የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለቀጣዩ ሁለት ዓመታት ምክር ቤቱን የሚመራ የፕሬዚዳንት፣ የምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ምርጫ ያካሄደ ሲሆን የአማራ ክልል የንግድና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤትን የወከሉት ኢ/ር መላኩ እዘዘው፤ 87 ድምፅ በማግኘት በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል፡፡
ም/ቤቱ 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ትላንት በሂልተን ሆቴል ያካሄደ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 18 የንግድ ም/ቤት አባላት መካከል 17ቱ ለምርጫው እጩዎችን አቅርበው ነበር፡፡ ኢ/ር መላኩ ቀደም ሲል የጎንደር ከተማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን ለአራት አመት በፕሬዚዳንትነት የመሩ ሲሆን በአሁን ሰዓት ደግሞ የክልሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ኢ/ር መላኩ ከ17 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋካልቲ በኤሌክትሪካል ኢኒጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን ከስድስት ዓመት በፊት ደግሞ በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስቴሬሽን ኤንድ ስፔሻላይዜሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ኢ/ር መላኩ ለሁለት አስርተ ዓመታት ገደማ በንግድ ስራና ክህሎት ላይ ያሳለፉ ሲሆን በኤሌክትሪካል ምህንድስናና በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በኮምፒዩተር ስልጠና፣ ጥገናና ሽያጭም ለተወሰኑ ጊዜያት ሰርተዋል፡፡ ኢ/ር መላኩ ከዚያ ቀጥለው በተለያየዩ የስራ መስኮች በጎንደር ከተማ የሚገኝ “ቤተ - መላኩ” የተሰኘ የሪል ስቴት፣ የተሽከርካሪ ማሰልጠኛና የትራንስፖርት ንግድ ባለቤት ናቸው፡፡
የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፈይሳ አራርሳ የኢ/ር መላኩ ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበሩ ቢሆንም በ12 ነጥብ ተበልጠው ሳያሸንፉ ቀርተዋል፡፡
በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የትግራዩ አቶ አስፋ ገ/ስላሴ ሲሆኑ ም/ቤቱ በአጠቃላይ 1 ፕሬዚዳንት 1 ም/ፕሬዚዳንት እና 9 የቦርድ አባላት በድምሩ 11 አመራሮችን መርጧል፡፡ የዘንድሮውም ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና መጠናቀቁን የሚናገሩት ታዛቢዎች አድንቀቅታል፡፡
Sunday, 29 October 2017 00:00
ኢ/ር መላኩ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት አዲስ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ
Written by ናፍቆት ዮሴፍ
Published in
ዜና