Saturday, 04 November 2017 11:36

ባለፉት ሶስት ወራት፡ ሳምሰንግ 9.8 ቢ. ዶላር፣ ፌስቡክ 4.7 ቢ. ዶላር አትርፈዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ሶስት ወራት፣ የደቡብ ኮርያው የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ በታሪኩ ከፍተኛው የሩብ አመት ትርፍ የሆነውን የ9.8 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ሲያስመዘግብ፣ የማህበራዊ ድረገጹ ፌስቡክ በበኩሉ፤ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉ በሳምንቱ መጀመሪያ ተዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ በሩብ አመቱ ያገኘዋል ተብሎ ከተገመተው ትርፍ በእጅጉ የላቀ ትርፈ ማስመዝገቡን የዘገበው ኤቢሲ ኒውስ፤ የሩብ አመት ሽያጩም ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በ30 በመቶ ብልጫ በማስመዝገብ፣ 55.1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል፡፡ የአለማቸን ቁጥር አንድ የስማርት ፎን አምራቹ ሳምሰንግ፣ በአለማቀፍ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የሚሞሪ ቺፕስ ሽያጩ ጋር በተያያዘ በትርፋማነት አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የሚሞሪ ቺፕስ ምርቱን የበለጠ ለማስፋፋት ባለፈው አመት ብቻ 29.5 ትሪሊዮን የደቡብ ኮርያ ዎን ወጪ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
ፌስቡክ በበኩሉ፤ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ4.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን ትርፉ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገበው ጋር ሲነጻጸር የ80 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሩብ አመት አስመዘግበዋለሁ ብሎ ካቀደው ገቢ የ47 በመቶ ብልጫ ያለው የ10.33 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን ከዚህ አጠቃላይ ገቢው 98 በመቶ ያህሉን ያገኘው ከድረ-ገጽ ማስታወቂያ አገልግሎቱ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

Read 1357 times