Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 April 2012 11:32

ኢንሹራንስ እና የግንዛቤ ችግር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ኢንሹራንስ ከፈጣሪ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም…

* ወላጅ ሲሞት ልጆች ያለ አሳዳጊ አይቀሩም - እንዴት?

* የህይወት ዋስትና ለሞት ብቻ አይደለም - ለጡረታም!

* አንድ ጃፓናዊ ገና ሲወለድ ነው የህይወት ዋስትና የሚገባለት…

አቶ ጌትነት አበራ ሺበሺ ለበርካታ ዓመታት በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያገለገሉ አንቱ የተሰኙ ባለሙያ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከኦፊሰርነት እስከ ም/ማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ከ20 ዓመት በላይ አገልግለው፣ አምና ነው ጡረታ የወጡት፡፡ በአሁኑ ወቅት ጌት ሪሊያብል ኢንሹራንስ ብሮከር የተባለ የግል ድርጅት መሥርተው በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እየመሩ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታቲስቲክስ የተመረቁት አቶ ጌትነት፤ በኢንሹራንስ፣ በተለይም በሕይወት ዋስትና ዘርፍ በተልዕኮ ትምህርት አሜሪካ ከሚገኘው ላይፍ ኦፊስ ማኔጅመንት አሶሲየሽን ሎማ የተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችን አጠናቀው በዲፕሎማ መመረቃቸውንና የተቋሙን የመጨረሻ ማዕረግ ኤፍ ኤል ኤም አይ [FLMI] መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ የትምህርት ዘርፍ (አሶስዬት ሪኢንሹራንስ አድሚኒስትሬሽን) የመጨረሻውን ትምህርት አጠናቀው (ኤ አር ኤ) እንዲሁም በደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ (አሶሽየት ከስተመርስ ሰርቪስ) ማስረጃዎች እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ጌትነት፤ ጡረታ ከወጡ በኋላ፣ ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም የኢንሹራንስ ድርጅቶች በሚሰጣቸው የህይወት ዋስትና ሥልጠናዎች ላይ  በተጋባዥ መምህርነት እያሠለጠኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣  ከአቶ ጌትነት ጋር በኢንሹራንስ ዙሪያ የተለያዩ አስደማሚና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጥያቄዎችን እያነሱ አውግተዋል፡፡ እነሆ ቃለ-ምልልሱ:-

 

ኢንሹራንስ ምንድነው?

የኢንሹራንስ (የመድን ዋስትና) አቢይ ተልዕኮ፣ ሊያጋጥም የሚችል የኢኮኖሚ እጦት ማርገብ ነው፡፡ በእንግሊዘኛው The fundamental purpose of insurance, whether of people or property is, Protection against possible economic loss. የሚል ነው፡፡ ማለትም በንብረት ወይም በሕይወት ላይ ሊያጋጥም የሚችልን የኢኮኖሚ እጦት የኢንሹራንስ ዋስትና ሊያረግብ የሚችል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የኢኮኖሚ እጦት የሚባለው ባልተጠበቀና ባልታሰበ ሰዓት የሚያጋጥም የገንዘብ እጦት ነው፡፡ ያም እጦት፣ ለረዥም ወይም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ሆኖ በገንዘብ ሊተረጐም የሚችል  ነው፡፡

ስንት ዓይነት ኢንሹራንስ አለ?

ዋና ዋናዎቹ የኢንሹራንስ ዓይነቶች፣ የንብረት፣ የኃላፊነት ግዴታና የሕይወት ዋስትና በማለት በሦስት መክፈል እንችላለን፡፡ የንብረት ዋስትና የሚባለው የተሽከርካሪ፣ የእሳት ቃጠሎ፣ የመርከብና የጭነት፣ … የሚባሉና ከንብረት ጋር የተያያዙ ናቸው፡ የሕግ ኃላፊነት ግዴታ ዋስትና ስንል በሦስተኛ ወገን ላይ ሊያጋጥም የሚችልን ጉዳት  የሚስተናገድበት ውል ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሆቴል ደንበኛ የሆነ ሰው፣ ሆቴሉ ውስጥ ሲገለገል አዳልጦት ቢወድቅና ቢጐዳ ሆቴሉ፣ ደንበኛውን የማሳከምና የመካስ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይኼ የግዴታ ዋስትና ከንብረት ዋስትና ጋር ተዳምሮ ስለሚሸጥ የመድን ዋስትናን በሁለት ትላልቅ ጐራ መመደብ እንችላለን - የንብረትና የሕይወት ዋስትና በማለት፡፡

በአገራችን የሁለቱ የዋስትና ሽፋን ደረጃ ምን ይመስላል?

በጣም የተለያየ ነው፡፡ በአገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከ93 በመቶ በላይ በንብረት ዋስትና ላይ ያተኮረ ሲሆን የሕይወት ዋስትና ከ7 በመቶ ወይም እጅግ ቢበዛ ከ8 በመቶ ያነሰ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆና ሳለ እንዴት ነው የሕይወት ዋስትና ይህን ያህል ሊያንስ የቻለው?

የሚገርመውም ይኼ ነው፡፡ በበለፀጉት አገሮች ያለው ሁኔታ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ለምሳሌ በጃፓን የንብረት ዋስትና 7 ወይም 8 በመቶ ሲሆን የሕይወት ዋስትና ከ93 በመቶ በላይ ነው፡፡ በአሜሪካም ተመሳሳይ ነው - የሕይወት ዋስትና ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዝ የንብረት ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ 80 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት አገር፤ የሕይወት ዋስትና ሽፋን 7 በመቶ ነው ማለት አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡

ምንድነው ምክንያቱ?

ለዚህ በዋነኛነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የግንዛቤ ችግር ነው ነው ማለት እንችላለን፡፡ ሕዝቡ ስለ ሕይወት ዋስትና ጥቅም በሚገባ እንዲያውቅ አልተደረገም፡፡ የባህል ተፅዕኖም ችላ የሚባል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሃይማኖትና ባህልን አንድ ላይ አድርገን ስለ ሕይወት ዋስትና ብናነሳ፤ “የእኔ ሕይወት በፈጣሪ እጅ ነው ያለው” በማለት ከፈጣሪ ጋር ማነካካት እንወዳለን፡፡ ነገር ግን ይኼ ከፈጣሪ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የኢንሹራንስ ዋስትና መግዛትን በራስ ላይ ከማሟረት ጋር ያያይዘዋል፡፡ ነገር ግን ጠብታ እውነትነት የለውም፡፡

ብዙ ሰው በየሰፈሩ እድሮች ይገባል፡፡ ዋና ዕድር፣ የሴቶች (የጓዳ)፣ የወንዶች፣ … ዕድር ሲገባ በራስ ላይ ማሟረት አይሆንም፡፡ እንዴት ነው ታዲያ የሕይወት ዋስትና ሲገዙ በራስ ማሟረት የሚሆነው?

በቀላሉ ለማስረዳት ያህል፣ እኔ ጌትነት አበራ በሕይወት እያለሁ፣ ሠርቼ ስገባ በየወሩ የማገኘው ገቢ አለ፡፡ ባልተጠበቀና ባልታሰበ ሰዓት ግን የወር ደሞዜ (ገቢ) ቢቋረጥ የገባሁት የሕይወት ዋስትና በሕይወት ካለሁ ለእኔ፣ በሕይወት ከሌለሁ ግን ለወራሾቼ ሊከፈላቸው ግድ ነው፡፡ ጌትነት እየሠራ በነበረበት ሰዓት በእሱ ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ለኢኮኖሚ እጦት የሚዳረጉበት ጊዜ ይመጣል፡፡

በሕይወት ዋስትና ሦስት ነገሮች ማንሳት ይቻላል፡ ባልተጠበቀና ባልታሰበ ጊዜ እሞታለሁ፡፡ ሞት ለማንም አይቀርም፡፡ ጌታ ራሱ ቀምሶታል፡፡ የሕይወት ዋስትና የሞት መድኃኒት አይደለም፡፡ እኔ ዋስትና ስላለኝ አልሞትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን መች እንደምሞት አላውቅም፡፡ ያ ሞት ሲመጣ ቤተሰቦቼ ለኢኮኖሚ እጦት መዳረጋቸው የግድ ነው፡፡ ሁለተኛ የኢኮኖሚ እጦት ይከሰታል ስንል ሕመምና የአካል ጉድለት ይኖራል፡፡ ከቀላል ህመም ጀምሮ እስከ ገዳይ ህመሞች (Dread Disease)  ድረስ ጌትነት ቢለከፍ ገቢው በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መጓደሉ አይቀርም፡፡ ሦስት ቀን ጉንፋን አሞኝ በሙሉ አቅሜ ማምረት ካልቻልኩ ገቢዬ በዚያው መጠን ይቀንሳል፡፡ ባልጠበኩትና ባላሰብኩት ሰዓት ግማሽ አካሌ በድን (ፓራላይዝ) ቢሆን ከዚያ ሕመሜ እንድፈወስ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለኢኮኖሚ እጦት መዳረጌ አይቀርም፡፡ ሦስተኛው ደግሞ እርጅና ነው፡፡ የዕድሜ ባለፀግነት ከአቅም ጋር ሲሆን ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አቅም ሲደክም ገቢ ይቀንሳል፡፡

ለምሳሌ የመንግሥት ሠራተኛ የሆነ ሰው ጡረታ በሚወጣበት ሰዓት ከፍተኛ አገልግሎት ቢያበረክት የጡረታ አበሉ በመጨረሻዎቹ ሦስት ዓመት ያገኝ የነበረውን ደሞዝ በአማካይ 70 በመቶ ይሆናል፡፡ ደሞዙ 1000 ብር የሆነ ሰው፣ የጡረታ አበሉ 700 ብር ይሆናል፡፡ ከገቢው ላይ 300 ብር እጦት (ጉድለት) ይፈጠራል፡፡ ልክ የጡረታ ደብተሩን ሲያገኝ የ30 በመቶ ወይም የ300 ብር ረሃብ ቤቱ ገባ ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው ከሞት፣ ከሕመምና ከአካል መጉደል፣ ዕድለኛ ከሆነ ደግሞ ከእርጅና (ከዕድሜ ባልፀግነት) ሊያመልጥ አይችልም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የኢኮኖሚ እጦት ስለሚያጋጥም የሕይወት ዋስትና ካለው ችግሩን በቀላሉ ይፈታል ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው የሕይወት ዋስትና ስላለው ብቻ ቢታመም አይታከምበትም፡፡ ነገር ግን የሕይወት ዋስትና የገዛ ሰው የሕክምና ዋስትናም አብሮ የመግዛት ዕድል አለው፡፡ ስለዚህ ከሕይወት ዋስትና ጋር የሕክምና ዋስትና የገዛ ሰው እሱና ቤተሰቡ የሕክምና ተጠቃሚ ቢሆኑ ሕጋዊ ፈቃድ ባለው የሕክምና ማዕከል፣ የጤና ምርመራ ማድረግ፣ መድኃኒት መግዛትና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው ሆስፒታሎች መታከም ይችላሉ፡፡

የሕክምና ዋስትና ሲገባ እሱና ቤተሰቡ ሲታመሙ ለመታከም ነው? ወይስ የበሽታ ዓይነት እየጠቀሰ ለልብ፣ ሳንባ፣ ኩላሊት፤ … እያለ በመለየት?

የለም ማንኛውንም ሕመም ማስተናገድ የሚችል ዋስትና ነው፡፡

የሕይወት ዋስትና ያለው ሰው በአደጋ አካሉ ቢጐዳ ወይም ቢጐድል ተጠቃሚ መሆን ይችላል?

እንደሱ አይደለም፡፡ ለተፈጥሮ ሞት የሚያገለግል የሕይወት ዋስትና ሲገዛ፤ ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግል የአደጋ ዋስትና በተደራቢነት መግዛት አለበት፡፡ ሁለት ዓይነት ሞት አለ - የተፈጥሮና በአደጋ የሚከሰት ሞት፡፡ ዋስትና ሲገባ ለሁለቱም ዓይነት ሞት እንዲያገለግል አድርጐ ውል መግባት ይቻላል፡፡

የዚህ ዓይነት ዋስትና ካለኝ አደጋ ቢያጋጥመኝ፣ ለአደጋዬ ካሣ እከፈላለሁ፡፡ አንድ እጄ፣ አንድ ጣቴ ቢቆረጥ፣ ዓይኔ ቢጠፋ፣ … የአደጋ ዋስትና ካለኝ ተገቢው ካሣ ይከፈለኛል፡፡

ስንት ዓይነት የሕይወት ዋስትና አለ?

ብዙ ናቸው፡፡ የተርም፣ የኢንዳውመንት፣ የኢንዳውመንት አኒዩቲ፣ የሆል ላይፍ (ዕድሜ ልክ)፣ የቤት ሠሪዎች የባንክ ቀሪ ዕዳ ማወራረጃ፣ … በማለት መዘርዘር ይቻላል፡፡

ኢንዳውመንት አኒዩቲ የተባለው የሕይወት ዋስትና ደንበኛው እንደፈለጉ ዕድሜያቸው  50፣ 55፣60፣65፣ … ሲደርስ የኢንሹራንስ ድርጅቱ እንዲጦራቸው የሚገቡት ዋስትና ነው፡፡ “እኔ ጡረታ ስወጣ፣ በየወሩ 500 ብር፣ 700 ብር፣ 1000 ብር፣ 10,000 ብር …ክፈለኝ ተብሎ የሚገባ ዋስትና ነው፡፡

ብዙ ሰው የሕይወት ዋስትና ለሞት ጊዜ ብቻ ካሣ የሚከፍል አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ በእርግጥ ለሞት ካሣ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን የቁጠባ ባህርይ ያለው ዋስትናም አለ፡፡ ለምሳሌ፤ እኔ ጌትነት ዕድሜዬ 45 ዓመት በነበረበት ጊዜ ጡረታ ከመውጣቴ በፊት (በአዲሱ የአገራችን ሕግ መሠረት ጡረታ መውጫ በ60 ዓመት ነው) ለ15 ዓመት ቆይታ ያለው የ50 ሺህ ብር ኢንዳውመንት ዋስትና ብገዛ፤ ልክ 60 ዓመት ሞልቶኝ ጡረታ ስወጣ፣ ሳልሞት 50 ሺህ ብር ይከፈለኛል፡፡

ኢንዳውመንት ሁለት ባህርይ አለው፡፡ በውሉ ዘመን (በ15 ዓመታት ውስጥ) በማንኛውም ጊዜ የሞትኩት በተፈጥሮ ሞት ከሆነ፣ 50ሺህ ብር ለወራሾቼ ይከፈላል፡፡ የሞትኩት በአደጋ ከሆነ ክፍያው እጥፍ ስለሆነ ለወራሾቼ 100 ሺህ ብር ይከፈላል፡፡ ውል በገባሁበት ጊዜ ካልሞትኩ፣ በ60 ዓመቴ ዕድሜዬ ለእኔው ለራሴ 50 ሺህ ብር ይከፈለኛል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የኢንዳውመንት ዋስትና ባለቤት ቢኮን ከውሉ ዘመን መጠናቀቂያ በፊት ቢሞት ለወራሽ፣ በህይወት ከቆዩ ደግሞ ለራስ የሚከፈል መሆኑ ነው፡፡ ከሞትኩ ቼኩ በወራሾቼ ስም፣ ካልሞትኩም በራስ ስም ይዘጋጃል፡፡

ከሕይወት ዋስትና ጥቅሞች አንዱ ደግሞ፤ የቀብር ዋስትና ነው፡፡ እኔ ስሞት፣ ሚስቴና ልጄ፣ እኔን በማጣታቸው ከሚደርስባቸው ኅዘን በተጨማሪ “ሬሳውን እንዴት በክብር እንሸኘው?” በማለት እንዳይጨነቁ፣ የቀብር ዋስትና ገብቻለሁ፡፡ እነሱ ማድረግ ያለባቸው ልክ እንደሞትኩ ስልክ አንስተው ለኢንሹራንስ ድርጅቴ “ጌትነት ሞተ” ብለው መደወል ብቻ ነው፡፡ ገንዘቡ ወዲያውኑ ይከፈላቸዋል፡፡

ልጆቹን የማይወድ ወላጅ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ወላጆች ለአብራካቸው ክፋይም ሆነ ለጉዲፈቻ ልጆቻቸው የልጆች የትምህርት ፖሊሲ ዋስትና ቢገዙ አንዱ ወይም ሁለቱም ወላጆች ቢሞቱ፣ ልጆቹ የት/ቤት ክፍያ ሳይጓዳልና ሳያስጨንቃቸው ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

እኔ፣ ለልጄ 10ኛ ክፍል ሳለች፤ ዩኒቨርሲቲ ገብታ አራት፤ አምስት ወይም ሰባት ዓመት እንድትማር ብዬ የመጀመሪያውን አረቦን (ፕሪሚየም) ገዛሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በማግስቱ ብሞት ልጄ እንድትማር ያሰብኩላት ዕቅድ አይጨናገፍም - የትምህርት ፖሊሲ ዋስትና ለመስጠት ውል የገባው ድርጅት፣ የልጅቷ ጉብዝና እስከፈቀደው ድረስ ያስተምራታል፡፡ የሕይወት ዋስትና የቤተሰብ ፍቅር መግለጫ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህ አንድ ጠንቃቃ ቤተሰብ፣ ኖሮ ብቻ ሳይሆን ሞቶም ቤተሰቡን መውደዱን በዚህ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

በበለፀጉት አገሮች ያለው የሕይወት ዋስትና እንዴት ነው? አገራችን ከአፍሪካስ አገራት ጋር ስትነፃፀር ደረጃዋ የት ነው?

ጃፓን በሄድኩ ጊዜ ያስተዋልኩትና የገረመኝ ነገር፤ አንድ ጃፓናዊ ገና ሲወለድ ነው የሕይወት ዋስትና የሚገባለት! በአፍሪካም ቢሆን ከደቡብ አፍሪቃና ከሰሜን አፍሪካ የተወሰኑ አገሮች በስተቀር በዝቅተኛ ደረጃ ነው የምንገኘው፡፡ በእኛ አገርም፣ ሕዝቡ ስለ ሕይወት ዋስትና እንዲያውቅ አድርገነው 80 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ የሕይወት ዋስትና ተጠቃሚ ቢሆን፣ ወላጅ ሲሞት ልጆች ያለ አሳዳጊ አይቀሩም፣ ቤተሰብ አይበተንም፣ ትምህርት አይቋረጥም፣ … በርካታ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ የሚሰበሰበው አረቦንም አገር ያለማል፣ ለባለአክሲዮኖችም ትርፍ ያስገኛል፡፡

ስለ ሕይወት ዋስትና ጥቅም ስናገር ራሴን ነው በምሳሌነት የማቀርበው፡፡ እኔ ብዙ የሕይወት ዋስትና ገዝቻለው፡፡ ከ15 ዓመት በፊት የገባሁት ኢንዶውመንት ውል በሚቀጥለው ዓመት ያበቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ከቆየሁ መጦሪያዬን እቀበላለሁ፡፡ ከሞትኩ ደግሞ ባለቤቴና ልጄ ተረክበው ሕይወታቸውን ያለጭንቅና ስጋት ይመሩታል፡፡ ለመቀበሪያዬም የ8ሺህ ብር ዋስትና ስላለኝ እኔን ወደመቃብር ለመሸኘት፣ ቤተሰቤ የሚጨነቅበት ነገር አይኖርም፡፡ ለራሴ፣ ለባለቤቴና ለልጄ የሕክምና ዋስትና ስለገዛሁ፣ ብንታመም ምን እንሆናለን? ብለን አንሰጋም፡፡ ልጄ በትምህርቷ ጐበዝ ስለነበረች ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባ አውቅ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ብትመደብ እንዳትቸገር ብዬ የህክምና ዋስትና ገዝቼላት ነበር፡፡ እንደሰጋሁት ከአዲስ አበባ ውጭ ተመድባ አንዳች ችግር ሳያጋጥማት ህክምናዋንም ያለሃሳብ እየተከታተለች ለአምስት ዓመት ሕግ ተምራ ተመርቃለች፡፡

የሕይወት ዋስትና ይህን ያህል ጠቃሚ ከሆነ ብዙ ሰው ያልገዛው በዋጋው ውድነት ይሆን?

ዋጋው ውድ አይደለም - በጣም ቀላል ነው፡፡ ሕዝቡ ስለ ሕይወት ዋስትና ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑና ግንኙነት ከሌለው ፈጣሪ ጋር ስለሚያያይዘው ነው፡፡ በእርግጥ የሕዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ብዙ አልተሠራም ማለት ይቻላል፡፡

ዋጋው ቀላል ከሆነ ስንት ነው?

አንድ ሰው አንዳንድ ፍላጐቶቹን በመግታት የሕይወት ዋስትና ሊገዛ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በቀን ሁለት ሻይ የሚጠጣ ሰው አንዱን ቀነሰ እንበል፡፡ የሁለቱ ሻይ ዋጋ 5 ብር ነው ብንል የአንዱ ሻይ ዋጋ 2.50 ይሆናል፡፡ ሌላ ደግሞ በቀን ሁለት ማኪያቶ የሚጠጣ ሰው፣ አንዱን ቀነሰ እንበል፡፡ የሁለቱ ዋጋ 10 ብር ነው ብንል፣ የአንዱ ዋጋ 5 ብር ይሆናል፡፡

እኔ የዛሬ 14 ዓመት የሕይወት ዋስትና የገዛሁት በአንድ ሻይ ዋጋ ነበር፡፡ ለዋስትናው በወር የምከፍለው 29 ብር ከ28 ሳንቲም ነው፡፡ ይኼ ቁጥር ወደ ቀን ሲለወጥ አንድ ብር አይሞላም፡፡ እኔ በሚቀጥለው ዓመት የሚያበቃውን ኢንዶውመንት የገዛሁት አንድ ሻይ በመፆም ነው፡፡ በቀን ለሻይ 2.50 የሚያወጣ ሰው፣ ለአንድ ወር ሻይ ቢፆም (ባይጠጣ) 75 ብር ያጠራቅማል፡፡ ለማኪያቶ 5 ብር የሚያወጣ ሰው ደግሞ ለአንድ ወር ባይጠጣ 150 ብር ያጠራቅማል፡፡ ለአንድ ወር ሻይ ወይም ማኪያቶ በመተው የሕይወት ዋስትና መግዛት ይቻላል፡፡

በእርግጥ አንድ ሻይ በመተው ብቻ የሕይወት ዋስትና መግዛት ይቻላል እያሉኝ ነው?

ገንዘቡን ካየን አዎ! ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሕይወት ዋስትና በዋናነት መሠረት የሚደረገው በዕድሜ ነው፡፡ የመሞት ምጣኔ የሚባል ነገር አለ፡፡ ቀድሞ የተወለደ ቀድሞ ይሞታል የሚል እሳቤ ነው የሚከተለው፡፡ 24 ዓመት ዕድሜ ላይ ያለ ወጣት ለሞት በጣም ሩቅ ነው፡፡ 52 ዓመት የሆነው ሰው ግን ለሞት ሩቅ አይደለም - ቅርብ ነው፡፡ ስለዚህ የዕድሜ ባለፀጋ የሆነ ሰው የሚከፍለው ወደድ ይላል፡፡ የልጅእግሩ ደግሞ ቀላል ነው፡፡

የሕይወት ዋስትና መሠረት የሚያደርገው ሌላው ነገር ጤና ነው፡፡ ዕድሜው ከፍ ያለ ሰው በበሽታ የመጠቃት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የሕይወት ዋስትና ለመግባት ከተወሰነ ዕድሜ በኋላ የጤንነት ሁኔታውን መመርመር ግዴታ ነው፡፡ ደም ግፊት፣ የኩላሊት፣ የአስም፣ የስኳር፣ የልብ፣ … ሕመም ያለበት ሰው ከሌለበት ጋር እኩል አረቦን አይከፍልም፡፡ ወጣት ከሆነ ደግሞ ላይመረመርም ይችላል፡፡

ብዙዎቻችን በየሰፈሩ ዕድር አለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በወር ከ10 ብር በታች የሚያስከፍል ዕድር ያለ አይመስለኝም፡፡ እኔ በወር 15 ብር እከፍላለሁ፡፡ በወር 10 ብር የሚያስከፍል ዕድር በዓመት 120 ብር ይጠይቃል፡፡ እኔ ለመቃብር ዋስትና በዓመት የምከፍለው 44 ብር ነው፡፡ በወር 3.67 ሳንቲም በቀን በ0.22 ሳንቲም ማለት ነው፡፡ በቀን 22 ሳንቲም  በመቆጠብ ብቻ የ8ሺህ የመቃብር ዋስትና አለኝ፡፡ ታዲያ ይኼ ውድ ነው? ርካሽ?

ኢንዳውመንት ገዝቶና የውል ዘመኑ ሲያልቅ በሕይወት ቆይቶ ገንዘቡ የተመለሰበት ሰው አለ?

አዎ! ብዙ አሉ፡፡ አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጥቀስላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሕይወት አቢይ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ባህል ነበረን፡፡ ውሉ ሊጠናቀቅ ወር ሲቀረው ለማስገረምና ለማስደነቅ መሰናዶ እንጀምራለን፡፡ ቼክ በስማቸው ይዘጋጃል፣ ደብዳቤ ይጻፋል፣ የሚወዱት አበባ ይበረከትላቸዋል፡፡

የእኒያ ታላቅ ደንበኛችን ውል የሚጠናቀቀው እንደ ነገ ሲሆን ዛሬ ስልክ ደወልኩላቸውና “ነገ ቢሮዎ መምጣት እፈልጋለሁ” አልኳቸው፡፡ “ለምን? ጌትነት እኔ እራሴ እመጣለሁ” አሉኝ፡፡ “የለም፤ የእኔ ጉዳይ ስለሆነ ቀጠሮ ስጡኝ” አልኳቸው፡፡ “በስንት ሰዓት?” አሉ፡፡ “በፈለጉት ሰዓት አልኳቸው፡፡” ሁለት ሰዓት ተኩል ቀጠሩኝ፡፡

ከዚያ በኋላ የሚወዱትን ዓይነት አበባ ፀሐፊያቸውን ጠይቀን ገዛንና ከቀጠሮአችን ሰዓት ቀደም ብለን አበባውን፣ ቼኩን፣ የምስራቹን ደብዳቤ ይዘን ቢሮአቸው ደረስንና ጸሐፊያቸውን “አበባ የት ሲቀመጥላቸው ነው ደስ የሚላቸው?” ብለን ጠየቅናትና ነገረችን፡፡ በተባለው ቦታ አስቀምጠን ጠበቅናቸው፡፡

“እንግዶች መጡ ወይ?” ብለው ጸሐፊያቸውን ደውደለው ጠየቁ፡፡ “አዎ!” ስትላቸው እየቸኮሉ መጡ፡ አበባውን ሲያዩ “ደስ የሚል አበባ! አያችሁ ፀሐፊዬ እንዴት እንደምትንከባከበኝ?” ብለው ቢሮአቸው ገባን፡፡ ቁጭ በሉ አሉና እንደቆሙ “ለምንድነው የፈለጋችሁኝ?” አሉ፡፡ “ቁጭ ይበሉና ነው የምናነጋግርዎት” አልናቸው፡፡ ቁጭ ሲሉ፣ የምሥራች ደብዳቤውን ቀጥለን ደግሞ ቼኩን ሰጠናቸው፡፡

አነበቡት፡፡ “ማመን ያዳግተኛል፡፡ እንደዚህም ይደረጋል እንዴ?” አሉ፡፡ “አዎ ተለውጠናል ይቻላል” አልናቸው፡፡ እሳቸውም እኛም በጣም ደስ አለን፡፡ እኚህ ሰው ማን መሰሏችሁ? እውቁ የማስታወቂያ ሰውና የአንበሳ ማስታወቂያ ድርጅት ባለቤት ክቡር አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ናቸው፡፡

ከሴትም አሉ፡፡ ዝግጅታችን ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገ እንመጣለን ቀጠሮ ያዙልን ብለን ስልክ ደወልንላቸው፡፡ ልጆቼ እኔ እመጣለሁ ብለው እንቢ አሉን፡፡ ባሉት ሰዓት መጥተው ለምን ፈለጋችሁኝ? አሉ፡፡ በአበባ አሸብርቀን ባዘጋጀነው ክፍል አስቀምጠናቸውና የአበባ እቅፍና ቼኩን ሰጥተናቸው ምክንያቱን ነገርናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑት እናት በጣም ደስ አላቸውና መረቁን፤ “ልጆቼን አሳድግበታለሁ” አሉ፡፡ እኒያ ውድ እናት ክብርት ዶ/ር አበበች ጐበና ናቸው፡፡

 

 

Read 4874 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:39