Tuesday, 17 October 2017 10:26

የአእምሮ ጤና፣ ሥራ እና ጥበብ

Written by  ዶ/ር ዳዊት አሰፋ (የኢትዮጵያ የአእምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት)
Rate this item
(10 votes)

 የአለም የአእምሮ ጤና ቀን፣ ዘንድሮ ለ25ኛ ጊዜ ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 30 ቀን ተከብሮ ውሏል፡፡ መሪ ቃሉም፡- “Mental Health in the Work place” (የአእምሮ ጤና በስራ ቦታ ላይ) የሚል ነበር፡፡ በአለማችን የተለያዩ አገሮች ይህ ቀን ሲከበር በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም መልዕክቶቻቸውን በብዙኃን መገናኛዎች እና በማህበራዊ ድረገፆቻቸው አማካኝነት አስተላልፈዋል፡፡  ተለይ ግን የአለምን ቀልብ የሳበው በእንግሊዝ የልዑላን ቤተሰቦች የሆኑት ፕሪንስ ሃሪ፣ ፕሪንስ ዊልያም እና ባለቤቱ የካምብሪጇ ልዕልት ኬት ሚድልተን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፣ በጋራ የሶስትዮሽ ዘመቻ ጉዟቸውን፣ በአእምሮ ጤና እና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ የሚያደርጉ መሆኑን በይፋ ማሳወቃቸው ነበር፡፡  በእኛም አገር ዕለቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የፓናል ውይይት በማካሄድ እንዲሁም በአማኑኤል ሆስፒታል እና ብሬማን ፊልም ፕሮዳክሽን ትብብር የተዘጋጀ በአአምሮ ጤና ዙሪያ የሚያጠነጥን አዲስ ነጠላ ዜማን በማስተዋወቅ ተከብሮ ውሏል፡፡
እኔም በዚሁ መድረክ ላይ አንዱ ተሳታፊ የነበርኩ በመሆኑ፣ በዚህ ፅሁፌ የዕለቱን የውሎ መንፈስ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ በመጀመሪያ ግን በመሪ ቃሉ ላይ የተጠቀሰውን የአእምሮ ጤና እና ሥራን ግንኙነት እንዲሁም በአለም ዙሪያ ያሉ የጥበብ ሰዎች፣ የአእምሮ ጤና ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ እያደረጉት ያለውን ጥረት እንመልከት፡፡
የአእምሮ ጤና እና ሥራን ምን አገናኛቸው?
የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው አዳም፤ “ጥረህ ግረህ ብላ” ተብሎ በፈጣሪ ከተፈረደበት ወዲህ ሥራ የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታው፤ ከራሱ ላይ የማይወርድ ዕዳው ሆኖ እንደኖሩ መንፈሳዊው /ሀይማኖታዊ አስተምህሮ ይነግረናል፡፡ የሰውን ልጅ ህይወት የሚመራመሩ አሳቢያንም፣ በየወቅቱ ስለ ሰው ልጅና ሥራ ግንኙነት ብዙ ብለዋል፡፡ በኋላም ላይ በዘመነ ሶሻሊዝም፤ “ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው” እስከሚል ድምዳሜ ተደርሷል፡፡
እውነትም በቅጡ ካሰብነው የሥራ ህይወታችን፣ የአዋቂነት ዘመናችንን አብዛኛውን ጊዜ ይሸፍናል። መደበኛ በሆነ የሥራ መስክ ተቀጥሮ ወይንም ራሱን ቀጥሮ የሚሰራ ሰው፣ በአማካይ በቀን ስምንት ሰዓት ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ እንግዲህ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎችን ሳይጨምር ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሰዎች መደበኛ ከሆነው የሥራ ጊዜያቸው በተጨማሪ በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸው የተለያዩ ተግባራት አሉ፡፡ ስለዚህ ሥራና የሰው ህይወት የማይነጣጠሉ መሆናቸው ብዙ ማብራሪያ አይፈልግም፡፡ እናም ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የዘንድሮው የአለም የአእምሮ ጤና ቀን መሪ ቃል፣“የአእምሮ ጤና በስራ ቦታ ላይ” የሚል ሆኗል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት፤ በአእምሮ ጤና ችግር ምክንያት አለማችን፣ በየዓመቱ እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚሆን ኪሳራ ይደርስባታል፡፡ ይህ ኪሳራ የሚመጣው ሰዎች በተለይም በድብርትና ጭንቀት ምክንያት በስራቸው ላይ የሚያስመዘግቡት ውጤት (ምርታማነት) ስለሚቀንስ ነው፡፡ መግለጫውም ከስራ መቅረት (Absenteeism) ወይም በስራ ላይም ሆኖ ውጤታማ ያለመሆን (Presenteeism) ሊሆን ይችላል፡፡
ይህንን ያህል ኪሳራ እያደረሰብን ያለውን የጤና ጠንቅ ምን ያህል ትኩረት ሰጥተነዋል ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ መስሪያ ቤቶቻችንስ የአእምሮ ደህንነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ሰላማዊ የስራ ሁኔታን (work enviroment) ለመፍጠር ምን ያህል ችለዋል? በእኔ እምነት የእነዚህን ጥያቄዎች ምላሽ የምናገኘው በተለያየ እርከን ላይ ያለውን የአመራር ዘይቤያችን በመመርመር ነው፡፡
የሥራ ኃላፊዎች፣ በሥራቸው ያሉ ሰራተኞች ከሥራ ሲቀሩ ወይንም ውጤታማ ለመሆን ሲቸገሩ፣ የሰራተኞቻቸውን ችግር መርምሮ በመረዳት ለመደገፍ ከመሞከር ይልቅ በምን አይነት መንገድ ቀጥቼ፣ አስተካክለዋለሁ ወደሚለው አቅጣጫ የሚያዘነብሉ ከሆነ፣ ፍትጊያና መጓተት የበዛበት፣ ለአእምሮ መታወክ የሚዳርግ ተቋማዊ ባህልን እያሰረፁ ነው፡፡ የተነገረውን ሁሉ ከላይ ወደ ታችና ከታች ወደ ላይ እንደ በቀቀን እያስተጋቡና ነገር እያመላለሱ ለመምራት የሚሞክሩ ሃላፊዎችም፣ የተቋምን ማህበረሰብ ሠላም የሚነሳ ባህልን ያነግሳሉ፡፡
በአንፃሩ ማዘር ቴሬዛ “Work without love is slavery” (ሥራ ያለ ፍቅር ባርነት ነው) እንዳሉት፣ ሥራና ሰራተኛ በፍቅር እንዲገናኝ የሚያደርግ ባህልን ለማስረፅ የሚታትር መሪ፣ የሠዎችን መልካም ሰብዕና ያንፃል፣ ተቋምን ያሳድጋል፣ አገርንም ያበለፅጋል፡፡ መሪ ሲባል ግን የተለያዩ ጥቂት ሰዎችን ብቻ የሚመለከት አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም ቢያንስ አንድ ሌላ ሰው ላይ በጎ ተፅዕኖ ማሳረፍ የምንችል መሪዎች ነን፡፡ መልካምነታችንና ፍቅራችን፣ ለሌሎች የመንፈስ ሰላምን የሚሰጥ እርሾ እንዲሆን፣ በውስጣችን ያለው በጎ መንፈስ ኮትኩተን እናሳድገው፡፡
ዶ/ር ፍራንክል “Man’s Search for Meaning” በሚለው ተወዳጅ መፅሐፉ እንዳተተው፤ ማንኛውም ሰው በሚያጋጥመው ክስተትና በሚሰጠው ምላሽ መካከል ያለውን ክፍተት የሚሞላው ራሱ ነው- በምርጫዎቹና በውሳኔዎቹ። ስለዚህ መሆን የምንችለውን ለመሆን፣ ምርጫው የኛው ነው ማለት ነው፡፡
የአእምሮ ጤና በጥበብ መንገድ ላይ
የጥበብ ምንጩ ስሜትና ሀሳብ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እናም በርካታ የአለማችን ጠቢባን፣ የአእምሮን ክቡርነት ተገቢውን ቦታ ሰጥተውት፣ የአእምሮ ጤና ቀንን በየራሳቸው መንገድ ዘክረውታል፡፡ በአሜሪካ ታዋቂ አርቲስቶች፣ በትዊተር ገፆቻችሁ ላይ ቀኑን ምክንያት በማድረግ መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በህንድ ታዋቂዋና ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑት የቦሊውድ ተዋንያን መካከል አንዷ የሆነችው ደፒካ ፓዱኮን፤ በዕለቱ የአእምሮ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው የጤና ተቋማትን ጎብኝታለች፡፡ ደፒካ ከዚህ ቀደም እሷም የድብርት ህመም ተጠቂ መሆኗን በይፋ መግለጧ የሚታወቅ ሲሆን በአእምሮ ህመም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችንም ትሰራለች፡፡  
ከአእምሮ ጤና ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን 20 የደቡብ ኮሪያ ሙዚቃዎች፣ በዚህ ዕለት በድረ ገፁ ላይ ይዞ የመጣው ደግሞ ቢልቦርድ ነው። እንደ ቢልቦርድ ገለፃ፤ እነዚህን ሙዚቃዎች የሰሯቸው ድምፃውያን፣ በሙዚቃዎቻቸው የራሳቸውን የአእምሮ ህመም፣ ትግልና ውጣ ውረድ ገልፀውበታል፡፡ በአንፃሩ “ዘ ቴሌግራም”፤የአእምሮ ጤና ችግራቸውን በይፋ የገለፁ፣ 19 ታዋቂ እንስቶችን ዝርዝር ይዞ ቀርቧል፡፡
በአገራችን “የአእምሮ ጤና ቀን”
እንዴት ተከበረ?
በዚህ ፅሁፍ መነሻ ላይ እንደገለጽኩት፣ በእኛም አገር ዕለቱ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማካሄድ ተከብሮ ውሏል፡፡ የመጀመሪያው ዝግጅት በአንጋፋው የአገራችን ሳይካትሪስት ዶ/ር መስፍን አርአያ የተመራ የፓናል ውይይት ነበር፡፡ በውይይቱም የአዕምሮ ጤና ጉዳይ በሁሉም አካል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ተገልጧል፡፡ በተጨማሪም በሥራ ቦታ ላይ ለአእምሮ ደህንነት ችግር የሚፈጥሩ አሉታዊ ሁኔታዎች ተዳስሰዋል፡፡
ከዚህ ውይይት በኋላ የቀረበው የጥበብ ሥራ ደግሞ የታዳሚውን ቀልብ ሙሉ በሙሉ የገዛ ነበር፡፡ በአማኑኤል ሆስፒታል እና በብሬማን ፊልም ፕሮዳክሽን ትብብር የተዘጋጀው ነጠላ ዜማ፣ በአዳራሹ ሲለቀቅ፣ በርካታ ሰዎች በሙዚቃው ስሜታቸው ተይዞ፣ እንባ ያረገዙ አይኖቻቸውን እያሻሹ፣ በጥሞና ያዳምጡ ነበር፡፡ በዚህ የሙዚቃ ስራ ላይ የአገራችን አንጋፋ ባለሙያዎች ጥበብ ነጥሮ ወጥቷል፡፡ ፀሀዬ ዮሀንስ፣ ታደለ በቀለ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ሞገስ ተካ፣ ይልማ ገብረአብ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ እና ወጣት የኳየር አቀንቃኞች የተሳተፉበት ድንቅ ስራ ነው፡፡ እነኝህ ባለሙያዎች በእለቱ የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ስራቸው ለህዝብ ይፋ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የህዝቡ ምላሽ፣ ትልቁ ሽልማታቸው ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መሠል የጥበብ ስራዎችም ተሰርተው፣ ለአእምሮ ህሙማን ተስፋን የሚፈነጥቅ ጊዜ እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡
ለዛሬ ግን የአእምሮ ጤና ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ የአውግቸው ተረፈን “እብዱ” የሚለውን መፅሐፍ እያነበባችሁ፣ የአእምሮ ህሙማንን የህይወት ፈተና፣ በህሊናችሁ እንድትቃኙ ጋብዣችኋለሁ፡፡
አውግቸው በመፅሐፉ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ይለናል፡- “ህልም ማየት ስጀምር ነብይ የሆንኩ መሠለኝ…”

Read 6739 times