Saturday, 21 October 2017 13:38

ኢህአዴግ ከሰማኝ፣ እነሆ ጥቂት ምክሮች!

Written by  ገለታ ገ/ወልድ
Rate this item
(7 votes)

 የነባር አመራሮች መታከት? የህግ የበላይነት መላላት? የዲሞክራሲያዊነት መቀጨጭ? የእርስበርስ ግጭት?
      
  ኢትዮጵያን ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ ያስተዳደራት ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ በተለያዩ የድልና የውድቀት ዜናዎች ታጅቦ እዚህ ደርሷል። እስከ አሁን የመጣበት ሂደት በተለይ ከኢኮኖሚ እድገት አንፃር ሲመዘን በመልካምነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ምንም እንኳን እዚህም ላይ የሚነሱ የፍትሃዊነትና የሀብት ክፍፍል  ጥያቄዎች  እንዳሉ  ቢታወቅም አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጡን ማንኳሰስ ግን ከእውነት መራቅ ነዉ፡፡ ያም ሆኖ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ወይም የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የታየውን ለውጥ ያህል በሰው ሃብት ልማት (ከብቃት፣ ተወዳዳሪነት፣ የሀገር ፍቅርና ሞራል) አኳያ ሲመዘን፣ተጨማሪ ጥረት ማድረግን የሚሻ ነዉ፡፡
ኢህአዴግ የሚታወቅባቸው መልካም ተሞክሮዎች ያሉትን ያህል በዲሞክራሲው መስክ ክፉኛ እየታማ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር  እጦትና  በህግ የበላይነት መጓደል ረገድ ያለው ክፍተት ራሱን መንግስትን ጨምሮ ከሞላ ጎደል ሁሉንም የሚያስማማ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በስርዓቱ ውስጥ በመስራችነት የሚታወቁትን የብሄር ፓርቲዎች ጭምር ውዝግብ ውስጥ የከተተ የወሰን፣ የማንነት፣ የፍትሃዊ ሀብትና ስልጣን ክፍፍል ጥያቄ የታጨቀበት ህዝባዊ መከፋት ተደጋግሞ እየተነሳ ነው፡፡ የህግ የበላይነት መላላት፣ የዲሞክራሲያዊነት መቀጨጭና አለመቻቻልም ሀገሪቱን እያናወዛት ይገኛል፡፡  
በዚህ መዘዝ  የዜጎች ስደት፣ መፈናቀልና እንግልት ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ በሚባል ደረጃ የእርስበርስ ግድያና ዘረፋም ሲፈፀምም ታይቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ  በፌደራል ስርዓቱ ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ ሃይሎች  ምቹ  የመከራከሪያ  አጋጣሚ እየፈጠረ ነው፡፡ በመሰረቱ አሁን በተጨባጭ በኢህአዴግ ነባር አመራሮች ውስጥ ሳይቀር እየታየ ያለው መሰላቸትና ከስራ እስከ መልቀቅ የሚደርስ ተስፋ መቁረጥ፣ ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ በብልሽት ውስጥ ለመቀጠል በሚታይ መንገታገትና የማይታወቅ ለውጥን በመናፈቅ  ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ይገምታሉ፡፡   
አንድ ፓርቲ  ህዝባዊ ከሚያሰኙት ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው በፓርቲው የውስጥ አሰራር ይሁን በመንግስት ስራ ተጠያቂነትና ግልፅነትን ማንገስ መቻል  መሆኑን ኢህአዴግ  ደግሞ ደጋግሞ ማጤን ይገባዋል፡፡ የቅርብ ጊዜውን እንተወውና  ካለፉት ሁለት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ወዲህ በሀገሪቱ እየታየ ያለው ዝንባሌ የሀሳብ ነፃነትን፣ የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴን፣ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን የመገደብ አካሄድ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን  ቀላል በማይባል ደረጃ  ለመጎተት አስገድዷል፡፡ ይህ ሁኔታም በኢኮኖሚ እድገቱና በገጽታ ግንባታው ረገድ ከተገኘው ድልም በላይ እንዳንጓዝ  ከማድረጉም ባሻገር  የሀገሪቱን ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሸረሸር ያደረገ  ይመስለኛል፡፡
ከሁሉ በላይ ፓርቲው የሚታወቅበት ወስጠ ድርጅት ዲሞክራሲያዊነት፣ ለመርህ ተገዥነትና ሚስጥራዊነት እየተሸረሸረ መምጣቱ ደግሞ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በተለይ የድርጅቱን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው (አቶ መለስን) በሞት ካጣ ወዲህ ማእከላዊነት ከመላላቱ ባሻገር ወሳኝ የፖለቲካውን  የአመራር ስራ  የተረከበና ህዝቡን ለመምራት በልጦ የተገኘ ሰው በግንባሩ ያለ አለመምሰሉ፣ ሀገራዊ መተማመኑን ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ እንደ ሀገር፣ ስርአት አልበኝነትም (ብድግ ብሎ ሰልፍ መውጣት፤ ካልተስተካከለ ግብር አልከፍልም ማለት፣ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ ምርት መደበቅ … ይጠቀሳሉ)  ብቅ ጥልቅ ማለታቸዉን ቀጥለውበታል፡፡   
ብዙዎቻችን  እንደምናውቀዉ  ሙስናን የመሰሉ ችግሮችን  ከአገኘባቸው  ኢህአዴግ ከፍተኛ የሚባሉ  መስራች አባላቱን ሳይቀር የሚቀጣ  ፓርቲ  ነበር። ከቅርብ ጊዜ በፊት እንኳን “የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ሲባል እንዳልነበር፣ አሁን ላይ ደግሞ “ኢህአዴግ ፖለቲካውን አትንካበት እንጂ አይነካህም” ወይም  “ሲሾም ያልበላ…” የሚለው የዛገ አስተሳሰብ በበርካታ የፓርቲው አባላት  ዘንድ እንደ  መፈክር የሚቀነቀን ደካማ አመንክዮ ሆኖአል።
በእርግጥ ባለፉት ዓመታት ወደ ስልጣን (በየደረጃው) ተጠግተውና ተዛምደው በአጭር ጊዜ በልፅገው የሚገኙት አንዳንድ ካድሬዎችና የሚሊተሪ ሰዎች እንዲሁም በኔትወርክ የተሳሳሩ ጉዳይ ገዳዮችና ደላሎች ቁጥራቸዉ በእጅጉ  መጨመሩ ህዝቡን ቅር አሰኝቶታል፡፡ እነዚህ ወገኖች ባልሰሩበት ገንዘብ በመዝናናትና የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ከልክ አልፈዉ ሲፋንኑ የሚታዩት በአደባባይ ከመሆኑ ባሻገር ራሳቸዉን እንደ ጤነኛና የስርዓቱ ጠበቃ በመቁጠር ሲንቀሳቀሱ፤ ደግመውም ዘረፋ ውስጥ ሲገቡ  መንግስትና ህዝብ ተባብረው አለማጋለጣቸው ቁጭቱን ያንረዋል፡፡
በፓርቲው ውስጥ የተገነባው ህዝባዊ ባህሪ እያደገና ሁሉን አሳታፊ እየሆነ ብቻ ሳይሆን እየጎመራ  መሄድ ሲገባው፣ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና ፀረ-ዲሞክራሲያዊነትና የጥላቻ ፖለቲካ  አስተምህሮት እንደ ጥንጣን እየበላው ሲመጣ፣ ተደጋጋሚ ችግሮች መታየታቸው እውን ሆነ፡፡ ለዚህም ነው ስርዓቱ ቆም ብሎ ውስጡን በመፈተሽ፣ በጥልቅ ከመታደስና ወደ ህዝብ ወርዶ ከመተማመን  ባሻገር ሁሉን አቀፍ ድርድርና ምክክር በማድረግ እንደገና ሊያብብ (Rejuvenate) ይገባል የሚሉ ወገኖች አሁንም በተስፋ እየጠበቁት ያሉት።
በተለያዩ የዓለም የፓርቲ ታሪክ ውስጥ እንደሚታየው፣ የፖለቲካ ፍፁምነት የሚባል ነገር የለም፡፡ የአብዛኛውን ህዝብ እንጂ የምልዓተ ህዝብን እርካታ ከዳር ዳር ለማሟላትም የሚቻል አይሆንም። ተደጋግሞ እንደሚባለው፣ ኢህአዴግም  ቢሆን የሰው እንጂ የመላዕክት ስብስብ ባለመሆኑ ይህን ማድረግ አይችልም። ነገር ግን ሲሰራ እንደሚሳሳት የምድር ያውም ብዙ ፍላጎቶችና ድህነት በታጎረበት ምድር እንደሚመራ ሃይል፣ ራሱን በሆደ ሰፊነትና ሁሉንም የሀገሬውን ህዝብ ፍላጎት ባቀራረበ መንገድ፣ ዓለምም በደረሰበት የአስተሳሰብ ደረጃ ልክ መምራት አለበት። በመሆኑም በየጊዜው ችግሮችን እየፈተሹና እየተከታተሉ ማጽዳት፣ የእርምት እርምጃ መውሰድ የግድ ነው፡፡ ማን አለብኝነትና እየሰሙ እንዳልሰሙ መሆን ግን የትም ሊያደርስ አይችልም፡፡
በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሚሰባሰቡ አባላት፣ ምልዑ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በአንድ  ፓርቲ ውስጥ ቢያንስ ሦስት አይነት አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ የመስኩ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በጠንካራ ፓርቲ ውስጥ  እውነተኛ የህዝብ ልጆች፣ ለህዝብ ጥቅምና ለአገር ተቆርቋሪ አባላት ይበዛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የድርጅትን ስም ተላብሰው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ፣ የህዝብን አደራ የረሱ፣ የአገር ልማትና ዕድገት የማያስጨንቃቸው፣ እርስ በርሳቸው በጥቅም የተሳሰሩና የሚደጋገፉ አካላት ናቸው፡፡   
ተደጋግሞ እንደሚታየው፣ እነዚህ አካላት የመድረክ አንበሶች ናቸው። የተገኘውን መድረክ ሁሉ  ለህዝብና ለድርጅቱ ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት በመሞከር እውነተኛ ማንነታቸውን ይደብቁበታል። በመድረክ ላይ ሁሉ  ታማኝ መስለው ይቀርባሉ። ገቢራቸው ግን በተቃራኒው ነው። በሦስተኛ  ደረጃ  የሚመደቡት  ወገኖች ደግሞ  አይተው  እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ  በሁሉም ነገር መስለው ማደር የሚሹ ናቸው፡፡
እንደኔ እምነት በኢህአዴግ ቤት በአሁኑ ሰዓት  እየበዛ ያለው  ምን አገባኝ የሚለው በሦስተኛ ደረጃ የሚመደበው ወገን ይመስለኛል። እነዚህ አካላት ብዙዎቹ፣ ድርጅቱን በቅርቡ የተቀላቀሉና ልምድ የሌላቸው በመሆናቸውም የተነሳ የድርጅቱን አላማ በቅጡ አልተረዱትም። ቀላል ቁጥር የሌላቸውም ለስርዓቱ ያላቸው ውግንና ተሸርሽሮና ተስፋ ቆርጠው፣ ያልታወቀ ለውጥ የሚፈልጉ መስለዋል። የራስን ጥቅም ብቻ ማሳደድና ሳይሳካ ሲቀር፣ ማፈግፈግም ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ህዝብን ለማገልገል ሲባል የሚከፈለውን መስዋእትነት ያለመረዳትና ግለኝነት የመጠናወቱ ችግር መበራከቱ ደግሞ ከህዝብ የሚያራርቅ መጥፎ  ተግባር መሆኑን ግንባሩ ሊያጤነው ይገባል፡፡
ከዚህ አንፃር  እነዚህ  በሦስተኛዉ ማዕቀፍ የሚመደቡትን በስልጠና ብቻ ሳይሆን በግምገማና በተግባር ተልዕኮ በመስጠት ማብቃትና ማስተካከል ያስፈልጋል፤ ይገባልም። ከላይ በሁለተኝነት ያነሳናቸው በኢህአዴግ ስም የመንግስት የስራ ሃላፊነትን የያዙ አባላትና አመራሮች ላይ ግን ጥብቅ እርምጃን መውሰድ ተገቢ ነው፡፡
በመሰረቱ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የስልጣን ደረጃና የብሄር ኮፍያ ቢጫንባቸው፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የግልና የቡድናቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ፣ ህዝብና መንግስትን የሚያራርቁ አካላት  ከመቼውም ጊዜ በላይ ፀሃይ የሞቃቸውና የተጋለጡበት  ወቅት ላይ ተደርሷል። ለዚህም ነው በቅርቡ ተሃድሶ የእገሌ የበላይነት እየተባለ የብሄር ታፔላ ሲለጠፍ፣ ህዝቡ “ሌባዉ ያለው በሁላችንም ውስጥ ነው” በሚል ስም እየጠቀሰ ወደ ማጋለጥ ሲገባ የነበረው፡፡ በቅርቡ  የፀረ ሙስና 9 የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እርምጃ ላይም  ቢሆን “ትግሉ ገና ነው፣ ያልተነኩ ዘራፊዎች አሉ” እያለ ስም ወደ መዘርዘርና ሀብት ወደ መቁጠር ሲገባ የታየው፡፡
መሪው ድርጅትና መንግስት፣ እነዚህን የውስጥ ቦርቧሪዎችና የጥፋት ሃይሎች  ለማጋለጥ ብሎም  የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ በጥልቀት መታደስ አለብኝ ብሎ ላይ ታች  ሲል ከርሟል፡፡  በየደረጃው የካቢኔ አባላትን ከመቀነስና መቀያየር ጀምሮ አጥፊዎችንም የመጠየቅ ስራ እስከ አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ያም ሆኖ  የጥልቅ ተሐድሶ ሂደት ህዝቡ የሚጠብቀውን ያህል እንዳልነበር የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህ መከራከሪያ ብለው የሚያነሱት ደግሞ በመንግስት በኩል እየተወሰደ ያለው አጥፊዎችን የመመንጠር እርምጃም ሆነ የማሻሻያው ስልት፣ በስፋት ህዝቡን ያላሳተፈ ከመሆኑ ባሻገር የተነሱ ጥያቄዎችን በቅደም ተከተል ያልፈታ በመሆኑ፣ ህዝባዊ ቅሬታዎች ዳግም እያገረሹ መሆኑን ነዉ፡፡
በሌላ በኩል መንግስትና ኢህአዴግ፣ ህዝቡ ለሚያነሳቸዉ ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ የሞከሩት በራሳቸው አጥር  ውስጥ ብቻ መሆኑ ብዙኃኑን ያስደሰተ አይመስልም፡፡ ለምን ቢባል በቀዳሚነት ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ አማራጭ ሃሳቦች የሚደመጡበት የሀሳብ ነፃነት ከገደቡ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ህዝቡም ተደራጅቶም ሆነ በተናጠል ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርግ ምቹ ምህዳር ሊያገኝ ይገባዋል። በተለይ የምሁራን የአካዳሚክ ነፃነትና በሀገራዊ ጉዳይ እንዲሳተፉ አለመበረታታቱ ፈጥኖ እንዲስተካከል የሚፈልገው ወገን ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ካለውም በላይ የኢህአዴግ ተነሳሽነት ጎልቶ መታየት ይኖርበታል፡፡
   ሌላው አሁንም ኢህአዴግ ትኩረት መስጠት ያለበት የመልካም አስተዳደር የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከመታገል ባሻገር ተቀናቃኝ  ሃይሎች  በድክመቱ ላይ ተመስርተው ከህዝብ እንዳይነጥሉት መስራት ላይ ሊሆንም ይገባል፡፡ በተለይ የፌደራል ስርዓቱ ለህዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት  ያበረከተዉን አስተዋፅኦ በመፈተሽ፣ ለህዝቦች ህብረ ብሄራዊ አንድነት መጠናከርም የጎላ ሚና እንዲጫወት ሳያሰልስ መታገል ይኖርበታል፡፡  
ለዚህ ደግሞ  ባለፉት አመታት ሲቀነቀን የነበረውን ልዩነትን የማጉላትና የታሪክ ውዝግብን በመተው፣ በአንድ ወገን የህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኛነት እንዲጠናከር፣ በሌላ ወገንና በዋናነት ግን ሀገራዊ የጋራ እሴቶችና የአንድነት መልህቆች እንዲጠናከሩ በትኩረት መስራትና ህዝቡንም ማነሳሳት  ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም አሁን ያለውን የተበላ ዕቁብ አይነት  ስልት ቀይሮና  አስተካክሎ፣ ሆደ ሰፊ ሆኖ ሀገርን ለመምራት ብሎም ዲሞክራሲውን ለማጠናከር ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ይገባልም፡፡
ከወራት በፊት የተጀመረው ጥልቅ ተሐድሶ የተሰኘው የፖለቲካ አብዮትም ስንዴውን ከአንክርዳዱ የማጥራት ስራ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በሁሉም ደረጃ አጠናክሮ መቀጠል መቻል አለበት። በተለይ ተሃድሶው ጥልቅና በረጅም ጊዜ ትግል የሚፈካ ነው ከመባሉ አንፃር አሁንም ችግሮች ተሽሞንሙነው እንዳይሾልኩም ሆነ አጥፊዎች እንደ ሰጎን አንገታቸውን  ቀብረው ዳግም ለጥፋት ቀና እንዳይሉ ማድረግ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ግን አሁን ያለው የላይኛው ፖለቲካ አመራር፣ ለዘብተኝነትና  ተዛዝሎ ህዝቡ ተስፋዉ እስኪደበዝዝ ድረስ የመሄድ  ፍላጎት  ከስሩ ሊታረም  ይገባዋል፡፡
በእርግጥ  ኢህአዴግ  የቆየና የዳበረ ልምዱን ተጠቅሞ ህዝብ ላይ የተጣበቁ፣ የድርጅትን ካባ ለብሰውና የብሄር ታፔላ ለጥፈው፣ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አባላቱን ቆርጦ ለመጣል የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡም ሊያግዘው ይገባል። በተለይ በሀገራችን ምሁራንና ኢሊቱ ላይ የሚታየው አድርባይነትና መስሎ ማደርም ለአገራችን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት አደገኛ    በመሆኑ በአፋጣኝ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ነገ ዛሬ ሳይባል አሁኑኑ፡፡
በየትኛውም ደረጃ  የሚገኝ  ምሁርና ንቃት ያለው ዜጋ፣ የኢህአዴግ አባል ይሁን አይሁን  መታገል ያለበት መርህ እንዲከበር፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት ብሎም የህዝብ አገልጋይነት ባህል እንዲቀጣጠል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ከካድሬውም አልፎ በህዝቡ ውስጥ ቅቡል የሆነ መንግስታዊ  ዲስፕሊን ተስቶ፣ መሪ ድርጅቱና የመንግስት መዋቅሩ  የግል  ጥቅም ማካበቻ ከሆነ የተገነባው ይፈርሳል፣ የተሳሰረው  የህዝብ አንድነት ሁሉ  ይበጠሳል፡፡ ስለሆነም ከዚህ ያውጣን እያሉ መፀለይ ብቻ ሳይሆን በፅኑ መታገልና በእኔነት ስሜት እንዲስተካከል ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ መልክ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ቀውስ እንዲነሳና ህይወት እንዲጠፋ እንዲሁም ንብረት እንዲወድም ያደረገው፣ ግለኝነቱ እየወለደው የመጣ ጠባብ ብሄርተኝነትና ዘረኝነት  ነው። ይህንን አሽሞንሙኖም  ሆነ ደብቆ ለማለፍ መሞከር ሌላ ሰደድ እሳት ማዳፈን ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንዲህ አይነት በታኝ የሆኑ ዝንባሌዎችን መሪው ድርጅት በውስጡም በውጭም ለማረም እንቅልፍ ሊወስደዉ አይገባም፡፡   
በአጠቃላይ ኢህአዴግ ሆይ!! “የዜጎችህን ምክር ስማ፤ ህዝብንም አዳምጥ” የሚለውን መልዕክት አትናቅ፡፡ አዳምጠህም ነገ ዛሬ ሳትል  ክፍተትህን አርም፣ በተግባርም አሳይ፡፡ ህብረተሰቡ  በመልካም አስተዳደር ረገድ (የግብር ትመና፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት፣ የዋጋ ብልሽት፣ የሙስና መባባስ፣ በህገወጥነትና ማን አለብኝነት፣ በህዝብ ሀብት ወረራ…) እንዲስተካከሉለት የጠየቃቸው ነገሮች በርክተዋል። ለዚህ ደግሞ እንደ መንግስት “ትላንት  ይህን ሰርቼልሃለሁ ወይም ልማት እያፋጠንኩ ነው”  በማለት ብቻ ዜጎችን ማርካት አይቻልም፡፡ ህዝብ ዛሬን ተስተካክሎና ተረጋግቶ  መኖር እንጂ በትዝታ ብቻ ሊኖር አይችልም፤ በተለይ ወጣቱ ሃይል፡፡ ስለሆነም ለእውነተኛ ለውጥና መሻሻል መትጋት ያስፈልግሃል፡፡
በእርግጥ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት መሆኗን ተገንዝቦ ለሚታዩ ችግሮች የጋራ መፍትሄ መፈለግ ከሁሉም ወገኖች ይጠበቃል። ስለሆነም የሀገሪቱን ወቅታዊ ዕዳና ችግር ሁሉ በኢህአዴግ ላይ መጫን ብቻ ሳይሆን ይመለከታቸዋል የሚባሉ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ምሁራንና አክቲቪስቶችም በቅንነትና ሀገራዊ ስሜት መሳተፍና ለመጭው የሀገሪቱ ህዳሴ የሚረዳ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም ወገኖች  የዲሞክራሲ ምህዳርና የፖለቲካ መስተጋብር መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ የሀገሪቱ ሁሉም ወገኖች ከመገፋፋትና ጥላቻ ወጥተው፣ ለለውጥ መነሳሳት  አለባቸው የሚለው የብዙዎች ጩኸት የሚመነጨውም ከዚህ መነሻ ነው፡፡

Read 5260 times