Sunday, 22 October 2017 00:00

በኢትዮጵያ የሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ መጥቷል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

 • ”የድርቅ ተረጅዎች ችግር ወደ ቀጣዩ ዓመት ሊሸጋገር ይችላል”
    • ለተፈናቃዮች የሚያስፈልገው ሰብአዊ ድጋፍ እየተጠና ነው

       በኢትዮጵያ የሰብአዊ ቀውሶች ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ መምጣታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት (OCHA) አስታውቋል፡፡ ፅ/ቤቱ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ወቅታዊ ሪፖርቱ፤ሃገሪቱ በሰብአዊ ቀውሶች ፈተና ላይ ወድቃለች ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ በፍጥነት ተለዋዋጭ ሆኗል ያለው ፅ/ቤቱ፤ ሃገሪቱ በድርቅ፣ በጎርፍና በእርስ በርስ ግጭቶች ሳቢያ ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውሶች እየተዳረገች መሆኑን ጠቁሟል፡፡  
በአሁኑ ወቅት 8.5 ሚሊዮን ዜጎች የድርቅ ተጎጂዎችና ተረጅዎች ናቸው ያለው  ጽ/ቤቱ ያወጣው ሪፖርት፤ 3.6 ሚሊዮን ህፃናትና ነፍሰጡር ሴቶች ተጨማሪ አልሚ ምግብ ፈላጊዎች መሆናቸውን እንዲሁም 10.5 ሚሊዮን ዜጎች አስተማማኝ የመጠጥ ውሃ እንኳ እያገኙ እንዳልሆነ  አስታውቋል፡፡
የድርቅ ተረጂዎችን እስከ መጪው ጥር ወር ለመደገፍ ብቻ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ተቋሙ፤ “በሃገሪቱ በተለይም ሰብል አምራች በሆኑ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የምስራቅ አማራ አካባቢዎች በክረምቱ በቂ ዝናብ ባለማግኘታቸው የሚፈለገው ምርት አይገኝም፤ ይህም ተጨማሪ ስጋት ፈጥሯል” ብሏል፡፡
የኦሮሚያ-ሶማሌ ግጭትን ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን የጠቀሰው ተቋሙ፤ለእነዚህ ዜጎች የሚያስፈልገውን ሰብአዊ ድጋፍ በተመለከተ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ በዚህ እንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ለድርቅ ተጎጂዎች ከተገዛው እህል ላይ 16 ሺህ ሜትሪክ ቶን በመበደር፣ለተፈናቃዮች እንዲውል ማድረጉን ተቋሙ ጠቁሞ፣ ይህም ሰብአዊ ቀውሱ የሰፋ ደረጃ መድረሱን ያመላክታል ብሏል፡፡ በተፈናቃዮች አካባቢ የአተት ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በመፈጠሩም የጤና ባለሙያዎች ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ነው ተብሏል፡፡   
የክረምቱ የሰብል ምርት የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ተከትሎም የድርቅ ተረጅዎች ችግር ወደ 2018 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ሊሸጋገር እንደሚችልም አስታውቋል - የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት፡፡

Read 3604 times