Saturday, 04 November 2017 11:37

ሳዑዲ በ500 ቢ. ዶላር ግዙፍ ከተማ ልትቆረቁር ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የከተማው ስፋት የኒውዮርክ ሲቲን 33 እጥፍ ያክላል ተብሏል

    ሳዑዲ አረቢያ 26 ሺህ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና ከኒውዮርክ ሲቲ 33 እጥፍ ያህል የቆዳ ስፋት የሚኖረውን ኒኦም የተሰኘ እጅግ ግዙፍ ከተማ፤ በ500 ቢሊዮን. ዶላር ወጪ ልትቆረቁር መዘጋጀቷን ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች፡፡
በሰሜን ምዕራባዊ የሳዑዲ ግዛት የቀይ ባህርን ዳርቻ ታክኮ የሚቆረቆረው አዲሱ ከተማ ኒኦም፤ ለኑሮ፣ ለንግድና ለመዝናኛ በአለማቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ተመራጭ ከተማ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን የዘገበው ሮይተርስ፤ ከተማው የሚቆረቆርበት ስፍራም ለእስያ፣ አውሮፓና አፍሪካ አገራት በቀላሉ ተደራሽ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ራዕይ 2030 የተባለውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደተሻለ ለውጥ በማሸጋገር ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን የመፍጠር ግብ ያስቀመጠው ዕቅድ አካል የሆነው ይህ ግዙፍ ከተማ፤የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አስታውቀዋል፡፡
ከተማው እጅግ የተዋበ፣ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የተሟላ፣ ሙሉ ለሙሉ በታዳሽ ሃይል አቅርቦት የሚሰራ እንደሚሆንና ራሳቸውን የቻሉ በጣም ሰፋፊ የቢዝነስና የኢንዱስትሪ ዞኖች አንደሚኖሩት የጠቆመው ዘገባው፤ የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በ2015 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመትም አመልክቷል፡፡
የአለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች የሆነቺው ሳዑዲ አረቢያ፣ የነዳጅ ዋጋ ከቀነሰበት ከ2014 አንስቶ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝና የፋይናንስ እጥረት መታየቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከልም ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለማስከፈል ማቀዱ እንደሚገኝበትም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2121 times