Saturday, 21 October 2017 14:01

“ጊዜ ኮንሰርት 2” የፊታችን እሁድ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 - ለናይጀሪያዊው አቀንቃኝ ከነባንዱ 200 ሺ ዶላር ተከፍሎታል
        - በኮንሰርቱ 20 ሺህ ታዳሚ እንደሚገኝ ይጠበቃል

    ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከዳኒ ዴቪስ ጋር በመተባበር “ጊዜ ኮንሰርት 2” የፊታችን እሁድ ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ፣ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ ይካሄዳል፡፡ ዊዝኪድ ለተሰኘውና በኮንሰርቱ ላይ ከኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ጋር ለሚያቀነቅነው ናይጄሪያዊ ዘፋኝ፤የትራንስፖርቱንና የባንዱን ወጪ ጨምሮ 200 ሺህ ዶላር የተከፈለው ሲሆን በአጠቃላይ ለኮንሰርቱ ከ7 ሚ. ብር በላይ መውጣቱን የጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ነብዩ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
 ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ ኮንሰርቱን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ አንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ፣ አብዱ ኪያር፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ዘሪቱ ከበደና አስገኘሁ አሽኮ (አስጌ ደንዳሾ) የተገኙ ሲሆን ለኮንሰርቱ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በናይጄሪያ የተወለደውና በአፍሮ ፖፕ፣ በአፍሮ ቢት፣ በሬጌ ዳንሶልና ሂፕሆፕ ስልቶች አለም አቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፈው የ27 ዓመቱ ወጣት ድምጻዊ አይወደጂ ኢብራሂም (ዊዝ ኪድ)፤ ከ11 ዓመቱ ጀምሮ ነው ወደ ሙዚቃ የገባው፡፡ በቢት አዋርድ፣ ቢልቦርድ፣ ሚዩዚክ አዋርድ፣ MTV እና በሌሎችም ሽልማቶች አሸናፊ የሆነው ዊዝ ኪድ፤ ከእነ ሙሉ ባንዱ የሚመጣ ሲሆን አንጋፋው ድምጻዊ  አሊ ቢራ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ አብዱ ኪያር፣ ሚካኤል በላይነህ፣ አብነት አጎናፍር፣ አብርሃም ገ/መድህንና አስጌ ደንዳሾ እያንዳንዳቸው ለ30 ደቂቃ እንደሚያቀነቅኑ ተገልጿል፡፡ ሚካኤል በላይነህና ዘሪቱ ከበደ በዘመን ባንድ የሚታጀቡ ሲሆን አስጌ ደንዳሾ እና አብዱ ኪያር በመሀሪ ብራዘርስ ባንድ እንደሚታጀቡና ዝግጅታቸውን መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ በሚቀርበው ኮንሰርት ላይ 20 ሺህ ታዳሚ እንደሚጠበቅ የገለፀው ጆርካ ኤቨንት አርጋናይዘር፤የመግቢያ ትኬት በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች፣ በሸራተን ሆቴል እና በተለያዩ ቦታዎች መሸጥ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

Read 2740 times