮ በቅርቡም አሜሪካ ኤምባሲ በአካባቢው መረጋጋትና ሰላም እንደሌለ በመግለፅ፣ ዜጎቹ ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ ክልከላ አውጥቷል፡፡ ይሄ እንዴት ነው?
ያው እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት አለመረጋጋት እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ይህ አለመረጋጋት ቱሪዝሙን መጉዳቱም የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጥረቶች አካባቢው አሁን ሰላም ነው፤ እናንተም ቦታው ላይ ተገኝታችሁ ያጋጠማችሁ ችግር የለም፡፡ የበፊቱን ያህል ባይሆንም አሁንም የቱሪስት የጉብኝትም ሆነ የስራ ጉዞ ክልከላ ሚዛናዊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም የአሜሪካ ኤምባሲ ሰዎች፣ በየቀኑ እየመጡ እዚህ ከተማ ላይ፣ በክልሉ ሌሎች ከተሞችም ስራ ሰርተው፣ ስብሰባ ተሰብስበው በሰላም ይመለሳሉ፡፡ እኔና አንቺ አሁን እየተነጋገርን ባለንበት ወቅት እንኳን (ማክሰኞ ምሽት ነው ቃለ ምልልሱ የተደረገው) የአሜሪካ አምባሳደር ነገ ጠዋት እዚህ ባህርዳር ለስራ ይመጣሉ፡፡ ሰላም ከሌለ ለምን ይመጣሉ? እሳቸው ከመጡስ ሌሎች ዜጎቻቸውን ለምን ይከለክላሉ? ይሄ ለኔም የሚገርመኝ ጥያቄ ነው፡፡
በአዊ ብሄረሰብ ዞን ያሉ ሁለት ቦታዎችን ይበልጥ ለማስተዋወቅና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ፕሮጀክት መቀረፁን ቀደም ብለው ነግረውኝ ነበር። ሁለቱ መስህቦች እነማን ናቸው? የተቀረፀው ፕሮጀክትስ ምን ይመስላል?
በዚህ ዓመት ሁለቱ ፕሮጀክት የተቀረፀላቸው መስህቦች፣ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበርና ዘንገና ሀይቅ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር፣ 78 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ፣ ከ48 ሺህ በላይ አባላት ያሉት በመሆኑ፣ ይህ የፈረስ ትርኢት በአገራችን ብሎም በአፍሪካ አለ ወይ የሚለውን መለየት ነው፡፡ ማህበሩ ከፈረስ ትርኢት ባለፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያልተነገረው ታሪክም አለውና፡፡ አንድም በፈረስ ማህበሩ ላይ ጥናት ማድረግ፣ ሁለትም ከዞን ትርኢትነት አልፎ አገር አቀፍ ፌስቲቫል ማድረግ ሲሆን በዚህ ዓመት ጥር 23 ብዙ ቱሪስቶች የሚገኙበት በርካታ የየክልል ባህል ቱሪዝም ሀላፊዎች በሚገኙበት በሰፊው የፈረስ ፌቲቫሉን ማካሄድ ነው፡፡ ለዚህም ከቢአርሲ ባጀት አስጎብኚ ድርጅት ጋር የስምምነት ፊርማ ሲካሄድ እናንተም ተመልክታችኋል፡፡ ዘንገና ሃይቅም ባለፈው ሀሙስ የፈረስ ትርኢቱ ከእንጅባራ ተነስቶ ፍፃሜውን ያደረገው ዘንገና ሀይቅ ላይ ነው፡፡ ሀይቁም ማራኪና ቀልብን የሚስብ ሆኖ ሳለ በአካባቢ ጎብኚዎች አረፍ ብለው ሻይ ቡና የሚሉበት ምንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ ዘንድሮ በአካባቢው ይህን አገልግሎት የሚሰጡ መሰረት ልማቶች እንዲስፋፉ ይደረጋል፡፡ እርግጥ ቀደም ሲል ሎጆችን በሀይቁ ዙሪያ እንዲሰሩ ለባለሀብቶች ቦታ ተሰጥቷቸዋል ግን አንዳንዶቹ ጀምረው ትተውታል፤ሌሎቹ ቦታውን ወስደው ግንባታም አልጀመሩም፡፡  
ለምን ይሆን ባለሃብቶቹ  መገንባት ያልፈለጉት?
እንግዲህ መሬት ወስዶ አጥሮ ረጅም ጊዜ ማቆየት እዚህ አገር እንደ ባህል ተቆጥሯል፤ ስለዚህ እርምጃ ወስዶ ለሌላ ባለሀብት ቦታውን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የዞን አስተዳደሪውም ቦታውን በአስቸኳይ የማያለሙ ከሆነ ለሌሎች ባለሀብቶች እንደሚሰጡት ሲያስጠነቀቅ አብረን ሰምተናል። ግንባታውን የጀመሩት ደግሞ ለምን እንዳቆሙ ሲጠየቁ፣ አንዳንድ የዲዛይን ለውጥ ስለሚያስፈልግ፣ ያንን አስተካክለን ወደ ስራ እንገባለን የሚል ምክንያት እንዳቀረቡ ሰምቻለሁ። በዕለቱም ከዞኑ አስተዳዳሪ ጋር እንደተነጋገርነው፣ እነዚህ ሎጆች በዚህ ዓመት ያልቃሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከተተገበሩ የፈረስ ፌስቲቫሉም ዘንገና ሀይቅም የቱሪስት መስህብነታቸው ወደተሻለ ደረጃ ያድጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ጥር 23 የሚካሄደው የፈረስ ፌስቲቫል፣ እቅድ ሰፋ ያለ ነው፡፡ ጥር 23 አዊ ላይ ይካሄድና፣ ጥር 25 ደቡብ ጎንደር የራሳቸው የፈረስ ፌስቲቫል አላቸው፡፡ እዚያ ተከብሮ ፍፃሜው ሁለቱም ተቀላቅለው ፌስቲቫሉን ባህርዳር ላይ በማሳየት ይጠናቀቃል፡፡
ዘንገና ላይ ሎጅ የሚገነቡትን ባለሀብቶች በተመለከተ ከነሱ ጋር ውይይት በማድረግ፣ ጥቅሙን በማስረዳት፣ ለሌሎች ኢንቨስትመንቶች የሚደረገው ማበረታቻና ድጋፍ ተደርጎላቸው፣ እንዲሰሩና እንደ ሌሎቹ ኢንቨስተሮች ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቡትም ካለ እሱ ተፈቅዶላቸው፣ ስራውን እንዲያፋጥኑ አናደርጋለን። በዚህም ላይ ተወያይተናል፡፡ አካባቢው የሚያስፈልገውን መሰረት ልማት፡- ውሃ መፀደጃና ሌሎችንም ነገሮች ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የተጀመረ ስለሆነ ይሰራል የሚል ጠንካራ እምነት አለን፡፡ ይሄ ይሄ ሲደረግ በአካባቢው ያሉ ዋሻዎች፣ ፏፏቴዎችና ሀይቆች አብረው የመጎብኘት እድልና የመታወቅ አጋጣሚ ስለሚኖራቸው ጠቀሜታቸው ብዙ ነው። በሌላ በኩል በ2010 በየአካባቢው አንድ አንድ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት እቅድ ተይዟል፡፡ እቅዱ ግን የመንግስት በጀት ላይ የተጣለ አይደለም። ባለሀብቶችንና የአካባቢውን ሰው በማሳመንና በማስረዳት፣ ህዝቡ ያለማዋል ተብሎ የተያዘ እቅድ ነው፡፡
ከአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶችና ከማህበረሰቡ ባለፈ በቱሪዝም መስፋፋት ላይ የሚሰሩ የውጭ አገር ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ግንኙነቶችን በመመስረት፣ ሃብት በማፈላለግና የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስፋፋት በኩል ክልሉ ምን ያህል ሰርቷል?
በዚህ በኩልም በግሌ ብዙ ተሰርቷል ብዬ አላምንም፡፡ እርግጥ ለዋና ዋና መዳረሻዎች በአብዛኛው ለምሳሌ ለፋሲል ግንብ፣ ለላሊበላ፣ ለጠና ባዮስፌርና ለመሳሰሉት በዩኔስኮም ስለተመዘገቡና የዓለም ሀብቶች ስለሆኑ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለአዳዲሶቹ ብዙ ስላልሰራን አላገኘንም፡፡ እንዳልሺው ቱሪዝምን ለማስፋፋት ትልቅ የሀብት ማፈላለግ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ሀብት ማፈላለጉ ከውጭም ከውስጥም መሆን አለበት፤ የሚጠብቀን ትልቅ የቤት ስራም ይሄው ነው፡፡
እርስዎ በተሾሙበት ወቅት እንዳጋጣሚ ሆኖ በአገሪቱ ላይ ሰላምና መረጋጋት የጠፋበት አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፡፡ ከሴትነት፣ ለስራው አዲስ ከመሆንና ከወቅቱ ሁኔታ  አንፃር ፈተናውን እንዴት ተወጡት?
እርግጥ ነው ወቅቱ ፈታኝ ነበር፡፡ ያስደነግጥም ነበር፡፡ የተፈጠረው አለመረጋጋት በክልል ተወስኖ የቀረ ሳይሆን አገራዊ ችግር ነበር ማለት ይቻላል። ዞሮ ዞሮ እንዳልሺው ሴትም ብሆን፣ ለስራው እንግዳም ብሆን ከአጋሮቼ ጋር ሆኜ ችግሩን ለመቋቋም፣ ሴትነቴም ለስራው አዲስ መሆኔም አላገደኝም። እርግጥ ነው ችግሩ ቱሪዝሙን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ኢኮኖሚውንም ሁሉንም ያዛባል፡፡ ችግሩ እኛ የምንሰራው ዘርፍ ላይ የሚበረታ ቢሆንም። ዞሮ ዞሮ እኔ በግሌ የማመጣው ነገር ባይኖርም ሌላው ቀርቶ ችግሩ በአንድ ቢሮ ላይ የሚጣል ጉዳይም አልነበረም፡፡ ከክልሉ መንግስት ጀምሮ እስከ ነዋሪው ድረስ መሰራት አለበት፡፡ የሰላም ጉዳይ በመሆኑ የሰላሙም መልሶ መስፈን የእነዚህ ሁሉ ውጤት ነው፡፡ እኔም እንደ ቢሮም እንደ ግሌም ችግሩ ሲከሰት ማድረግ የምችለውን የአቅሜን የማድረግ ግዴታ አለብኝ፡፡ ስለዚህ ከሁሉም ጋር ተባብሬ የበኩሌን በማድረግ ችግሩን መቋቋም ችለናል፡፡ ችግሩ እኔ የምመራውን ቢሮ ለይቶ ችግር ላይ የሚጥል ስላልሆነ ማለቴ ነው፡፡
እዚህ ከተማ ላይ አንዳንድ ባለ ሆቴሎችን ተዘዋውረን እንዳነጋገርነው፣ በክልሉ አለመረጋጋት ከተከሰተ በኋላ በስራቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን የእርስዎ ቢሮም ሆነ የክልሉ የሆቴሎች ማህበር መስራት ያለበትን ያህል ባለመስራቱ አካባቢው ከተፅዕኖው እንዳልተላቀቀ ገልጸልናል፡፡ ይሄ ምን ያህል እውነት ነው? የተከሰተው ችግር ሙሉ በሙሉ መጥፋቱንና አካባቢው ሰላም መሆኑን ለማስተዋወቅ ቢሮው ምን ምን ስራዎችን ሰርቷል?
ብዙ ባይሆንም ቢሮው የሚችለውን ያህል ሙከራ አድርጓል፡፡ አካባቢው ፍፁም ሰላም መሆኑን የሚያመላክቱ የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርገናል። ለምሳሌ ከዚህ ክልልና ከተማ ውጭ ሆኖ ለሚያስብ ሰው፣ በከተማዋ የተለያዩ ጉባኤዎችና ትልልቅ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ ቢባል ለማመን ይቸግራል። ሰው ከሌላ አካባቢ መጥቶ ስብሰባ የሚካሄድ፣ የተለያዩ ፌስቲቫሎች፣ ባዛሮችና ጉብኝቶች የሚካሄዱ አይመስለውም ግን ተካሄደዋል እየተካሄዱም ነው፡፡ የባህልና የሙዚቃ ፌስቲቫሎች ይካሄዳሉ፡፡
ተካሂደዋል ከተባሉት ጉብኝቶች፣ ጉባኤዎች እና ፌስቲቫሎች በምሳሌነት የሚጠቅሷቸው ካሉ ቢነግሩኝ?
እኛ እንግዲህ ባህርዳር ብቻ ሳይሆን ጎንደርም ውስጥ ትልልቅ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ አድርገናል በተለይ ከፌዴራል አካባቢ የሚደረጉትን በነዚህ ከተሞች እንዲካሄዱ አድርገናል በኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል የሚካሄዱት ከሚኒስትር እስከ ቢሮ ያሉ የቱሪዝም ስብሰባዎች ጎንደርና ባህርዳር እንዲከርሙ በማድረግ ሰላም መስፈኑን እንዲያረጋግጡ አድርገናል፡፡ ከዚ ውጭ ጥምቀትን ለማክበር ከጥምቀት ጋር የተያያዙ ስራዎች የሚሰሩ ማህበረሰቦችን በማወያያት ጥምቀት በድምቀት እንዲከበር አድርገናል እንዲህ እያለ ጎንደር ላይ ሌላውም ቀጠለ ማለት ነው፡፡
ባህርዳር ላይም የተለያዩ ትልልቅ ስብሰባዎችን አካሂደናል፡፡ ከዚያ እኛ የክልሉን የባህል ፌስቲቫል ለአንድ ሳምንት በድምቀት አካሂደናል ይሄ ሰላም መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ የሚገርምሽ በዚህ ፌስቲቫል መዝጊያ ላይ ትልልቅ ደራሲያን ሀያሲዎች ገጣሚዎችና ጋዜጠኞችን የያዘ የጉብኝት ቡድን ሙሉ አለም አዳራሽ ተገኝቶ መዝጊያውን አድምቆት ነበር፡፡ አንደኛ ደራሲያን ማህበር ከደብረ ማርቆስ ጀምሮ በባህርዳር ጣናን በማቋረጥ እስከ ጎንደር ጉብኝት ሲያደርግ አካባቢው ሰላም መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ እንደነገርሺኝ ከደራሲያን ማህበር ጋር አንቺም ነበርሽ፡፡ የሆቴል ማህበሩ ከቢሮው ጋር በመሆን የክልሉን ገፅታ ለመመለስ ብዙ እየሰራ ነው እንደውም ባዛሮችን ስናዘጋጅ ሌሎች ዝግጅቶችን ስንሰራና የገንዘብ እጥረት ሲገጥመን ሆቴል ማህበሩ ስፖንሰር እየሆነን አመቱን ሙሉ ከእኛ ጋር ሲለፉ ስለነበር እንቅስቃሴ አላደረገም የሚለው ላይ አልስማማም፡፡ ሌላው ቀርቶ በባህል ፌስቲቫሉ ሰው አይገባባቸውም ሲባል በመዝጊያው አዳራሹ ሞልቶ ሰው ቆሞ ሁሉ ዝግጅቱን ሲከታተል ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም መግቢያ የምግብ አውደርዕይ ኤግዚቢሽን ለአምስት ቀን ተካሄደ በነገራችን ላይ ይህንን ኤግዚቢሽን በዋናነት ያዘጋጀው የሆቴል ማህበሩ ከዘንባባ መልቲ ሚዲያ ጋር በመተባበር ነበር በድምቀት ነው የተጠናቀቀው፡፡ በርካታ የአዲስ አበባ ነጋዴዎችም ተሳትፈውበታል ይህንን ሰርተናል ሆኖም አሁንም የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅብን አምናለሁ፡፡ በባዛሩ ላይ በላይነህ ክንዴ የተባሉ የሰከላ ወረዳ ተወላጅ ትልቅ ድጋፍ አድርገውልናል፡፡
ምንም እንኳን ሰላም ቢሰፍንም ቱሪስት ፍሰቱ እየተሻሸለ ቢመጣም ክልሉ ከተፅዕኖ እንዳልወጣ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልፅ ለማድረግ እንደ ጀርመን ፈረንሳይና መሰል የቱሪስት አመንጪ አገራት ኤምባሲዎች ጋር ቀርባችሁ በግልጽ የመነጋገር ጉዳይ ላይ ምን የተሰራ ነገር አለ?
በዚህ ጉዳይ ላይ አምናም የፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአሜሪካና ከጀመርን ኤምባሲዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተደረገ ውይይት አለ እኛም ወደ ክልላችን የሚመጡ ቱሪስቶች የሚታወቁ ስለሆነ ከነዚህ ኤምባሲዎች ጋር ደብዳቤ በመፃፍም ሆነ በአካል በመቅረብ ሰላም መሆኑን በማስረዳት አብረን እንድሰራ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ አሁን መሻሻል አለ፡፡
በመጨረሻ ቀሪ የሚሉት ካለ?
ጥሩ ቆይታ አድርገናል ክልላችን ሰላም ነው መጥታችሁ ጎብኙ ስራ ስሩ እላለሁ፡፡ አለመረጋጋት በነበረበት ወቅት እንኳን እንድም ቱሪስት ላይ የደረሰ አደጋ የለም፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ሰላም ነው ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ክልሉ ያለውን ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ጎብኙ እላለሁ አመሰግናሁ፡፡

Read 2498 times