Monday, 23 October 2017 00:00

አይሲስ በአሜሪካ ላይ ከ9/11 የከፋ ጥቃት ለመፈጸም እያሴረ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     አሸባሪው ቡድን አይሲስ እና ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖች በአሜሪካ ላይ ከ16 አመታት በፊት ከተፈጸመው አሰቃቂው የ9/11 የሽብር ጥቃት የከፋ ሌላ  የአውሮፕላን የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እያሴሩ እንደሚገኙ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የትራምፕ የአገር ውስጥ ጉዳይ ጸሃፊ ኢላኒ ዱክ ይፋ ያደረጉትን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አይሲስና አጋሮቹ በአሜሪካ አውሮፕላኖች ላይ የከፋ ጥፋት የሚያስከትል የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በድብቅ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚያመለክት የደህንነት መረጃ ተገኝቷል፡፡ የአሜሪካ ደህንነት ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፣ ሽብርተኞች በአገሪቱ ላይ ለማድረስ ያቀዱት ጥፋት እጅግ የከፋ ነው ያለው ዘገባው፤ አገሪቱ ይህንን ጥቃት ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መዘጋጀቷንና አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰዷን ጠቁሟል፡፡
ከቀናት በፊትም የእንግሊዙ የስለላ ተቋም ኤምአይ5 ሃላፊ፣ የሽብር ቡድኖች በአገሪቱ ላይ ያልተጠበቀ አደገኛ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ በይፋ ማስጠንቀቃቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ እ.ኤ.አ በ2001 መስከረም 11 ቀን በአሜሪካ መንትያዎቹ ህንጻዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ 2 ሺህ 996 ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉን አስታውሷል።

Read 3777 times