Saturday, 21 October 2017 13:11

አይጥ ለማባረር ቤትን ማቃጠል!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(7 votes)

 ባለፉት ዓመታት በሀገራችን አራቱም ማዕዘናት በብሄር፣ ብሄረሰቦች መካከል በርካታ ህይወትና ንብረት የበሉ የተለያዩ ዘር-ተኮር ግጭቶችን አይተናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ግጭቶችን አይናችን ጆሮአችንም ሆነ ልቦናችን ለምዶታል፡፡ በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሞ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች  የተከሰተውን  ግጭት ብዙዎቻችን እንደ ዱብ እዳ የቆጠርነው አይመስልም፡፡    
የግጭቱ ስፋትና አስከፊነት እንዲሁም በግጭቱ ሳቢያ በአሳዛኝ ሁኔታ የረገፉትና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ቁጥር ግን እንደ ሀገርና ህዝብ፣ በወደፊቱ እጣ ፋንታችን ላይ ጥላ ያጠላ ሲሆን በአብዛኞቻችን ልብ ውስጥ ከባድ ጭንቀትና ስጋት መፍጠሩን ጨርሶ መካድ አይቻልም፡፡
እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ባለንበት በዚህ ክፉ ወቅት ታዲያ አንድ የኢህአዴግ መራሹ  መንግስት አንጋፋ  ባለስልጣን፣ መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው የሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ነው፡-
“የእኛ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየውን መሰረታዊ ቅራኔ ፈቷል፤ በብሄር እኩልነት ይነሳ የነበረውን ግጭት አስተካክሎታል፡፡ ይሄ ብሄር የበላይ፣ ያኛው የበታች የሚል የለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ብሄር የበላይነት አክትሟል፤በህግም በተቋምም በራስ አስተዳደርና ስልጣንም ምላሽ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት የሚባል እንዳይኖር አድርጓል፡፡”
ይህን የመሰለው የባለስልጣኑ ንግግር፣ አንዳችም ስህተት የለበትም ቢባል ያስኬዳል፡፡ ለምን ቢሉ፣ ባለሥልጣኑ የተናገሩት እሳቸው ስለሚያውቋት ኢትዮጵያ ነው፡፡ የእሳቸው ኢትዮጵያ ደግሞ ለሌሎች የምትገለፀው፣ ይህን በመሰል አነጋገር ነው፡፡ በእኛዋ ኢትዮጵያ ግን ጉዳዩ ሌላ ነው፡፡ በእኛዋ ኢትዮጵያ ያለው ገለፃ፣ “ኢትዮጵያን የብሄርና ብሄረሰቦች እስር ቤት አድርገዋት ነበር” እየተባሉ ዛሬም ድረስ በሚወቀሱት ቀደምት ስርአቶች ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ  ሁኔታ የበርካታ ዜጎች ህይወት በመስዋዕትነት የሚቀርብለትን የብሄር ብሄረሰቦች የእርስ በርስ ግጭት፣ ክፉ መርዶ የሚተርክ ነው፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ ሚኒስትር፣ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ደም አፋሳሽ ግጭት በተመለከተ ሲናገሩ፤ “ከወሰን ጋር በተያያዘ የተፈጠሩት ችግሮች ትክክለኛ መንስኤዎች ምን እንደሆኑ ወደፊት ተጣርቶ ይገለፃል፡፡” ብለዋል፡፡
እውነት ለመናገር ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት፣የብሄር ብሄረሰቦችን ጉዳይ በተመለከተ ላለፉት 26 ዓመታት የሰራውን ስራ ጨርሶ ረስቶታል፡፡ እንዲያ ቢሆን ነው እንጂ አለዚያማ በሁለቱ ክልሎች በሚኖሩ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች መካከል “የተነሳውን ግጭት ትክክለኛ መንስኤ ወደፊት አጣርቼ እገልፃለሁ” ለማለት አይደፍርም ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ከብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤትነት፣ ወደ የመፈቃቀድና የመቻቻል አዲስ ሀገርነት የመቀየር ጉዳይ የኢህአዴግ የፖለቲካ ትግል አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ ይህን የፖለቲካ አላማ ለማሳካት በማለም፣ ኢህአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት ዘርን ዋነኛ መነሻና መድረሻ ያደረጉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እርምጃዎችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ወስዷል፡፡
በዚህ የተነሳም “የህዝቦችን እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአት እየገነባች ያለች አዲስ ሀገር፣ አዲስ ኢትዮጵያን መፍጠር ችያለሁ” እያለ የጀብዱውን ተረክ በኩራት ሳይተርክ ያመለጠው ጊዜም ሆነ አጋጣሚ የለም ማለት ይቻላል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የህዝቦችን እኩልነት፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአት እየገነባች ያለች አዲስ ኢትዮጵያ የመፈጠሯን ጉዳይ የሚያውቀው  ኢህአዴግና ጥቅም ያስተሳሰራቸው ጅሪዎቹ ብቻ ናቸው፡፡
አረቦች፤ “ግመል መካ መሄድ ይችላል፤ሲመለስ ግን ሀጂ አድርጓል አይባልም” የሚል አሪፍ አባባል አላቸው፡፡ የኢህአዴግም ነገር እንደዚህ ነው፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ ስሜቱ የመራውን ወይም ልቡ የፈቀደውን ማናቸውንም አይነት የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ ጉዳይ “ፈፀምኩት፣ አሳካሁት” ብሎ ጉማዬ ሊጨፍር ይችላል፡፡ ፈፀምኩት፣ አሳካሁት ያለው ነገር ሁሉ የምር ተፈጽሟል ብሎ እርግጡን መደምደም ግን አይቻልም፤ አይገባምም፡፡
ኢህአዴግ በብሄር፣ ብሄረሰቦች እኩልነት፣ መከባበርና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች አዲስ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚል ላለፉት 26 አመታት በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት ያከናወነው “የዘር ፖለቲካ ኢኮኖሚ ስራ” የፈጠራት የአሁኗ አዲሲቱ ኢትዮጵያ፣ ኢህአዴግ ከሚላት በእጅጉ የተለየች፣ ኢህአዴግ በሚገልፃት አይነት ጨርሳ የማትገለጽ ናት፡፡
ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ድፍን አለሙ ሁሉ እንደሚያውቀው፣ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ላለፉት 26 ዓመታት ወጥሮ የሰራው፣ በአብሮነት ተከባብረን በሰላም ስለመኖር ወይም በኢህአዴግኛ፣ በእኩልነት፣ በመከባበርና፣ በመፈቃቀድ አብሮ ስለመኖር ጨርሶ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት በከፍተኛ ትጋት የሰራው ብሄር፣ ብሄረሰቦች በጋራ ከሚያገናኛቸውና አንድ ከሚያደርጓቸው እጅግ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች ይልቅ ለሚለያዩዋቸው ጥቃቅን እንቅፋቶች ከመጠን ያለፈ ትኩረትና ቅድሚያ እንዲሰጡ፤ የቀደመ የታሪክ ዕዳ ያለአበሳቸው እንዲያወራርዱ፤ ከትልቋ የጋራ ብሄራዊ ሀገር ይልቅ ትንሹን መንደርና ጎጣቸውን ብቻ እንዲያስቡ፤ በዘርና በጎጣቸው ብቻ የእሾክ አጥር ሰርተው እንዲኖሩ ነው፡፡
ይህን የመሰለው የኢህአዴግና የሚመራው መንግስት የሩብ ምዕተ አመት ድርጊት፣ አይጦችን ለማጥፋት ሲባል ቤትን እንደ ማቃጠል የሚቆጠር ነው፡፡፡ ይህን በመሰለው ድርጊት የተፈጠረች አዲሲቱ ኢትዮጵያ ኢህአዴግና ጀሬዎቹ እንደሚገልጿት፣ የህዝቦችን እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአት እየገነባች ያለች ሳትሆን ብሄር፣ ብሄረሰቦች በጥላቻና በጥርጣሬ የሚተያዩባት፤ ጠባብነትና ጎሰኝነት በመንገሱ የተነሳ ተራ የግለሰብ አለመግባባት ከፍተኛ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ወደሚያስከፍል የዘር ግጭት በቀላሉ መቀየር ወደሚቻልባት ሀገርነት ነው፡፡
ዛሬ የተፈጠረችው አዲሷ ኢትዮጵያ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመላ የአገሪቱ ግዛት ውስጥ ሰርቶ የመኖር ህገ መንግስታዊ መብቱና ነፃነቱ የተጨፈለቀባት፣ ዜጎች መርጠው ያገኙት ይመስል በዘራቸው የተነሳ ከሚኖሩበት አካባቢ ለዘመናት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት በጠራራ ፀሐይ እየተነጠቁ የሚባረሩባት፤ ማንም ጊዜ የሰጠኝ ነኝ ባይ፣ የጋራ የሆነውን ሀገር የግል ጓሮው አድርጎ የእሾክ አጥር ሲያጥርና ለዘመናት የኖሩትን ዜጎች፣ የአያት ቅድመ አያት ዘራቸውን እየቆጠረ፣ “መጤ ናችሁና ከአካባቢው ውጡ” እያለ፣ የሺዎችን ቤትና ቤተሰብ ሲያፈርስና ሲበትን፣ ሀይ ባይ የሌለበት ኢትዮጵያ ናት፡፡
ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት፣ባለፉት 26 ዓመታት ባራመዱት የዘር ፖለቲካ-ኢኮኖሚ በተፈጠረችው “አዲሷ ኢትዮጵያ”፣ ስንት ግፋአን ወገኖቻችን በዘራቸው የተነሳ ህይወታቸውን እንዳጡና ከመኖሪያ ቀያቸው ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተፈናቀሉ በሚገባ እናውቃለን፡፡ ለእኛ የኮኩ ፍሬ ከኮኩ ዛፍ ርቆ እንደማይወድቅ በጣም ግልጽ ነው፡፡ እናም የወቅቱ ዘር-ተኮር ግጭት ትክክለኛ መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅ ዛሬም ሆነ ወደፊት ማጣራት አስፈላጊያችን አይደለም፡፡
አይሁዳውን፤ “ውሻ የገዛ ጩኸቱን ሲሰማ ዝሆንን የሚያስንቅ ግዙፍ የሆነ ይመስለዋል” ይላሉ፡፡ ኢህአዴግና ጀሪዎቹም የዛሬዋን ኢትዮጵያ፣ የህዝቦችን እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአት እየገነባች ያለች አዲስ ሀገር ናት” እያሉ ነጋ ጠባ የሚወተውቱን፣ የራሳቸውን ጩኸት ብቻ በመስማት ለራሳቸው ካደረባቸው “ልዩ” ስሜት በመነሳት ነው፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ የቤድዊን አረቦች ግን ልክ እንደ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት አይነት ሲያጋጥማቸው የሚገልፁት፤ “በአርባ አመቱ ጅል የሆነ ሰው እድሜ ልኩንም ጅል ነው” በሚለው አሪፍ አባባላቸው ነው፡፡ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት፣ ለ25 አመታት ይሁነኝ ብሎ በመለያየት ፋስ ያለ ርህራሄ ሲፈልጠው የነበረውን የብሄር፣ ብሄረሰቦች አንድነት፤ ለ25 አመታት በሚገባ ታቅዶ በተቀነባበረ የጠባብነትና የጎጠኝነት መጋዝ ያለማሰለስ ሲገዘግዘው የኖረውን የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜትና የህብረ-ብሄራዊ ብዝሃነት መንፈስ፣በአንድ ሳምንት የፕሮፓጋንዳ ከበርቻቻና የአዳራሽ ውስጥ አታሞ ድለቃ መልሶ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ የፈየደው ነገር ቢኖር፣ ኢህአዴግ በ25 ዓመቱም ሞኝ ምናልባትም ጅል መሆኑን በግልጽ ማሳየት ብቻ ነው፡፡
 ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት፣ “የእኛ ህገ-መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየውንና በብሄር እኩልነት ሳቢያ ይነሳ የነበረውን ግጭት አስተካክሎታል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት የሚባል እንዳይኖር አድርጓል” ያሉን የኢህአዴግና የሚመራው መንግስት አንጋፋና ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ለምን እዚህም እዚያም ግጭቶች ይታያሉ? ተብለው ሲጠየቁ የመለሱት፤ “በየደረጃው ያለው አመራር ለህገ መንግስቱ በመገዛት፣ ህገ መንግስቱ የሚያዘውን ባለማከናወኑ የተከሰቱ ናቸው” በማለት ነው፡፡
ከ1949 እስከ 1967 ዓ.ም የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ቶማስ ካምቤል ክላርክ፣ የህግ የበላይነትን አስመልክተው ሲናገሩ፤ “ያወጣውን ህግ አለማክበርን የመሰለ አንድን መንግስት ባጭር ጊዜ ውስጥ እንኮታኩቶ የሚጥል ነገር የለም” ብለው ነበር፡፡ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት መቼም ቢሆን በጄ ብሎ ሊያዳምጣቸው ከማይፈልጋቸው በጎ ምክሮች ወይም አስተያየቶች ውስጥ አንዱ ይህ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ግን ለኢህአዴግና ለመንግስቱ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ጥያቄ ማቅረብ በጣም አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ በየደረጃው ያሉት የኢህአዴግም ሆነ የአጋር ድርጅቶቹ እንዲሁም የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ለሆነው ለህገ መንግስቱ እስኪገዙ ወይም መገዛት እስኪጀምሩ ድረስ የስንት ግፉአን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ህይወት፣ በአሰቃቂ ሁኔታ እንገብር? የስንት ወገኖቻችን አካልስ ይጉደል?
በየደረጃው ያሉ አመራሮች ህገ መንግስቱ የሚያዘውን እስኪከውኑ ወይም መከወን እስኪጀምሩ ድረስ ስንት ግፉአን ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን፣ ከቀያቸው እየተነቀሉ ተፈናቅለው ይበተኑ? የስንት ወገኖቻችን በመከራ የተገኘ ቤትና ንብረትስ የእሳት ሲሳይ ይሁን?
እስከ መቼስ አይጦችን ለማባረር ቤታችን እየተቃጠለ እንኑር?

Read 4097 times