Sunday, 29 October 2017 00:00

እንቦጭን የሚያጭድ ‹‹የእኛ›› የተሰኘ ጀልባ እየተሰራ ነው

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • 80 በመቶ ተጠናቋል ቀሪው 2.3 ሚሊዮን ብር ይፈጃል
         • በ8ሰዓት እስከ 3ሺ ካሬ ሜትር እንቦጭ ያጭዳል
         • ጣናን ለመታደግ 7 ተመሳሳይ ጀልባዎች ያስፈልጋሉ
            
    በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በማጨድ የሚያስወግድ ልዩ ጀልባ በኢትዮጵያዊው የቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ መንግስቱ አስፋው እየተሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹የእኛ›› የተሰኘው ጀልባ፤ በሐይቁ ላይ በፍጥነት እየተዛመተ ያለውን አረም ከስሩ በማጨድ፣ ትንንሽ ጀልባዎች ላይ እየጫነ ማስወገድ ይችላል ተብሏል፡፡ ጀልባዋን ለመገጣጠም ከልጆቻቸውና ሌሎች ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር መተባበራቸውን ለአዲስ አድማስ የገለፁት አቶ መንግስቱ፤ ስራው 80 በመቶ መገባደዱን ተናግረዋል፡፡
2.60 ሜትር ስፋትና  4.60 ሜትር ቁመት ያለው ‹‹የእኛ›› ጀልባ ባህር ሰርጓጅ የሚመስል ሲሆን የተሰራው በማይዝግ ብረት ከውጪ በፋይበርፕላቲክ  የሚለበጥ  ነው፡፡‹‹የእኛ›› የሚለው ስያሜ የገጠመንን ሃገራዊ ችግር ለመፍታት በራሱ በሃገሬው ሰው የተበጀ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን ለማመልከት ነው ብለዋል የጀልባው ፈጣሪ፡፡ ጀልባው የቀሩት የመጨረሻዎቹ ስራዎች የኤሌክትሪክና የሐይድሮሊክ ሲስተሙን መዘርጋትና ሞተሩን መትከል ብቻ መሆኑ የገለፁት አቶ መንግስቱ፤ ሙሉ በሙሉ ጨርሶ ወደ ስራው ለማስገባት የሚያስፈልገው 2.3 ሚሊዮን ብር ነው ብለዋል፡፡
በዝቅተኛ ፍጥነት በውሃ ላይ የበቀለውን እንደእቦጭ ያለ አረም ማጨድ የሚችለው ጀልባው፤ በነጠላ ክብደቱ 1.5 ቶን ሲሆን እስከ 6.5 ቶን ጭነት የመጫን አቅም ያለው ሲሆን በውሃ ላይ ሲንሳፈፍ በድምሩ እስከ 8 ቶን ይመዝናል፡፡
‹‹የእኛ›› ጀልባ በአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን መመዝገቡን ለአዲስ አድማስ ያስታወቁት አቶ መንግስቱ፤ ለጀልባው መፈጠር ፈር-ቀዳጅ ሃሳብ ያፈለቀው የእፅዋት ሳይንስ ባለሙያ የሆነው ልጃቸው ዶክተር መስፍን መንግስቱ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡
ጀልባውን ለመገጣጠም 6 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ የመጀመርያው የቴክኖሎጂ ፈጣሪው አቶ መንግስቱ አስፋው፤ ከዚያም የእፅዋት ሳይንስ ባለሙያው ዶክተር መስፍን መንግስቱ፤ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ባለሙያው አዲሱ ጌታቸው፤ የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ ክንፈና ሁለት የብረታብረት ስራ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ወጣቶች “ግሪን ፎረም ለፕሮጀክቱ እስካሁን የማይቋረጥ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጀልባው በዓመት በ85ሺ ሄክታር ላይ የበቀለ እንደ እንቦጭ ያለ አረም የሚያጭድ ሲሆን ለጣና ሐይቅ በተመሳሳይ የሰሩ 7 ጀልባዎችን በማቆም በየጊዜው የሚበቅለውን የእንቦጭ አረም በየወሩ ለማፅዳት ወይንም ለማስወገድ ይቻላል፡፡ አቶ መንግስቱ እንደገለፁት፤ ጀልባው በ8ሰዓት ውስጥ 3ሺ ካሬ ሜትር ላይ የበቀለ የእንቦጭ አረምን አጭዶ  ማስወገድ ይችላል፡፡
በአሰብ ወደብ ላይ በተለያዩ የቴክኒክ ስራዎች ያገለገሉትና በተለያዩ የስራ መስኮች ከ38 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው አቶ መንግስቱ ፤በቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራቸው ከ“የእኛ” ጀልባ በፊት ብዙ ሰርተዋል፡፡ በሌሎች አምስት የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ፓተንት ያገኙ ሲሆን ያለ ኤሌክትሪክ በተቃጠለ ዘይት የሚሰራ የእንጀራና የዳቦ መጋገርያ ማሽን፤ ከጤፍ ውጭ ማንኛውንም የእህል ዘር በመስመር የሚዘራ፣ በእንስሳ የሚጎተት መሳርያ፤ ዘመናዊ የንብ ቀፎ እንጀራ ማተሚያና በአንድ ጊዜ አምስት የህብስት ዳቦዎችን የሚጋግር የከሰል ምድጃ  ናቸው፡፡
‹‹የእኛ›› ጀልባን ለመስራት በደቡብ አሜሪካና በአውሮፓ ያሉ ተመክሮዎችን ቢያጠኑም ሙሉ ዲዛይኑ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በአዲስ መልክ ተሰርቶ መገጣጠሙን የገለፁት አቶ መንግስቱ፤ በዓለም ዙርያ በተመሳሳይ  የሚሰሩ ጀልባዎች ሁለት አይነት አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል፡፡ የመጀመርያው ያጨደውን ወደ ዳር እያወጣ የሚያከማ፣ች ሌላው ደግሞ እያጨደ በሚከተሉት ጀልባዎች ላይ የሚጭን መሆኑን በማስረዳት ፕሮጀክታቸው  በውሃ ላይ የሚያጭደውን አረም በሚከተሉት ጀልባዎች ላይ እየጫነ የሚያስወግድ ነው ብለዋል፡፡ ጀልባውን በገጣጠሙበት ዎርክሾፕ በነበረን ጉብኝት እንደገለፁት፣ በሞዴልነት ለሰሩት አንድ የእኛ ጀልባ ለአረም አጨዳ ሲሰማራ እያንዳንዳቸው 2 ቶን የመጫን አቅም ያላቸው 6 ትንንሽ ጀልባዎች በመከተል፣ ጭነቱን ማመላለስ ያስፈልጋል፡፡ “የእኛ ጀልባ” በአንድ ሰው ሙሉ የኦፕሬተርነት ስራ ሊንቀሳቀስ የሚችል ነው፡፡  
እንቦጭ በጣና ላይ የበቀለው ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ  ሲሆን በሰዓት 200 ሜትር በሚሸፍን መራባት ወረራውን  ቀጥሏል፡፡ በሳይንሳዊ አጠራሩ Eichhornia crassipes በመባል የሚታወቀው አንቦጭ፤ በአማዞን ተፋሰሶች ላይ የሚበቅል  የውኃ ተክል ባለው ተፈጥሯዊ የወራሪነት ባህሪ የተነሳ እንደ አረም የሚታይ ነው፡፡ በዓለማችን በተለይም በዉሃ አካላት ላይ በፈጣን ተስፋፊነቱ  ተጠቃሽ የሆነው  እንቦጭ፤ ከ50 በላይ አገራት በሚገኙ ተፋሰሶች ወራራ እንደየሚያደርግ ታውቋል፡፡
እንቦጭን ለሰው ሰራሽ አፀድ ማስዋቢያነት፣ ለወረቀትና ለጌጣጌጥ ስራ፣ ለሽቶና ኮስሞቲክስ፣ ለማዳበሪያና ለእንስሳት መኖ፣ ለአካባቢያዊ ጥበቃ እንዲሁም ለሀይል አቅርቦት የተለያዩ አገራት የሚጠቀሙበት ተክል ቢሆንም  ከጥቅሙ ግን  ጉዳቱ ያመዘነ  ተክል ነው።
እንቦጭ በመላው አፍሪካ ባለፉት 30 ዓመታት በተፈጥሮ አመቺ በሆኑት ተፋሰሶቻቸውና አካባቢዎች የተዛመተ ሲሆን በኢትዮጵያ ከ45 ዓመታት በፊት በቆቃ ግድብናና በአዋሽ ወንዝ ላይ መገኘቱን፤ በጋምቤላ ክልል ረግረጋማ ቦታዎች ላይ በመብቀል የሚታወቅ መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ እንቦጭ ከ10 እስከ 20 ሴ. ሜ ርዝመት ያለው ተንሳፋፊ፣ እስከ 5 ሴ.ሜ የሚሰፋ አበባ ያለውና ጥቅጥቅ ብሎ የሚንሰራፋ ተክል ነው። እንቦጭ ከ 10 እስከ 15 ሳምንት ውስጥ ሲያብብ፤ ዘሩ ደግሞ 15 እስከ 30 አመት በሴድመንት ውስጥ መቆየት ይችላል።
እንቦጭ በጣና ሀይቅ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ እንደወረረ የሚገልፁ መረጃዎች የዚህ አረም በስፋት መብቀል የኦክስጅን፣ የናይትሬትና የአሞንያ መጠን እንደሚቀንስ  የአሳ እና አፅዕዋት ዝርያዎችን እንደሚያጠፋ፤ የውሃ ትነትን እንደሚቀንስ፤ በሐይቁ ዙርያ ያሉ የግብርና ስራዎችን እንደሚያስተጓጉል፤ የመስኖ እና የውሃ ሃይል ማመንጨት ስራዎችን እንደሚያቃውስ እና የሐይቅ ላይ ትራንስፖርት እና የቱረዝም መስኩን እንደሚያበላሽ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡    
ጣና የዓለማችን ረጅም ርቀት ተጓዥ የሆነው  የአባይ ወንዝ ምንጭና  በስፋቱ የኢትዮጵያ  ትልቁ ሐይቅ ሲሆን በ3,500 ካሬ ኪ.ሜ. ላይ የሰፈረ ነው፡፡ ከሐይቁ በዓመት  1,454 ቶን አሳ ይመረታል፡፡ በተያያዘ ሐይቁ በሚገኝበት የብዝኃ ህይወት ክምችት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ፣የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በቅርስነት የተመዘገበ እንደሆነም መታወቅ ይኖርበታል፡፡

Read 1806 times