Tuesday, 17 October 2017 10:30

“መንገደኛ”ን መጽሐፍ እኔ እንዳየሁት

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

  የዛሬው ርዕየ-ነገሬ አንድ በቅርቡ የወጣ አዲስ መጽሃፍ ነው። መጽሐፉ “የእኛ ሰው በአሜሪካ”ን አስታወሰኝ። ባለኮሮጆው ወዳጄ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ የጻፈው “መንገደኛ” የሚለው መጽሃፍ ነው። ኮሮጆው የመንገደኛ ምልክት ይሆን እንዴ? ሳትሉ አትቀሩም። በአንድ አንፃር ነው ብል ከዕውነት አልርቅም።
ይህ መጽሐፍ ባለ 360 ገፅ ሕይወት-አዘል የሥነጽሁፍ ሥራ ነው። በአራት ትላልቅ ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን፣ ከልዩ ባህሪዎቹ አንዱ በግርጌ ማስታወሻ ዝርዝር መታገዙና ያም ጥናት-ጠገብ መሆኑ ነው።
መጽሐፉ የታሪኩን ፍሰት ከመዋቅረ-ነገሩ ጋር በወጉ ያሰናሰለ በመሆኑ፣ የመጽሐፉን ቡጥ አውጥቶ፣ ዐይኑንና ሰበኸቱን ለይቶ፣ መንጠብ ለአንባቢ አይቸግርም!
መጽሐፉ የገጸ ባህርያቱን ታሪክ ተንተርሶ የተቀነበበ በመሆኑ መውጪያ መግቢያው አስጎምጂ ነው። ዕሙናዊ ገጠመኞቹ ገሃድነትን ከፈጠራ ያዋሃዱ ናቸው። ይህን መጽሐፍ የጀመረው ሳይጨርስ አያርፍም። የስደት ዓይነቶች ተተንትነውበታል። የስደት አሰቃቂም፣ አስደሳችም መልክዐ-ምድር ተጢኖበታል። አያሌ ባለቀለም ትርክቶች አሉት። መጽሃፉ ግዘፍ-ነስቶ የመንፈስ ከፍታን ቀስ በቀስ ያላብሰናል።
የመንገደኞቹን መስከንተሪያ ነጥብ ስናይ የገዛ ቀዬአችን፣ ጎረቤታችን፣ ቤታችን ፍንትው ብሎ ከመታየቱም በላይ የስደት ባለጉዳዮች የሆኑት ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከነጥረት-ግረታቸው፣ ከነምኞታቸው፣ ከነሥቃያቸው፣ ከነጓዝ-ጉዝጓዛቸው ምሉዕ ስዕላቸው ይመጣብናል!
የአበሾች የዋህነትና ቅድስና፣ ምቀኝነትና መሰሪነት፣ እርግማንና ተንኮል ከስደተኞቹ ጋር እንደ ጥቁር ጥላ ተከትሏቸው መሄዱ፤ በዚያም ውስጥ ማንነታቸው መገለጡ፤ ገመናቸው ግልጥልጥ ብሎ መፍጠጡ፤ በምናባዊ አፃፃፉ ውስጥ ተውጠንጥኗል! የመጽሐፉ ጅምላ መልክ በስደት መነፅር ውስጥ ሲታይ፤
“መሄድ መሄድ አለኝ ጎዳና ጎዳና
አልግደረደርም ዘንድሮስ እንዳምና” ብሎ በወኔና በፉከራ ቅጥ ጀምሮ፤
“ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ
ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ” ሆኖ ማብቃቱን እናስተውላለን።
ይህ በአብዛኛው ስንታዘብ የኖርነው የስደት ህይወት ጠባይ ነው! ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች፣ በተለይም ከሆሳዕና ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚፈስሰው የሰው ኃይል ያሳዝናል፣ ያስፀፅታል። ተሳክቶ እሰየው የሚያሰኘውና የሚያስደስተው እንደ እናት ጡት ውል የሚል የማሸነፍ ስሜት ነው! የሽንፈቱና የውድቀቱ ፈሊጥ እጅግ ሲለመድ፥ “ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል” ያሰኛል።  
መጽሐፉ መልከ-ብዙ ነው! ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ ባህልን እና ሌላውን ዘርፋ-ዘርፍ ሁሉ ማቀፉ በየትኛውም የዕድገት መልክ ለቆመና በየትም የዕድሜ ክልል ላለ አንባቢ ማለትም፥ ወጣት፣ አዛውንት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወዘተ ሁሉ ገፆቹ ክፍት ናቸው! ራሳችንን የማንበብ ያህል ቅርብ ሆኖ ነው የምናገኘው!
ከውበቶቹ አንዱ ቀላልነቱ ነው! ጥበባዊ ውስብስብነቱ ሌላው ቁንጅናው ነው! መፅሐፉ በአፃፃፍ ዘዴው ከሁለት መሰረታዊ ነገሮች የተቀነበበ ነው። ከሁለት ቅርንጫፎች የተዋሃደ በመሆኑ ምሉዕነቱ ያጠግባል። ከእነዚህም አንዱ በየቤታችን ለኢኮኖሚ ችግራችን ሁሉ መፍቻ ስደትን ዋና መፍትሄ አድርገን መቁጠራችን ሲሆን፤ ሁለተኛው በጥናት የተደገፈ መረጃ በብዕር ወግ ተቀምሞ መከሸኑ ነው!
ስደትን እንደ መፍትሔ ለመውሰዳችን በ“ሸጌ በዶላር” ስር የተቀመጠው የቢንያም ታሪክ አንድ መስታወት ነው፤ «…‘ሸጌ በዶላር’ ከደቡብ አፍሪቃ በሚላክላቸው ብር የአቡዬን ፅዋ ማውጣትና የማርያምን ንግስ መደገስ እንዲሁም ሌሎች አጋጣሚዎችን እየጠበቁ በሰበብ አስባቡ ድግስ አበዙ። የመንደሩ ሰውም በድግስ ግብዣው ላይ እየታደመ የሚበላና የሚጠጣው ሳያንሰው “ተማርን” የምንለውንና ሌሎች በመንደሩ የቀሩ “አልሄድ ባይ” ወጣቶችን በቁማችን መዘልዘሉን ተያያዘው፡፡ ስደተኞች በመንደራችን ሰዎች ፊት ክብርና ሞገስን ተላበሱ፡፡ በተቃራኒው አልሄድ ባዮች ተዋረድን፤ ተነቅረን ተተፋን። መንደርተኛው “እነሱማ ጀግኖች ናቸው፡፡ ሰው ሀገር ሆነው ለቤተሰቦቻቸው ይሄን ሁሉ አደረጉ” ተባለ፡፡ “ሸጌን ልጇ ካሳት” ተባለ። ተወራ! ተነገረ! ጊዜ ጌታ ነገሮችን ቀለበሰ፡፡ ድሮ ድሮ እንደነ ቢንያም አጥኑ እየተባሉ ይገረፉና “ተማር ልጄ” ይዘፈንላቸው የነበሩት እነ በረከት ዛሬ ላይ ለእኛ አርአያ ሆነው ቁጭ አሉ፡፡ በተራችን እንደነ በረከት “ሰው ሆናችሁ ሰው አድርጉን” የሚል የሰው ፊትና ምላስ አኮርባጅ ሆኖ ይዠልጠን ጀመር፡፡»
በመንገድ ላይ
ከኢትዮጵያ ተነስተው ደቡብ አፍሪቃ ከሚገቡት ውስጥ ስኬታማ የሚባሉት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። አብዛኞቹ የመከራው ሰለባዎች ናቸው - የሞቱም ጭምር! መሄጃውም ጎዳና ቀጥ ያለ አይደለም። ‘ከዚህ ተነስቼ እዚህ እደርሳለሁ’ የሚባል ሳይሆን እዚህ አገር እሄድና፣ እዛ ቪዛ ካገኘሁ እዚያኛው አገር እገባና፤ ከዚያ በእግር ማቅጠን ነው! ቅርብ ናት። መንገድ መሪው ቅርብ ያለው ድንበር ዘንድ እስኪያደርስ፣ በየቦታው ይታደራል፣ ይዋላል፣ ገንዘብ ይራቆታል።
አንዴ እግር ከአፈር ከተነቀለ ውጤት እስኪገኝ መከራው ሁሉ ይቻላል። የቆረጠ ሞት አይፈራም ሆኖ ነው እንጂ ሥቃዩስ የሥቃያት ጥግ ነው! እነሆ አስረጅ፥ «…አስቸጋሪዎቹን የኬንያና የታንዛኒያ ኬላዎች ውኃ ላይ ሆነው ካቋረጡ በኋላ ወደ ሞዛምቢክ፣ ማላዊ ወይም ዛምቢያ በመሻገር ጉዟቸውን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመቀጠል ወጥነው አንድ መቶ ሃያ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ በኩል አድርገው በአንድ ግዙፍ ኬንያዊ ካፒቴንነት ጀልባ ላይ ይሳፈራሉ። ጀልባዋ ጠባብ ስለሆነች ቦታ ሽሚያ ነው። ያገኘ ይሄዳል፣ ያጣ ይቀራል። “ራስን ማዳን” የሚለው ነገር የሚጀምረው ይሄኔ ነው። በዚህ ሁኔታ የቀናቸው ጀልባዋን ተሳፍረው ወቅያኖሱን እየቀዘፉ እያለ ከየት መጣ ሳይባል አንድ ሻርክ ጀልባዋን ባፍጢሟ ሊደፋት ግብግብ ገጠመ። ግዙፉ ኬንያዊ ካፒቴን ያለምንም መደንገጥ “ለዚህ ሻርክ አንድ ሰው መገበር አለብኝ” ካለ በኋላ ልክ ድንጋይ አንስቶ እንደሚወረውር ሁሉ ጀልባዋ ጫፍ ላይ ተቀምጦ የነበረን ትኩስ ኢትዮጵያዊ ወጣት አንስቶ ወደ ውኃው ወረወረው! በካፒቴኑ ላይ ይታይ የነበረው ሁኔታ የሰውን ልጅ ለአውሬ የሰጠ ሳይሆን ቁራጭ ዳቦ ለተራበች ድመት የጣለ ነበር የሚመስለው!»
መንገድ ላይ አውሬዎችን መፍራት ራሱን የቻለ ዓለም ነው! የሥቃይና የሲቃ ዕጣ-ፈንታ! በመፅሐፉ ምዕራፍ ሁለት የተቀመጠው የኢዛና ታሪክ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፥ «…ከወደቅኩበት ተነስቼ ወደፊት ላመራ ስል የ“ወደፊት” አቅጣጫ ራሱ ጠፋኝና ሌላ ፍርሀት ሰቅዞ ያዘኝ፡፡ በሩቁ የአራዊት ድምፅ ይሰማኛል፡፡ አንበሶች ያገሳሉ፡፡ ጅቦች ያሽካካሉ። ከመሬት ሆድ ውስጥና ከዛፎች ላይ የሚወጡ የተለያዩ የእንስሳት ድምጾች ጆሮዬ ላይ ያንቃጭላሉ። ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ እሰማው የነበረ አሰቃቂ ታሪክ በእኔም ላይ ሊደርስብኝ እንደሚችል ገመትኩ፡፡ በዱር አራዊት የተበሉና በድንገተኛ ጎርፍ የተወሰዱ በርካታ ስደተኞች፤ ታሪክ ኬንያም ሆነ ሌላ ሀገር በነበርኩበት ወቅት በወሬ መልክ ሰምቼ ነበር፡፡ በጭንቅላቴ ውስጥ እነዚህን ታሪኮች እያሰላሰልኩ ከአሁን አሁን እኔም የዚህ ክፉ እጣ-ፈንታ ገፈት ቀማሽ ሆንኩ በሚል ጭንቀት ተሞልቼ “ጄምስ”፣ “ጄምስ፣ “ጄምስ” እያልኩ እየተጣራሁ እግሬ ወዳመራኝ መሄድ ጀመርኩ፡፡ ግን መልስ የለም። ውሳኔዬን ቀልብሼ “ወደ ኋላ” ተመልሼ እጄን ለፖሊሶቹ እንዳልሰጥ፣ የቻልኩትን ያህል ሮጫለሁ። በዚያ ላይ አቅጣጫው ጠፍቶኛል፡፡ “ወደኋላስ” ወዴት ነው?...»
አስገራሚ የስደት ገጠመኞች፣ የመፅሐፉ ጨውና ቅመም ናቸው። የሚከተለው አስረጂ ነው፥ «…መጥፎ አጋጣሚ ሆነና እኛ የተሻገርን ዕለት በዋናው ሰውዬ የሚመራ ግብረ ኃይል የቁጥጥር ሥራውን አጧጡፎት ነበር፡፡ ሁላችንም ተያዝንና “ፓስፖርታችንን” ተቀማን፡፡ የድንበር ፖሊሶች ኃላፊው፤ ፓስፖርታችንን ይዞ አንድ በአንድ ስማችንን እየጠራ ከኛ መልክ ጋር ያመሳስላል። ስማችንን እንኳን ሸምድደን ለመያዝና ርስበርስ ለመጠናናት የነበረን ጊዜ አጭር ስለነበር ብዙዎቻችን በደንብ አናውቀውም፡፡ ኃላፊው ገና አንድ ሁለት ስም እንደጠራ የውሸት ፓስፖርት እንደሆነ አውቆታል፡፡ ከጎኑ የነበሩ ረዳቶቹም ፎቶውንና እኛን እያመሳሰሉ እንደመገረምም ግራ እንደመጋባትም አድርጓቸዋል፡፡ ስማችን ሲጠራ ሰነፍ ተማሪ ይመስል እርስበእርስ እየተያየንና “አንተን ነው እኔን?” በሚል እየተጠቃቀስን እንደምንም አንዳችን እንመልሳለን። ሰውዬው ነገሩ ከገባው ቆይቷል ግን የመገረም፣ የመኮሳተር እና የመናደድ ድብልቅልቅ ስሜት ፊቱ ላይ እየታየ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ ልክ የፍቅሩን ስም ጠርቶ ፎቶውን ከፍቅሩ መልክ ጋር ሲያመሳስለው ግን ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም። ከትከት ብሎ ከልቡ ሳቀ፡፡ አብረውት ያሉትም ተከትለው ሳቁ፡፡ እኛም አጀብናቸውና ቤቱ በሳቅ ተሞላ!»
የ“መንገደኛ” አንዱ ባህሪው ሰው ሰው የሚሸት መሆኑ ነው። መሬት ላይ ያለ ዕውነት መሆኑ ነው። አፍሪካዊ እውነታ መሆኑ ነው። ስለሆነም ዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ያነብበው ዘንድ ወደ ሌላ ቋንቋ ቢተረጎም ሁለንተናዊነትን ይላበሳል እላለሁ። ስደትም ዓለም አቀፍ ከሆነ በጣም ሰንብቷልና! በዚያ ላይ ምዕራቡ ዓለም የአማርኛን ውበት ከይዘት ነገረ-ሥራ ያጣጥምበታል!
የትርጉም እሴቱ ሥራውን ከቤት ወደ ጎረቤት ብሎም ወደ መላው ዓለም ማጓጓዝ ነው። በዚህም ህይወት፣ ፅንሰ ሃሳብና አመለካከት ይንሸራሸራል። አዕምሮ ከአዕምሮ ይናበባል። ይተርጎምና የአማርኛ ጉዱም ይታይ! እላለሁ። በራሱ ባህላዊ የወፍ ጎጆ ውስጥ የሚኖረው አማርኛ ልዩ ጠባያቱን፣ ቅኔያቱን፣ ርዕዮቱን ዓለም ይጋራ ዘንድ ማመቻቸት ሁነኛ ነገር ነው። የማያውቀው ዓለም ይወቀው! ከቋንቋዊ ፋይዳው እስከ ሰዋሰዋዊ መላ-ጨመቁ (essence) ድረስ ዓለም ዐይን ያልገባ ነውና እነሆ በ“መንገደኛ” በኩል መንገድ ይጀምር!
እያንዳንዱ ንዑስ ምዕራፍ ከታወቁ ኢትዮጵያዊ ገጣሚያን የተቆነፀሉ ስንኞችን ይዞ ይነሳል። ይህም ድርሰቱን ከጧቱ ፀሐያማና ጠሊቅ ያደርገዋል። የስደት ቡጡ በፀሃፍት ብዕር ውስጥ በስሎ እንዲታይ ቅኔው ልዩ አቅም ያደረጅለታል። የጠረቃ ዕውቀት ግጥም ውስጥ መታመቁንና በወፍ ዜማ የተጌጠ ስለመሆኑ ለኢትዮጵያውያን አንባቢያን አይነግሩም! ለምዕራባውያን ግን ግድ ነው! ዞሮ ዞሮ የግጥም ወዝ ያለበት ነገር ነብስን ማብሰክሰኩ ለማንም አንባቢ ግልፅና አበጀ የሚያሰኝ ነው።

Read 2657 times