Sunday, 29 October 2017 00:00

ኳሱን ማን ይመራዋል? ጁነዲን፤ አሸብር ወይስ ተካ...

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ጥቅምት 30 ላይ በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር የተወሰነ ሲሆን የፕሬዝዳንት ምርጫው በቀረቡት እጩዎች የስራ ልምድ እና ተቀባይነት ከፍተኛ ትኩረት እየሳበ መጥቷል፡፡    የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጉባኤው የሚካሄድበትን ከተማ መቀየሩን አስመልክቶ የአፋር ክልልን በደብዳቤ ይቅርታ የጠየቀ ቢሆንም የክልሉ መስተዳድር በውሳኔው ድንገተኛነት ማዘኑን ገልጿል፡፡
ከ2 ሳምንት በኋላ በሒልተን ሆቴል በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ መደረጉ ከፍተኛ ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ የወቅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በሁለተኛ የስራ ዘመን ሃላፊነታቸውን ለመቀጠል በድጋሚ የሚወዳደሩ ሲሆን በቀድሞ የፌደሬሽን አስተዳደሮች በፕሬዝዳንትነት ለ6 ዓመታት ካገለገሉት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ከሰሩት አቶ ተካ አስፋው ጋር ከባድ ፉክክር ይገጥማቸዋል፡፡ በፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫው በስራ ላይ የነበሩ የፌደሬሽኑ አመራሮች፤  በቀድሞ የፌደሬሽን አስተዳደሮች የሰሩ እና አመራሮች የነበሩ፤  የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ተጨዋች በእጩነት ተወክለው ለውድድር መግባታቸው በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ታሪክ ልዩ ምዕራፍ የሚከፍት ይሆናል፡፡
ከሚከተለው አስተዳደራዊ መዋቅር አጠቃላይ ይዘት ከውሳኔ አሰጣጥ፤ ከልማት እና ከዘላቂ የእድገት ስራዎች በተያያዘ  በየጊዜው የሚተቸው የእግር ኳስ ፌደሬሽን በአመራር ደረጃ የተለየ ለውጥ ለመፍጠር ጊዜ እንደሚፈጅበት ግን አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለያዩ ፌደሬሽኖች ለአመራርነት የሚመጡ በስፖርቱ ያለፉ ግለሰቦች ቢሆኑ ይመረጣል  በሚል ሃሳብ ያስተላለፉት መልዕክት በእግር ኳሱ አስተዳደር ላይ ተፅእኖ የፈጠረ ሲሆን የጠቅላላ ጉባኤው ወሳኝ አካላት የሆኑት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች፣ ለምርጫ የሚያቀርቧቸውን ተወካዮች በጥንቃቄ እንዲመርጡ በማሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ  ፌደሬሽን ጉባኤ የቀድሞ አትሌቶች እና አሰልጣኞች በፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባልነት በመግባት መስራታቸው ከፍተኛ መነቃቃት እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ዕጩዎቻቸውን ቀደም ብለው ባለማሳወቃቸው፤ በሁሉም የሚዲያ አውታሮችስለ ጉባኤው የምርጫ ሁኔታዎች እና የመወያያ አጀንዳዎች ዙርያ ብዙ የተጋጋለ ነገር አለመስተዋሉ፤ በተለይ ለፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ለስራ አስፈፃሚ አባልነት የሚፎካከሩ እጩዎች በይፋ አለመታወቃቸው እና ስለ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ወይንም የፌደሬሽን አስተዳደሩን ለመምራት ስለሚኖራቸው አቅም እንዲሁም ማስመዝገብ ስለሚፈልጉት ስኬት በዝርዝር አለመታወቁ የስፖርቱን ዋና ባለድርሻ አካላት አላስደሰተም፡፡
በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በሚደረገው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እያንዳንዱ ክልልና የከተማ አስተዳደር የሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ማንነትና ምንነት በይፋ የማሳወቂያው ቀነ ገደብ በሳምንቱ አጋማሽ ጥቅምት 15 ላይ ቢያበቃም በተለያዩ ሁኔታዎች የእጩ ማሳወቂያ መርሃግብሮችና አስፈላጊ ስራዎች ሊፈፀሙ ባለመቻላቸው  እስከ ጥቅምት 20  እንዲራዘም በፌደሬሽኑ ተወስኗል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው 15 ቀናት ሲቀሩት በፕሬዝዳንትነት ምርጫው 6 እጩዎች እንዲሁም  ከ10 ወደ 7 እንደሚቀንስ የሚጠበቀው የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ በተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች 11 እጩዎች መቅረባቸውን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡
ያለፈውን 4 ዓመት ካገለገሉት የፌዴሬሽን አመራሮች ፕሬዝዳንቱን አቶ ጁነዲን ባሻ ጨምሮ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክለይኒ አሰፋ፤ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ   እና  አቶ አሊ ሚራ  በድጋሚ  ለመቀጠል የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ በሥልጣን ላይ የሚገኙት አቶ ጁነዲን ባሻ ከድሬዳዋ ተወክለው ለሁለተኛ የስራ ዘመን በእጩነት ለመወዳደር ቀርበዋል። ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ምርጫ በዕጩነት የቀረቡት ሌሎቹ እጩዎች የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፤ አሁን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የሆኑት  ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ  ከደቡብ ክልል፣ እንዲሁም የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው ከአማራ ክልል፤ አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ ከሐረሪ ክልል፤   ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ቡና ተጫውቶ ያለፈው አንተነህ ፈለቀ ከኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ አራት ክልሎች ቤኒሻንጉል፤ አፈር፤ ሶማሌ እና ጋምቤላ የፕሬዝዳንት እጩዎቻቸውን የማያቀርቡ ሲሆን የትግራይ ክልልና የአዲስ አበባ መስተዳደር በፕሬዝዳንትነት ምርጫው ማንን እንደወከሉ አለሳወቁም፡፡
አቶ ጁነዲን ባሻ በሁለተኛ የስራ ዘመን ለመቀጠል ፈተና የሚሆንባቸው በተለይ ከሁለት እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር በመሰለፋቸው ነው፡፡ በሁለት የፌደሬሽን አስተዳደሮች ያገለገሉት ቅርብ የስፖርት ሰዎች ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ እና አቶ ተካ አስፋው ናቸው። ከዓመት በፊት የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን ወደ ስፖርቱ ከተመለሱ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ለመሆን የበቁት ዶክተር  አሸብር ወልደጊዮርጊስ  ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ምርጫ  ከሃላፊነቱ ከተነሱ ከ9 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሹመቱን ለማግኘት መመለሳቸው በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችን አስገርሟል፡፡ ዶክተር አሸብር ከወር በፊት  በሃላፊነት የነበሩበትን የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንነት በመልቀቅ ሃላፊነቱን አሸጋግረው የደቡብ ክልልን ውክልና በማግኘት ወደ እግር ኳሱ አመራር ለመመለስ ወስነዋል። ከዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ፕሬዝዳንትነት ፌደሬሽኑ ካለፈበት 6 የስራ ዓመታት በኋላ ስልጣኑን በአቶ ሳህሉ ገብረወልድ የሚመራው አስተዳደር ሲረከብ፤ አቶ ተካ አስፋው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ዋልያዎቹ ወርቃማ ዘመን ባሳለፉበት የስራ ዘመን በፌደሬሽኑ የስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴዎች፤ በተጨዋቾች በገንዘብ ስጦታ እና የማበረታቻ ሽልማቶች ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ የነበራቸው አቶ ተካ አስፋው የዳሸን ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ የሚያገለግሉ ሲሆን ወደ እግር ኳሱ አመራርእንዲመለሱ በተደጋጋሚ ለሚቀርበው ጥያቄ ምላሽ በሰጠው ውሳኔያቸው ከየአቅጣጫው ድጋፍ እየተሰጣቸው ነው፡፡
በስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫው ኢ/ር ሃ/ኢየሱስ ፍሰሐ ከአዲስ አበባ፤   የኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሀፊ ታምራት በቀለ ከኦሮሚያ ክልል ፤ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ ክልል፤ የብሄራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ከአማራ ክልል፤ አቶ አብዱራዛቅ ከሶማሊ ክልል፤ አቶ አሊ ሚራህ ከአፋር ክልል፤ ኤንጅነር ቾል ቤል ከጋምቤላ ወይዘሮ ፎዝያ ከቤንሻንጉል ክልል ናቸው፡፡ የጠቅላላ ጉባኤው አባላትም የቀረቡት  እጩዎች  በአመራርነትና በስፖርቱ ዘርፍ ያላቸው ልምድ፣ ያበረከቱት አስተዋጽኦና ያስመዘገቡት ውጤት ግምት ውስጥ በማስገባት ምርጫውን ውጤታማ ያደርጉታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ የፕሬዝዳንት ምርጫው ግልፅ በሆነ መንገድ በመካሄድ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ይሁንታ እንዲያገኝ ተስፋ ተደርጓል፡፡  ካልተገባ ሒደት ነጻ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።
 በሁለተኛ የስራ ዘመን ጅምር ስራቸውን መቀጠል የሚፈልጉት አቶ ጁነዲን ባሻ
በትውልዳቸው ከአርሲ ክልል የሆኑት ጁነዲን ባሻ አሁን 56ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በBSC  እንዲሁም በዩኒቨርስቲ ኦፍ ግሪንዊች በBMA ድግሪዎችን የቀበሉ ሲሆን በቢዝነስ አስተዳደር ከፍተኛ ልምድ አላቸው፡፡ የሐረር ቢራ ስራ አስኪያጅ እና የንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ከመስራታቸውም በላይ የሐረር ቢራ የእግር ኳስ ክለብ በፕሪሚዬር  ሊጉ ተወዳዳሪ በሆነበት ጊዜያት የክለቡ ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ አቶ ጁነዲን ወደ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራርነት ከመምጣታቸው በፊት ‹‹የኢንዱስትሪያል ፒስ አዋርድ›› ፤ በኢትዮጵያ የጥራት ምዘና ተቋም  ‹‹ሊደርሺፕ አዋርድ›› እና ‹‹የግሪን አዋርድ›› ሽልማቶችን በተለያዩ ጊዜያት ያገኙም ናቸው፡፡
ከ4 ዓመታት በፊት አቶ ጁነዲን ባሻ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ  የድሬዳዋ ክልልን በመወከል  ሲሆን   በጠቅላላ ጉባኤው አባላት ከሚሰጡት 101 ድምፆችን 55 በማሸነፍ ነበር፡፡  የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ማገልገል ከጀመሩ በኋላ በፊፋ የማርኬቲንግ እና ቲቪ ኮሚቴ፤ እንዲሁም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ኮሚቴ አባልነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡  
አቶ ጁነዲን በ2017 በጋቦን በተስተናገደው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በፌደሬሽኑ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን ለሁለተኛ የስራ ዘመን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ ‹‹በኢትዮጵያ ስፖርት መሾም እና መሻር ያለ ነው። ብዙ አዲስ ይመጣል፤ ይሄዳል።  አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚ እንዲቀጥል ወይም እንዲቀየር የሚያደርገው የእግር ኳሱ የበላይ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡ በሚመለከተው አካል ሳይመረጥ መቀጠል የሚፈልግ ማንም የለም። ይሁንና በእኔ አመለካከት የምረዳው ብዙውን ግዜ አዲስ ፊት ማየት ለውጥ ማምጣት አለመሆኑን ነው። በዚህ አይነት አቅጣጫ ስፖርቱን መምራት ብዙ ሃሳቦች እና እቅዶች በእንጥልጥል እንዲቀሩ ያደርጋል። ስለዚህም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ተመክሮ ልንወስድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ለምሳሌ እንደ ጋና ባሉት አገራት አንድ የፌደሬሽን አመራር  አራት ዓመት የስራ ዘመኑን ካበቃ በኋላ ያገኘውን ተምክሮ ተጠቅሞ የላቁ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንዲችል ተጨማሪ የስራ ዘመን እንዲያገኝ መደረጉን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ በፌደሬሽኑ አስተዳደር ባከናወንናቸው ፈርቀዳጅ ተግባራት ባስመዘገብናቸው ውጤቶች ደስተኞች ነን፡፡ በተጨማሪ የስራ ዘመን ሃላፊነታችንን ለመቀጠል የምንችልበት ሁኔታ  ጊዜው ሲደርስ እንመለከተዋለን። በኛ በኩል ስራችንን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡›› ብለው ነበር፡፡
በ2020 እኤአ ላይ የቻን ውድድርን ማስተናገዷ፤ በ2025 እኤአ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ በምታዘጋጅበት እቅድ ከሶስት የመጨረሻ እጩዎች መገኘቷ፤ ከፊፋ እና ካፍ አስተዳደር ጋር ያለው መልካም ግንኙነት የጁነዲን ባሻ አስተዳደር ቀጣይ 4 ዓመት የስራ ዘመን እንዲኖረው የሚያመለክቱ ሁኔታዎች ናቸው። እግር ኳሱ በመላው አገሪቱ በመስፋፋት ላይ መሆኑ፤ በሁሉም ክልል ክለቦች እየተመሰረቱ መሆናቸው፤ በታዳጊ እና ወጣቶች እግር ኳስ ላይ በፕሮጀክት ታቅፈው ስልጠና የሚከታተሉ እና በአካዳሚዎች ውስጥ የሚገኙ የነገ ተስፈኛ እግር ኳስ ተጨዋቾች ቁጥርም መብዛቱ፤ የሀ 20 ውድድር በወንዶች ደረጃ በፕሪሚዬር ሊግ፤ በከፍተኛ ሊግ፤ በብሄራዊ ሊግ ከኮካኮላ ኩባንያ ጋር በአጋርነት የሚሰራበት መልካም ተመክሮዎችንም የፌደሬሽን አመራራቸው ጥንካሬ መሆኑን አቶ ጁነዲን ባሻ ይገልፃሉ። ባለፉት 4 ዓመታት በካፍ እውቅና የተሰጣቸው የኢንስትራክተሮች ብዛት ከ4 ወደ 8 ማደጉ፤  የፌደራል ዳኞች ብዛት ከ250  ወደ 412 ከፍ ማለቱ፤  የወጌሻዎች ብዛት ከ2 ወደ 87 መጨመሩ እንዲሁም በ2008 ከፍተኛ ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ 87 የህክምና ሙያተኞች የሙያ ማሻሻያ ማግኘታቸው በፌደሬሽኑ ታሪክ በፈርቀዳጅነት የተከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት ሶስት ዓመታት በስሩ የተለያዩ ሰባት ያህል ውድድሮችን በየውድድርዘመኑ በዋናነት እያካሄደ በቀን እስከ 65 ጨዋታዎች በዓመት እስከ 1ሺ600 ያህል ጨዋታዎችን የሚመራበት  ደረጃ ላይም ደርሷል፡፡
በስፖርት መሰረተልማቶች በተለይም ከ13.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ሆኖባቸው በተገነቡ ስታድዬሞች የተመዘገቡ ስኬቶችም የጁነዲን ባሻ አስተዳደርን መልካም ተመክሮዎች የሚያመለክቱም ናቸው፡፡እስከ 2025 የአፍሪካ ዋንጫ በ24 ብሄራዊ ቡድኖች የሚካሄድ ከሆነ አህጉራዊ ውድድሩን ለማስተናገድ ከሚችሉ ጥቂት ሀገራት ኢትዮጵያ እንዷ ልትሆን ትችላለች፡፡  አዳዲስ የሰታዲየም ግንባታዎችን አዲስ አበባ እና ሌሎች የክልል ዋና ከተሞች እንደ ባህር ዳር, ሀዋሳ, መቀሌ እና ድሬዳዋ ያሉት በቂ የሆነ የሆቴልና መዝናኛ መስተንዶ ስላላቸው በመጪዎች አመታት በርካታ ስራዎችን በማከናወን  አህጉራዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እንደሚቻል አቶ ጁነዲን ባሻ ገልጸዋል፡፡
አስቀድሞ ከአዲስ አበባ ስታድዬም በስተቀር ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የማስተናገድ ፈቃድ የነበራቸው ሌሎች ስታድዬሞች አልነበሩም፡፡ በጁነዲን ባሻ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ከአዲስ አበባ ስታድዬም በኋላ አበበ ቢቂላ ስታድዬም፤ ድሬዳዋ ስታድዬም፤ ባህርዳር  ስታድዬም፤ ሐዋሳ  ስታድዬም ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉበት እውቅና ማግኘት ችለዋል፡፡ በወልዲያ ከተማ ተመርቆ ስራ የጀመረው መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከልም በሂደት ላይ ነው፡፡
 በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የማስተናገድ እውቅና እና ብቃት ያላቸው ስታድዬሞች ብዛት የመቀሌ እና የነቀምት የጋምቤላ፤ የሐረር እና የድሬዳዋ ስታድዬሞች  ሙለ ሙሉ ተገንብተው ሲያልቁ በሚቀጥለው የእግር ኳስ ፌደሬሽን አስተዳደር  ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስታድዬሞች ብዛት ከ10 በላይ ይሆናል፡፡ በጁነዲን ባሻ አስተዳደር በየክልሉ ያሉት ስታድዬሞች አህጉራዊና የአገር ውስጥ እግር ኳስ ጨዋታዎችን በማስተናገድ አገልግሎት መስጠት በመጀመር  የፈጠሩት መነቃቃት ትልቅ ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል በጁነዲን የሚመራው ፌደሬሽን ካስመዘገባቸው ውጤቶች የሚጠቀሰው በእግር ኳስ አስተዳደሩ ታሪክ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለብሄራዊ ቡድኑ መገኘቱ ነው፡፡ ከጣሊያናዊው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ኤርያ ጋር ፌደሬሽኑ በተፈራረመው የስፖንሰርሺፕ ውል የ90ሺዮሮ ትጥቅ በስጦታ 50ሺ ዮሮ በግዥ ያገኘ ሲሆን  በየዓመቱ እስከ አራት ሚሊዮን ብር የሚወጣበትን የትጥቅ ግዢ ያስቀረመ እርምጃነቱን መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም የፌደሬሽኑ ዓለም ዓቀፍ ተሳትፎና ተሰሚነት እያደገ መምጣቱን ማንሳት አስፈላጊ ነው። የፊፋው ፕሬዝዳንት ጣሊያናዊው ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ማህበር እንዲመሩ በተመረጡ በአጭር ግዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሥራ ጉብኝት  ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ጉብኝቱ  በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻሽል ፤ የአገሪቱን ተጠቃሚት የሚያሳድግ ውይይትና ምክክር የተደረገበት ነበር፡፡ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የካፍ እና የፊፋ ሁለት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ ያገኘችው እድል የሚጠቀስ ሲሆን በተለይም በካፍ 60ኛ ዓመት መታሰቢያነት በአዲስ አበባ የተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ኢሳ ሃያቱን በማሰናበት አዲሱን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ የተሾሙበት መሆኑ የፌደሬሽኑ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ ይሆናል፡፡
የኦሎምፒኩ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ወደ እግር ኳስ በድጋሚ ለመመለስ የፈለጉት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ለስፖርቱ አመራርነት አዲስ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  ፕሬዝዳንት ሆነው በሁለት  የስራ ዘመናት ለ6 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በዶክተር አሸብር ፕሬዝዳንትነት ሲመራ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሳትፎው በክፍለ አህጉር ደረጃ የተወሰነ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በሴካፋ ዞን ሁለት የሻምፒዮናነት ድሎችን በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ማስመዝገቡ ትልቁ ውጤት ሲሆን በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ በታሪክ ከፍተኛውን በታሪክ የተሻለውን 86ኛ ደረጃን ያስመዘገበበት ጊዜም እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዶክተር አሸብር የስራ ዘመን የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሁለት የሴካፋ ውድድሮችን ማስተናገዱ፤ ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ለምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ በስፖንሰርሺፕ እስከ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠታቸው፤ የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን፤ እንዲሁም  የጎል ፕሮጀክት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር  የተመቻቹ ሁኔታዎች በመልካም ተመክሮነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  
በሌላ በኩል ግን በዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የተመራው የእግር ኳስ ፌደሬሽን በአገር ውስጥ ውድድሮች ያን ያህል አበረታች ውጤቶች ባለማስመዝገቡና ከትልልቅ ክለብ አመራሮች ጋር በየጊዜው ይጋጭ ስለነበር በውዝግብ ሲናጥ እንደነበር ማስታወስ ይበቃል። በተለይ ዶክተር አሸብርን በመቃወም  የክለቦች ህብረት የተባለ ቡድን ተመስርቶ ከሌሎች የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት እንደተሰበሰበ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በሁለተኛ የስራ ዘመን  የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ከስልጣን እንዲወርዱ የክለቦች ህብረት ውሳኔ ካሳለፉ በኋላ ዶር አሸብር ግን ውሳኔ በመቃወም ከስልጣን አልወርድም ማለታቸው ከዚያም መደበኛ ስራቸውን ለማከናወን በአዲስ አበባ ስታድዬም ወደ የሚገኘው ቢሯቸው ለመግባት ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር የነበረው ውዝግብና ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ ተባብሶ ነበር፡፡ ውዝግቡን በቅርብ ይከታተል የነበረው ዐዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ በጠቅላላ ጉባኤ ከሃላፊነት መውረዳቸውን በመቃወም፤ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የውስጥ አስተዳደር እና ችግር መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል ምክንያትም ኢትዮጵያ በፊፋ የነበራትን አባልነት በጊዜያዊነት ማገዱን ገልፆ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ከዚሁ ውዝግብ በኋላ ስልጣናቸውን ከ6 ዓመታት ሃላፊነት በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራነታቸው ከተነሱ በኋላ  ዶክተር አሸብር በቀጥታ ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ፖለቲካ ነበር፡፡  በትውልድ ከተማቸው ቦንጋ ለፓርላማ ተወካይነት በገለልተኛ እጩነት ተወዳድረው አሸንፈው ፓርላማ የገቡ ብቸዓው የግል ተወዳዳሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት ለአራት ዓመታት  በግል ተወዳዳሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በዚሁ የፓርላማ ተወካይነታቸውም ወቅት የአፍሪካ ህብረት የሕግ አውጪ አካል የሆነው የፓን አፍሪካ ፓርላማን በአባልነት መቀላቀል ቢችሉም በተወካዮች ምክር ቤት በግል ተወዳዳሪነት ለሁለተኛ የስራ ዘመን ለመመረጥ ተወዳረው ግን ሳይሳካላቸው ቢቀርም የአህጉራዊው ተቋም 4ኛ የክብር ምክትል ፕሬዘዳንት ሊሆኑ በቅተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለተኛ፤ ለኢኮኖሚ አቅሙ ተስፋ የሚፈጥሩት አቶ ተካ አስፋው
አቶ ተካ አስፋው በህግ  ትምህርት የLLB ዲግሪ ያላቸው ሲሆን የቦርድ ሰብሳቢ፤ አማካሪ እና የህግ ጠበቃ ሆነው በማገልገል ከ33 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ዘንድሮ በዳሽን ባንክ  ጠቅላላ ጉባኤ አቶ ተካ አስፋውን በከፍተኛ ድምጽ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። በቋሚ የስታድዬም ተመልካችነት፤ ከበርካታ የክለብ አመራሮች፤ እውቅ ተጨዋቾች፤ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች ባላቸው መልካም ግንኙነት የሚታወቁት አቶ አስፋው በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አስተዳደር  በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንትነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች በተጨዋቾች እና አሰልጣኞች የሽልማት እና የማበረታቻ ድጋፎች የጎላ አስተዋፅኦ ያላቸው  በተለይ  ዋልያዎቹ በአፍሪካና አለም ዋንጫ ተሳትፏቸው በገንዘብ ማሰባሰብ ረገድ ባለውለተኛ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ አቶ ተካ አስፋው ወደ ፌደሬሽኑ አመራርነት መምጣት ቢችሉ የክለቦች የሊግ ውድድሮች በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንዲሁም ገቢ በሚያስገኙ የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫዎች አስተዳደሩ ይጠናከራል በሚል ተስፋ በጠቅላላ ጉባኤው  የመራጮችን ትኩረት ሊስቡበት እንደሚችሉ የተገመተ ሲሆን፤ በፌደሬሽኑ አመራር ውስጥ በመቆየታቸው የተሻለ ልምድን እንዳላቸው፤ ያሉትን ችግሮችም በዘላቂ መፍትሄ ሊቀርፉ እንደሚችሉ በፌደሬሽኑ ከፍተኛ አመራር ላይ በነበሩበት ወቅት ምስጉንና የተሻለ የአመራር ብቃትን ማሳየታቸውም ይጠቀሳል።  ከ4 ዓመት በፊት ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የአማራ ክልልን ወክለው በዕጩነት የቀረቡት አቶ ተካ አስፋው ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው የሚታወስ ነው፡፡
በወቅቱ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አቶ ተካ አስፋው በጠቅላላ ጉባኤ ሲሳተፉ በፕሬዝዳንትነት ምርጫው በመወዳደር ያሸንፋሉ የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፤ ግልፅ ባለደረጉት ምክንያት ከምርጫ መገለላቸው ብዙዎቹን የስፖርት ቤተሰቦች ለቁጭት ያደረገ ነበር፡፡ መገደዳቸውን ለጉባኤው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተመሰረተ ከ75 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በ1952 እ.ኤ.አ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ፤ በ1957 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ አባልነት እንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡ የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ በጀት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን አምና ያስመዘገበው ከ118.8 ሚሊዮን ብር በላይ  በታሪኩ ከፍተኛው ገቢ ሆኖ የተመዘገበ ነው። ፌዴሬሽኑ በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ኦዲተሮች፤ የፍትህ አካላት፤ አማካሪ ቦርድ፤ የሊግ ኮሚቴና ድጋፍ የሚሰጡ ልዩልዩ ኮሚቴዎች የተደራጀ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ፅ/ቤት በአንድ የፅ/ቤት ኃላፊ የሚመራ 24 ቋሚና ጊዚያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡

Read 3413 times