Saturday, 21 October 2017 12:50

ሂልተን አዲስ አበባሆቴል፣ ለ4ኛ ጊዜ የዓለማቀፍ ሽልማት አሸናፊ ሆነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው ሂልተን አዲስ አበባ ሆቴል፣ ከኢትዮጵያ ሆቴሎች በአገልግሎት ጥራት የመሪነት ደረጃን በመያዝ፣ለአራተኛ ጊዜ የ”ዎርልድ ትራቭል አዋርድ” ሽልማት ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ሰሞኑን በሩዋንዳ ኪጋሊ በሚገኘው ራዲሰን ብሉ ሆቴል በተደረገው የቀይ ምንጣፍ የሽልማት ስነ ስርአት ላይ ሽልማቱን የተቀበሉት የሂልተን አዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ ካላኦስ ኮቴነር፤ “ይህ ሽልማት ለሆቴሉና ለሰራተኞቹ ትጋት፣ትልቅ ትርጉም ያለው ስኬት ነው” ብለዋል፡፡
“አዲስ አበባ የሚመጡ በርካታ የዓለም እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ እየተቀበልን እንገኛለን” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ለዚህ ቀና መስተንግዶአችን ለተሰጠን እውቅና እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
ሂልተን አዲስ አበባ ሆቴል በ”ዎርልድ ትራቭል አዋርድ” ከኢትዮጵያ ሆቴሎች በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የመሪነት ደረጃውን ይዞ ከዘንድሮው ጋር ለ4 ተከታታይ አመታት ተመሳሳይ ሽልማት ለማግኘት መቻሉን ሆቴሉ ለአዲስ አድማስ ያደረሰው መግለጫ ያመለክታል፡፡ ሆቴሉ በሽልማቱ በመበረታታት የበለጠ አገልግሎቱን ለማዘመን እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
“ዎርልድ ትራቭል አዋርድ” በዓለማቀፍ ደረጃ ከቱሪዝምና ሆቴል አገልግሎት ጋር በተያያዘ ምርጥ የተባሉትን እየለየ፣ በየዓመቱ እውቅና የሚሰጥ አለማቀፍ ተቋም መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 2369 times