Saturday, 21 October 2017 13:52

“የኢትዮጵያ ፍልስፍና” አዲስ አቀራረብ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(5 votes)

    ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ባለፈው እሁድ ጥቅምት 5፣ 2010 ዓ.ም ሚዩዚክ ሜዴይ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ላይ ያዘጋጀው ውይይት ነው፡፡ መቼም ስለ ራስ መፃፍ በሀገራችን ባህል ውስጥ የተለመደ ባይሆንም፣ ለዛሬ ይሄንን ባህል እንድተላለፍ ይፈቀድልኝና በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ላልነበሩ ሰዎች “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ይዞት የመጣውን አዲስ ነገርና ውይይቱ ላይ የተነሱትን አንዳንድ ነገሮች ላካፍላችሁ፡፡
ስለ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት እንድናወራ የሚያስገድደን በርካታ ምክንያቶች አሉን፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ የመጀመሪያው ማህበረሰባችን የጣለውንና ያዋረደውን ሥጋዊና ዓለማዊ ህይወቱን ለማንሳት ሙከራ ያደረጉ የመጀመሪያ ባለውለታዎቻችን መሆናቸው ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች በአፍሪካ ውስጥ በፅሁፍ የተዘጋጁ የመጀመሪያዎቹ የፍልስፍና መፅሐፍ መሆናቸው ነው፡፡ ይሄም በሀገር የተቆርቋሪነት ሚዛን ከተለካ በኩራት የሚያስኮፍሰን ነው፡፡ ከዚህ ሐቅ በመነሳት “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፍልስፍና መነሻ ነች” የሚሉ አሉ፡፡
የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ ታትመው በአውሮፓ ከተሰራጩ ጀምሮ አነጋጋሪነታቸው ጨምሯል፡፡ የተለያዩ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ምሁራን በእነዚህ ፈላስፋዎች ላይ በርካታ ወረቀቶችንንና መፃህፍትን ፅፈዋል፡፡
ለምሳሌ ከኢትዮጵያውያን ምሁራን ውስጥ እንኳ የቅኔ መምህሩ የኔታ አለማየሁ ሞገስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ መመረቂያ ፅሁፋቸውን በ1961 ዓ.ም የፃፉት Hatata Za-Zara Yaëqob, Ethiopian Philosopher በሚል ርዕስ ነው፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ ኪሮስም  እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም Zara Yacob. A 17th Century Rationalist: Philosopher of the Rationality of the Heart የሚል መፅሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፤ በዚሁ መፅሐፋቸው ውስጥም ”የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና የዓለም የአብርሆት (Enlightenment) አካል ነው” ብለውታል፡፡ አባ ዳዊት ወርቁ ደግሞ እ.ኤ.አ በ2012 የዶክትሬት ፅሁፋቸውን The Ethics of Zara Yaëqob: A Reply to the Historical and Religious Violence in the 17th Century በሚል ፅፈዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ጥናት በማድረግ (6 ቅፆችን በማዘጋጀት) ካናዳዊውን ፕ/ር ክላውድ ሰምነርን የሚያክል የለም፡፡ በንጉሱ ዘመን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፍልስፍና ሲያስተምሩ በነበሩት ፕ/ር ክላውድ ሰምነር ከተዘጋጁት ከእነዚህ ስድስት ቅፆች ውስጥ ቅፅ-2፣ ሁለቱን የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎችን እንደወረደ የያዘ ሲሆን የዘርዓያዕቆብን የዜግነት ጭቅጭቅም ያካተተ ነው፡፡ ቅፅ-3 ደግሞ የሐተታዎቹ ትንታኔ የቀረበበት ነው፡፡
ክላውድ ሰምነር የሀገራችንን የፍልስፍና ታሪክ በሁለት ዘመን ይከፍሉታል - ብሉይና ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና በማለት፡፡ ሰምነር ብሉይ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚሉት ጥንት በውጭ ሀገር ፀሐፊዎች ተፅፈው ወደ ግዕዝ ቋንቋ የተተረጎሙትን የፍልስፍና ሥራዎችን ሲሆን ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚሉት ደግሞ የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ሕይወት ሐተታዎችን ነው፡፡
ሌላው በውይይቱ ላይ የተነሳው ሐሳብ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው አዲስ መፅሐፍ፣ የሀገራችንን ፍልስፍና በተመለከተ እስከ ዛሬ ድረስ ከነበረው አቀራረብ ምን የተለየ ነገር አለው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
የክላውድ ሰምነር “ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና“ አቀራረብ ሁለት ውስንነቶች አሉበት። የመጀመሪያው ውስንነት፣ ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ሕይወትን ከሀገሪቱ የቆየ ልማድ፣ ባህል፣ እምነትና ታሪክ ነጥሎ መመልከቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ውስንነት ደግሞ፣ 17ኛው ክ/ዘ ላይ የተነሳው “ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና“ ወደ ኋላ ከጥንታዊ አክሱም ገናና ሥልጣኔ መዳከም ጋርና ወደፊት ደግሞ በ19ኛው ክ/ዘ ከሚጀመረው የነገሥታቱ የዘመናዊነት (ሀገር የማዘመን) ፕሮጀክት ጋር ያለውን የመንፈስ ትስስር ማሳየት አለመቻሉ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው መፅሐፍ እነዚህን ሁለት ውስንነቶች የሚቀርፍ ነው፡፡
ፍልስፍና በባህሪው ደረቅ ያለና በአብዛኛውም ሰማይ ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ግን ወደ መሬት አውርደውታል። የአንድ ሀገር ፍልስፍና ከሀገሪቱ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና ሥነ ፅሁፍ ጋር ተለንቁጦ ሲቀርብ ደግሞ ውበትና ወዝ ይኖረዋል፡፡ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ እኔም ይሄንን ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህም መሰረት የ17ኛው ክ/ዘ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ወደ ኋላ ከአክሱም ስልጣኔ መዳከምና ከማህበረሰባዊ የብሕትውና ታሪካችን ጋር፣ ወደፊት ደግሞ ከከሸፉት የነገስታቱ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ጋር ለማስተሳሰር ሞክሬያለሁ፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው የኢትዮጵያን ፍልስፍና (ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ህይወትን) ከሀገራችን ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ሥነ ፅሁፍ ጋር ለንቁጬ ያቀረብኩት፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ኪሮስ በበርካታ ትንታኔዎቻቸው ላይ ዘርዓያዕቆብን ከፈረንሳዊው ፈላስፋ ዴካርት ጋር እያነፃፀሩ አቅርበውታል፡፡ ሆኖም ግን ዘርዓያዕቆብ ከዴካርት ጋር ሊነፃፀር የሚችለው ከሥነ ዘዴ (Philosophical Method) አንፃር እንጂ ከይዘት አንፃር አይደለም፡፡ ከይዘት አንፃር የዘርዓያዕቆብ የሜታፊዚካል ፕሮጀክት በጣም በአስገራሚ ሁኔታ የሚመሳሰለው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን የጀርመን ሐሳባውያን ፈላስፎች (ሼሊንግና ሄግል) ጋር ነው፡፡ ከዚህ መፅሐፍ አበርክቶዎች ውስጥ ትልቁና ዋነኛውም ይሄው ነው - በ17ኛው ክ/ዘ የኢትዮጵያ ፍልስፍናና በ19ኛው ክ/ዘ የጀርመን ሐሳባዊ ፍልስፍና መካከል ያለውን ዲበ አካላዊ ተመሳስሎ ማሳየት መቻሌ ነው፡፡
በተለይ “የዘርዓያዕቆብ አዲስ የማስተማሪያ ዘዴ” እና “የፈላስፎቹ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ፍለጋ” የሄዱባቸው ድካሞች ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት እንዴት ከጥንቱ የገዳማቱ ሥርዓተ ትምህርት አፈንግጠው እንደወጡና የሥነ ሰብዕ (Humanities) ትምህርት ይዘት ያለው ሌላ ተገዳዳሪ ሥርዓተ ትምህርት ለማቅረብ ያደረጉትን ጥረት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመፅሐፉ ውስጥ ይህ ትንታኔ የቀረበው በመጀመሪያ በንባብ ቤት፣ በዜማ ቤት፣ በቅኔ ቤትና በትርጓሜ ቤት ውስጥ ያሉት የጥንቱን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በዝርዝር ከተዳሰሱ በኋላ ነው፡፡ ይሄም ለአንባቢዎች ስለ ጥንቱ የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ያስችላቸዋል፡፡
ሌላው በውይይቱ ላይ ከፍተኛ ክርክር የተደረገበት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም የኢትዮጵያን የኋልዮሽ ጉዞ ለማሳየት ያደረጉት ሙከራና ይህ ሐሳባቸው “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ውስጥ የተካተተበት መንገድ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በሃገራችን ታሪክ ውስጥ በጣም እንቆቅልሽ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ የኋላ ቀርነታችን መንስኤው እስከ አሁን አለመጠናቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሄንን ነገር ለማጥናት ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ይሄንን ሙከራ ካደረጉ ምሁራኖቻችን ውስጥ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋና እና ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው በ2002 ዓ.ም ላይ “አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት“ የሚል ትምህርት ይዘው መጡ። ይህ ትምህርት ሀገራችን የቁልቁለቱን ጉዞ መቼ እንደጀመረችው ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ እንግዳ ትምህርት እየተብሰለሰልኩ እያለሁ፣ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም ደግሞ በ2005 ዓ.ም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ“ በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ የታሪክ ምሁራኖቻችን የኢትዮጵያን የታሪክ ክሽፈት (ለምሳሌ የሥራ መሳሪያዎቻችንና ኑሯችን ላይ ለዘመናት ለውጥ አለመታየቱ) ለማጥናት አለመነሳሳታቸውን በወቀሱበት ቦታ ላይ የክሽፈታችንን መንስኤ “እንደ ማህበረሰብ የብሕትውና ህይወትን መምረጣችን ሳይሆን አይቀርም“ የሚል መላምት አስቀመጡ፡፡
ይህ የዶ/ር ዳኛቸው ሐሳብ እና የፕ/ር መስፍን መላምት ለኔ ትልቅ ትርጉም ነበረው፡፡ አሁን ላይ ድሃና ኋላቀር መሆናችን የኋላ ታሪካችንና ባህላችን ላይ የተበላሸ ነገር እንዳለ በግልፅ ይመሰክርብናል። እነዚህ ሁለት የሀገራችን ምሁራን የአሁኑን የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት ምንጭ በተመለከተ ወደ ኋላ የታሪክ ዱካዎችን ተከትለው ሄደው ባህላችን ውስጥ የተበላሸውን ነገር ለማሳየት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህ አካሄዳቸው ከአንድ ግዙፍ ከሆነ እውነታ ጋር የሚያጋፍጣቸው ሆነና ወደ ኋላ አፈገፈጉ፡፡ በዚህም ዶ/ር ዳኛቸው “ሐሳቡን ትቼዋለሁ” ሲሉ፤ ፕ/ር መስፍን ደግሞ “ይሄንን ማጥናት የታሪክ ምሁራኖቻችን ድርሻ ነው” በማለት ኃላፊነታቸውን ለታሪክ ምሁራኖቻችን አስረክበው አለፉት፡፡ እናም የሀገራችንን ኋላ ቀርነት የኋላ መንስኤውን “ሊነግሩን ነው” ብለን ተስፋ አድርገን ስንጠብቃቸው እነሱ ግን አንጠልጥለውት ሄዱ። እነሱ ጀምረውና አንጠልጥለው የተውትን ነገር እኔ ጨረስኩት፡፡ በመፅሐፌ ውስጥ “የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ ለምን እንደ አውሮፓዊው አቻው ዘመናዊ ማህበረሰብን መፍጠር ተሳነው?” የሚለው ምዕራፍ፣ ዶ/ር ዳኛቸውና ፕ/ር መስፍን ጀምረውና በእንጥልጥል የተውት ፕሮጀክት ፍፃሜውን የሰጠሁበት ፅሁፍ ነው፡፡
በጣም የሚገርመውም ነገር ደግሞ ይህ የዶ/ር ዳኛቸውና የፕ/ር መስፍን ሐሳብ በስውርም ቢሆን የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ፍልስፍናዎች ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ እኔም በዚህ  መፅሐፍ ላይ በትንታኔ ያወጣሁት ይሄንን ሐሳብ ነው፡፡ ይህ የዶ/ር ዳኛቸውም ሆነ  የፕ/ር መስፍን ሐሳብ፣ እንዲሁም እነ ዘርዓያዕቆብ አጥብቀው ሲኮንኑት የነበረው ማህበረሰባዊ የብሕትውና ባህል ሁሉ ወደ ኋላ ወደ 6ኛው ክ/ዘ ተጉዤ ታሪክን (በተለይም የሀገራችንን ማህበረሰባዊ የብሕትውና ጉዞ) እንድበረብር  አድርጎኛል፡፡
6ኛው ክ/ዘ ከ9ኙ ቅዱሳን መነኮሳት መምጣትና ከቅዱስ ያሬድ መነሳት ጋር ተያይዞ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሥነ ፅሁፍና የኪነ ጥበብ ዘመን ሆኗል፡፡ በዚህ ዘመን ላይ የተጀመረው የምንኩስና ባህል በባህሪው “ምድራዊ የበላይነትን መቀዳጀት” በሚል መርህ ላይ ከተመሰረተው የአክሱማውያን ሥልጣኔ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነበር፡፡ የዶ/ር ዳኛቸውን፣ የፕ/ር መስፍንን፣ የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ሕይወትን ሐሳቦች በአንድነት ተገምደው የምናገኛቸው እዚህ የ6ኛው ክ/ዘ ቅራኔ ላይ ነው፡፡ ባጭሩ፣ የኔ አዲሱ አቀራረብ 6ኛውን ክ/ዘ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ አድርጌ አምጥቸዋለሁ። ለዚህም ነው የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና፣  በሁለት ዘመኖች (በ6ኛውና በ17ኛው ክ/ዘ) መካከል የተደረገ ፍልስፍናዊ ንግግር (Philosophical Conversation) አድርጌ ያቀረብኩት፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሐፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 3195 times