Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 April 2012 11:19

የግብፃውያን ጥያቄ ካልተመለሰ መፍትሄው ታህሪር አደባባይ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የግብፁ ህዝባዊ አብዮት ቀጣይ ሂደት እንደሆነ የተናገሩት በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሃመድ ኢድሪስ፤ የታህሪር አደባባይ ሰልፈኞች የጠየቁት የነፃነትን፣ ክብርንና ፍትሃዊነትን እንደነበር በማስታወስ አብዮቱ ገና አላበቃም፡ በምርጫ ሥልጣን ላይ የሚወጣው ፓርቲ ወይም ድርጅት ይሄን የህዝብ ፍላጐት እንዲያሟላ ይጠየቃል፤ ህዝቡ የጠየቀው ካልተሟላለት ግን እንደገና ወደ አደባባይ ሊወጣ ይችላል የሚሉት አምባሳደሩ፤ የፈለገው መንግስት ቢነግስ የህዝብ ጥያቄን መመለስ ካልቻለ ግብፃውያን መፍትሄው የት እንዳለ ያውቁቃል - ታህሪር አደባባይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኞች መልካሙ ተክሌና ኤልሳቤጥ ዕቁባይ ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ስለ አባይ ተፋሰስ አገሮች ስምምነት፣ ግብፅ በኢትዮጵያ ስላላት የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እያነሱ ጠይቀዋቸዋል እነሆ ቃለ ምልልሱ፡-

የግብፁ አምባሳደር - በተለይ ለአዲስ አድማስ

በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩዎች ታውቀዋል፡፡ አንዳንዶች አሸናፊውም ቀድሞውኑ ይታወቃል ይላሉ፡፡ እርስዎስ?

እጩዎቹ ቀድመው ቢታወቁም አሸናፊውን ማንም አያውቅም፡ ይህ በአዲሱ የግብፅ ፖለቲካ ምህዳር የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡ ግብፃውያን ከበርካታ እጩዎች መካከል ፕሬዚደንታቸውን ሲመርጡ ያሁኑ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤቱ ቀድሞ ያልታወቀበትም ምርጫ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን ፕሬዚደንት ማን ይሆናል የሚለው ሳይሆን ሂደቱ ነው፡፡ ሂደቱ ነፃ ውድድር፣ የተለያዩ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ እጩዎች መኖራቸውና ነፃ የሕዝብ ፍቃድ መኖሩ ነው፡፡ አሁን ጠቅላላ ፖለቲካዊ አመለካከቱ ተቀይሯል፤ ማንም ፕሬዚደንት ቢሆን ያልተገደበ ስልጣን አይኖረውም፡፡ ሥልጣኑ በፓርላማ፣ በሕዝብና በሕገ መንግሥት ይገደባል፡፡ አዲሱ ፕሬዚደንት ለሕዝብ አስተያየት፣ ለፓርላማና ለሕገ መንግሥት ተገዢ ይሆናል፡፡

ተቃውሞ የቀረበባቸው ጀነራል ዑመር ሱለይማን የጦር ሠራዊቱ ድጋፍ ስላላቸው ፕሬዚደንታዊ ምርጫውን በቀላሉ ያሸንፋሉ እየተባለ ነው?

ይኼ ትክክለኛ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም አሁን የተለያዩ ድረገፆችን ብታገላብጥ የተለያዩ አመለካከቶችን ታገኛለህ፡፡ እሳቸውን የሚደግፉ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል የሚቃወሟቸውም አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ ሆኖ እገሌ ያሸንፋል ብሎ በእርግጠኝነት መተንበይ አይቻልም፡፡

የሙስሊም ወንድማማቾች ለግብፅ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሥጋት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…

ሙስሊም ወንድማማቾች የተጀመረው በ1928 እ.ኤ.አ ነው፡ የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው፡፡ ሃይማኖትና ሥነምግባር ለማስተማር ነው የተቋቋመው፡፡ ቀስ በቀስ ቡድኑ እያደገ በመምጣት ፖለቲካዊ ሚናው ጐላ፡፡ ቢሆንም የድርጅቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ -  አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥት ክልከላ ስር ነበር፡፡ ይህ ከ1957ቱ አብዮት በፊት በንጉሣዊ  አገዛዝ ጊዜ እና ከአብዮቱ በኋላ የሆነ ነው፡ በተለያየ ዘመን እና ጊዜ የሙስሊም ወንድማማቾች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ክልክል ነበር፡፡ ከጥር 2012 አብዮት በፊት ድርጅቱ ታግዶ ነበር፡፡ ከአብዮቱ በኋላ ግን በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሆነዋል፡፡ በፓርላማው አብላጫ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በፕሬዚደንታዊ ምርጫም ብርቱ ተፎካካሪ አቅርበዋል፡፡ እንደሚመስለኝ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ሕዝብ እስከ ደገፈህ ድረስ በፓርላማም ሆነ አስፈፃሚ አካልና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተሳትፈህ ሥልጣን መያዝ ትችላለህ፡፡ ቢሆንም ወቅቱ ለሙስሊም ወንድማማቾች አስቸጋሪ ጊዜ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቱ አስቸጋሪ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታዎችን ስለሚወርሱ ነው፡፡ የምርጫው ሂደት ከምርጫው በኋላ ያሉ ችግሮችን ለማቃለልና የሕዝቡን የፖለቲካ፣ ጤና፣ ምጣኔ ሀብት ደረጃ ያሻሽላል፡፡ በእርግጥ አዲስ ዘዴ እና አስተሳሰብ ያመጣል፡፡ ሕገወጥ ሲባል የነበረው ፓርቲ ምን ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ ችግሮችን በመፍታት ከተሳካላቸው ለድርጅቱም ለግብፅም ሕዝብ ጥሩ ነው፡፡ ያን ማድረግ ካልቻሉ ግን በምርጫ ሂደት እና በሕዝቡ በመጪው ምርጫ የተለየ ውጤት ነው የሚጠብቃቸው፡፡ ሕዝቡም ሌላ የተለየ አማራጭ ወደመፈለግ ይሄዳል፡፡

የህዝቡ አብዮት በፕሬዚደንታዊ ምርጫው ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስልዎታል?

አብዮቱ በግብፅ አዲስ የፖለቲካ ባህል አምጥቷል፡፡ በሕዝቡ፣ በመንግሥትና በፕሬዚደንት መካከል ያለውን ግንኙነት ቀይሮታል፡፡ ሕዝቦች የለውጥ ሃይሎች መሆናቸውን ተገንዝበዋል፡፡ አብዮቱ አላበቃም፡፡ ቀጣይ ሂደት ነው፡፡ የራሱ ግቦችም ነበሩት፡፡ የታህሪር አደባባይ ሰልፈኞች የጠየቁት ነፃነትን፣ ክብርንና ፍትሃዊነትን ነው፡፡ ይኼ ሁሉ በአንድ ጊዜ ወይም አዲሱ ፕሬዚደንት ስልጣን እንደያዘ የሚሳካ አይደለም፡፡ ለአዲሱ የግብፅ ፖለቲካ መሰረት ሆኗል አብዮቱ፡፡ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል እንጂ በአዲስ ፕሬዚደንት መመረጥ የሚቋጭ አይደለም፡፡ አዲሱ ፕሬዚደንት የህዝቡን ፍላጐት እንዲያሟላ ይጠየቃል፡፡ ህዝቡ በታህሪር አደባባይ የጠየቀው ካልተሟላለት እንደገና ወደ አደባባይ ሊወጣ ይችላል፡፡ አዲስ ምዕራፍ ግን ከፍቷል፡፡

የታህሪር አደባባይ አብዮት በጦር ሠራዊቱና በሌሎች ተጠልፏል የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ ላይ አስተያየትዎ ምንድነው?

አብዮቱ ሂደት እንጂ ድርጊት አይደለም፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች የተለያዩ ፍላጐቶች አሉዋቸው፡፡ ስለዚህ ከአብዮት በኋላ ባለ ሽግግርም የተለያዩ አመለካከቶችና የተለያዩ ተፎካካሪ ሃይሎች ይኖራሉ፡፡ አብዮቱ አዲስ ጠቅላላ አስተሳሰብ አምጥቷል፡፡ ያለፈውን በማየት የወደፊቱን እናልማለን፡፡ በዚህ የጋራ አስተሳሰብ ሳይሆን የግል አስተሳሰብ ነው የሚኖረን፡፡ በግብፅ አንድ ሊቀለበስ የማይችል ለውጥ ተከስቷል፡፡ ይህም የሕዝቡ ሃይል ነው፡፡ በፊት መለወጥ ያልቻሉ ሕዝቦች መለወጥ እንደሚችሉ ተረድተዋል፡፡ የፈለገው መንግስት፣ የፈለገው አገዛዝ፣ የፈለገው ሃይል በግብፅ ይንገስ፣ የሕዝብ ጥያቄ መመለስ ካልቻለ ሕዝቦች መንገዱን አውቀውታል፡፡ ታህሪር አደባባይ ነው አድራሻው፡፡ በፊት ባያደርጉትም ካሁን በኋላ እንደሚያደርጉት ተረድተውታል፡፡

የአረብ ስፕሪንግ አብዮቶች በአጠቃላይ በአፍሪካ ምን አንድምታ ይኖራቸዋል?

የአረብ ስፕሪንግ የአፍሪካ ስፕሪንግ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም አብዮቱ የተቀጣጠለባቸው የሰሜን አፍሪካ ሀገሮች አካባቢ የአፍሪካ አህጉርም አካል ነው፡፡ የእነዚሀ አካባቢዎች አብዛኛው ሕዝብ አዲስ ትውልድ ነው፡፡ ይህ አዲስ ትውልድ በብዛት ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና ሰብአዊ መብት ከሚያከብረው የውጭው ዓለም ጋር ይገናኛል፡፡ የምጣኔ ሀብት እድገት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አዲሱ ትውልድ ይሄን ተረድቶታል፡፡ አፍሪካ አህጉርም ይህን ተረድቶታል፡፡ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ፋይዳ ያላቸው የዲሞክራሲ ልምዶች አሉ፡፡ ሕዝቦች ለጥቅማቸው ሲባል ይሄ ተስፋፍቶ መቀጠል እንዳለበት ተረድተዋል፡፡ በአፍሪካ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም መልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ግልፅነትና የሰብአዊ መብት አከባበርን ማዳበር አለባቸው፡፡

የማሊን የመንግሥት ግልበጣ እንዴት ያዩታል?

በሁለት ጉዳዮች የማሊ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ መጀመርያ ውጤት መሆን ይችላል፤ ከዚያም መንስኤ ነው፡፡ በሳህል አካባቢ ያለ ሰፊ እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ በእርግጥ አሁን የአፍሪካ ሕብረት ከተጠመደባቸው ጉዳዮች አንዱ በሳህል አካባቢ ሁኔታ ላይ መነጋገር ነው፡፡ ይህም በጦር መሣርያ ቅነሳ ይገለፃል፡፡ በርካታ የጦር መሳርያ ለተለያዩ ቡድኖች ይደርሳል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ሃሳባቸውን ለማስረፅ ይሞክራሉ፣ ለዚህ ነው ህብረቱ በብልሃት የያዘው፡፡ የሕብረቱ ዋነኛ አካል የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ጉዳዩን ይዞታል፡፡ ግብፅም ካለፈው የካቲት ጀምሮ የምክር ቤቱ አዲስ አባል ሆናለች፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም ጉዳዩን የሚያወግዙ በርካታ መግለጫዎች አውጥቷል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግስት ለውጥ ነው፡፡ ህብረቱ ሕገ መንግሥታዊ ስርአት በማሊ እንዲመለስ ጠይቋል፡፡ በዚሁ ወቅት በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ትልቅ ቀውስ አለ፡፡ ሕብረቱ በሰሜን ማሊ የሚደረጉ ለውጦችን ባዶና ተቀባይነት የሌላቸው አድርጐ ገልጿል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ቀጠና ኢኮዋስም በመሪዎች ደረጃ ተወያይቶበት፣ ማእቀብ ለመጣልና ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት ይህን ሁኔታ ለመቋቋም ፅኑ አቋም ይዟል፤ ወደ ሌሎች ሀገራት እንዳይዛመትም ጭምር፡፡ ይህ በኢኮዋስ፣ በአፍሪካ ሕብረትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቧል፡፡ ሁሉም አካላት ግልፅ አቋም አሳይተዋል፡፡ ለወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱም ሆነ ለአመፁና መገንጠሉ እውቅና አይሰጡም፡፡ ምክንያቱም የማሊ የግዛት ሉአላዊነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ላይ እየገነባች ያለችውን የሕዳሴ ግድብ ግብፅ እንዴት ታየዋለች ምን ያህል ያሳስባታል?

ወደዚህ ጉዳይ እመለሳለሁ፡፡ በቅድሚያ ወደ አረብ ስፕሪንግ አንድ ክፍል ላምራ፡፡ በግብፅ የተከሰተው ዶፍ ቁጣ፣ አዲስ ዘመን እና አዲስ አስተሳሰብ አምጥቷል፡፡ በዚህም የኢትዮ-ግብፅ አዲስ ዘመን መጥቷል፡፡ ይህም በጐ፣ አዲስ፣ ፈጣን እና አስፈላጊ የግብፅ አብዮት መገለጫ ነው፡፡ ከአብዮቱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስታውሱ፡፡ ካሁን በፊት ባልተለመደ መልኩ የመንግስት ከፍተኛ ልኡካን ጉብኝቶችም ተካሂደዋል፡፡ ይሄም በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መካከል የጋራ ፍላጐቶችን የሚገልፅ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

ወደ ግድቡም ስንመጣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ኦፊሴላዊ ጉብኝቶች ተደርገዋል፡፡ በአዲስ ገንቢ ስሜት፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሁለት አስፈላጊ ተነሳሽነቶች ተወስደዋል፡፡ አንደኛው የሲኤፍኤ ስምምነት ማፅደቂያን የግብፅ የሽግግር ጊዜ እስኪያልቅ ማራዘሙ ነው፡፡ ሌላው የግድቡ ቴክኒካዊ ተፅእኖዎች የባለሙያዎች ቡድን ማቋቋሙ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ተነሳሽነቶች በቀናነት እየተራመዱ ነው፡፡ የቡድኑ ዋነኛ አላማም በሦስቱ ሀገራት ግድቡ የሚያመጣውን ተፅእኖ ማጥናት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ በኩል ሦስቱንም ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና ከሦስቱ አንዱንም ሀገር እንደማይጐዳ ተነግሯል፡፡ ይህ በጣም ይደነቃል፡፡ ይህ እንደ ኢትዮጵያ ካለ ወዳጅ ሀገር የምንጠብቀው ነው፡፡ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተካተቱበትን የዚህን ቡድን ውጤት ድምዳሜ እንጠብቃለን፡፡ ፕሮጀክቱም ሀገራቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ፍሬያማ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ የአባይ ውሃ የትብብር እና የውዝግብ መስክ ነው፡፡ እናም ይኼ ታላቅ ወንዝ በመጨረሻ የሦስቱን ሀገራት እጣ ፈንታ ይወስናል፡፡ ስለዚህ በተናጠል ሊጠና አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም በጋራ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ነው፡፡ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች መስራት አለብን፡፡ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞች እና እህቶች ጋር እንጠቃቀም በሚል ነው የተስማማነው፡፡

የ1959ኙን ስምምነት ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በማነፃፀር እንዴት ያዩታል?

ይህ ጉዳይ በአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሴንሴቲቭ ጉዳይ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ መረዳት ያለብን ይኼን እውነታ ነው፡፡ አሁን ወደ አዲስ እውነታ ልናመጣው እንፈልጋለን፡፡ ወደ አዲስ እውነታ ስንመጣ ሁላችንም መተባበር አለብን፡፡ ለምሣሌ የአፍሪካ ሀገራት ድንበሮች ስምምነቶች ቀድሞ የተደረጉ ናቸው፡፡ አሁን የተፈጠረ አይደለም፡፡ ወደ አዲስ ዘመን ስንሸጋገር ወደ መሻሻል ማምራት ሕጋዊ ነው፡፡ የሁሉንም ሀገራት ፍላጐት የጠበቀ ስምምነት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ወደ አዲስ እውነታ ስንሄድ ግን በፍላጐታችን ስለተሳሰርን በድርድርና በጋራ መግባባት አብረን መጓዝ አለብን፡፡ በግብጽ የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች የማደግ መብት እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ በዚህ እድገት አጋሮች መሆን እንዳለብን እንረዳለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የግብጽ ሕዝብ ፍላጐትም እንዳለ እናውቃለን፡፡ ለሕዝቡ፣ ለአትክልቱና ለእንስሳቱ ስለሚያስፈልግ ውሃ በግብጽ ሕይወት ነው፡፡ ፍላጐታችን በሌሎች ኪሳራ ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሌለበትም እንረዳለን፡፡ ሌሎችም ለግብጽ ፍላጐት ያስባሉ ብለን እናምናለን፡፡

የቀድሞው አምባሳደር ሚስተር ታሪቅ ከአብዮቱ በኋላ ያንን ስምምነት ጨምሮ ግብጽ ለመደራደር ፈቃደኛ ነች ብለዋል፡፡ እስካሁን ምን ሠራችሁ በዚህ ረገድ?

አንድ ወይ ሁለት ስምምነቶችን ሳይሆን ጠቅላላ ሕጋዊ ይዞታን ነው የማየው፡፡ ግብጽ አባል የሆነችበት የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭን በ1990ዎቹ ማስተዋወቅ ስትጀምር ሁለት ውህዶች ነበሩት፡፡ አንደኛው የፕሮጀክቶች የጋራ ዓላማ እና ፈርጀ ብዙ ፕሮጀክቶች ሀገራቱን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ነው፡፡ ሌላኛው አዲስ የስምምነት ማዕቀፍ በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ማዘጋጀት ነው፡፡ የፕሮጀክቶቹ የፋይናንስ ችግርን ለመፍታት እንቅስቃሴ አለ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አዲስ የስምምነት ማዕቀፍ መፈለጉም አለ፡፡ በድርድርና ሃሳብ በመለዋወጥ የሁሉንም ሀገራት ጥቅም የሚያስከብር፣ በማንም ሀገር ላይ ጉዳት የማያመጣ ማዕቀፍ እንደሚመጣ እናምናለን፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ከሚወድቅባቸው ወንዞች አንዱ አባይ ነው፡፡ ይህ ለግብጽ ምን አይነት ውጤት ይኖረዋል?

በሌሎች የአባይ ተፋሰስ ቤተሰቦቻችን የሚመጣው ተጽእኖ በእኛም ላይ ይመጣል፡፡ ሁሉንም ሀገሮች የሚመለከት አዲስ አቅጣጫ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የሆነው የአየር ለውጥ በአፍሪካም ላይ ከፍተኛ  ተጽእኖ በማምጣት በሀገሮቻችንም ትልቅ ጫና የሚፈጥር ነው፡፡ በተናጠል ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ልንነጋገርበት የሚገባ ነው፡፡ ቢያንስ በአፍሪካ ደረጃ የጋራ አቋም መኖር አለበት፡፡ ለመቋቋምም የጋራ ትብብር ያስፈልጋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አስፈላጊ የሆነ ተደራዳሪ አካል አለ፡፡ ይኼ አካል የመጨረሻ ስብሰባውን ያደረገው በደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ ይህ ሂደት ባደጉት እና እያደጉ ባሉት ሀገራት መካከል በጣም አጨቃጫቂ ነው፡፡ የአፍሪካውያን ፍላጐትን በጋራ ማንፀባረቅ አለብን፡፡ ይህ ጉዳይ በአባይ ውሃ ላይ ቴክኖሎጂ ተኮር እርምጃ ለመውሰድም ያስችላል፡፡ ከዚህ ወንዝ 60% ብቻ ነው ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ የቀረው ይባክናል፡፡

ወንዙን ይበልጥ ለመጠቀም እርስበርስ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በብሔራዊ ፖሊሲያችን መተባበር አለብን፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ሀገሮች የእድገት እቅድ ላይ ተጨማሪ ሸክም ነው፡፡

የሕዳሴው ግድብ የሚገነባበትን ቦታ አይተዋል?

የግድቡን ቦታ ሳይሆን ወንዙ የሚመነጭበትን ባህርዳር አካባቢ ጐብኝቻለሁ፡፡ ሕዝቦቻችንን ሲያስተሳስር የነበረውና ለዘላለሙ የሚያስተሳስረውን ወንዝ መነሻ መጐብኘቴ አስገርሞኛል፡፡

በኢትዮጵያ የግብፃውያን ኢንቨስትመንት ምን ይመስላል?

ከአብዮቱ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመርነው ግንኙነት ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ግንኙነቱ በአንድ ጠባብ ማዕዘን ብቻ መታየት የለበትም፡፡ ከፊሉ ፖለቲካዊ የተቀረው ምጣኔ ሀብታዊ የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው፡፡ በቅርቡ የቢዝነስ ሰዎች እና ኢንቨስተሮች ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ባህላዊ ዘርፍም አለው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የግብጽ ፊልም አውደርእይ ማስታወስ ይቻላል፡፡ የሁለቱን ጥንታዊ ሀገሮች የባህል ግንኙነት ይበልጥ ለማዳበር ይበልጥ እንሰራለን፡፡ መንፈሳዊና ሐይማኖታዊ ዘርፍም አለው፡፡ የሕክምና ዘርፍም አለ፡፡ በቅርቡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የገስትሮ ኢንቴስታይናል ሂፖቶሎጂ በሽታዎች የኢንዶስኮፒ ክፍል አቋቁመናል፡፡ አሁን ደግሞ ለሬናል ሕመሞች ቀዶ ሕክምና ያካተተ ሌላ ክፍል አቋቁመናል፡፡ ግልጋሎቶቻችን በአዲስ አበባ እና በክልሎች ይሰጣሉ፡፡ ኢንቨስትመንትንና ንግድን በተመለከተም በጣም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የግብፃውያን ኢንቨስትመንትም በኢትዮጵያ ሁለት ቢሊየን ዶላር ደርሷል፡፡ አሁን ሁሉም ሥራ ላይ ናቸው ማለት ባንችልም 134 የግብፅ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ እያገለገሉ አይደለም፡፡ ሌሎቹ እያገለገሉ ናቸው፡፡ በሁለቱ ሀገራት እያንዳንዳቸው 85 ሚሊዬን ሕዝብ ያላቸው ሁለት ትላልቅ ገበያዎች አሉ፡፡ እኛ ግብፃውያን ብዙ መሠረታዊ ፍላጐቶቻችንን ከኢትዮጵያ እናገኛለን፡፡ የቁም እንስሳት፣ ቡና፣ ሰሊጥና በርካታ ሸቀጦችን ከኢትዮጵያ ነው የምናገኘው፡፡ ለፋብሪካ ውጤቶቻችንም እዚህ ትልቅ ገበያ አለ፡፡ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ለምሣሌ በኤሌክትሪክ:- ኬብልና ትራንስሚተር፣ ለመስኖ ቧንቧ የሚሆን ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አሉን፡፡ እነዚህ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ ስለሚያደርጉ ማጠናከር አለብን፡፡ እንዲያም እያደረግን ነው፡፡

ከአምናው የግብጽ አብዮት እርስዎ በግል ምን … ተገነዘቡ?

የሚያኮራ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ የዚህ ታሪክ መለወጥ የሚችል ሕዝብ አካል በመሆኔም ኮርቻለሁ፡፡ ሁለተኛም በዚህች ታላቅ ወዳጅ ሀገራችን የታላቅ ህዝብ አምባሳደር ሆኜ መጥቻለሁ፡፡ በመስራቴ የሚያኮራኝን ሥራ እየሰራሁ ነው፡፡ በሙሉ ልብ እና ጉልበት በጉጉት እሠራለሁ፡፡ በሀገሬ እና በቤተሰቤ መካከል እንዳለሁ ይሰማኛል፡፡ እነዚህ ሁለት ሕዝቦች ሁለት የጋራ ፍላጐቶች ያሏቸው ናቸው፡፡ አንዱን ሀገር የሚጠቅም ጉዳይ ሌላውንም ይጠቅማል፡፡ አንዱ ሀገር የሚጐዳበት ሌላውም ሀገር ይጐዳበታል፡፡

ከምርጫው በኋላ የበለጠ ሃላፊነት ምናልባት የካቢኔ ሚኒስትርነት ቦታ አይጠብቁም?

በምሰራው ሥራ ደስተኛና ኩሩ ስለሆንኩ የሃላፊነት ለውጥ አልጠብቅም፡፡ ከምርጫው በኋላ የበለጠ ሃላፊነት ማለት ለእኔ ባለሁበት ሃላፊነት ላይ መቀጠል ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በራሴ ወጪ እሰራዋለሁ ያለው ግድብ ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል ብሏል …

የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጠቅም ሁሉ እኛንም ይጠቅማል፡፡ የባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙን እናደነቃለን፡፡ ቢሮዬ ሆኜ በግል አንድ ነገር ጥሩ ነው ወይም መጥፎ ነው ማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ በጣም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ባለሙያዎቹ አጥንተው የተፅእኖውን ድምዳሜ ይነግሩናል፡፡ ይህም ቴክኒካዊ ማረጋገጫ ስለሚሰጥ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ተቀባይ ሀገራችን ግድቡ ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል ማለቷን እናውቃለን፡፡ ይህ ተነሳሽነት ይደነቃል፡፡ በፖለቲካም፣ በሕግና ቴክኒክም፣ በኢኮኖሚም ረገድ ሕዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ይህ አዎንታዊ ነው፡፡ የባለሙያዎች ቡድን ውጤትንም እንጠብቃለን፡፡ ይህም ለሀገራቱ ካሉት በርካታ ጥቅሞች ሁሉ የተሻለ ይሆናል፡፡

መቼ ነው ባለሙያዎቹ ጥናታቸውን የሚያቀርቡት?

በተቻለ መጠን በፍጥነት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፤ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ሊገጥሙ ግን ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ባለሙያዎች ለማሰማራት የራሱ ሂደት አለው፡፡ ቴክኒካዊ ስራውም ጊዜ ይፈጃል፡፡ በጥቂት ቀናት ወይም በጥቂት ሳምንታት የሚጠናቀቅ ሥራ አይደለም፡፡

የተቆረጠለት ጊዜ የለም?

በተቻለ መጠን በፍጥነት ተስፋ የምናደርገው ፈጣን ውጤት ነው፡፡ በሦስቱ ሀገራት በባለሙያ እና በሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄዱ ስብሰባዎች በገንቢ መንፈስ የተከናወኑ ናቸው፡፡ በጋራ ጥቅም ላይ የመተባበር ገንቢ ፍላጐት አለ፡፡ ስራውን የሚሰሩት ባለሙያዎቹ ስለሆኑ እኛ ቁርጥ ቀን ልናስቀምጥ አንችልም፡፡ ተጨማሪ ጊዜ ቢያስፈልጋቸውም እነሱ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ቴክኒካዊ ሥራ እንጂ ፖለቲካዊ ውሳኔ አይደለም፡፡

የግብፅ አምባሳደር የቀን ውሎ… በሥራ ቀናት፣ በሳምንቱ መጨረሻ ምን ይመስላል?

የአምባሳደር ዋነኛ ሥራ ቢሮ ውስጥ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከአስተናጋጁ ሀገር ጋር የተለያየ መስተጋብር ሊኖረው ይገባል፤ በኦፊሴልም በሕዝብ ለሕዝብም ደረጃ፡፡

የግብጽን ጨምሮ በኢትዮጵያ አንድ አምባሳደር ሦስት የሥራ መስኮች አሉት፡፡ አንደኛው ከተቀባይ ሀገር ጋር ያለ ግንኙነት ነው፡፡ ሌላው በአፍሪካ ሕብረት ያለ ሥራ ነው፡፡

ሦስተኛው በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ ከጧት ሦስት ሰዓት እስከ ውድቅት ሌሊት ያባትላሉ፡፡ ሁሉም ስብሰባዎችና ጉብኝቶች አሉዋቸው፡፡ የዝግጅትና ክትትል ጊዜም አላቸው፡፡ የዛሬ (ማክሰኞ ማለታቸው ነው) ውሎዬን ብነግራችሁ… ለምሣሌ ጧት ሦስት ሰዓት ከኢፌዲሪ ፍትህ ማኒስትሩ ጋር ስብሰባ ነበረኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ከአረብ ቡድን አምባሳደሮች ጋር መደበኛ ስብሰባ ነበረኝ፡፡ ሌሎች ሥራዎችም ይኖራሉ፡፡ የማላዊ ፕሬዚዳንት በመሞታቸው የተሰማንን ሀዘን ለመግለጽም ማላዊ ኤምባሲ ተገኝቻለሁ፡፡ ከዚያ ከእናንተ ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ወደ ኤምባሲ ተመለስኩ፡፡ እናንተን ሸኝቼ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለሥራ እሄዳለሁ፡፡

የየቀኑ ሥራ በፕሮፌሽናል እና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም በመሄድ እወያያለሁ፡፡ ትናንት ማታ ደግሞ በኢትዮጵያ ፋብሪካዎች ያሏቸው የግብጽ ባለሀብትን አስተናግደናል፡፡

ከኢትዮጵያ ባለሀብቶችና ከመንግስት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተናል፡፡ የሐገራት ብሔራዊ ቀኖችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ የበርካታ ሀገሮች ተወካዮች እና ትልቅ ዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ አባላት ስላሉ በየሀገራቱ ብሔራዊና ሌሎች በዓላት ላይ መገኘት ይኖርብናል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት እልቂትን የሚዘክር ዝግጅት ላይ ጧት በአፍሪካ ሕብረት፣ ምሽት ላይ በሩዋንዳ ኤምባሲ ተሳትፈናል፡፡ የእረፍት ቀን ቢሆንም አንድ አምባሳደር በተለይ የግብጽ በእንዲህ ያለ ዝግጅት ላይ መገኘት አለበት፡፡ ከተቀባይ ሀገር ጋር በቀናነት ለመስራት መንገዱ እንዲህ ነው፡፡ ሥራ የምትሰራው በዚህ መልኩ እንጂ የቢሮህን በር ዘግተህ የተወሰኑ ወረቀቶች በማንበብ ሥራዬን አሟላሁ የምትልበት አይደለም፤ የአምባሳደር ሥራ፡፡

ክቡር አምባሳደር የቀረ መልእክት ካለዎት…

አመሰግናለሁ፡፡ ከናንተ ጋር ቃለምልልስ በማድረጌ ደስተኛ ነኝ፡፡ መልእክቴም በዚህች ታላቅ ሀገር በዚህ ወቅት እዚህ በመሆኔ እኮራለሁ፡፡ ግንኙነቶች በገንቢና በትክክለኛ መንገድ እየሄዱ ነው፡፡ ትልቁ አብሮነታችን ለጋራ ጠቀሜታዎቻችን የበለጠ ምቹ እየሆነ ነው፡፡ የሁለቱንም ሀገራትና ሕዝቦች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ እዚህ በግብፅ ቤተሰብ ውስጥ እንዳለሁ ይሰማኛል፡፡ ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከመተባበርም ብዙ ተጠቃሚ እንሆናለን ሁላችንም፡፡ ይህን አቅም ይበልጥ መጠቀም አለብን፡፡ አሁን አየሩ ጤናማ ነው፡፡ ጤናማ አየር ሳይኖር በመሬት ላይ ፕሮጀክቶች መተግበር አይቻልም፡፡ ጤናማ የፖለቲካ አየር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ወደ አዲስ እውነታ መለወጥ አለብን፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች፣ አዳዲስ የትብብር ስምምነቶች እና በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል የላቀ መስተጋብር ያስፈልጋል፡፡ ፈታኝ ሥራ ቢሆንም በጣም ውድና ብርቅ፤ በጣም ጠቃሚም ነው፡፡ እዚህ አምባሳደር እንደመሆኔ ግንኙነታችንን ይበልጥ ለማጐልበት ጠንክረን እንሰራለን፡፡

 

 

Read 5657 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 13:19