Sunday, 29 October 2017 00:00

“ውበት ያለ ቦታው!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(21 votes)

ይህን የመሰለ የውበት ዛላ፣ይህን የመሰለ የፍቅር አድማስና የፍቅር ሙዚቃዊ ድምፅ፤ እንዴት በሞት ጭጋግ፣ በሀዘን እልፍኝ ይቀመጣል? .. እያልኩ በልቤ እንዳልጎመጎምኩ ጉንጭና ጉንጭዋን ስሜያት ተቀመጥኩ፡፡ እሷም ፊት ለፊቴ መጥታ ተቀመጠች። የቀይ ዳማ ፊትዋ በማራኪ ቅኝት፣ ልቤ ላይ ንፋሱን ጣደ፡፡
“ምናለ ስራ ብትቀይር?” ብዬ አሰብኩ፡፡ ልነግራት ግን ድፍረት አልነበረኝም፡፡
“ሔዋ” አልኳት፡፡
“አቤት ጌችዬ… ዛሬ ደሞ ጨፍገግ ብለሃል”
መልስ አልሰጠኋትም፡፡ እውነት ለመናገር በጣም ፈርቻለሁ፡፡ የመቃብር ቦታና የሬሳ ሳጥን መሸጫ ሥፍራ አይደላኝም፤ ይቀፈኛል፡፡ ሆኖም  ይህንን ለርሷ መንገር፣ የፍቅራችን እሳት ላይ ውሃ መድፋት ነው፡፡
በዚህ የሬሳ ሳጥን መሸጫ፣ ይህን ዓይነት ውበት፣ ይህቺን የመሰለች ፅጌረዳ ማየት፣ ነፍስን ወዳልታሰበ ፍልስፍና ይነዳል፤ ወዳልተገመተ አቅጣጫ  ይበትናል፡፡
“እሺ ሥራስ? ኑሮስ?” አለችኝ፡፡
ፀሐይ ለብቻዬ የወጣልኝ ነው የመሰለኝ፡፡ የአጠገቤ ፀሐይ… የበራፌ ሀመልማል!
“የናንተስ ሥራ?” አልኳት፤ በአጸፋው፡፡
“የኛ ሥራ ያስጠነቅቃል፣ ከጥፋት ይመልሳል!”
“እንዴት ማለት?”
“በሬሳ ሳጥኖች መካከል ስትሆን፣ ሁሌም የሞትን ከንፈር ለመሳም የተዘጋጀህ ፍቅረኛ መሆንህን ጨርሶ አትረሳም !”
“እኔ ግን ..”
“እ … አንተ ግን ..?”
“ከዚህ ሥራ ብትለቂ ደስ ይለኛል … አንቺን የመሰለ ሸጋ!”
“ተሳሳትክ! ህይወት ሁሌም ጫንቃዋ ላይ ሞት ተፈናጥጧል፡፡ እዚህ ቤት ደግሞ ህይወትና ሞት በጉርብትና ሳይሆን በደባልነት ይኖራሉ!”
“መቼም ህይወት አንቺ ነሽ!”
ሳቀች፡፡
“በነገራችን ላይ ቢዝነሱ የአክስቴ ነው፡፡ … ሌላ ቦታ የሙሽራ ቬሎ ማከራያና ልብስ ቤትም አላት፡፡ እኔ ግን ይህንን መርጬ ነው …”
“ግን የሬሳ ሳጥን አይስፈራም? … ተስፋንና የትጋት ኃይልን አይሰብርም?”
“ለኔ እንደውም ትጋት ጨምሮልኛል፡፡ አንድ ረጅም ልቦለድ እየፃፍኩ ነው፡፡ ለፈጠራ ሥራዬ ዋነኛ ግብዐት ሆኖኛል፡፡”
“ደራሲ መሆንሽን አላውቅም---ማለቴ አልነገርሽኝም?”
“መፃፍ ደስ ይለኛል፤ ህይወቴ ነው ባልልም፣ የህይወቴ መንገድ ነው”
“ግን ደራሲ አትመስይም!”
“ደራሲ የተለየ መልክ አለው እንዴ?”
“ትንሽ ቀጠን ያለ፣ ትካዜ የሚያበዛ፣ ነጭናጫ … ከማህበረሰብ የተነጠለ፣ ወፈፌ ነገር ይመስለኛል---”
ረጅም ሳቅ  ሳቀች፡፡ እኔም በልቤ “ደራሲው” የሚለውን መጽሐፍ እያስተዋልኩ ተመሰጥኩ፡፡
“የሬሳ ሳጥን፣ የሰውን ልጅ ሰፊ የህይወት መዝገብ ገልጦ ያስነብብሃል፡፡ የእንባ ኳሶች ውስጥ፣ የተንጠለጠሉ የተስፋ ጠብታዎች ሲረግፉ፣ ልብህ ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ ብዙ ትዝታዎችና ረመጦች ታገኛለህ--”
“ወደ ፍልስፍናው ታደያለሽ ማለት ነው?”    
“የሰው  ልጅ ከአንቀልባ ጀምሮ እስከ ቃሬዛ የፍልስፍና ቆረቆንዳ ነው፡፡ ብዙ ነገር ከርሱ ታገኛለህ፡፡ ሞትና ህይወት ተቃቅፈው ሲወለዱ፣ እልልታው ውስጥ፣ የሩቅ ሙሾ ድምፅ ታደምጣለህ። ያ ፍልስፍና ነው---”
“ግን  እንደምወድሽ ታውቂያለሽ አይደል?”
“በዚህ ጭጋጋማ ድባብ መምጣትህ ያልከውን ያረጋግጥልኛል! እኔም እኮ እወድሃለሁ!”
 ደስታ በውስጤ ሲንጠባጠብ ይሰማኛል፡፡
“ለምን ፍልስፍና አልተማርሽም?”
“ለማህበራዊ ሳይንስ አደላለሁ!”
“ይገርማል!”
“አይግረምህ፣ ማህበራዊ ሳይንስ፤ የሰው ህይወት ፍተሻ ነው፡፡ ለየብቻ በመኖር፣ የህይወት ንፋስ አንጠልጥሎ እንዳይጥለው፣ ሰንሰለት ሰርቶ የሚሳሳብበትን ገመድ ተርትሮ፣ መገምገምና ስምምነቱን በሳይንስ ማፅደቅ ነው”
“በል ተጫወት … ደንበኞቼን ላስተናግድ”
“ደንበኞቼ ማለት?”
“ሳጥን የሚገዙ ደንበኞቼ! እነርሱ ለኔ የታሪክ መዝገብ፣ የህይወት ፊርማዎች ናቸው”
“ደንበኞቼ ስትይ --- ደጋግመው የሚመጡ ናቸው ማለት ነው?”
“ላይሆኑ ይችላሉ … ግን በቃ ተጠቃሚዎች ናቸው!”
ወቸ ጉድ፤ እንደ ሆቴል፣ ካፌና ሱፐርማርኬት--- የሬሳ ሳጥን ደንበኞችም አሉ ማለት ነው ብዬ  በግርምት ተሞላሁ፡፡
አለባበሱና ነገረ ሥራው የጠገበ ቱጃር መሆኑን የሚያሳብቅበት አንድ በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገመት ጎልማሳ፣ የመኪናውን ቁልፍ እያሽከረከረ ወደ መሸጫው መደብር ዘለቀ፡፡  
“እመቤት፤ የትኛውን ብወስድ ትመክሪኛለሽ?” ጠየቀ ደንበኛው፤ ከተደረደሩት ሳጥኖች መካከል በዓይኑ የተሻለውን እየቃኘ፡፡
 ሰውየው ራሰ በራ ነው፡፡ ጢሙን በ”ኦ” ቅርጽ ተላጭቷል፡፡
“ልዩነታቸው የዋጋና የቅርፅ ነው!” አለችው፤ ትካዜውን እያነበበች፡፡
“ማን ነው የሞተብህ? ወጣት ነው?” ጠየቀችው።
“አይደለም፤ ወላጅ አባቴ ነበር--”
አባቴ ነበር---- ማለቱ ደነቀኝ፡፡ ለነገሩ  ሰው እስትንፋሱ ካበቃ በኋላ “ነበር” እንጂ ሌላ ምን ይባላል!?
“ሶሪ!... እንግዲህ ከእነዚህ ውስጥ ምረጥ!” አለችው፡፡
ይኸኔ ስልክ ተደወለለት፡፡ ባለቤቱ መሆንዋን ከንግግሩ ገመትኩ፡፡ ደስ በማይል ገጽታና ቅላጼ ለቅጽበት ያህል አናግሯት ዘጋ፡፡
“የማይመጥን ሣጥን አትግዛ--- የአስከሬን መኪናውም ቆንጆ ይሁን ነው የምትለኝ...” ሚስቱ ያለችውን ደግሞ ተናገረ፡፡
“እውነቷን ነው፤ የተመቸህን ምረጥ” አለችው፡፡
“ውዱን ሳጥን አድርጊልኝ፤ አለበለዚያ  ቁጭትና ፀፀት ጥርስ አውጥቶ ሊበላኝ ነው!” አላት በትካዜ ውስጥ ሰጥሞ፡፡
“ምነው --- ታመው አልጠየካቸውም?”
“አዎ፤ ቢዚ ነበርኩኝ---”
“በገንዘብስ አልረዳሃቸውም?”
ሰውየው ዝም ብሎ፣ የመኪናውን ቁልፍ ማሽከርከር ያዘ፡፡  
“ያኛውን አድርጊልኝ!” አለና ከመኪና ውስጥ ሰው ጠራ፡፡
 አንድ ጆፍጃፋ፣ የጥበቃ ልብስ የለበሰ ሰውዬ መጣ፡፡  
“የቱ ይሁን ጋሼ?”
“ያው ጥቁሩ - አባዬ ጥቁር ልብስ ይወድ ነበር--” አሁንም ትካዜ ውስጥ ገባ፡፡   
“በቃ--- አይዘኑ” አለና ሣጥኑን ወስዶ ጫነው - ጥበቃው፡፡
“እመቤት አመሠግናለሁ፤ ህይወት ድራማ እንደሆነ ዛሬ ገባኝ፤ አባቴን ሳላስታምም፤ የቸገረውን ሳልሰጠው - ስባ --- እርሱ አረፈና ተገላገለ----እኔ ግን ረመጥ ውስጤ ገባ፤ ፀፀት በላኝ---”
“አሁን አልፏል፤ ለሌላ ጊዜ መጠንቀቅ ነው” ስትል ልትመክረው ሞከረች፡፡
“አባቴ፤ በረሀብ ሞቶ በሊሞዚን ተቀበረ - የሚለው ነገር ነበረው፡፡ አሁንም እንዲያ ነው የሆነው--”
ሰውየው ብሩን ሰጥቷት፣ እንደተከዘ ከመደብሩ ወጣ፡፡  
“ለድርሰቴ ሌላ ግብዐት አገኘሁ….” አለችና እየፈነደቀች ጉንጬን በመዳፍዋ መታ አደረገችኝ፡፡
ሕይወት እንደዚህ ናት፡፡ ከአንዱ ፀፀትና እንባ፣የሌላው የጥበብ እንጀራ ይጋገራል፡፡  
“በረሀብ ሞቶ --- በሊሞዚን መቀበር! ግሩም አባባል አይደል? ና ሣመኝ--” አለችኝ፤ በእርካታ ተሞልታ፡፡
ማር ያጠቀስኩ መሠለኝ፡፡ እነዚያ የሬሳ ሳጥኖች መካከል፣ እንቡጥ ፅጌሬዳ ሣቀች፡፡
“መጽሐፌን በቅርቡ አሳትምና ይህን ሥራ እለቃለሁ”
“ከዚያስ?”
“ባል አግብቼ ደግሞ-- ህይወት ይቀጥላል”
“ደስ ይላል---እኔም በጉጉት የምጠብቀው በጋብቻ አንድ የምንሆንበትን ጊዜ ነው!”
“ካንተ ጋርማ አይደለም!” አለችኝ፤ ኮስተር ብላ እያየችኝ፡፡
ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ…
 “አንተማ የድርሰቴ አካል ነህ!”
“እንዴት?”
“ገፀ ባህሪ አድርጌሃለሁ!”
ሳላስበው ቦክስ ሰነዘርኩባት፡፡ አንደኛው የሬሳ ሳጥን ላይ በጀርባዋ ወደቀች፡፡
“ውበት ያለ ቦታው!” ብዬ አሰብኩ፡፡

Read 5876 times