Saturday, 21 October 2017 13:07

የሙጋቤ ሚስት የ1.35ሚ. ዶላር የአልማዝ ቀለበት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አጭበርብሮኛል ያሉትን ባለሃብት ከሰሱ

     የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ “1.35 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአልማዝ ቀለበት ሊሸጥልኝ ተስማምቶ ክፍያውን ከፈጸምኩለት በኋላ 30 ሺህ ዶላር ብቻ የሚያወጣ ቀለበት ሰጥቶ ሸውዶኛል” ባሉት ሊባኖሳዊ ባለሃብት ላይ ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
ጀማል አህመድ የተባለው ባለሃብቱ፣ ሙጋቤ የጋብቻቸውን የ25ኛ አመት ክብረ በዓል አስመልክተው ለቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ በስጦታ ያበረከቱትን ቀለበት አጭበርብረሃል በሚል ባለፈው አመት ተከስሶ የነበረ ሲሆን እሱ ግን “በተስማማነው መሰረት፣ ትክክለኛውን የአልማዝ ቀለበት ነው የላክሁላት፣ በመካከል ላይ አጭበርባሪዎች ቀይረውባት ይሆናል” ሲል መናገሩንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ይህን ተከትሎም ባለሃብቱ የተከፈለውን ገንዘብ እንዲመልስ የቀረበለትን ጥያቄ አልቀበልም በማለቱ፣ ግሬስ ሙጋቤ የባለሃብቱን መኖሪያ ቤት አስገድደው መውረሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፍርድ ቤትም ግሬስ ቤቱን ለባለሃብቱ እንዲመልሱ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር ብሏል፡፡ ባለሃብቱ በውሳኔው መሰረት ቤታቸውን ቢረከቡም፣ ግሬስ ሙጋቤ ግን ተበልቼ አልቀርም በማለት ሊባኖሳዊው ባለሃብት ጀማል አህመድ 1.23 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በካሳ መልክ እንዲከፍላቸው ሰሞኑን ሌላ ክስ መመስረታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡

Read 3250 times