Saturday, 21 October 2017 13:47

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

  “…ለማን አቤት ይባላል?”
                 
    ሰውየው ለስራ በሄደበት አንድ አፍሪካዊ ሀገር ኤርፖርት፣ ሰነድ ማረጋገጫ ጣቢያ ላይ ተጓዦች አስር፣ አስር ዶላር ጉቦ፣ ከሰነዶቻቸው ጋር ለተቆጣጣሪዎቹ እየሰጡ ምልክት እየተደረገላቸው ያልፋሉ፡፡ አንድ በራሱ የሚተማመን የሚመስል ሰው ግን ተራው ሲደርስ ሰነዱን ብቻ ሰጣቸው፡፡ ተቆጣጣሪዎቹም ሰነዱ ባዶ መሆኑን ሲያውቁ መለሱለትና ሌሎቹን ማስተናገድ ቀጠሉ፡፡ በሁኔታው የበሸቀው ሰውም፡-
“ምነው?” ቢላቸው መልስ አልሰጡትም፡፡
“እናንተን‘ኮ ነው የማናግረው!”
አሁንም መልስ የለም፡፡ ዞር ብሎ ያየውም አልነበረም፡፡ በጣም ተበሳጨና፤
“አለቃችሁን ማናገር እፈልጋለሁ” አላቸው፤ በቁጣ።
“ያውና” አለው አንዱ፤ ወደ አለቃቸው ቢሮ እንደ ዘበት እያመለከተው፡፡ …. ሰውየው እየተቆናጠረ ወደ ቢሮው ሲያመራ … ከኋላው፤ “የበለጠ ያስከፍልሃል!” (He will charge you more) … እያሉ ሲያሽሟጥጡት ሰማቸው፡፡ … ጉዳዩን ለአለቃቸው አስረድቶ የተሰጠው መልስ ግን የበለጠ አበሸቀው …  
“እዛው ጨርስ፣ ከነሱ ጋር ተስማማ” ነው የተባለው።
ወዳጄ፤ ሙስና ባህል በሆነበት፣ ፍትህ በቆረቆዘበት ሥርዓት ለማን አቤት ይባላል? ማንስ ይሰማሃል?
እናት ዶሮ ጫጩቶቿን አውሬ እየነጠቀ እየበላ ቢያስቸግራት ምናልባት አውራው ያግዛት እንደሆነ አስባ…
“…ትናንት፣ ትናንት አንዲቱን፣
ዛሬ ደግሞ ሁለቱን፤
ለቅሞ፣ ለቅሞ ፈጃቸው፣
መቼም አባት የላቸው፡፡”
    ብላ ስትጣራ - ቆሌ ስታጓራ
አባት ወንድ ሊመስል
       ወኔው እንዳልሸና
“እስቲ ስጪኝ ዱላውን፣
ብየው ልምጣ ጀርባውን”
ብሎ ሲጎረና …
 “አንተም. አንቱም አትዋሹ፣
አጥር፣ ላጥር ልትሸሹ፣”
    ብላ ፍርጥ አርጋ - ብትነግረው ደንግጦ
“ካልሽ ሆዴ ፈራብኝ፣
እስኪ ቅርጫት ድፊብኝ፣
ከላይ ድንጋይ ጫኚብኝ”
ብሎ ሲለምናት - ላብ በላብ ተውጦ … እያለ ይቀጥላል፡፡ (ግጥሟ የተቀነጨበችው ፑሽኪን ፅፎት አያልነህ ሙላት ተርጉሞታል ከተባለ በቃል ከተነበበ ግጥም ላይ ነው፡፡)
አውራው … እንኳን ጫጩቶቹን ሊያስጥል ለራሱ ፈርቶ የሚገባበት ጨንቆታል፡፡ … እና እቺ ምስኪን ዶሮ ለማን አቤት ትበል?
ሐረር አካባቢ አንድ ሰው ‹ገድለሃል› ተብሎ፣ ‹ሞተ› የተባለ ሰውም አስከሬን ከጉድጓድ ውስጥ ለኤግዚቢትነት ወጥቶ፣ ‹ገዳይ› ላይ ተመስክሮበት፣ በእስር ቤት ፍዳውን እያየ ሲኖር፣ ‹ሞተ› የተባለው ሰው በህይወት ተገኘ፡፡ … ይሄን ምን ትለዋለህ ወዳጄ? … ለማንስ አቤት ይባላል?
“መስቀል ከቤተ ክርስቲያን ዘርፋችኋል” የተባሉ አባትና ልጅ እንደዚሁ ‹ካላወጣችሁ እንገድላችኋለን› ተብለው መቃብራቸውን እስከ ማስቆፈር ድረስ ብዙ ስቃይና እንግልት ከደረሰባቸው በኋላ “ሌባው ተገኘ” ተብለው ተለቀቁ ተባለ፡፡ … ለማን አቤት ይባላል?
ወዳጄ፤ እንደዚህ ዓይነት ሺ ነገሮችን በሚዲያ እንሰማለን፡፡ የማንሰማቸው ደግሞ ይበዛሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት መንግስትና ህዝብን የሚያቃቅሩ ስንትና ስንት ወንጀሎች የሚፈፀሙት በራሱ “ህግ አስፈፃሚ” በሚባለው አካል ስለሆነ … ለማን አቤት ይባላል?
“ፍትህ በጥቅሉ ነፃነትን፣ ዕኩልነትን፣ መብትን፣ ግዴታን፣ ፍላጎትን፣ ቅጣትንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ወግ፣ ባህልና ልምድን ባገናዘበ መንገድ አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ካላቸው ይሁንታዎችና መርሆዎች ጋር በማስታረቅ፣ መርምረንና አገናዝበን፤ በግልና በጋራ በተመቸ መልኩ ፈቅደንና ወደን የምንተዳደርበት ስርዓት መሆኑ ቀርቶ የ”ጥቂት ሰዎች” ጥቅም ማስጠበቂያ ከሆነ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሠረትነቱ ተንዶ ጨቋኝነት ይነግሳል፡፡” ይሉናል፤ የፖለቲካ ሊቆች!!
“…ጥቁር ሆነ ነጭ፣ ወንድ ሆነ ሴት፣ አካለ ሙሉ ሆነ አልሆነ፣ የተማረ ሆነ ያልተማረ በአጠቃላይ ማንኛውም ሰው በሚኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ በማናቸውም ጉዳይ ዕኩል ዕድል፣ ዕኩል ተሳትፎ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡… እንደ ዜጋ፡፡…
“…አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ሰዎች በችሎታና በውጤት እስካልተበላለጡ ድረስ ዕኩል ደሞዝና ጥቅም፣ ዕኩል ተጠያቂነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሐብታምና ድሃ፣ ባለስልጣን ሆነ ተራ፣ ‹ዱርዬ› ሆነ አርቲስት፤ አንድ ዓይነት ጥፋት ቢፈፅሙ ወይም ተመሳሳይ ጥቅም የማስከበር ክርክር ቢኖራቸው ያለምንም አድልዖ በህግና ህግ ብቻ ይዳኛሉ፡፡ ሰዎች ሁሉ ለኔ ‹ሰው› ብቻ ናቸው፡፡… ምንም ይሁኑ ምንም። ልዩነታቸውን ላለማየት ነው አይኔን የተሸፈንኩት” ትለናች … በቀኝ እጇ ሚዛን አንጠልጥላ፣ በግራ እጇ ሰይፍ የጨበጠችው ‹ፍትህ›!! (The blind figure of Justice)…!!
ወዳጄ፤ “ህግ ማንም ዳቦ እንዲሰርቅ፣ በየድልድዩ ስር እንዲተኛ፤ በየመንገዱ እንዲለምን አይፈቅድም” (The law in its majestic equality, forbids the rich as well as the poor to sleep under bridges, to beg in the streets and to steael bread) ይለናል አናሌ ፍራንስ፡፡… ድህነት የጭቆናና የመብት መጓደል ውጤት ነው እንደማለት ይመስላል፡፡
“መብት የፍትህ ፍቺ ዋና መገለጫ ነው” ይላሉ ሊቃውንት፡፡ መብት ስንል እኛነታችን በግል ወይም ከማህበረሰብ ጥቅም አኳያ ግዴታዎቻችንንም ጨምሮ የምንስማማባቸው፣ እንደ ትራፊክ ህግና የመሳሰሉት የሚከበሩበት፣ የመምረጥ፣ መመረጥ፣ የመናገር የመፃፍና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች የታቀፉበት (Civil) እንዲሁም ያለመደብደብ፣ ያለፍርድ ያለመታሰርንና የመሳሰሉትን የሚያካትተው ተፈጥሯዊ በረከታችን ማለታችን ነው፡፡
እነዚህ መብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበቱ፣ የግለሰብ ማንነትን በማጉላት፣ ፍላጎቱና ነፃነቱ እንዲከበርለት የሚያግዙ ሁኔታዎች ቢመቻቹም አሁን በምንገኝበት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የተሻለ ነፃነትና ደህንነት የሚገኘው በማህበራዊ አስተዳደር ጥላና አንድነት መርሆዎች ራስን አስገዝቶ፣ የጋራ ጥቅም ተካፋይ በመሆን ነው የሚሉ አያሌ ናቸው፡፡
ግለሰባዊ ማንነትን የሚያስበልጠውን አስተሳሰብ የሚከተሉ ወገኖች ምክንያቶቻቸው ከብዙ በጥቂቱ፡-
የመንግሥትንም ሆነ   የማንንም ጣልቃ ገብነት (በኑሯቸው) ይቃወማሉ፡፡
ባፈራነው ንብረት የመወሰን መብት የራሳችን ብቻ ነው ይላሉ፡፡
የግብር (tax) አስፈላጊነትን አይቀበሉም፣ የተማከለ ትልቅ መንግሥትን የበላይነት አይፈልጉም፡፡
ይህን አስተሳሰብ ሊበርታርያኒዝም (Libertarianism) ይሉታል፡፡ ሁለተኛዎቹ፤ የግለሰብ ጥቅምና ደህንነት ዋስትና የሚኖረው ለማህበራዊ ኑሮ (Social affairs) ተገዢ ሲሆን ነው፤ ለዚህም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት መኖር አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ የሊበራሊዝም (Liberalism) አስተሳሰብ በብዙ ቦታዎች በስራ ላይ ውሎ ታይቷል፡፡
ሌላው፤ ሶስተኛው አቀራረብ፣ ኮምዩኒቴሪያኒዝም (Communicterianism) የሚሰኘው ሲሆን ሰው መመዘን ያለበት በግለሰብዓዊ መብት ሳይሆን በስራው በሚያበረክተው አስተዋፅዖ ሊሆን ይገባል፣ ሰው ሙሉ ለሙሉ ተገዥነቱ በጋራ ለሚያቋቁመው ማህበር ወይም መንግሥት ካልሆነ እሱነቱ የለም፤ “ላገሬ ምን ላድርግላት እንጂ አገሬ ምን ልታደርግልኝ ትችላለች?” ብለህ አትጠይቅ ባይ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በብዙ መልኩ ቶታሊታሪያኒዝም (totalitarianism) ወይም ፋሽዝም (Fascism) ወደሚባለው ፍልስፍና ያደላል፡፡ ሙሶሎኒ “The Doctrine of Fascism” በሚለው መፅሃፍ ይህንኑ አረጋግጧል፡፡
እና ወዳጄ፤ ወደ መነሻችን እንመለስና አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡፡፡ ዜጎች የበድንነት ባህሪ (Zombie) ማሳየት ከጀመሩ ፍትህ ኪሳራ ውስጥ የመውደቋ ምልክት ነው።… ያኔ አቤት የምትልበት ቦታ ስለማይኖር ተጠንቀቅ!! ሠላም!!

Read 1050 times