Saturday, 14 October 2017 15:32

በልጅሽ ሞትን ድል ታደርጊያለሽ!!

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(3 votes)

 ልጅ መውለድ በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ አስደናቂ ነገሮች መካከል ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ልጅ መፍጠርን ቴክኖሎጂ ከመፍጠር ጋር ብናነፃፅረው እንኳ በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ከተፈጠሩትና ወደፊትም ከሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች ሁሉ እጅግ አስደናቂውና ውስብስቡ ነው፡፡ የልጅ መውለድን ተዓምራዊ ስሜት በፅሁፍ ከማንበብ ይልቅ በዜማ መስማት ይመረጣል፡፡ ልክ አርቲስት ብፅዓት ስዩም “ልጄን አደራ!!” እያለች ልብን በሚነካ ዜማ እንዳዜመችው፡፡ ሆኖም ግን፣ ንግግር ከፅሁፍ፣ ዜማም ከንግግር ይበልጥ ገላጭና ስሜት ቀስቃሽ ነውና ስለ ልጅ የሚቀነቀን ዜማ፣ ግጥሙ አጥንት የሚሰረስር፣ ዜማውም ከባድ ትካዜ ላይ የሚጥል መሆን አለበት፡፡ በዚህ መጣጥፍ ውስጥ ይሄንን ጥልቅ ስሜት በፅሁፍ ለመግለፅ እሞክራለሁ፡፡
የልጅን ፍቅር ፈልገን የምናመጣው አይደለም፤ ሳናቀው እላያችን ላይ የተጫነ ተፈጥሯዊ ኃላፊነት እንጂ፡፡ ሁሉም ሰው በልጅ ፍቅር እንዲያር፣ ለትውልድ እንዲሰዋ የተፈጥሮ ባሪያ ሆኗል፡፡ እኛ በፍቅር የልጆቻችን ባሪያ ነን፡፡ የባሪያ የሥራ ድርሻ ምንድን ነው? መታዘዝ አይደል!!? መታዘዝ ብቻ!! የልጅ ባሪያ መሆን ግን በፍቅር መታዘዝ ነው፤ በፍቅር ባሪያ መሆንም ሐሴት ነው! ልምላሜ ነው፡፡
ተፈጥሮ እኛን ምክንያት አድርጋ በእኛ በኩል ልጆቻችን ይመጣሉና፣ እኛ በፍቅር የልጆቻችን ባሪያ ነን፡፡ የልጆቻችን ባሪያ የሆነው እኛ ስለወለድናቸው ብቻ አይደለም፤ ይልቅስ የየዋህነታቸው ብዛት ጭምር እንጂ፡፡ እንዴት ዓይነት የዋህነት ነው! ዓለም ምን እንደምትመስል አያውቋትም፣ ሆኖም ግን የእኛን ዓለም እንድናስተዋውቃቸው ከእኛ ይወለዳሉ፡፡ እንዴት መኖር እንዳለባቸው አያውቁም፣ ሆኖም ግን እንደኛ ሊኖሩ ከእኛ ይወለዳሉ፡፡ ብቸኝነቱ፣ መሰልቸቱ፣ ተስፋ መቁረጡ፣ ድህነቱ፣ የኑሮ ውጣ ውረዱ አስመርሮን ሳለ ከየዋህነታቸው የተነሳ ግን የእኛን ኑሮ ሊኖሩ ከእኛ ይወለዳሉ፤ ከእኛ ጋር ሊቸገሩ፣ ከእኛ ጋር ሊሰደዱ ከእኛ ይወለዳሉ፤ የእኛን ሸክም እነሱም ሊሸከሙ ከእኛ ይወለዳሉ፡፡
ራስ ወዳድነታችን ባህሪያችንን ሞልቶት ሳለ፣ ጥላቻችንም ዓይናችንን አቅልቶት ሳለ፣ ከራስ ወዳድነታችን የተረፈ ርህራሄ ካለ ብለው፣ ከጥላቻችንም የቀረ እንጥፍጣፊ ፍቅር ካለ ብለው እኛን አምነው ከእኛ ይወለዳሉ፡፡ ሰውነታቸው በጣም ስስ ነው፤ ለበሽታም በቀላሉ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በበረዳቸው ሰዓት እኛን ሊለብሱ፣ ሲታመሙም ሐኪማቸው እንድንሆን ከእኛ ይወለዳሉ፡፡ የዋህነታቸው አይሰፈርም፤ እኛ ላይ ያላቸው እምነት ጥልቅ ነው፡፡ ለእኛ ያላቸው ፍፁም ፍቅርና እምነት አንጀታችን ድረስ ገብቶ ያስለቅሰናል፡፡
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የልጅ መውለድ ሌሎች አስገራሚ ነገሮችም አሉት፡፡ ልጅ ስንወልድ ሦስት ነገሮቻችንም አብረው ይወለዳሉ፡፡ የልጅ መውለድ አንድም የእናትነት ባህሪሽ መወለድ ነው፤ ሌላም የዳግም አንቺነትሽ መወለድ ሲሆን ሲያሰቃዩሽ የነበሩ ፍላጎቶችሽም አብረው ይወለዳሉ፡፡ ስሜቱ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡
ኦሾ ‹‹ልጅ ሲወለድ፣ የሴቷ የእናትነት ባህሪና የወንዱም የአባትነት ባህሪ አብሮ ይወለዳል›› ይላል። በሴትና በእናትነት ባህሪ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ በወንድና በአባትነት ባህሪ መካከልም እንዲሁ፡፡ ሰዎች ልጅ ሲወልዱ፣ ለልጁ እድገት አስፈላጊ የሆኑ ባህሪያትን እንደ አዲስ ተላብሰው እንደገና እንደ አዲስ ይፈጠራሉ፡፡ እናትነትና አባትነት የፍቅር፣ የርህራሄ፣ የደስታና የተስፋ ሙላት ነው፡፡ እነዚህ ባህሪዎች ደግሞ ለህፃናት እድገት ብቻ ሳይሆን ቤተሰብንም እንደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብንም እንደ ማህበረሰብ ይዘውት የቆሙ ምሰሶዎች ናቸውና እጅግ ያስፈልጉናል፡፡
ማንኛውም ቤተሰብና ማህበረሰብ የአብሮነት ህልውናው በእነዚህ ባህሪዎች ላይ የተመሰረተ ነውና ሐብቶቻችንና እሴቶቻችን ናቸው፡፡ ልጅ በመውለድ ወላጆች ላይ የሚፈጠሩት እነዚህ አዳዲስ ባህሪያት የማህበረሰቡ እሴቶች ናቸው። ስለዚህ ልጆች የማህበረሰቡ እሴቶች መገኛና መጠበቂያ መንገዶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ማህበረሰብ ከመልካም እሴቶቹ ጋር መቀጠል ከፈለገ ሴትነት ወደ እናትነት፣ ወንድነትም ወደ አባትነት የሚሸጋገርበትን ባህል ጠብቆ መኖር አለበት፡፡ ግብረሰዶማዊነት ለማህበረሰቡ አደገኛ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡
ሴትነት ወደ እናትነት፣ ወንድነትም ወደ አባትነት የሚሸጋገርበትን ባህል እያጣን በሄድን ቁጥር በእናቶችና በአባቶች መሞላት የሚገባው ማህበረሰባዊ ፍላጎት ክፍት ይሆናል፡፡ በዚህ ክፍተት ውስጥም ሴሰኛነት፣ ወንጀለኛነት፣ ብኩንነት፣ የሥነምግባር ብልሹነት ይነግሳል፡፡ ማህበረሰባችንንም ይዘውት የቆሙ እሴቶቻችን መደርመስ ይጀመራሉ፤ ሥነ ምግባርም ትርጉሙን ያጣል፡፡ ልጅ መውለድ ከመፃዒ ኢኮኖሚ ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም፤ ለማህበራዊ እሴት ግንባታ ያለው አስተዋፅዖም መታየት አለበት፡፡ንረሰዶማዊነት
ሌላው የልጅ መውለድ አስገራሚ የሚያደርገው ነገር፣ የልጅ መወለድ የዳግም አንቺነትሽ መወለድ መሆኑ ነው፡፡ ልጅ ስትወልድ እንደገና ተወልዶ የሚያድገው አንተው ራስህ ነህ፤ በወንድ ልጅህ ወንድ፣ በሴት ልጅህ ደግሞ ሴት ሆነህ ተወልደህ ታድጋለህ፡፡ ሴት ብትሆን ምን ዓይነት ሰው እንደምትሆን ራስህን በሴት ልጅህ ውስጥ ታየዋለህ። አንቺም እንደዚያው፤ ወንድ ብትሆኚ ኖሮ ምን ዓይነት ወንድ እንደምትሆኝ በወንድ ልጅሽ ውስጥ ራስሽን ታይዋለሽ፡፡ እናም ራስሽን በወንድ መልክ ስታይው፣ አንተም ራስህን በሴት መልክ ስታየው ትገረማላችሁ፤ እውነትም ተፈጥሮ ድንቅ ነች ትላላችሁ፡፡
ስለ ልጅ መውለድ ተፈጥሯዊ ክስተት ሲታሰብ በጣም አስገራሚው ነገር የሀገራችን ሰዎች ሲወልዱ፣ ክስተቱን የሚገልፁበት አገላለፅ ነው - “አይኔን በአይኔ አየሁት!!” እጅግ ድንቅ የሆነ አገላለፅ ነው፤ ተፈጥሯዊ ስሜቱን በደንብ ማንፀባረቅ የሚችል ፍልስፍናዊ አገላለፅ ነው፡፡ ማህበረሰባችን እንደዚህ ዓይነቱ የነጠረ አገላለፅ ላይ እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡
ትክክል ነው! ልጅ ስትወልጅ የምታይው ራስሽን ነው፡፡ ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ በአንድ ወቅት በፍቅር ያበድሽለት ጎረምሳም አብሮሽ መወለዱ ነው፡፡ ክንድሽ ላይ በታቀፍሽው ህፃን ውስጥ ራስሽን ትፈልጊያልሽ፤ አባቱም እንዲሁ በልጁ ውስጥ ራሱን ይፈልጋል፡፡ አይኑ ውስጥ ራስሽን ስታይ እንባ ቅር ይልሻል፤ አንተም በልጅህ እርግጫ ውስጥ የድሮ ጀግንነትህን ትፈልጋለህ፤ ምኞትህን ሁሉ ለልጅህ ትሰጣለህ፡፡ በልጅህ እንደገና በዓለም ላይ የመኖር ዕድል ተሰጥቶሃልና ምን ዓይነት ሰው ሆነህ መኖር እንደምትፈልግ ያለህን ምኞት ሁሉ ለልጅህ ሰጥተህ የልጅህን ስኬት ትጠባበቃለህ። በልጅህ ዕድገት ውስጥ ሁሉ አንተም አብረህ በቅለህ ታድጋለህ፤ በስኬቱ ውስጥም አንተም አብረህ ትናኛለህ፡፡
ልጃችሁ የውህደታችሁና የሙሉነታችሁ ማህተም ነው፡፡ ልጅሽ የዘር፣ የባህሪና የምኞትሽ ካዝና ነው፤ የአንቺነትሽ ግልባጭ ነው፡፡ እናም ትገረሚያለሽ!! የልጅሽ ለቅሶ የአንቺ ለቅሶ ነውና ልብሽ ድረስ ይነዝርሻል፡፡ የልጅሽ ህፃን መሆን የአንቺ ህፃንነት ነው፡፡ ልጅሽ ሲያድግ የአንቺን እድገት በውስጡ ታይዋለሽ፡፡ የልጅሽ መወለድ የእናትነትሽና የዳግም አንቺነትሽ መወለድ ብስራት ነውና አጥብተሽና አቅፈሽ የምታሳድጊው ራስሽን ነው፡፡  ህፃኑ በልብሽ ውስጥ ፍቅርን ይሞላዋል፤ አንገቱ ሥር ያለው ጠረን፣ ኮልታፋነቱ፣ እርግጫው፣ መዳሁ፣ አስተያየቱ፣ አረማመዱ … ሁሉ ደስ ይልሻል። ተፈጥሮ በአንቺ በኩል ህፃኑን ወደዚህ ዓለም አምጥታዋለችና የተረከብሽው አደራ እንቅልፍ ይነሳሻል፡፡ ምንም የተለየ ቁሳዊ ሐብት ሳይጨመርልሽ ልጅ በመውለድሽ ብቻ ደስተኛ ትሆኛለሽ፤ ሕይወት ትጣፍጥሻለች፤ ለልጅሽ ዘላለም ነዋሪ ብትሆኝ ደስ ይልሻል፡፡ ረጅምና የማያንቀላፋ፣ ራሱንም የሚያድስ ደስታ፣ ዳግም ሕይወትን በተስፋ የሚሞላ ክስተት ነው ልጅ መውለድ፤ ተፈጥሮ ለትዕዛዟ በመገዛታችን የምትሰጠን ሽልማት ነው፡፡
ሴት ልጅ በመውለድ የምታገኘውን የደስታ ጣሪያ ግን ወንዱ አያገኝም፡፡ “በዚህ ረገድ ወንዱ የበታች ነው” ይላል ኦሾ፡፡
ወንዱ እናት መሆን ባለመቻሉ ልጅ ከመውለድ ጋር የሚስተካከል ደስታን ለማግኘት የማይፈነቅለው ዲንጋይ የለም፡፡ ለዚህም ነው ወንዱ በይበልጥ በፈጠራ ሙያ ላይ የተሰማራው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ አስደናቂ ፈጠራዎች ሁሉ የወንዱ የሆኑት ለዚህ ነው።
ልጅ በመውለድ ወንዱና ሴቷ የሚያገኙት ደስታ የተስተካከለ ባይሆንም ሁለቱም ግን የልጆቻቸው ተቀዳሚ አገልጋዮች ናቸው፡፡
ባጠቃላይ ሁለመናችንን ለትውልድ እንድንሰዋ የትውልድ ባሪያዎች ሆነናል፤ አለበለዚያ የተፈጥሮ መረጣ አንጓሎ ያስቀረናል፡፡ ተፈጥሮ የምትፈልገው ከተጓዳኛችን ጋር በፍቅር እየተወቀጥን በልጆቻችን እንደገና እንደ አዲስ እየተወለድን፣ እንደ አዲስ እያደግን እንድንኖር ነው፡፡ ያለበለዚያ ሞታችን ትንሳኤ ተነፍጎት እኛው ላይ ማብቃቱ ነው። በልጃችን ግን ሞትን ድል እናደርጋለን፤ ልክ ፕሌቶ እንዳለው “በልጆቻችን ውስጥ የምናፈቅረው ህያውነታችንን ነው!!”
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሐፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 2703 times