Saturday, 28 October 2017 10:46

ሕብረት ባንክ ከታክስ በፊት ከ488 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

· የባንኩ ተቀማጭ 17.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል
· አጠቃላይ ክምችቱ 11.9 ቢሊዮን ሆኗል

ሕብረት ባንክ አ.ማ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ከግብር በፊት፣ ነገር ግን መጠባበቂያ ከተቀነሰ በኋላ 488.69 ሚሊዮን ብር ማትረፉንና ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ተመዝግቦ ከነበረው የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር 14.04 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ 19ኛውን የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከትናንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ያደረገ ሲሆን የዲሬክተሮች ቦድ ሊቀመንበር አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ፤ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ አምና የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ እጅግ ከባድ እንደነበር ጠቅሰው፣ የፖሊሲ አለመረጋጋቶች፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ሁኔታ ተፅዕኖና ዝቅተኛ በነበረው ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ላይ መንፀባረቁን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሁኔታም ቢሆን በባንኩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ሆነ በትርፍ ረገድ መሻሻሎ ታይተዋል ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ የተቀማጭ ገንዘብ ግንባር ተጠቃሽ እንደሆነና አምና በተመሳሳይ ወቅት ተመዝግቦ ከነበረው መጠን 4.01 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት፣ 17.1 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ 30.2 በመቶ የተመዘገበው የዕድገት ምጣኔ፣ በኢንዱስትሪው ከተመዘገበው አማካይ ዓመታዊ ጭማሪ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
11.9 ቢሊዮን የደረሰው የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 3.4 ቢሊዮን ብር ወይም 40 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ያሉት አቶ ዛፉ የሱስወርቅ፣ የተገኘው ውጤትም በኢንዱስትሪው ካለው አማካይ የዕድገት ምጣኔ የላቀ መሆኑን፣ ለደንበኞች የተሰጠው የብድር መጠንም የዚህን ያህል ጭማሪ ማሳየቱን፣ የባንኩ የብድር ጥራትም ጠንካራ እንደነበር አስታውቀዋል።
37 አዳዲስና 7 ንዑስ ቅርንጫፎች በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹ ቁጥር 205 ያደረሰው ሕብረት ባንክ፤ የሕብር ኦን ላይን ተጠቃሚዎች ቁጥር አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲተያይ 24 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን፣ የካርድ የባንክ አገልግሎት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 42 በመቶ፣ የሞባይል አገልግሎትም 54 በመቶ ማደጉን፣ የ851 ሚሊዮን ብር የኤቲኤምና ፖስ ማሽኖች ግብይት መደረጉን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ15.8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
ብቁ የክፍያ አማራጮችን በመዘርጋት ከተለያዩ ትልልቅ የኮርፖሬት ተቋማት ጋር የሥራ ግንኙነት ፈጥረናል ያሉት የዲሬክተሮች ሊቀ መንበር፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጀመሩት የሥራ ግንኙነት፣ በአየር መንገዱ የሚጓዙ መንገደኞች፣ በድረ-ገጽ ላስያዙት የጉዞ ቦታ፣ በባንኩ የሞባይል ወይም ኢንተርኔት ባንኪንግ ወይም ወደ አንዱ የባንኩ ቅርንጫፍ ጎራ በማለት ክፍያቸውን መፈጸም የሚችሉበት መንገድ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ2.1 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር፣ 443.15 ሚሊዮን ወይም የ21.38 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 2.52 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 1.56 ቢሊዮን ብር፣ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 305.68 ሚሊዮን ብር ወይም 24.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡

Read 2109 times