Sunday, 29 October 2017 00:00

ሰማያዊ ፓርቲ ነገ ህዝባዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ ያካሂዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

ሳምንት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅዷል

   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ወዲህ በመዲናዋ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በተደጋጋሚ ቢሞክርም ከመስተዳደሩ ዕውቅና ባማግኘቱ ማድረግ አለመቻሉን ሰማያዊ ፓርቲ፤ ነገ ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ መብራት ኃይል አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያካሂድ ያስታወቀ ሲሆን በሳምንቱም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል፡፡
በነገው እለት ፓርቲው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር እገናኝበታለሁ ባለው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተሳታፊዎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳባቸውን በነፃነት እንደሚያንሸራሽሩ የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ከፓርቲው በቀጥታ የሚቀርብ አጀንዳ እንደማይኖር የጠቆሙት አቶ ጌታነህ፤ ተሳታፊዎች በወቅቱ የሀገሪቱ ችግሮች ዙሪያ አስተያየታቸውን፣ ስጋታቸውንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ይገልፃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ታዋቂ ምሁራንና አንጋፋ ፖለቲከኞች እንደሚገኙ የገለፁት ም/ሊቀመንበሩ፤ ህዝባዊ ስብሰባው ከአዲስ አበባ አስተዳደር ህጋዊ እውቅና መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
ሰማያዊ፣ በቀጣዩ ሳምንት ጥቅምት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ያቀደ ሲሆን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ “ከሰሞኑ በኦሮሚያ በኢሊባቦር በቡኖ በደሌ ዞንና በጮራ፣ በዴጋና በገቺ ወረዳዎች ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት የተከሰተው በስርአቱ ካድሬዎች ስውር ቅስቀሳ ነው” ብሏል፡፡
በካድሬዎች ስውር ቅስቀሳ ስለመፈፀሙ ምን ማስረጃ አላችሁ ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት የፓርቲው አመራሮች፤ መንግስት ራሱ ጥቅማቸው የተነካ ኪራይ ሰብሳቢዎች የፈጠሩት ነው ማለቱን በአስረጂነት ጠቅሰዋል፡፡
በሥርአቱ ላይ የህዝብ ቅሬታና ጥላቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለው እንደሚያምኑ የገለፁት አመራሮቹ ገዥው ፓርቲ ይህን ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ የራሱን አወቃቀር በመገምገም ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ስልጣኑን ለህዝብ ለማስረከብም በመጀመሪያ በራሱ ተነሳሽነት ከህዝብና የሀገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ የታጠቁም ሆነ ያልታጠቁ ቡድኖች ጋር ድርድርና ውይይት ማካሄድ አለበት ብለዋል-የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ፡፡  

Read 3647 times