Saturday, 28 October 2017 10:41

የአውሮፓ ህብረት አዲስ አምባሳደር ሥራ ጀምረዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ለቀጣዩ 5 ዓመታት ለሚሰሩ የልማትና ትብብር ስራዎች 1.5 ቢ ዮሮ ተመድቧል
           
    አውሮፓ ህብረት ለመጪው አራት ዓመታት ህብረቱን ወክሎ የሚሰራ አዲስ አምባሳደር ሾመ፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት የዘለቀውን የአውሮፓ ህብረት፣ የኢትዮጵያን የልማትና የትብብር ስራ አጠናክሮ ለመቀጠል አምስት ዓመታት 1.5 ቢሊዮን ዮሮ መመደቡም ተገልጿል፡፡
 ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ አዲሱን አምባሳደር ለማስተዋወቅና ቀጣይ የልማት የትብብር ስራዎችን ሁኔታ ለመግለፅ በደሳለኝ ሆቴል በተዘጋጀ ፕሮግራም አምባሳደር ዮሃን ቦርግስታም ባደረጉት ንግግር የሁለቱን አገራት የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት አድንቀው፤ ምንም እንኳ በአፍሪካ ስሰራ የመጀመሪያዬ ባይሆንም የኢትዮጵያ ግን የተለዬና ጥሩ ይሆናል ብለዋል፡፡
ላለፉት አራት አስርተ አመታት የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በተለያዩ ዘርፎች ማለትም፡- በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ በቀጠናው ሰላምና ደህንነት፣ በኢኮኖሚና በልማት፣ በባህል ልውውጥና በሌሎችም የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር መቻሉን አዲሱ አምባሳደር ገልፀዋል፡፡
ህብረቱና ኢትዮጵያ እንደ አገር ከሚያደርጉት ግንኙነት ባለፈ፣ በግል ኢንቨስትመንቶችም በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስራ ዕድሎች መፈጠራቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የባህል ማዕከል እንደመሆኗ በዚህም ረገድ የበለጠ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
አዲሱ አምባሳደር አክለውም፤ የህብረቱ አባል አገራትና ኢትዮጵያ በ1975 እ.ኤ.አ ከተፈራረሙት የ“ሎሜ” ስምምነት ጀምሮ በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው ኢትዮጵያ ለህብረቱ አገራት ቁልፍ ቦታ ለመሆኗ የህብረቱ 21 አባል አገራት በአዲስ አበባ ኤምባሲያቸውን መክፈታቸው ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ህብረቱ ከኖርዌይ (ከስዊዝላንድ) ጋር በመተባበርና በአመት 1 ቢ. ዩሮ በመመደብ፣ የኢትዮጵያን ልማት ሲደግፍ መቆየቱንም ገልፀዋል፡፡
የ52 ዓመቱ አምባሳደር ዮሃን በርግስታም በቀጣዮቹ አምስት አመታት በባህላዊ ሀብቶች፣ በመሰረተ ልማት፣ በጤና፣ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በግብርና፣ በስራ ፈጠራና በኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ወደ 1.5 ዮሮ የሚገመት በጀት መያዙን አብራርተዋል፡፡ ህብረቱ የአባላት አገራቱንና የኢትዮጵያን ባህልና ስነ-ጥበብ ለማስተሳሰርና ልምድ ለማለዋወጥ ከኖቬምበር ሶስት እስከ ኖቬምበር 19 የሚቆይ የፊልም ፌስቲቫል በብሄራዊ ቴአትር እንደሚያካሂድም ተገልጿል፡፡
በፊልም ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ የፊልም ተመልካች፣ የአውሮፓን የስራ፣ የባህልና የእድገት ጎዳና እንዲቃኝ ሁለተኛ እድል ይሰጠዋል የተባለ ሲሆን ከ18 የአውሮፓ አገራት የተውጣጡ ፊልሞች  እንደሚቀርቡም የህብረቱ ተወካዮች አምበሳደሩን ባስተዋወቁበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
ኖቬምበር 3 በብሔራዊ ቴአትር የፌስቲቫሉ መክፈቻ የሚሆነው “Toni Eramann” የተባለ ፊልም ሲሆን “Lejardind ewald” የተሰኘ የአፍሪካ ፊልም መሆኑ ታውቋል፡፡ ፊልሞቹ ለአንድ ወር የሚታዩት በህብረቱ የባህል ተቋማት ነው ተብሏል፡፡

Read 1036 times