Sunday, 29 October 2017 00:00

የኡጋንዳው ገዢ ፓርቲ አባል፣ አጥር ስር በመሽናት ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

10 ዶላር ተቀጥተው ተለቅቀዋል

   በኡጋንዳ የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የግንብ አጥር ስር ሽንታቸውን በመሽናታቸው ክስ የተመሰረተባቸው የአገሪቱ ፓርላማ አባል አብራሃም አብሪጋ፤ በካምፓላ ፍርድ ቤት 10 ዶላር ቅጣት እንደተጣለባቸው ተዘግቧል፡፡
ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት የተሰኘው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ አባል የሆኑት ግለሰቡ፣ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጥር ስር ሽንታቸውን ሲሸኑ ባልታወቁ ሰዎች ፎቶ መነሳታቸውንና ፎቶግራፉም በማህበራዊ ድረ ገጾች በስፋት ተሰራጭቶ መነጋገሪያ መሆኑን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህን ተከትሎም መታሰራቸውንና ለፍርድ መቅረባቸውን ጠቁሟል፡፡
የግለሰቡ ድርጊት የመዲናዋን የአካባቢ ንጽህና ህግ የሚጥስ በመሆኑ ክስ እንደተመሰረተባቸው የጠቆመው ዘገባው፤ መሰል ድርጊቶችን የፈጸመ ሰው በሁለት ሳምንት እስር ወይም በገንዘብ እንደሚቀጣ በማስታወስ፣ ግለሰቡም ጥፋተኛነታቸውን በማመናቸው የገንዘብ ቅጣቱ እንደተጣለባቸው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም የኡጋንዳውን ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የስልጣን ዘመን ለማራዘም ያለመ ነው የሚባለውን የዕድሜ ገደብ ማሻሻያ ህግ በመደገፍ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማግባባት፣ለእያንዳንዳቸው 8 ሺህ ዶላር በሙስና መልክ ከገዢው ፓርቲ የተሰጣቸው ስምንት የፓርላማ አባላት፤”ገንዘቡን አንፈልግም” ብለው መመለሳቸውን  ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ገዢው ፓርቲ የህገ መንግስት ማሻሻያው በከፍተኛ የድምጽ ድጋፍ እንዲያልፍ ለማድረግ ለፓርላማ አባላቱ በድምሩ 3.5 ሚሊዮን ዶላር መደለያ  መስጠቱ እየተነገረ መሆኑን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1474 times