Sunday, 29 October 2017 00:00

የኢሊባቡር ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

· በግጭቱ 20 ሰዎች ሲሞቱ፤ 2500 ተፈናቅለዋል
· ግጭት በማነሳሳት 240 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል
   ባለፈው እሁድ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቡር ዞን ቡኖ በደሌ ወረዳና ሌሎች ወረዳዎች በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች፤ ከረቡዕ ጀምሮ ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ሲሆን በዞኑ ግጭቱን በማነሳሳት የተጠረጠሩ 240 ግለሠቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ከረቡዕ (ጥቅምት 15) ጀምሮ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ሃላፊዎች፣ ግጭቱ በተከሰተበት ሥፍራ በመገኘት ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸው ታውቋል፡፡ በቡኖ በደሌ ዞን 4 ወረዳዎች፣ 2500 ያህል ሰዎች በግጭቱ መፈናቀላቸው የተጠቆመ ሲሆን ፣ 52 ቤቶች እንደተቃጠሉና 20 ሰዎች እንደሞቱ በጉብኝቱ ወቅት ማረጋገጣቸውን፣ አቶ ንጉሱ አስረድተዋል፡፡
በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ፣ የአማራና የትግራይ ብሄር ተወላጆች በአካባቢው እንዲሰፍሩ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ንጉሱ፤ ከአካባቢው የኦሮሞ ህዝብ ጋር ተዋልደው፣ ባህል ለባህልም ተወራርሰው፣ በአንድነትና በመተሳሰብ የሚኖሩ ህዝቦች እንደሆኑ ተረድተናል ብለዋል፡፡ በግጭቱ ወቅትም በአማራ ብሄረሰብ አባላት ላይ የሚደርስ ጥቃትን ሲከላከሉ ጉዳት የደረሰባቸው የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላትን መመልከታቸውንም አቶ ንጉሱ ይናገራሉ፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በግጭቱ የተፈናቀሉ የአማራ ብሄር ተወላጆች በሰጡት አስተያየት፤ “እኛ የኦሮሞ ህዝብ ጥላ ከለላችን ነው፡፡ ህዝቡ ባይከላከልልን ኖሮ ከባድ ጉዳት ይደርስብን ነበር፤ ያዳነን የኦሮሞ ህዝብ ነው” ማለታቸውን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ የተሣተፉ የአካባቢው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በበኩላቸው፤ “በእናንተ የመጣ በእኛ የመጣ ነው፤ የእናንተ ችግር የኛ ችግር ነው፤ አብረናችሁ የመጣውን እንመክታለን፣ የፈረሰውን እንጠግናለን፣ የተዘረፈውን እናስመልሳለን፤ አብረን እስከ መጨረሻው እንዘልቃለን” በማለት አብረዋቸው ለዘመናት ለኖሩ ወገኖቻቸው፣ አለኝታነታቸውን መግለፃቸውን ኃላፊው መስክረዋል፡፡
“ግጭቱ በህብረተሰቡ መካከል የተነሳ አለመሆኑን እንዳረጋገጡ የጠቆሙት ኃላፊው፤ “ከሌላ አካባቢዎች ጭምር ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ፣ የጥላቻ መልዕክት ያላቸው ወረቀቶችን በመበተን የህብረተሰቡን ሰላም ለማወክ የሚደረግ ጥረት እንዳለ ተረድተናል፤ የክልሉ መንግስትና የአካባቢው ህዝብ አደጋውን ለመቀልበስ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ተገንዝበናል” ብለዋል፡፡  
ከውይይቱ በኋላም ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ መስማማታቸውንና ከረቡዕ ጀምሮ በተለይ ከበደሌ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸውን፣ እስካሁንም 2099 ተፈናቃዮች መመለሳቸውንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “ከእንግዲህ የሁለቱን ብሄረሰቦች ወንድማዊ ትስስር ለማላላት የሚደረግ ጥረት ዋጋ ያስከፍላል” ብለዋል፤ አቶ ንጉሱ፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ለተፈናቃዮች ፈጥኖ በመድረስ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የሌሊት ልብሶችና የድንኳን መጠለያ በማቅረብ፣ እንክብካቤ ማድረጉን ማረጋገጣቸውን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ፤ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን የህዝቡን አንድነትና ሰላም መልሶ ለመገንባት እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቤታቸው ለፈረሰባቸውም የአካባቢው ህዝብ በርብርብ ቤቶቹን መልሶ እየገነባ መሆኑን አቶ ንጉሱ ገልፀዋል፡፡  
የክልሉ መንግስትም ለተፈናቃዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ለቀጣይ ኑሮአቸውም ዋስትና እንደሚሰጣቸው ማረጋገጫ ማግኘታቸውንም ኃላፊው አስታውቀው፤ የአካባቢው ሚሊሻና የፀጥታ አስከባሪ አካላትም ሰላም ለማስከበር እየሰሩ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል- ኃላፊው፡፡

Read 2930 times