Sunday, 29 October 2017 00:00

የጦቢያ ኋላ ቀር ፓለቲካ!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የሚፈለገውና የማይፈለገው ምንድነው?

  በአሁኑ ወቅት ብዙ የሚያስገርሙና የሚያስደነግጡ ነገሮችን እናያለን እንሰማለን። ይህም ባልተማሩም፣ በመማር ላይ ባሉም፣ በተማሩም፣ በሐሳብ አመንጭዎችም፣ በሐሳብ አንሸራሻሪዎችም፣ በሐሳብ አራማጆችም፣ አራጋቢዎችም ...የማየው ስህተት የሚመስል ክስተት ነው። ወዳጆቼን እንዳላስቆጣ ነገሩን በቅድሚያ በውጭ ምሳሌ ላቅርበው።
በአሜሪካ በርካታ የፖለቲካ ፖርቲዎች ሲኖሩ፣ ዋናዎቹ ዴሞክራቲክ ፓርቲና ሪፐብሊካን ፓርቲ ናቸው። ሁሉም ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች አሏቸው። በየአራት ዓመቱም ምርጫ ያካሂዳሉ። አሸናፊው ፓርቲ ስልጣን ይይዛል። ከምርጫ በኋላ መሪው ብቃት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል።  ችግር ካለበት ተቃዋሚዎችም ደጋፊዎችም ተቃውሟቸውን በልዩ ልዩ መንገዶች ይገልጣሉ። ፓርቲው ድጋፉን ከነፈገውና አስነዋሪ ነገር ከተገኘበት ከስልጣኑ ይለቃል። አለበለዚያ ተቃዋሚ ስለተንጫጫ ብቻ ስልጣኑን አይለቅም። አስፈላጊ ከሆነ ለሁለተኛ ጊዜ ሊመረጥ ይችላል። ለምሳሌ ኦባማ እንደተመረጡ ከፍተኛ ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን ውርደትም ደርሶባቸዋል። ግን በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት 8 ዓመት በስልጣን ላይ ቆዬ። ትራምፕም የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክሎ ተመረጠ። ከተቃዋሚዎቹ ጎራ ውርጅብኝ እየወረደበት ነው። በዚህ መሠረት ችግሩ የመሪው እንጂ የፓርቲው አይሆንም። የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት አይነካም። ዳሩ ግን ኮንግረሱ እስካላወረደውና እስካልተካው በስልጣን ላይ ይቆያል። ሪፐብሊካን ፓርቲ ይውረድ፣ ዴሞክራቲክ ይውጣ ብሎ ነገር የለም። በአንዱ ፓርቲ መቃብር፣ ሌላው ስልጣን ለመያዝ አይመኝም። ፓርቲ እንደ ማስቲካ አይታኘክም። ለፓርቲውም ለአባላቱም ክብር አላቸው። የህዝብ ድምፅ ዋጋ አለው።
በእንግሊዝም፣ በፈረንሳይም፣ በጀርመንም... የፓርቲ ብዛት ቢኖርና በሚከተሉት ፍልስፍና ቢለያዩም አሠራራቸው ተመሳሳይ ነው። በፓርቲዎች መካከል መከባበር አለ። በአንዱ ህልውና እንጂ በአንዱ መቃብር ሌላው ስልጣን ለመያዝ አይመኝም። አብርሃም ሊንከን፤ አገር ላፍርስ የሚል ጀኔራል ሊ የተባለ ጦረኛ ተቀናቃኝ ሲነሳባቸው፤ “የመርከቧን መሪ ለመያዝ፣ መጀመሪያ መርከቧ መኖር አለባት” ነበር ያሉት። ሌሎችም በመጀመሪያ ለሀገራቸው ህልውና ይጥራሉ እንጅ በወቅታዊ የስልጣን ጥም ሰክረው አገር ትውደም አይሉም።
እኛስ ቤት? እኛ ቤትማ… ከራሳችን በስተቀር ሌላው እንዲኖር አንፈልግም። ሁላችንም ለራሳችን ትክክል ስንሆን፣ ከኛ ውጭ ያለው ስህተት ነው። ይህም አመለካከት በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታችንም፣ በባህላችንም፣ በኑሯችንም ይንጸባረቃል። ካልተማረው ጀምሮ አንቱ እስከተባለው ምሁር፣ ሥራ ከሌለው እስከ ባለስልጣኑ፣ ከድሃው እስከ ቱጃሩ፣ ከአንባቢው እስከ ጸሐፊው፣...ይንጸባረቃል።
ከዚህም በላይ ቆርጦ መቀጠሉ፣ ስም ማጥፋቱ፣ አሉባልታው፣ ፈጠራው፣ ... ብዙ ነው። ፓርቲው ሲሰደብበት ዝም የሚል ወይም የሚፈራ የሚመስላቸው የዋሆቹ መሃይማቱ ብቻ አይደሉም፣ ምሁራኑም ጭምር ናቸው። ለምሳሌ ቅይጥ ፓርቲ የሚባል ቢኖርና ባይወዱት “ዓይንህን ላፈር” ይሉታል። አባላቱን፣ ደጋፊዎቹን፣ ጥቅመኞቹ፣ ድርጅታዊ አቅሙን፣ ወዘተ ከግምት ውስጥ አያስገቡም። ብቻ ይውደም ነው። መውደሙንስ እንደ ምኞት ይውደም። እንዴት? ለሚለው እንኳን መልስ የላቸውም። የአንዳንዶቹ መሣሪያ ከምላሳቸው ቀጥሎ ተአምር ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ እነሱ ሲወረውሩበት ደረቱን ገልብጦ የሚሰጣቸው እንጂ የአጸፋ መልስ የሚሰጥ አይመስላቸውም። “እኔም ልኑር፣ አንተም ኑር” የሚል መርህ አያውቁም፡፡
እና በፍልስፍናም፣ በፖለቲካም በእምነትም በሌላውም… የማንፈልገውንና የምንፈልገውን ለይተን እንወቅ። አሜሪካውያን፣ እንግሊዛውያን፣ ጀርመናዊያን… እንደሚያደርጉት የተመረጠውን እንጂ ፖለቲካዊ ድርጅቱን እንደማያዩ ሁሉ ምን እንደሚደረግ ለይቶ ማወቅ ለስኬታማነቱም ይጠቅመናል።

Read 2511 times