Sunday, 29 October 2017 00:00

በአንድ ኩላሊት ሙሉ ቤተሰብን መታደግ!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

በአሁኑ ወቅት የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ አባል የሆኑ 413 ህሙማን የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ህሙማን በሳምንት እስከ 1500 ብርና ከዚያ በላይ በማውጣት የኩላሊት እጥበት (ዲያሊስስ) ያደርጋሉ፡፡ የበጎ አድራጎት ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ እንደገለጹት፤ ማህበሩ በሳምንት 600 ብር ለህሙማኑ በመደጎም፣ ወጪያቸው ወደ 900 ብር ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡ ማህበሩ የተለያዩ ገቢዎችን በማሰባሰብ ዲያሊስስ የሚያደርጉ ህሙማንን እንደሚደግፍ ጠቁሞ፤ የህሙማን ቤተሰቦች፣ የቅርብ ዘመዶችና ወዳጆች ለህሙማኑ ኩላሊት በመለገስ፣ ህይወታቸውን እንዲታደጓቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ በኢትዮጵያ ሆቴል የኩላሊት ንቅ ተከላ (Transplant) ያደረጉና ወደ ቀድሞ ጤናቸው የተመለሱ ህሙማንና ኩላሊት የለገሱ የህሙማን ቤተሰቦች፣ የትዳር አጋሮችና ወንድምና እህቶች ለማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩና ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ በተዘጋጀ መድረክ፤ ”ህብረተሰቡ ግንዛቤ ስለሌለው ነው እንጂ ኩላሊት ተቀባዮችም ሆነ ለጋሾች ያለ ምንም ችግር በጤንነት ህይወታቸውን መቀጠል ይችላሉ” ብለዋል - ራሳቸውን በምሳሌነት በመጥቀስ፡፡ ከኩላሊት ለጋሾችና ተቀባዮች መካከል የፌደራል ፖሊስ ዕውቁና አንጋፋው ሙዚቀኛ፣ ጋዜጠኛ ኮማንደር አበበ ሙሉጌታና ታናሽ ወንድሙ እሸቱ ሙሉጌታ ይገኙበታል፡፡ ኮማንደሩ የኩላሊት ህመም ተጠቂ መሆኑን እንዴት አወቀ? አስጨናቂ የሆነውን የኩላሊት እጥበት ጊዜያት እንዴት አሳለፈው? ታናሽ ወንድሙ እሸቱ ሙሉጌታ፣ ኩላሊቱን ለግሶ ህይወቱን የታደገው እንዴት ነው? ግንዛቤውን፣ ውሳኔውን፣ ድፍረቱን፣ ደግነቱን --- ከየት አገኘው? የወንድማማቾቹን ልብ የሚነካ አስደማሚ ታሪክ እነሆ ከአንደበታቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሁለቱንም አነጋግራቸዋለች፡፡  
=========

 “ሁሉም ተረባርቦልኝ ጤናዬ ተመልሷል”
 
  ኮማንደር፤ እንኳን ለዚህ አበቃህ--- እንኳን ወደ ጤናህ ተመለስክ።
እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እግዜር ይስጥልኝ፤ አሁን ወደ ሙሉ ጤንነቴ ተመልሻለሁ፡፡
ከ30 ዓመት በላይ በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ በሙዚቀኝነትና በጋዜጠኝነት አገልግለሃል፡፡ ለመሆኑ ፖሊስን እንዴት ተቀላቀልክ?
ተወልጄ ያደግኩት ኮልፌ ወረዳ 25 ቀበሌ 06 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ አንዳንዴ ያደግሽበት አካባቢ በሙያሽም በኑሮሽም ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ አጠገብ ተወልጄ  እንደማደጌ፣ ለሙዚቃም ቅርብ ነኝ፤ እዛው ሲለማመዱ ከት/ቤት መልስ እየሄድን እንከታተል ነበር፡፡ ይሄም ለሙዚቃ ፍቅር እንዲኖረኝ እርሾ ሆነ ማለት ነው፡፡ ከዚያም አድጌ 18 ዓመት ሲሞላኝ፣ ሙዚቀኛ ሆኜ ተቀጠርኩኝ፡፡ አሁን አንቺ የምታውቂኝ ጋዜጠኛ ሆኜ ነው፡፡ እንዳልኩሽ ግን ቀደም ብዬ ሙዚቀኛ ነበርኩ፡፡
ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ነበርክ? ድምፅስ ትሞክር ነበር?
በፍፁም! ድምፅ አልሞክርም ነበር፡፡ ያው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ውስጥ የሙዚቃና የቴአትር ክፍል ባልደረባ ሆኜ ተቀጠርኩኝ፡፡ በዚህ ሙያ ሰልጥኜ ከተመረቅኩኝ በኋላ በአጋጣሚ አለመረጋጋትና ሰላም ማጣት ሰፍኖ ስለነበረ፣ በወቅቱ አጠራር ባሌ ክ/ሀገር ወደተባለው ቦታ ተዛወርኩኝ፡፡
ወቅቱ መቼ ነበር?
በ1971 ዓ.ም ነበር፡፡ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ውትድርና ገብተን፣ ግዳጃችንን ከተወጣን በኋላ ወደ ሙያቸው ይመለሱ ተባልን፡፡ እዚያው ባሌ ውስጥ “ቢላምባስ” የተባለ የሙዚቃ ባንድ ተቋቁሞ፣ የባንዱ መሪ ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ እኔ ድራም (ጃዝ) ተጫዋች ነበርኩኝ፡፡ ከዚያ ሜጀር ፒያኖ ተምሬ፣ ለ14 ዓመት በሙዚቃው ሰርቻለሁ፡፡
ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ እንዴት ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ገባህ?
በልጅነትሽ “ስታድጊ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?” ተብለሽ ተጠይቀሽ ታውቂያለሽ?
አዎ የተለመደ ጥያቄ ነው፡፡
ያኔ ጋዜጠኛ መሆን እፈልጋለሁ እንደማትይ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔ ስጠየቅ የሙዚቃው ተፅዕኖ ውስጤ ቢኖርም የጋዜጠኝነትም ፍላጎት ነበረኝ። ከሙዚቃው ቀጥሎ ብሆን ብዬ የምመኘው ጋዜጠኝነት ስለነበር እማር ነበር፡፡ ወታደር ቤት ትምህርት ጨርሰሽ አትገቢም፡፡ እኔም ወታደር ቤት ነው ትምህርቴን የጨረስኩት፡፡ ነገር ግን እዚያ ጋዜጠኛ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ፣ ምንም እንኳን ድራም ተጫዋች ብሆንም ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መድረክ እመራ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ፣ ክህሎቴን አሳደገልኝና የፖሊስ ጋዜጠኛ መሆን ቻልኩኝ፡፡
በትክክል ጋዜጠኝነት የጀመርክበት ወቅት መቼ ነው?
ከመንግስት ለውጥ በኋላ ነው፡፡ የፖሊስ የሚዲያ ባለሙያ  የሆንኩት በ1989 ዓ.ም ነው፡፡
በጋዜጠኝነት ያሳለፍካቸው ዓመታት ምን ይመስላሉ?
መጀመሪያ ለሬዲዮ ጋዜጠኝነት ተፈትኜ አልፌ፣ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ማገልገል ጀመርኩ። በዚህ እየሰራሁ ሳለ ባጋጣሚ ሰራዊቱ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማዘጋጀት ሲጀምር፣ ለዛ የምንመጥን ሰዎች ተመርጠን ገባን፡፡ ሻምበል ግዛው ዳኜን ታስታውሺዋለሽ? እሱ የእኛ ፋና ወጊ ነው፤ አርአያችንም ነበር፡፡ ነፍሱን ይማረውና እሱን ተከትለን--- ብዙ ወንጀል መከላከሎችን፣ ማጋለጦችን በመስራት፣ ከባልደረቦቼ ጋር ሳገለግል ቆይቻለሁ፡፡ ሥራዬን ያቋረጥኩትም በህመሜ ምክንያት ነው፡፡   
ኩላሊትህን መታመምህን ያወቅከው እንዴት ነው? የህመም ስሜቶችና ምልክቶች ነበሩብህ?
የሚገርምሽ ነገር እኔን በቅርብ የሚያውቁኝ ብዙ ሰዎች፤ ”አበበ ከታመመ ታዲያ እኛ ምን ልንሆን ነው” ይሉ ነበር፡፡
ለምን ነበር እንደዛ የሚሉት?
ምን መሰለሽ--- እኔ ቤት ፊት ለፊት ሜዳ አለ፡፡ ጦር ሀይሎች ነው የምኖረው፡፡ ይህ ሜዳ የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሰዎች ስፖርት የሚሰሩበትና ልጆች ኳስ የሚጫወቱበት ነው፡፡ ታዲያ እኔ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ስራ ከመግባቴ በፊት ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ እሮጥና፣ ሻወር ወስጄ፣ ነቃ ብዬ ነው ቢሮ የምገባው፡፡ ይሄ የዘወትር ተግባሬ ነው። ለዚህ ነው ስታመም፣ ይህን የሚያውቁ ሰዎች፤ ”እሱ ከታመመ እኛ ምን ልሆን ነው” ይሉ የነበረው። ህመሙ ምንም ምልክት አልሰጠኝም፡፡ አቅቶኝ ቤት እስክውል ድረስ ሥራ ላይ ነበርኩኝ። ከዚያ ሀኪም ቤት ስሄድ “ኩላሊትህ እየሰራ አይደለም” አለኝ፤ ሀኪሙ፡፡ እኔ ታምሜ ተኝቼ አላውቅም፤ ሌላም በሽታ የለብኝም፡፡ ሀኪሙ የአንተ ኩላሊት “ሆለስታት ዲዚዝ” ነው አለኝ - በተፈጥሮ ከዘር የተነሳ ኩላሊት ያለው የጡንቻ ደረጃ ደካማ መሆንና እድሜ እየጨመረ ሲሄድ፣ ቀስ በቀስ እየቀነስ ሄዶ፣ ከዚያ የሆነ ቀን ላይ ሙሉ በሙሉ ስራውን የሚያቆምበት ሁኔታ ነው፡፡ ይሄ ነው ችግርህ ነው ያለኝ፡፡
ከዚያስ?
እኔ መጀመሪያ ጨጓራዬን ነበር ያመመኝ የመሰለኝ፤ ምክንያቱም ምግብ ውስጤ አልቀመጥ አለ፡፡ ኪሎዬ በጣም በአጭር ጊዜ አሽቆለቆለ፤ ሁኔታው አሳሳቢ ሲሆን ባለቤቴ የግል ህክምና ቦታ ወሰደችኝ፡፡ ምርመራውን ያደረገው ዶ/ር ሲደነግጥ አየሁት፤ ምንድነው ስል “ኩላሊትህ እየሰራ አይደለም” ብሎ ከላይ የገለፅኩልሽን ነገር ነገረኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ድንጋጤው ነው የባሰኝ፡፡ ኪሎዬ መቀነስና የምግብ አለመቀመጥ ቢኖረኝም የከፋ ህመም አልነበረኝም፡፡ ከዚያ ነው ዲያሊስስ የጀመርኩት። ይህ ከሆነ 3 ዓመት ሊሆነው ነው። ዲያሊሲስ ያደረግኩት ከአንድ ዓመት በላይ ነው። በዚህ ጊዜ አገርም መንግስትም ሰራዊቴም የማላውቀው ሁሉ ተረባረበ፡፡ ከኪሴ ምንም ሳላወጣ፣ እንደ ሌላው ቤት ንብረት ሳልሸጥ ዲያሊሲስ ሳደርግ ቆየሁ። ከዚያም ወንድሜ ኩላሊት ለግሶኝና ጳውሎስ ሆስፒታል እድል አግኝቼ፣ ንቅለ ተከላውን አድርጌ ወደ ጤናዬ ከተመለስኩ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ሞላኝ፡፡ ወንድሜ ስድስተኛ ታናሼ ነው፤ ከእሱ በላይ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሉ፡፡ ግን ጤነኛ ሆኖ የተገኘው እሱ ነው፡፡ ሌሎቹ በእድሜም ከፍ ከፍ ያሉ፣ ትዳር ያላቸውና የወለዱ ናቸው፡፡ ይህ ወንድሜ ስለ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ያለው ግንዛቤ ይገርማል፡፡ ያለሁበትን ሁኔታ ሲመለከት፣ “አይኔ እያየ ወንድሜ አይሞትም እሰጠዋለሁ” አለ፡፡ ይሄው ዛሬ ሁለታችንም በጤና አለን፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
በህመምህ ወቅት “በቃ መሞቴ ነው” ብለህ ተስፋ ቆርጠህ ነበር?
በፍፁም! ሰው የሚሞተው ተስፋ የቆረጠ ዕለት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ አንደኛ በእግዚአብሔር በፅኑ የማምን ነኝ፡፡ ሁለተኛ ብርታትና ተስፋ የሆኑኝ፣ ከተለያየ አገርና ቦታ፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጎንደር ከአዲስ አበባና ከሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች፣ የማላውቃቸው አራት ወጣቶች ኩላሊት ሊሰጡኝ መጥተዋል፡፡ ከማላውቃቸው ሰዎች ለመታከሚያ የሚሆን ገንዘብ ወደ ባንክ አካውንቴ ይገባል፡፡ ከውጭም ከአገር ውስጥም ስልክ ይደወላል፡፡ ይሄ ሁሉ ርብርብ ሲመጣ “በቃ አልሞትም ወገን አለኝ፤ ቤተሰብ አለኝ” የሚል ብርታት ሰጠኝ፡፡ እርግጥ ሰው ነሽ ትፈሪያለሽ። ቤተሰብሽን ታስቢያለሽ፤ በቃ ቤተሰቤን በትኜ-- የሚለው ይሰማሻል፡፡ በበዓል ያ ሁሉ ደስታ ፌሽታ ይጎድላል፡፡ እኔ አንዴ ታምሜአለሁ፤ ቤተሰቤ ግን እኔን እያየ በጣም ነበር የሚጨነቀው፡፡ ዲያሊሲስ ማድረግ ያለው አስጨናቂ ሂደት፣ ራሱን የቻለ ሌላ ችግር ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኜ ግን ተስፋ አደርግ ነበር (ንግግሩን የእንባ ሳግ እያቋረጠው…)፡፡
ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ከተማ ከበደ፤ ”የፈጀውን ይፍጅ በሚሊዮንም ይቆጠር አሳክመዋለሁ” ብለዋል፡፡ ይሄ ራሱ ብርታት ይሰጥሻል (አቶ ከተማ፤ ለኩላሊት ህሙማን እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ከወራት በፊት 5 ሚ. ብር መለገሳቸው ይታወሳል)፡፡ ይሄ ሁሉ አልፎ አሁን እንደምታይኝ፣ ወዜ ተመልሶ በሙሉ ጤንነት ላይ እገኛለሁ፡፡ ደግሞ ንቅለ ተከላው እዚሁ አገራችን በነፃ መካሄዱ የህሙማንን ተስፋ በእጅጉ የሚያለመልም ነው፡፡ እንደነገርኩሽ፣ ሰው ሀብት ንብረቱን ሸጦ ታክሞ እንኳን አይድንም፤ እኔ ቤሳቤስቲን ሳላወጣ በወገን እገዛ ለዚህ በቅቻለሁ፡፡
ታዋቂ የሚዲያ ሰው መሆንህ፣ ለዚህ አስተዋፅኦ ያደረገ ይመስለኛል?

=========

“ለወገናችን ኩላሊት እንስጥ፤ ወገናችንን እናትርፍ”

እራስህን አስተዋውቀን?
እሸቱ ሙሉጌታ እባላለሁ፤ ዕድሜዬ 30 ነው። የኮማንደር አበበ ሙሉጌታ የመጨረሻ ታናሽ ወንድሙ ነኝ፤ እሱም የመጀመሪያ ታላቅ ወንድሜ ነው፡፡
የታላቅ ወንድምህን የኩላሊት ህመም የሰማኸው እንዴት ነበር?
ወቅቱ  ለእኛ  አስቸጋሪ ነበር፡፡ ወንድሜ ኩላሊቱን ከመታመሙ አንድ ዓመት በፊት እናታችንን ያጣንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከእናታችን ሀዘን ብዙም ባላገገምንበት ወቅት የእሱን ኩላሊት ስራ ማቆም ሰንሰማ፣ ሊሰማን የሚችለውን መገመት ይቻላል፡፡ የአቤን የጤና መርዶ የሰማንበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ፡፡ ከመስማታችን ቀደም ብሎ ጠቅላላ ቤተሰብ ይሰበሰብና ወጣ ብለን የቤተሰብ ማህበር አለ፤ እናከብራለን፡፡ እዛ ሄደን ከመጣን በኋላ ነው የተከሰተው፡፡ በዕለቱ እሱም በሙሉ ጤንነት ላይ ነበር፡፡ ከዚያ ለአንድ ሳምንት አልተገናኘንም፡፡ ደወልኩለት፡፡ ምነው ጠፋህ? ስለው፣ ”ትንሽ አሞኛል፤ ሀኪም የነገረኝ ጥሩ አይደለም” አለ፡፡ በነጋታው ደግሜ ስደውል፣ ፖሊስ ሆስፒታል ተኝቶ ነበር፤ እሱም ተረብሿል እኔም ቤተሰቤም በጣም ነበር የደነገጥነው፡፡
ከዚያ  በኋላ ያሳለፋችሁት ጊዜ ፈታኝ መሆኑን መገመት አያዳግትም----
እሱም ቤተሰቡም ብዙ ፈተና አሳልፈናል፡፡ ብቻ አልፎ ስናወራው ቀላል ይመስላል፡፡ በተለይ ዲያሊሲስ ከገንዘቡ መብዛት እስከ ሂደቱ ስቃይ በጣም ያሳዝናል፡፡ በሳምንት እስከ 3 ሺህ ብር ድረስ ነበር የሚያስወጣው፡፡ ከዚያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠቱ ዲያሊስስ በየቦታው ተጀመረና ወደ 1500 ብር ዝቅ አለ፡፡ አሁን የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን፣ ወደ 900 ብር ዝቅ ማለቱን ሲናገሩ ስሰማ ደስ ብሎኛል፤ ሆኖም ይሄም ከባድ ነው፡፡ ምከንያቱም የኑሮ ሁኔታችን የሚታወቅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኑሮውም ገቢውም ከባድ ነው፡፡ እኛ እንደውም አቤ ታዋቂ በመሆኑ የገንዘቡ ጫና አልነበረብንም፤ ግን የጤናው ሁኔታ--- ስቃዩ አስጨናቂ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ ንቅለ ተከላው መካሄዱ ራሱ ትልቅ ነገር ነው፤ ውጭ ይሂድ ቢባል ፕሮሰስ እስከሚደረግ ታማሚው ሊያልፍ ይችላል፡፡
ቀደም ሲል ስለ ኩላሊት ንቅለ ተከላና ሂደት ስትናገር በቂ ግንዛቤ እንዳለህ ጠርጥሬ ነበር፡፡ ትምህርትህ ምንድን ነው? ሙያህስ?
ሙያዬም ሆነ ስራዬ ከወንድሜ የተለየ ነው። እኔ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ነው ያጠናሁት፤ የምሰራውም በዚሁ ዘርፍ ነው፡፡ ስለ ኩላሊት ህመም በዝርዝር ባላውቅም በአንድ ወቅት (ከረጅም አመት በፊት) አንድ ታዋቂ የውጭ አገር አርቲስት፣ በአንድ ኩላሊት እንደሚኖር ሰምቼ ነበር። መረጃውን የሰማሁት በሚዲያ በመሆኑ ውስጤ ቀርቷል፡፡ ይህን ከሰማሁ ከረጅም ዓመት በኋላ ችግሩ በሬን አንኳኩቶ ቤቴ ገባ፡፡ እርግጥ ነው፣ አቤ ከኔ በላይ ያሉ ወንድምና እህቶች አሉት፤ ልጆችም ወልዷል፤ እኔ ግን ግንዛቤው ስለነበረኝ ወደዚህ ውሳኔ መጣሁ፡፡
ወንድምህ ኩላሊት እንድትለገሰው ጠይቆህ ነበር?
በፍፁም! በራሴ ፍቃደኝነት ነው፡፡ ይህን የወሰንኩት የአቤን የጤና ሁኔታ ሳይ ነው፡፡ ሙሉ ጤነኛ፣ ሥራውን በአግባቡ የሚሰራ፣ ቤቱንና ቤተሰቡን ይመራ የነበረ ሰው፤ በአንድና በሁለት ቀን ልዩነት በዊልቸር ሲገፋ ማየት፣ ያውም የእናትሽ ልጅ - ወንድምሽ ሆኖ በጣም ያምማል፡፡ ይሄ ነው ውሳኔ ላይ ያደረሰኝ፡፡ በዚህ ላይ የነበረኝ ግንዛቤ፣ ራሴን ለማሳመን ጊዜ እንዳይወስድብኝና ቶሎ እንድወስን አድርጎኛል፡፡
አንድ ኩላሊት ለጋሽ፤ ወደ ንቅላ ተከላው ከመሄዱ በፊት ምን ዓይነት ሂደቶችን እንደሚያልፍ ልትነግረኝ ትችላለህ?
መጀመሪያ በውስጤ ብወስንም እስኪ ራሴን ልፈትን፣ ስሜታዊ ሆኜ ነው የወሰንኩት? ይህን ነገር ሳደርግ ራሴን ብጎዳና ደግሞ ቤተሰቤ በኔ ቢጎዳስ? በሚል በግል ሀኪሞችን ማናገር ጀመርኩኝ፡፡ ከሁሉም ሀኪሞች የሰማሁት፣ እኔ ኩላሊቴ ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ምንም አይነት ጉዳት እንደማይደርስብኝና በጤና መኖር እንደምችል ነው። ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ ጋር ተደምሮ ውሣኔዬን በግልፅ ለማሳወቅ ድፍረት አገኘሁኝ፡፡ ንቅለ ተከላው በሚደረግበት ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ከሁለት ወር በላይ እስኪሰለቸኝ ድረስ የጤና ምርመራ ተደርጎልኛል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሥነ-ልቦና ባለሙያዎች፣ ግንዛቤ ተሰጥቶኛል፤ ጥያቄዎች ቀርበውልኛል፡፡ ሁሉንም አልፌ ነው፣ ኩላሊቴን ሰጥቼ ወንድሜን ያተረፍኩት፡፡
የንቅለ ተከላው ጊዜ ሲቃረብ፣ ፈርተህ ውሳኔህን ለማጠፍ አልዳዳህም?
በፍፁም ውሳኔዬን ለማጠፍ አላሰብኩም፤ አልፈራሁምም፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ይህን እንዳላደርግ በተደጋጋሚ በግሌ ሀኪሞችን ካማከርኩ በኋላ ነው በይፋ ውሳኔዬን ያሳወቅኩት። እርግጥ የሰው ልጅ በጥቅም ተደልሎ፣ ሰዎች አስገድደውት ወይም ሰው በመሆኑ ብቻ ሰብአዊነት ተሰምቶት፣ ስሜታዊ ሆኖ ኩላሊት ለመስጠት ሊወስን ይችላል። ይህን ካደረገ በኋላ ሊቆጨውና ሊፀፀትም ይችላል፡፡ ይህ እንዳይሆን በሀኪሞች ቀድሞ ይነገራል ይመከራል፡፡ ይህንን ሁሉ አልፎ አንድ ሰው ተስማምቶ የሚፈርመው ፊርማ አለ። እኔ ይህን ሁሉ አልፌያለሁ፤ ነገር ግን “ይህንን ብትፈርምም ለንቅለ ተከላው ገብተህ ማደንዘዣ ልትወጋ ሰከንዶች እስኪቀሩህ ድረስ አልፈልግም፤ ሀሳቤን ለውጫለሁ ማለት መብትህ ነው፤ ሀሳብህን መቀየር ትችላለህ” ተብያለሁ፡፡ መብቱ እስከዚህ ድረስ ነው የሚሰጥሽ፡፡ ኩላሊት ለጋሹ እስከመጨረሻው በራሱ እንዲወስንና እንዳይፀፀት እድል መሰጠቱ በጣም ያስደስታል፡፡ እኔም እስከ መጨረሻ መብቴን ተጠቅሜ በውሳኔዬ ፀንቻለሁ፡፡
በአሁኑ ሰዓት ታላቅ ወንድምህ ጤናው ተመልሶ፣ ከጎንህ ተቀምጦ ስታየው ምን ይሰማሀል?
እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በህይወቴ ታሪክ የሰራሁ ይመስለኛል፤ ይሄ ጉራም አይደለም፡፡ የእኔ ይህን ማለት ሌሎችን ያስተምራል፡፡ አየሽ፣ አቤ የቤተሰቡ ብቻ አይደለም፤ የህዝብ ሀብት ነው፤ ወንጀል ሲከላከል ቀማኛና ሌባን ሲታገል የኖረ፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለውለታና ልጅ ነው፡፡ ስለ ወንድሜ ይህን ስናገር፣ ኩራት ይሰማኛል፤ ይሄም ጉራ አይደለም፡፡ የወንድሜ ስራዎች በግልጽ በህዝብ የሚታወቁ ምስክሮች ናቸው፤ ስለዚህ የህዝብን ልጅ ነው ፈጣሪ እኔን ምክንያት አድርጎ ያተረፈው፡፡ ለእኔም ፈጣሪ ነው ይህን ድፍረትና የርህራሄ ልብ የሰጠኝ፡፡ አየሽ ሰው በተለያየ ምክንያት ህይወቱ ማለፉ አይቀርም፤ በሰውም በፈጣሪም ዘንድ ክብር ያለው ስራ ሰርቶ ማለፍ ግን ይለያል። አሁን ንቅለ ተከላው ከተካሄደ አመት ከሰባት ወር ሆኖታል፤ በነዚህ ጊዜያት ደስታውን ፈገግታውን፣ የቤተሰቡንና የልጆችን ደስታና እፎይታ ማየት ለእኔ ትርጉም አለው፡፡ እሱና እኔ ያለን ፍቅር ከድሮም የተለየ እንደሆነ ነግሮሻል፡፡ ዛሬ ላይ ከእሱ ውጭ እህታቸው፣ ሚስታቸው፣ ወንድማቸው---- ኩላሊት ለግሰዋቸው፣ ህይወታቸው የቀጠለ ወንድሞችና እህቶች በመካከላችን ተገኝተው መስክረዋል፡፡ እኔ ሰስቼ ወንድሜ እስካሁን ዲያሊሲስ ላይ እየተሰቃየ ቢሆን ወይ ቢያልፍ ምን ይሰማኝ ነበር፡፡ አሁን ክብሩም ደስታውም የእኔ ነው፤ ሁሉም ሰው አጠገቡ ያለውን ሰው ማዳን ይችላል፡፡ ቀላል ነው፡፡
ባለትዳር ነህ? ልጆችስ ወልደሀል?
እስካሁን ያልገለፅኩትን ጥሩ ጥያቄ አነሳሽልኝ። እኔ ባለትዳር ነኝ፤ የ7 ዓመት ልጅ አለኝ፡፡ አሁን ንቅለ ተከላ ካደረግኩ በኋላም ልጅ ሊኖረኝ ነው፡፡ ብዙ ሰው ከንቅለ ተከላ በኋላ መውለድ የሚቻል ሁሉ አይመስለውም፡፡ ግን ይቻላል፤ ባለቤቴ የሰባት ወር ነፍሰጡር ናት፡፡ እንዲያውም ደስተኛ ነኝ፤ ማህበረሰቡ ግንዛቤ ቢኖረው አንድም ሰው አይሞትም ነበር፡፡
አሁን አንተ የምትወስደው የተለየ ህክምና ወይም መድሃኒት አለ?
የተለየ ህክምና አላደርግም፡፡ ከተለያዩ ሱሶች ከሲጋራ፣ ከጫትና ከአልኮል ሱስ ራስን ማራቅ እንደሚገባ ሀኪም ያዝዛል፡፡ እኔ ድሮም የለሁበትም። ይሄ ኩላሊት ለለገሰ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰው የሚመከር ነው፡፡ ውሃ በቀን ከሁለት ሊትር በላይ መጠጣትና ከላይ የተገለፁትን የሀኪሞች ትዕዛዞች ማክበር ከተቻለ፣ ያለምንም ችግር መኖር ይቻላል። ሥራዬን እየሰራሁ ነው፣ ጤነኛ ነኝ፤ በወንድሜ ደስተኛ ነኝ፣ በየስድስት ወሩ ምርመራ አደርጋለሁ። እስካሁን ሶስት ጊዜ አድርጌ፣ በጣም ጥሩ ጤንነት ላይ እንደምገኝ ሀኪም አረጋግጦልኛል። አቤ አሁን በሀኪም ትዕዛዝ፣ መድሀኒት ይወስዳል፤ እኔ ግን አንዳችም መድሀኒት አልወስድም፡፡ የሰጪ ጥቅም ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ ለወገናችን ኩላሊት እንስጥ፤ ወገናችንን እናትርፍ እላለሁ፡፡ ኩላሊት በመስጠታችን፣ ለዲያሊሲስ የምንከፍለውን ብር ለማግኘት ከሚመጣው ውጣ ውረድ እንድናለን። የሰው ፊት ከማየት አይብስም፡፡ ለህመምተኛው ብቻ ሳይሆን ለአስታማሚ ቤተ-ዘመድም እፎይታ ነው እላለሁ፡፡
የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖርሃል?
በዚሁ አጋጣሚ ሀኪሞችንም ጋዜጠኞችንም መንግስትንም የምማፀነው፣ ህመሙ እየተስፋፋና የስነ-ልቦናም የኢኮኖሚም ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ አሁን ለህመሙ የተጋለጡትን እየረዳን፣ ጎን ለጎን ለህመሙ መስፋፋት ምክንያቱ ቢጠና ጥሩ ነው፡፡ የህመሙ መንስኤ ምንድን ነው? የአኗኗር ዘይቤያችን ነው? አመጋገባችን ነው? ---- ይሄ ተጠንቶ መከላከል ላይ ብናተኩር፣ የችግሩ ሰለባ ከመሆን እንድናለን  የሚል መልዕክት አለኝ። አመሰግናለሁ፡፡

Read 2324 times