Saturday, 04 November 2017 11:32

‹‹…የመራቢያ አካላት የካንሰር ሕመም ሕክምና…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(0 votes)

 Gynecology oncologist…. የሚባሉት ሙያተኞች በሴቶች የመራቢያ አካላት ላይ የሚደርሱ የካንሰር ሕመሞችን ለማከምና ለማስወገድ በነበራቸው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያነት ላይ በተጨማሪ ልዩ ትምህርት የሚወስዱ የህክምና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም Gynecology oncologist የሚባሉት ባለሙያዎች በሴቶች የመራቢያ  አካል ላይ የሚከሰት ካንሰርን ማከም የሚችሉ ልዩ ትምህርት የተማሩ ባለሙያዎች ናቸው ስንል በአገራችንስ ያለው ሁኔታ ምን መልክ አለው? የሚለውን ለመመልከት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በመሄድ ያነጋገርናቸው ባለሙያ አሉ፡፡ ባለሙያው ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ ይባላሉ፡፡ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በዚያው ላይ በተጨማሪ Gynecology oncologist ትምህርትን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት ይህ Gynecology oncologist ለተሰኘው ልዩ ባለሙያነት የሚያበቃውን ትምህርት መውሰድ ቀደም ሲል ከነበረው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስትነት በተጨማሪ የማህጸንና ከማህጸን ዙሪያ አካላት ጋር በተያያዘ የሚኖረውን የካንሰር ሕክምና በተሙዋላ መልኩ ለመስጠት ያበቃል፡፡ በእርግጥ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያ ለመሆን የሚያበቃው ትምህርትም የካንሰር ሕክምናን ያካተተ ቢሆንም ይሕ ግን የተለየ እውቀትን እንደመስጠቱ ሁሉ ተጨማሪ ኃላፊነትም መቀበልን ያካትታል፡፡ አንድ Gynecology oncologist በሚል የተመረቀ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እእስፔሻሊስት ባለሙያ በዚህ በመራቢያ አካላት ለሚከሰቱ የካንሰር ሕመሞች የተሙዋላ የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን መስጠት ይችላል፡፡ እንዲሁም የጨረር ሕክምናና የካንሰር መድሀኒት ማለትም ኬሞቴራፒን መስጠት ይችላል፡፡ በተጨማሪም  የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ ለሆኑት ልምዱን ከማካፈል ባሻገርም የቡድን ኃላፊ በመሆን ያገለግላል፡፡
ዶ/ር ታደሰ እንደገለጹት በማህጸን ዙሪያ የሚሰሩ የካንሰር ሕክምናዎች የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ስለሆነም  የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችም ቀላል የማይባሉና ጊዜም የሚፈጁ ናቸው፡፡ ለሕመምተኛውም ቀላል ያልሆነ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሲሆን ለብዙ ችግሮች ሊያጋልጥ የሚችል ነው፡፡ ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምናው አገልግሎት በሁዋላ ለማገገም ሰፊ ጊዜን ይወስ ድባቸዋል፡፡ ስለሆነም በGynecology oncologi ሙያ መሰልጠን ማለት እነዚህን ውስብስብ የሆኑ ኃላፊነቶችን ተቀብሎ በጥንካሬ እና በተሳካ መልኩ አገልግሎቱን መስጠት ማለት ነው፡፡
የመራቢያ አካላት ካንሰር በሚል በአማርኛው ለአጠራር እንዲመች ጠቅለል የተደረገው አገላለጽ በእንግሊዝኛው አካላቱን በሚገልጽ መንገድ የተለያየ ስያሜ አለው፡፡ ለምሳሌም…
Ovarian cancer .. የዘር ፍሬዎች የሚኮርቱበት ላይ የሚከሰተው የካንሰር አይነት ይባላል፡፡
Fallopian tube cancer ...ማለትም ከዘር መተላለፊያ ቱቦዎች የሚነሱ የካንሰር ሕመሞች፣
Endometrial cancer ...ማለትም ከዋናው ማህጸን የውስጥ ግድግዳ የሚነሳ፣
Sarcoma cancer   ከዋናው ጡንቻ የሚነሳ የካንሰር አይነት፣
Cervical cancer   የማህጸን ጫፍ (በር) ካንሰር  ወዘተ…በመባል ይታወቃሉ፡፡
ዶ/ር ታደሰ የቀዶ ሕክምና የደረጉላቸውን ሴት በሆስፒታሉ ተኝተው አግኝተናል፡፡ የካንሰር ሕመም የተከሰተው ከማህጸን የዘር ፍሬ ክፍል ወይንም ኦቫሪያን ከተሰኘው ክፍል የሚነሳው ነው፡፡ እሳቸውም የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡  
‹‹….እኔ ሕመም የሚሰማኝ በጎኔ አካባቢ ነበር። ሕመሙ ሲጸናብኛ ወደግል ሐኪም ቤት በመሄድ የተለያዩ ምርመራዎችን አደረግሁኝ፡፡ የእነርሱም የህክምና ውጤት በጣም ያደገ እጢ እንዳለብኝ የሚያሳይ ስለነበር የማህጸንና የጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስቶች የሚገኙት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ነው በመባሉ ወደ ሆስፒታሉ መጥቼ ሕክምናው ተደረገ ልኝ፡፡ የህክምናውን ክትትል በማደርግበት ወቅት ምንም ጊዜ ሳይፈጅ ነው ኦፕራሲዮኑ የተሰራልኝ፡፡ አሁን በጣም ደህና ነኝ፡፡ ከሆስፒታል ከወጣሁ በሁዋላ ለክትትል ስመጣ እንደገና በተወሰነ ጊዜ እርቀት መድሀኒቱን መውሰድ አለብሽ ስለተባልኩ አሁን እዚህ የተኛሁት በዛ ምክንያት ነው፡፡ ይህን መድሀኒት በየሶስት ሳምንቱ ለስድስት ዙር እንድወስድ ተነግሮኛል።››
ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና የGynecology oncologist ተማሪ እንደሚገልጹት አንዲት ሴት በተለይም የኦቫሪያን ካንሰር ሕመም ሲይዛት በፍጥነት የምታው ቅበት መንገድ የላትም። ለሕክምናው የምትቀርበውም  በሽታው ከሰፋ በሁዋላ የተለያዩ የህ መም ስሜቶች ሲከሰቱባት ነው። ስለዚህ የቀዶ ሕክምና በሚደረግበት ጊዜ በአይን የሚታዩትን ሁሉ ለቅሞ ከማውጣት ባሸገር በአይን የማይታዩ ጥቃቅን የሆኑት ግን ሳይወጡ ይቀራሉ። ስለ ዚህም ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ በሚደረገው ክትትል በአይን የማይታዩት የካንሰር ሕዋሳቶች መጥፋት ስላለባቸው በተወሰነ ጊዜ ወደሆስፒሉ እየመጡ መድሀኒት እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ በእርግጥ በሌሎች ማለትም እንደ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ያሉት በቀጣይነት መድሀኒት መውሰድ አለመውሰዳቸው የሚወሰነው በሚደረግላቸው የምርመራ ውጤት ነው፡፡
ሴቶች የማህጸን ካንሰር ምልክት ሲታይባቸው በፍጥነት ወደ Gynecology oncologist ዘንድ መቅረብ አለባቸው፡፡ ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በፍጥነት ወደ ባለሙያው መቅረብ የእናቶች ሕይወት በዚህ በሽታ ምክንያት እንዳይጠፋ ያግዛል፡፡ምክንያቱም…
Gynecology oncologist ሴቶች በስነተዋልዶ  በተለይም በመራቢያ አካላቸው ላይ የሚደርሰውን የካንሰር ሕመም በማከም ረገድ ልዩ ትምህርት የወሰዱ በመሆናቸው፣
Gynecology oncologist በዘርፉ በተለየ ትምህርት ከ3-5/ አመት ድረስ የቆዩ ናቸው፡፡ ይህ ጊዜ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ትምህርት ጊዜን ኤጨምርም፡፡
ባለሙያዎቹ የማህጸን ካንሰር እንዲወገድ በማድረግ ረገድ በሙያው ካልተካኑት በ5/እጅ የተሻሉ ናቸው።
80/ከመቶ የሚሆኑት የማህጸን ካንሰር ታማሚዎች በGynecology oncologist ካልታከሙ የካንሰር ሕመሙ ጥርት ባለ መንገድ ተወግዶአል ማለት አይቻልም፡፡
ስለሆነም የማህጸን ካንሰር ታማሚዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲያገግሙ በGynecology oncologist መታከም አለባቸው፡፡ በተለይም ደግሞ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ታማሚዎች በአቅራቢያቸው ባለው የህክምና ተቋም ለመታከም በሚቀርቡበት ጊዜ የሚታከሙባቸው ተቋማት በፍጥነት የGynecology oncologist ባለሙያዎቹ ወደሚገኙበት የህክምና ተቋም ሊያስተላልፉአቸው ግድ ይሆናል፡፡
ምንጭ ፡- ovarian cancer research fund alliance  
ይህ ትምህርት በአገራችን በምን ሁኔታ ይሰጣል ስንል ለዶ/ር ታደሰ ኡርጌ ጥያቄ አንስተን የነበረ ሲሆን እሳቸውም እንዳሉት፡-
የGynecology oncologist ትምህርት በአሁኑ ወቅት የቅዱስፓውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ካሪኩለም ቀርጾ በውጭ አገር ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስምምነት በማድረግ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ትምህርቱም የሚሰጠው በትምህርት ክፍል ተቀምጦ ሳይሆን በስራ የተደገፈ ወይንም ስራውን እየሰሩ መማር ነው፡፡ ስለዚህም በአገራችን በርካታ ታማሚዎች በመኖራቸው እነርሱን እንደግብአት በመጠቀም በስራ ላይ ትምህርት እየወሰድን ነው፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉ ተማሪዎችም መምህሮቻቸው ባሉበት ሀገር በመሄድ የበለጠ እውቀቱን የማዳበር እድል አግኝተናል፡፡
የካንሰር ህክምና በአጠቃላይ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይሰጥ የነበረ ሲሆን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት ትምህርትን ሲያስተምሩ የነበሩ ባለሙያዎች ይህንን የካንሰር ሕክምና ትምህርት ሲያስተምሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ትምህርቱ ከአሁን ቀደምም በሰፊውና ቀጣይነት ባለው መንገድ ሲሰጥ ነበር ባይባልም ቀድመው በተማሩ በተወሰኑ የ Gynecology oncologist ባለሙያ ዎች እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ባለሙያዎችም እገዛ ይሰጥ ነበር፡፡ የካንሰር ህክምና አገልግሎ ትም ሲሰጥ የነበረው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው አሁንም የጨረር ሕክምና የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡  ይቀጥላል፡፡

Read 4489 times