Tuesday, 17 October 2017 10:28

ከዶሮና ከእንቁላል ማንኛው ይቀድማል?!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 አጭር ቁመት ባለው መስታወት ሙሉ ቁመናዋን ማየት ፈልጋ ስታማርር የሰማሁዋት አንዲት ሴት፣ ሀሳብ ቀሰቀሰችብኝ፡፡ የተማረረችው አጭሩ መስታወት ሙሉ ተክለ ቁመናዋን አካትቶ ሊያሳያት ባለመቻሉ ነው፡፡ በመሰረቱ “ማሳየት”፣ “መተርጎም” እና “ማንፀባረቅ” የሚሉ ቃላቶች ላይ ነው ጉዳዩ ያለው፡፡
ሴቲቱን አጥሮ ያማረረውን መስታወት፣ እንደ “አጭር ልብ ወለድ” ልናየው እንችላለን፡፡ ግን፤ በአጭሩ መስታወት ውስጥ የተንፀባረቀችው ሴት፤ በተጨባጭ አካል፣ አለም ላይ ያለችው ሴት ናት? መስታወቱ ጠፍጣፋ መስታወት ነው፡፡ ክቧ ሴትዮ፣ እንዴት በጠፍጣፋው ዝርግ መስታወት ላይ ተቀመጠች? ወይንም ተተረጎመች? …
ምትሀት ካልሆነ በስተቀር ይህ በተጨባጭ ሊከናወን አይችልም፡፡ ጥያቄው የመስታወቱ ማጠር ወይንም መስፋት ላይ አይደለም፡፡ መስታወቱ ሊያንፀባርቅ እንጂ የእሷን ምትክ መልሶ ሊሰራ አይችልም፡፡ አጭሩን መስታወት “አጭር ልብ ወለድ” ለማለት ከደፈርኩ … ትልቁን ወይንም “ወጡን” ደግሞ “ረጅም ልብ ወለድ” ከማለት ማንም የሚመልሰኝ የለም፡፡
በመስታወቱ ውስጥ የተንፀባረቀችዋ ሴትዮ …ወይንም ከሴትየዋ ጀርባ ያለው አለም ተጨባጩ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላው ምትክ ሊሆን አይችልም። ይሄ ነው እውነቱ፡፡ ግን እንደዚህም ሆኖ ሰው ከሌላ ሰው ስለ ራሱ መልክ ወይንም ገፅታ ከሚቀበለው መረጃ ይልቅ መስታወቱ የሚሰጠውን ያምናል፡፡
መስታወቱ ጥበብ ነው ማለት እንችላለን፡፡ የትኛው ነው ተጨባጭ (Real)? ብለን መጠየቅ ግን የዋህነት ነው፡፡ መስታወቱ የሚሰጠው መረጃ፣ በ“መስታወትኛ” ቋንቋ ከታየ … ለራሱ እንደ ራሱ “Real” ነው፡፡ … መስታወቱ ፊት በአካል የቆመችውን ሴት “Real” (ተጨባጭ) ካልን ግን የመስታወቱ ነፀብራቅ “vertual” ይሆናል፡፡
በጥበብና በተፈጥሮ ወይንም በጥበብና በህይወት መሀል ያለው ግንኙነትም ሆነ ልዩነት በሴትየዋና በመስታወቱ መሀከል ለማሳየት የሞከርኩት ነው፡፡ ሴትየዋ የራሷን አካላዊ ሁኔታ ለማወቅ መስታወቱን ትፈልገዋለች፡፡ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ከመስታወቱ አትርቅም፡፡ … ሰው ስለ ራሱ ለማወቅ፣ ወይም ስለ ራሱ መላልሶ ለመስማት ከጥበብ እንደማይርቀው ማለቴ ነው፡፡
ማን ማንን ተረጎመ? ወይንም ማን ማንን አንፀባረቀ? የሚለው ጥያቄ ራሱ ቀረብ ብለን ከመረመርነው ቀላል የራስ ምታት አይሰጠንም። … መስታወቱ የሴቲቱን ገፅታ አንፀባርቋል፡፡ ግን ሴትየዋ ከመስታወቱ ጎን ገለል ካለች መስታወቱ የሚያንፀባርቀውን ያጣል፤ ባዶ ይሆናል፡፡ መስታወቱ ምን እንዳስመሰላት መልሳ የምትገመግመውም ራሷው ሴትየዋ ናት፡፡ በመስታወቱ ፈጠራ ላይ፤ የእሷ ተሳትፎ ካልታከለበት፣ እሷ ነፀብራቋን መረዳት ካልቻለች፣ ሁለቱ መናበብ አይችሉም፡፡ አሁን የፃፍኩትን አረፍተ ነገር እውነትነት ለማወቅ አንድ አይነ ስውር የሆነ ሰውን መስታወቱ ፊት አቁሞ … ምን እንደሚታየው መጠየቅ ይቻላል፡፡
ፈጠራውን የሚያከናውነው ተፈጣሪው ራሱ ነው፡፡ መስታወቱ ራስን የመፍጠሪያ ሜዳውን ብቻ ነው የሚያበረክተው፡፡ መስታወቱ አይንን አይሰጥህም፡፡ አይንህን ከራስህ፣ አይንህን ተገልግለህ ስለ ራስህ ምዘና ለመስጠት የሚያስችለውን መድረክ ግን መስታወቱ ይለግስሀል፡፡ የጥበብን ትርጉም በአጭር ማስቀመጥ ከተቻለ ይሄ ብቻ ነው፡፡
መድረክ ላይ ቃለ ተውኔት በከያኒው አማካኝነት ሲቀርብ አብረው ተመልካቹ የሚሰማውን ስሜት አያቀርቡም፡፡ የስሜት ህዋሳትና ስሜቱን ሁሉም ታዳሚ ከእየራሱ ጓዳ ይዞ መምጣት ይኖርበታል፡፡ ከያኒያኑ “የመኮርኮርን” ስራ ብቻ ነው የሚሰሩት፡፡ ማንጸባረቅ መኮርኮር ነው፡፡
“The work of art does not provide the current, like the electricity company, but merely the installation; the current has to be genederated by the consumer” ይላል አርተር ኮስለር፡፡ መስታወቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ መስታወቱ ጥበብ ነው፡፡ ብርሀን ከሴትየዋ አካል ላይ ተፈናጥቆ መስታወቱን ይመታዋል፡፡ በብርሃንና ጥላ ምስል፣ ቅርፅ መልሶ ያፈናጥቃል፡፡ የተፈናጠቀውን ምስልና ቅርፅ ግን የሚተረጉመው መስታወት ሳይሆን መስታወቱ ፊት የቆመው ሰውዬ ራሱ ነው፡፡
አርቲስት መስታወት ሰሪ ነው፡፡ ሕይወት ከተጨባጩ አለም ተንፀባርቆ ተመልሶ ወደ ህይወት የሚመለስባቸውን መስተዋቶች ይቀርፃል። ይደርሳል፡፡ ወደ ህይወት ተመልሶ የወጣው ነፀብራቅን የሚተረጉመው ግን ራሱ ተደራሲው ነው፡፡ “A really well made buttonhole is the only link between art and nature” የሚለውን የአስካር ዋይልድን ምክር ወይንም እምነት ችላ የማንለው ያለምክንያት አይደለም፡፡
እንደው በተጨባጭ እንመዝነው ከተባለ በመስታወቱና በሴትየዋ መሀል ምንም ግንኙነት የለም፡፡ ሰው ስለ ራሱ በሌላ ሰዎች ወይንም የሰው ልጆች አማካይነት መረዳት ይገባው ነበረ፡፡ ግን ሰው ስለ ራሱ ከሌሎች ሰዎች ከሚማረው ይልቅ በጥበብ በኩል ሲቀርብለት ልቡን ሰጥቶ ይሰማል። ሰዎችን ከሰዎች፣ ህይወት ከሚያግባባቸው ይልቅ ጥበብ ያግባባቸዋል፡፡ እርስ በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም በጥልቀት ማየት የሚችሉት በጥበቡ በኩል ነው፡፡ ግን ኦስካር ዋይልድ እንዳለው፤ በመስታወትና በሰው መካከል ያለው መመሳሰል ምንም በሆነ ነበር፡፡ “መስታወቱና ሰውን ያቀራረባቸው ጥበብ ብቻ ነው፡፡ ሰው ራሱን መልሶ የሚረዳበት… የሚፈጥርበት አለያም የሚያጠፋበትን መስመር ጥበብ ውስጥ ይመለከታል፡፡ “ሰውየውና ገለፃው ተመሳሳይ ናቸው” ከተባለ ግን የሚያመሳስላቸው ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበች ሽንቁር ብቻ ናት፡፡ እቺ ሽንቁር “ጥበብ” ተብላ ትጠራለች፡፡
የነፀብራቅን ጉዳይ በብዙ መንገድ መስለን አዟዙረን መርመር እንችላለን፡፡ “GENOME” የሚለው አይን ከፋች መፅሐፍ ውስጥ ስለ ዘረ-መል ተፈጥሮም ቢሆን፣ እኔ እያወራሁ ካለሁት ጭብጥ ጋር የሚቀራረብ ነጥብ ተነስቷል፡፡
የመፅሀፉ ደራሲ እንደሚከተለው ይላል፡-  “A protein is just a gene’s way of making another gene, and a gene is just a protein;s way of making another protein. Cooks need recipes, but recipes also need cooks. Life consists of the interplay of two kinds of chemicals፡ Proteins and DNA”
በአጭሩ ሲተረጎም፡- ዘረ-መል ራሱን ለማንፀባረቅ፣ ለመተርጎም… ለመግለጥ ፈልጎ በሚፈጥርበት ጊዜ በድጋሚ ዘረ-መልን ሳይሆን “ፕሮቲን” የተባለውን ንጥረ ነገር ነው። የሚያበረክተው ፕሮቲንም ራሱን ለመፍጠር በሚሞክርበት ጊዜ ዘረ-መልን በመስራት ይጠናቀቃል…እንደ ማለት ገደማ ነው፡፡
ይኼንኑ እይታ ወደ ዶሮና እንቁላል ለውጠን ልንመልሰው እንችላለን፡፡ ዶሮ፤ ሌላ ዶሮን ለመፍጠር የሚሰራው ጥበብ “እንቁላል” ተብሎ ይጠራል … እንደ ማለት ሊቆጠር ይችላል፡፡
ሰው ራሱን ለመግለፅ ሲፈልግ መስታወት ነው የሚሰራው፡፡ የጥበብ መስታወት፡፡ መስታወቱ ከሰው የተገኘ፣ ወደ ሰውም መልሶ የሚያደርስ መንገድ ነው፡፡ ግን ሰው እና መንገዱ .. ወይንም ስዕል እና ሰው …. ወይንም ድርሰት እና ህይወት አንድ ናቸው ወይ? ከተባለ … መልሱ አይደሉም ነው። ፊደል እና ሰው … ወይንም ስዕል መሳያ ቀለምና ሰው አንድ እና ያው ናቸው ወይ? ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ አይደሉም፡፡ መንገድ ናቸው። ዶሮ ሌላ ዶሮ ለመፍጠር ሲፈልግ በእንቁላል መንገድ ማምራት እንዳለበት … ሰውም … ራሱን መልሶ ለመረዳትም ሆነ ሌሎች መሰሎቹ ዘንድ ለመድረስ የግድ “በጥበብ” ነፀብራቅ ውስጥ ማለፍ አለበት፡፡
ምንም እንኳን ሰው እና መስታወት … ወይንም ሰው እና ፊደል … አልያም ሰው እና ቀለም በራሳቸው እንደ ራሳቸው ግንኙነት ያላቸው ባይመስልም .. ተቀናብረው ሲገናኙ ግን መልሰው ሰውን የሚሰፉ ይሆናሉ፡፡ መንገድን (ጥበብን) ከሰው ጋር ወይም ማንፀባረቂያውን መስታወት ከሚንፀባረቀው ሰው ጋር የሚያገናኘው የጥበብ ቄስ … “አርቲስት” ተብሎ ይጠራል፡፡ … “ከዶሮ እና እንቁላል ማን ይቀድማል?” ለሚለው ጥያቄ … ቀልድ መሳይ መልስ ተከሰተልኝ። በተለይ በየዕለቱ ጠዋት … ጠዋት እንቁላል የሚቀድም ይመስለኛል፡፡ ለፋሲካ ለፋሲካ ደግሞ ዶሮ እና እንቁላሉ ሳይቀድሙ አንድ ላይ ቢቀርቡልኝ ደስ ይለኛል፡፡

Read 2402 times