Print this page
Sunday, 29 October 2017 00:00

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

• በተፈጠረው ችግር የአቶ ኃይለማርያም መንግስት ሥልጣን መልቀቅ ነበረበት
• በየዞኑና በየወረዳው የሚፈጠረውን ግጭት የሚያነሳሱት ካድሬዎች ናቸው
• ህዝቡ የህግ ጥበቃ ያስፈልገዋል፤ አጥፊዎች በህግ መጠየቅ አለባቸው
• የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ዶግማ አይደለም፤መከለስ ይችላል
  አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳው ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል በሚል ቢሆንም ግጭቱና አለመረጋጋቱ በየጊዜው እየተባባሰ ነው የመጣው። ለዚህ ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል?
ህዝብ ጥያቄዎቹን በዝርዝር አቅርቦ፣ ይመለሱልኝ ሲል፣ ገዥው ፓርቲ በተቃራኒው ራሴን በጥልቀት እየገመገምኩ ነኝ ማለቱና ይሄም ከህዝብ ቀጥተኛ ጥያቄ ጋር የሚገናኝ አለመሆኑ ነው፡፡ ፓርቲው በራሱ ጣጣ ሲገማገም ሊኖር ይችላል፤ የእነሱ መገማገም ግን  የህዝቡን ጥያቄ መፍታት ማለት አይደለም፡፡ የህዝቡ ቀጥተኛ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ደግሞ ጥያቄዎቹ በየጊዜው ተጨማሪ ገፅታ እየያዙ ነው የሚመጡት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀድሞ በነበሩት ጥያቄዎች ላይ “የታሰሩ መሪዎቻችን ይፈቱ” የሚለውም ተጨምሮበታል፡፡ አሁን የህዝቡ ብሶት በላይ በላዩ እየተደራረበ ነው ያለው፡፡ የዚህ መጨረሻው ምን ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ ግን ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡
ገዥው ፓርቲ “ጥልቅ ተሃድሶ አደርጋለሁ” ሲል ምን ነበር  የተጠበቀው?
እንግዲህ አንዱ “አጠልቀዋለሁ” የሚለው የዲሞክራሲ ጉዳይ ነው፡፡ ዲሞክራሲን እያጠለቅን ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ የሚሉት ዲሞክራሲና ዓለም የሚያውቀው እንዲሁም እኛ የምንታገልለት ለየቅል ናቸው፡፡ ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ እነሱ ዲሞክራሲ የሚሉት፡- በማርክሲስት ሌኒኒስት ቀኖና የተቃኘ፣ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ሁሉንም ፀጥ ለጥ አድርጎ፣ እኔን ብቻ ስሙ የሚለውን አስተሳሰብ ነው፡፡
እናንተ የምትሉት “ዲሞክራሲ” እና ኢህአዴግ የሚለው “ዲሞክራሲ” ትርጉሙ የተለያየው ከመቼ አንስቶ ነው? በፊትም አንስቶ ነው ወይስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ?  
አስታውሳለሁ፤ በሽግግር ወቅት ከእነሱ ጋር አብሬ ለመስራት በሞከርኩበት ወቅት አንዱ ወደ ፖሊቲካው ለማግባት መነሻ የሆነኝ፣ ኢህአዴግ የመደብለ ፓርቲ ስርአት አሰፍናለሁ የሚል ቃል በመግባቱ ነው፡፡ ነገር ግን በሂደት አቋማቸውን ቀይረው፣ የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ፍጹማዊ አገዛዝን እውን ለማድረግ ነው የተንቀሳቀሱት። እነሱ አሁን የቻይናውን ኮሚኒስት ፓርቲ ሞዴል ለመከተል የሚፈልጉ ነው የሚመስለው፡፡ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ላለፉት 70 ዓመታት በተግባሩ የብዙዎችን ይሁንታ ያገኘ ይመስላል፡፡ የቻይና እና የእኛ አገር ሁኔታ ግን ጨርሶ የተለያየ ነው። ቻይና አንድ ህዝብ ነው፡፡ “ይሄ ብሔር ያንን ጨቆነ፣ ተጨቋቆንን” የሚባል ነገር የለም፡፡ እነሱ በዚያ መነሻ በአንድ ፓርቲ ቢመሩ ምንም ላይሆን ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ግን ለዚያ የሚበቃ ተክለ ሰውነት የለውም፡፡ የሃገሪቱ ሁኔታም ያንን በቀላሉ አይፈቅድም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ፍላጎቶች አሉ፡፡ ያንን ማግባባት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እየተደረገ  ያለው ነገር ብዙም ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡
የመድብለ ፓርቲ ሥርአት የመመሥረት ተስፋ  ለምን የተዳፈነ  ይመስልዎታል?
እኔ ለረጅም ጊዜ አውጥቼ አውርጄ የደረስኩበት ዋናው ምክንያት፣ ደርግን ከስልጣን ማውረዳቸውን “የኢትዮጵያ ህዝብ  ሙሉ ለሙሉ  እንደ ውለታ ይቆጥርልናል” የሚል ሃሳብ ይዘው መነሳታቸው ነው፡፡ ህዝቡ እነሱን እንደ ነፃ አውጪ ቆጥሮ፣ ከማንም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ቢወዳደሩ፣ ማሸነፍ እንደሚችሉ አስበው  ነው የተነሱት፡፡ ወደ ተግባር ሲገቡ ነው ችግር የገጠማቸው፡፡ የመጀመሪያ ምርጫ ሲካሄድ በየቀበሌውና ወረዳው በእጅ በማውጣት ነበር፡፡ በዚያ ምርጫ ላይ ኢህአዴግ በአዲስ አበባም በክልሎችም በከፍተኛ ብልጫ ተሸንፎ ነበር። በተለይ በኦሮሚያ ኦነግ ነበር ያሸነፈው። ይሄ ምርጫ ለኢህአዴግ ከፍተኛ ምልክት ነበር ያሳየው። በወቅቱ “ዛሬ በእጅ በማውጣት ምርጫ ህዝብ እንዲህ ከጣለን በኮሮጆ ምርጫስ  ምን ሊያደርገን ይችላል?” በሚል  ግራ ተጋብተው ነበር። ይሄንን መነሻ አድርገውም ግምገማ አድርገዋል፡፡ እኛ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ ገብተን የነበርነውንም በዚህ ምክንያት ማግለል ጀመሩ። በግልም በድርጅትም ላይ ነው ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት። በሃዋሳ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ መሥራች አቶ ወልደአማኑኤል ላይ  የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡ አቶ አሰፋ ጫቦና ፊታውራሪ መኮንን ዶሪ፤ የሽግግር መንግስቱን ብስራት ለህዝቡ እናሰማለን ብለው፣ ደብዳቤ ከጠ/ሚኒስትሩ ተፅፎላቸው፣ ወደ ጋሞ ጎፋ ሲሄዱ፣ መኪናቸው የድንጋይ ናዳ ወርዶበታል፡፡ እነዚህ (ኢህአዴጎች) ጠባያቸውን እየቀየሩ የመጡበት አጋጣሚዎችን ማሳያዎች ናቸው፡፡
የኢህአዴግ ትልቁ ችግር የርዕዮተ ዓለሙ መሰረት ነው፡፡ ይሄ ሲስተካከል ብቻ ነው መለወጥ የሚችሉት፡፡ ከማርክሲስት ሌኒኒስት አመለካከት ሲላቀቁ ነው ለውጥ የሚያመጡት፡፡ 21ኛው ክ/ዘመን ምን ይፈልጋል የሚለውን ሲያጤኑና ለውይይትና ክርክር በራቸውን ክፍት ሲያደርጉ ነው በራሳቸው ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት። አለበለዚያ ግድብ ገደብን፣ ፎቅ ገነባን፣ መንገድ ሰራን ወዘተ -- ብቻውን ፋይዳ  የለውም፡፡ የለውጥ ተስፋ የሚኖረው ውስጣቸውን በደንብ ሲፈትሹ  ነው፡፡ በመነጋገርና በመደራደር ማመን ሲጀምሩ ነው የሚለወጡት፡፡ ኢህአዴጎች፤ “እኛ ነን ለዚህች ሀገር ያለናት” የሚለውን መመፃደቃቸውን ትተው፣ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ በጎ ነገር ይመኛል” ብለው ማሰብ መጀመር  አለባቸው፡፡ “ባለፉት 26 ዓመታት የገነባነው ስርአት አሁንም የህዝብ ጥያቄን ማስቆም አልቻለም ወይም ምላሽ መስጠት አልቻለም” የሚለውን ግምገማ አድርገው፣ የፖለቲካ መስመራቸውን ቢፈትሹ  ሁነኛ መፍትሄ የሚገኝ ይመስለኛል፡፡
የዚህችን ሀገር  የወደፊት እጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ የተቃዋሚዎች ድርሻ ምንድን ነው ይላሉ?
የተቃዋሚዎች ድርሻ ህዝብን ማደራጀት ነው፡፡ ያ የተደራጀ ህዝብ ጥያቄ ለመጠየቅ እስኪበቃ ድረስ አብሮ መስራት ነው ያለባቸው፡፡ አንድ የተደራጀ መሪ የሆነ አካል፣ በሌለበት ሁኔታ በአንድ ሀገር ውስጥ ስለ ለውጥ ማሰብ አይቻልም፡፡ የጎበዝ አለቃ ሁሉ ተነስቶ፣ የዘመነ መሳፍንት ሁኔታ ውስጥ እንግባ ካልተባለ በስተቀር የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች ለህዝቡ አማራጩን ማሳየት አለባቸው። አሁን ከምንግዜውም በላይ ይሄ ነው በጥልቀት መካሄድ ያለበት፡፡ ዝም ብሎ የስርአት መውደቅ ብቻ አይደለም የሚታሰበው፤ በወደቀው ቦታ ማን ነው የሚተካው የሚለው መታሰብ አለበት፡፡ ይሄን ቦታ መተካት የሚችሉት የተደራጁ ኃይሎች ናቸው። የተደራጁ ኃይሎች ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ይህን ነው የ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ፖለቲካ የሚፈልገው፡፡
በሌላ በኩል ግን አመራሩን መረከብ የሚችል ጠንካራና ብቃት ያለው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር ተቀናጅተው፣ ብቃት ያለው እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ፣ እንቅፋት የሆነባቸው አሁን ያለው ሥርዓት ነው፡፡ በሌላ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ፓርቲዎች፣ በየእስር ቤቱ እየታጎሩ ያሉ የተቃዋሚ መሪዎች--- ዕድሉን ቢያገኙ ሃገር የመምራት ሚናን አይወጡም ማለት የተንሸዋረረ አመለካከት ነው፡፡ የ97 ምርጫ እኮ ብዙ ነገር አሳይቶን ነው ያለፈው። በተፈጠረችው ክፍተት የፖለቲካ ፓርቲዎች 6 ወር ባልበለጠ እንቅስቃሴ ነው ብዙ ታሪክ የሰሩት። አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ አመራሮች፣ ጨርሶ ብቃት የላቸውም የሚለው አመለካከት ስህተት ነው፡፡ ትንሽ ክፍተት ነው የሚፈለገው፡፡
እየተጎሳቆልንም፣ እየተሳደድንም ህዝቡን አደራጅተናል፡፡ ህዝቡ ነፃነቱን የሚያንፀባርቅበት መድረክ ቢፈጠርለት እኮ ብዙ መቀስቀስም አያስፈልገንም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች የት አሉ? ምን ተቃዋሚ አለና? የሚባለው ነገር ጨለምተኛ አመለካከት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች አሉ። እየጠበቁ ያሉት መልካም አጋጣሚን ብቻ ነው፡፡
አዲሱ ትውልድ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር የሚጣጣም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተቃዋሚውም ሆነ በገዥው ፓርቲ ማምጣት አልተቻለም ብለው የሚያምኑ  ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እኔ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድ፣ ከጨረቃ የወረደ ነው እንዴ? አይደለም። የፖለቲካ ትግል መዳረሻው ዲሞክራሲ ማስፈን ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡ አዲሱ ትውልድም በራሱ መንገድ ተደራጅቶ መታገል ይችላል፡፡ እኛም በራሳችን እንታገላለን፡፡ በኔ እምነት ያለችው አንድ ሀገር ናት፡፡ ጥያቄውም አንድ ነው፤ እሱም የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የቀረው ሁሉ ትርፍ ነው፡፡ ዝንጀሮ እንዳለችው፤ መጀመሪያ የመቀመጫዬን ነው ነገሩ፡፡ ዋናው ጉዳይ ዲሞክራሲያችንን በትክክለኛ ፈር ውስጥ ማስቀመጥ ነው፡፡ የዘመኑ ትውልድ ከዚህ ውጪ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ተቆፍሮ የሚወጣ ነገር የለም፡፡ የተለየ ጥያቄም አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ ሊግባባ የሚችለው በዲሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ዋናው የኔ አቋም፣ ሁሉም የየድርሻውን ያዋጣ ነው፡፡ እኛም ሆንን አዲሱ ትውልድ የምናዋጣው ተደማሪ ውጤት ለዚህች ሀገር መፍትሄ ያመጣል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎችን ስጋት ላይ የጣለ የድንበርና ብሄር ተኮር ግጭቶች እየተከሰቱ ነው? ይሄ አዝማሚያ ወዴት ያደርሰናል? መፍትሄውስ  ምንድን ነው?
የድንበር ጉዳይ ከሰው ልጅ ጋር አብሮ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ መሬት ከሁሉም በላይ ዋጋ ያለው እሴት ሆኗል። አሁን የሚታየው አዝማሚያም ከመሬት መስፋፋት ጋር የተያያዘ ነው የሚመስለው። በሌላ በኩል ደግሞ ነገሩን ከብሄር ጉዳይ ጋር እያያያዙት፣ ሁኔታውን ውስብስብ እያደረጉት ነው፡፡ ይሄ  በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ለምሳሌ የሶማሌና የኦሮሞ ህዝብ፣ በወንድማማችነት አንዱ በሌላው ውስጥ መኖር የጀመረው በኢህአዴግ ዘመን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ነው። በህዝቦች መካከል ድንበርን በመስመር ማስመር አይቻልም፡፡
በየዞኑና በየወረዳው የሚፈጠረውን ችግር የሚያነሳሱት ካድሬዎች ናቸው፡፡ ህዝቡ እርስ በእርሱ የተጋመደ፣ ለብዙ መቶ አመታት አብሮ የኖረ ነው፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለው ነገር፣ ለመናገርም የሚያሳፍር እብደት ነው፡፡ ልናፍርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ምሬት ነው ያለብኝ፡፡ ለዚህም ነው ይሄ ሥርአት አገር ማስተዳደር አቅቶታል፤ ይበቃዋል የምለው፡፡ እንደ ሌላ ሀገር ቢሆን እኮ የአቶ ኃይለማርያም መንግስት፣ በዚህች ምክንያት በገዛ ፍቃዱ ስልጣን መልቀቅ ነበረበት፡፡ ለዘመናት አብሮ በኖረ ህዝብ ላይ ጥቃት የሚፈፀመው እኮ በአስተዳደሩ ውድቀት የተነሳ ነው፡፡ ህዝቡ የህግ ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡ አጥፊዎች በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡
እነዚህ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ ካልተሰጣቸው ፌደራሊዝሙ አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ስጋት እየተስተጋባ ነው፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ፌደራሊዝም ለሀገሪቱ የአስተዳደር ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የተቸገርነው ፌደራሊዝምን ከዘረኝነት ጋር እያደባለቁ፤ ህዝብን እያናቆሩ ያሉ ወገኖች በመኖራቸው ነው፡፡ ይሄ ነው ትልቅ ስጋት ውስጥ እየከተተን ያለው፡፡ እኔ የፌደራሊዝም ሥርዓት ላይ ችግር የለብኝም፤ ነገር ግን አሁን ያለው የፌደራሊዝም ሁኔታ እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ “26 ዓመት ተሞክሯል፤ ምን ተገኘ?” የሚለው ተጠይቆ፣መከለስ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ዶግማ አይደለም፤ መከለስ ይችላል፡፡ አሜሪካኖች ህገ መንግስታቸውን ከ30 ጊዜ በላይ ከልሰው ነው፣ ጠንካራ ሥርዓት መገንባት የቻሉት፡፡     

Read 6179 times