Saturday, 21 October 2017 13:32

“አመስግናለሁ” ማንን ገደለ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
መንገድ ላይ እየሄዳችሁ ነው፡፡ የሆነ ሰው መጥቶ ፊት ለፊታችሁ ይገተራል፡፡ ልክ እኮ የሆነ ሰው “ዋ አልፎህ ይሄድና!” ያለው ነው የሚመስለው፡፡
“ስማ፣ ስንት ሰዓት ነው?”
“አቤት!”
“ሰዓት ስንት ነው?”
ልክ እኮ ስኳር ሲሰርቅ እንደተገኘ አራስ፣ ሊቆነጥጣችሁ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡
“ሦስት ሰዓት ከሀያ”
“አመሰግናለሁ” የለ፣ “እግዜር ይስጥልኝ…” የለ…ብቻ “ብራዘር ለቁርስ ሳንቲም…” ምናምን ያላችሁት ይመስል በቆማችሁበት ትቷችሁ ይሄዳል፡፡
መከባበር እየጠፋ ነው፡፡ ለተደረገልን ነገር ምስጋና ማቅረብ እየቀረ ነው፡፡ ጥያቄዎችን በስርአት ማቅረብ እየቀረ ነው፡፡
“አምስት ኪሎ በየት በኩል ነው?” ሲላችሁ አቅጣጫውን እንድትጠቁሙት ትብብር እየጠየቀ ሳይሆን የሆነ የቃል ፈተና እያቀረበላችሁ ይመስላል።
እናማ…“አመስግናለሁ” ማለት ማንን ገደለ! “እግዜር ይስጥልኝ፣” ማለት ማንን ገደለ!
“ወንድም፣ እባከህ ስንት ሰዓት እንደሆነ ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብሎ ማለት እያለ ደረቱን ነፍቶ፣ ግንባሩን ከስክሶ “ስማ…ስንት ሰዓት ነው?” ይላል፡፡ ልክ እኮ… አለ አይደል… ሰዓት እንደትነግሩት በምግብ ለሥራ የቀጠራችሁ አይነት ያስመስለዋል። “እባክህ…” ምናምን የመሳሰሉ የትህትና ቃላትን መጨመር፣ ይህን ያህል ትንፋሽ የሚጨርሱ ሆኖ ነው እንዴ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ነዳጅ ማደያ አካባቢ ነገሬ ብላችሁልኛል፡፡ ስንት ሰዓት ሙሉ ሰልፍ ይዘው የሚጠብቁ መኪኖች፣ ረጅም ርቀት ተደርድረው እያሉ፣ ሌሎች ደግሞ ባልተፈቀደ በኩል በጎን ተደርበው ገብተው፣ መቅደም ይፈልጋሉ፡፡ ተደርበው የሚመጡት እንዳይገቡ መከላከያ የሚያስቀምጡ ማደያዎች አሉ። በሠራተኞቹ ቸልተኝነት ብዙ ጊዜ የሚሳካላቸው አሉ፡፡ አንዳንዴ እንደውም ይባስ ብሎ ተደርቦ የመጡ ሰዎች፣ ከመኪና ወርደው መከላከያውን ለማንሳት ሲሞክሩ እናያለን፡፡
በስነ ስርአት ተራ መጠበቅ ማንን ገደለ! “እኔ ማነኝና ነው ያለ ተራዬ የምገባው!” ብሎ ማለት ማንን ገደለ!  
ተራ የመጠበቅ ነገር ካነሳን፣ ይቺ ጣጣዋ የበዛ ከተማ ካሏት መልካም ነገሮች አንዱ የታክሲ ተጠቃሚዎች በሰልፍ ተራ የመጠበቃቸው ነገር ነው፡፡ ዝም ብሎ ሲታሰብ እንደዛ አይነት ነገር ባይኖር ኖሮ፣ በዘንድሮ ባህሪያችን ተባልተን ባናልቅ ነው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሰው የማይሰለፍባቸው፣ ተራ አስጠባቂዎች የሌሉባቸው፣ ወይም በስርአት ተራ የማያስከብሩባቸውን ታክሲ መሳፈሪያዎች ነገሬ በሉማ፡፡ አንድ ሚኒባስ ሲመጣ ወጣት በሉት፣ አዛውንት በሉት፣ ምን በሉት …ሁሉም ቅድሚያ ለመግባት ሲገፈታተር ነው የምታዩት፡፡ ነፍሰጡሮች ተገፍተው ሲሽቀነጠሩ በተደጋጋሚ እናያለን፣ አዛውንቶች ተገፍተው ሲንገዳገዱ በተደጋጋሚ እናያለን፡፡ አሁን ምን መጣ? “አንተ ትብስ፣ አንቺ፣” መባባልን ምን ጠርጎ ወሰደው! እንደውም አንዳንዴ ረዳቶቹ ራሳቸው “አባባ  እርሶ ይምጡ…” ብለው ደከም ላሉ አዛውንት፣ “እህት ነይ…” ብለው ለነፍሰ ጡር ሴት ቅድሚያ ሲሰጡ ማየት ጥሩ ነው፡፡
ሰዎቹ ሰብሰብ ብለው ተቀምጠዋል፡፡ የሆኑ አዛውንት ይመጣሉ፡፡ እናም… የተወሰኑ ሰዎች ብድግ ይላሉ፡፡ የተወሰኑት ግን… አይደለም ሊነሱ ነቅነቅ እንኳን አይሉም፡፡ በእድሜ  የገፉ ሰዎች ሲመጡ በአክብሮት ብድግ ማለት የቆየ ባህል አልነበረም እንዴ!  ትልቅ የመከባበር ምልክት አልነበረም እንዴ! እና አሁን ምን መጣ? በትንሹ ለሴኮንዶች ክፍልፋይ ብድግ ማለቱ፣ ይህን ያህል ትንፋሽ የሚጨርስ ሆኖ ነው እንዴ!
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ በፊት ጊዜ “ምን የዘንድሮ ወጣት ታላላቆቹን አያከብር፣ ስርአት የለው…” አይነት ወቀሳዎች የተለመዱ ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ተለውጧል፡፡ ዕለት በዕለት የሚገጥሙንን የባህሪይ፣ የስነምግባር ችግሮችን በወጣቶች ላይ ብቻ የምንጭንበት ዘመን አልፏል፡፡ የሚገርም እኮ ነው… ሁለትም፣ ምናልባት ከዛ በላይም ጸጉር ያወጣው ሁሉ የሚያሳየው ባህሪ፣አንዳንዴ ከማስገረምም አልፎ አስደንጋጭም ነው፡፡ የሰባ ምናምን ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ፣ የአሥራ ምናምን ዓመቷን ታዳጊ መቀመጫ ቸብ ማድረግ…ያውም በአደባባይ…ምን የሚሉት ስልጣኔ ነው! የፓስቲ ሀራራ የሚሠራውን ያሳጣው የሰፈር ልጅ ያደረገው አይነት እኮ ነው የሚመስለው!
በቀደመው ጊዜ የሆነ ልጅ ሲያጠፋ የሚሰደበው እሱ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የውግዘት ናዳው የሚወርደው ወላጆቹ ላይ ነው፡፡ “ይሄ አሳዳጊ የበደለው!” ምናምን ይባላል፡፡ ወላጆቹ በስርአት ቢያሳድጉት ኖሮ እንዲሀ አይሆንም አይነት ነገር ነው፡፡ ዘንድሮ ግን የባህሪይ ችግሩ በወላጆችና ወላጅ ለመሆን በሚበቁት ላይ እየባሰ ይመስላል፡፡ “እነኚህ ልጆቻቸው የበደሏቸው!” አይባል ነገር!
እኔ የምለው…ለምሳሌ አውቶብስ ውስጥ ደከም ላሉትና እንዲሁም ለሴቶች ወንበር መልቅቅ የተለመደ ነበር፡፡ እሱም እየቀረብን ነው፡፡ ደካማ፣ በእድሜ የገፉ እናቶችና አባቶች ቆመው ሲንገላቱ እያየ፣ የጂብራልታርን አለት መሸከም የሚችል ጎረምሳ፣ ወንበር ላይ ተለጥጦ ታገኙታላችሁ፡፡ አሁን ምን መጣ? ደግሞ ለሴቶች ቅድሚያ የመስጠት ባህል ነበር፡፡ የምር ግን እሱ ነገር ሙሉ ለሙሉ የቀረ እኮ ነው የሚመስለው፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሴቶችም ዋና ተጋፊዎች ሆነዋል፡፡
ደግሞላችሁ…ከግለሰባዊ የባህሪይ ችግሮች ሲያልፍ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ውስጥም የሆኑ አድማጭና ተመልካችን ዝቅ አድርጎ የመገመት ነገሮች እናያለን፡፡ በወዲያኛው ጫፍ ያሉትን የመርሳት የሚመስል በጣም በበራድ ሻይ ዙሪያ የሚባሉ የሚመስሉ አስተያየቶች፣ ከሳቅ ይልቅ ለእንባ ቅርብ የሆኑ ‘ቀልዶች’ … “እነዚህ ሰዎች በእንቅልፍ ልባቸው ነው እንዴ የሚያወሩት!” የሚያሰኙ ትንተናዎች መአት ናቸው፡፡ ከእነኚህ ሁሉ ጀርባ ሰውን ያለማክበር፣ “ሌላው የእኛን ያህል አያውቅም፣” አይነት የባህሪይ ችግሮች ይኖራሉ፡፡
ነገሬ ብላችሁ እንደሁ አሁን፣ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ብሔራዊ ትያትር በር ላይ ቆሞ፣
“ብሔራዊ ትያትር የት ነው?” አይነት ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች በዛ ብለዋል፡፡ የማያውቁትን መጠየቅ ምንም ችግር የለውም፡፡ የሚያበሽቃችሁ ነገር የሰዉ አጠያየቅ ነው፡፡ ትህትናን ምን ወሰደው! መከባበርን ምን ወሰደው! “አመሰግናለሁ”ማንን ገደለ!
መቼም የብዙ የከተማችን ስፍራዎችን መጨናነቅ ላየ ነገ፣ ተነገ ወዲያ እንዴት ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው እንደምንቀሳቀስ ማሰቡም አስቸጋሪ ይሆናል። መንገድ ላይ ከጀርባችሁ የመጣውን ሰው፣ ዘወር ብላችሁ ቅድሚያ ትሰጡታላችሁ፡፡ ብቻ ዘወር ብሎ ሳያያችሁ ይነጉዳል፡፡ “አመሰግናለሁ” ማንን ገደለ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ማታ ቴሌቪዥናችን ፊት ‘ተጥደን’ እያመሸንም ለሰው… “እኔ እነሱን አላይም…” የምንላቸው እነዚህ የቱርክ ፊልሞች ላይ በብዛት የምንሰማው ነገር አለ… “አመሰግናለሁ…” ይላሉ፡፡ ችግር ላይ ሆነው እንኳን፣ የሆነ ያበሳጫቸው ነገር ኖሮ እንኳን፣ የሆነ ሰው ከፍቶባቸው እንኳን… አንድ ነገር ሲደረግላቸው “አመሰግናለሁ…” ሲሉ እንሰማለን፡፡ አይደለም ሌላ ሰው፣ ሥራው የሆነ ሰው አንድ ነገር ሲያደርግ… ለምሳሌ ጸሀፊዋ ለአለቃዋ የሆኑ ሰነዶች ስታቀርብ አለቃዋ፣ “አመሰግናለሁ…” ይላታል፡፡ ይሄ አሁን በኛ ዘንድ፣ አይደለም ሊደረግ፣ ከመጀመሪያውስ  ይታሰባል! ጭርሱን በስህተት እንኳን “ምናለ አመሰግናለሁ ብትላት?” ቢባል… “ለምን ብዬ! ደሞዝ የምትዝቅበት ሥራዋ አይደለም እንዴ! አመሰግናለሁ ብዬ ደግሞ ነገ አናቴ ላይ ትውጣ!” ሳይባል አይቀርም፡፡ “አመሰግናለሁ” ማንን ገደለ!
በዚች ለመተንፈስ እንኳን በቂ ስፍራ እየጠፋባት ያለች በምትመስል ከተማ፣ ዘና ብሎ መንገድ ላይ መጓዝ ብሎ ነገር ቀርቷል፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ገሚሱ ወዲህ ሲመጣ፣ ገሚሱ ወዲያ ሲሄድ፣ መሀል ላይ ፊት ለፊት መገናኘት የተለመደ ነው፡፡ ይሄኔ ታዲያ አንዱ ለሌላው ቅድሚያ ሰጥቶ ከማሳለፍ ይልቅ ሁሉም መቅደም ይፈልጋል፡፡ ለአንድና ለሁለት ሴኮንዶች ቆም ብሎ ማሳለፍ ማንን ገደለ!
ተራ መጠበቅ ማንን ገደለ!
ለአቅመ ደካሞችና ለሴቶች ወንበር መልቀቅ ማንን ገደለ!
በትህትና “እባክህ/እባክሽ” ብሎ መጠየቅ ማንን ገደለ!
“አመሰግናለሁ” ማንን ገደለ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6337 times