Sunday, 29 October 2017 00:00

የቱርክ መንግስት ከስራ ያባረራቸውን 121 ዜጎች ሊያስር ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እስካሁን 50 ሺህ አስሯል፤ 110 ሺህ ከስራ አባርሯል

    ባለፈው አመት ከተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ከ50 ሺህ በላይ ዜጎቹን ያሰረውና 110 ሺህ ያህሉንም ከስራ ገበታቸው ያባረረው የቱርክ መንግስት፤ከትናንት በስቲያ በተጨማሪ 121 የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀድሞ ሰራተኞች ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ሀሙስ እለት የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው 121 ቱርካውያን፣ ከዚህ ቀደም ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ጋር ንክኪ አላችሁ በሚል ከስራ ገበታቸው ያባረራቸው እንደሆኑ የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ፖሊስ በ30 ያህል ግዛቶች ግለሰቦቹን አድኖ ለመያዝ ዘመቻ መጀመሩን አመልክቷል፡፡ ግለሰቦቹ በሚስጥር መልዕክት መላላክ በሚያስችል የሞባይል አፕሊኬሽን አማካይነት ከመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾችና ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ይገናኙ ነበር መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የቱርክ መንግስት ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ ከሆነውና “የመፈንቅለ መንግስቱ ፊታውራሪ” ከሚላቸው ጉሌን ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የሚጠረጥራቸውን ዜጎቹን በጅምላ ማሰሩ በአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና መንግስታት ሲያስተቸው መቆየቱንም አስታውሷል፡፡

Read 1316 times